
አዲስ አበባ፡- ባለፉት 9 ወራት በላሊበላ ከተማ የሰላምና የልማት ተኮር ሥራዎች በስፋት እየተሠሩ እንደሚገኙ የላሊበላ ከተማ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ገለጸ:: የላሊበላ የአቢያተ ክርስቲያናቱ መጠለያ (ሼልተር) ይነሳልን ጥያቄ እንደ ከተማ አንገብጋቢው ጥያቄያቸው መሆኑንም አመልክተዋል::
የላሊበላ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ወንድሙ ወዳጅ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በከተማዋ ባለፉት 9 ወራት ሰላምን የማረጋገጥ እና የልማት ሥራዎች እየተሠሩ ቆይተዋል:: ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ አራት ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል::
ከንቲባው ከሰላም ማስከበር ጎን ለጎን በከተማዋ የልማት ሥራዎች እንዲከወኑ መደረጉን ገልጸው፤ ለአብነትም የትምህርት ቤቶች ግንባታ ማከናወን፣ ተማሪዎች በተገቢው ሰአት እና ቦታ ትምህርት ገበታቸው ላይ እንዲገኙ የማድረግ ሥራ በሰፊው ተሠርቷል ብለዋል::
እንደ አቶ ወንድሙ ገለጻ ፤ ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ተማሪዎችንም ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በጋራ በመሆን ከ2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ በመመደብ ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ ማድረግ ተችሏል:: የትምህርት ቁሳቁሶችን በማሟላት ተማሪዎች ትምህርታቸውን ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ለማድረግ ተሠርቷል::
ከዓለምአቀፍ የቀይ መስቀል ድርጅት ጋር በጋራ በመሆን በከተማዋ 90 ሜትር ጥልቀት ያለው የውሃ ጉድጓድ በማስገንባት የንጹህ ውሃ አቅርቦት ችግር ለመቀነስ እየተሠራ መሆኑን የገለጹት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው፤ የከተማ አስተዳደሩን የቢሮ ማደስ ሥራዎች እና የጤና ጣቢያ ግንባታ ሥራዎችም መከናወናቸውን አብራርተዋል::
ከገቢ አሰባሰብ ጋር ተያይዞም በከተማዋ ሥራዎች እየተከወኑ መሆኑን ጠቁመው፤ የቅርጽ ጥገናንም አስመልክቶ ከዘላቂ የልማት ፕሮጀክት ጋር በመተባበር የቤተክርስቲያናቱን መንገዶች የመክፈት፣ የውሃ ፍሳሽ መውጫዎችን የመሥራት፣ ድልድዮችን እና ጥገና የሚፈልጉ አብያተ ክርስቲያኖችንም ጥገና የማድረግ ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት::
ባለፉት 9 ወራት ከንቲባ ጽህፈት ቤቱ ሰላም እንዲመጣ እና ሕዝቡ የተጋረጠበትን ፈተና በትዕግስት እንዲያልፍ ከሚመለከታቸው የጸጥታ አካላት ጋር በጋራ በመሆን ሲሠራ መቆየቱንም ገልጸዋል::
በተሠሩ ሰላም የማስከበር ሥራዎች ሙሉ በሙሉ ውጤት ማምጣት ተችሏል ባይባልም፤ አቅም በፈቀደ መጠን ተስፋ ሰጪ ሥራ ተሠርቷል:: ከባለፈው ተመሳሳይ ዓመት ጋር በንጽጽር ሲታይ አንጻራዊ ሰላም ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል::
ከተማዋ የቱሪስት መዳረሻ እና የስበት ማዕከል በመሆኗ የከተማዋን ሰላም የመጠበቅ ሥራ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል::
ቱሪዝም ለላሊበላ ከተማ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ነው:: ኮቪድ፣ የሰሜኑ ጦርነት እና አሁንም ያለው ግጭት የቱሪዝም ዘርፉ በእጅጉ ጎድቶታል:: ግጭቱ በሰውም በቁሳቁስም ሊገመት የማይችል ጉዳት አድርሷል:: ነገር ግን እንደመንግሥት ከዚህ ችግር ለመውጣት በርካታ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል::
እንደ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ገለጻ፤ ላሊበላ የዓለም ቅርስ እንደመሆኑ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ብዙ ናቸው:: የአቢያተ ክርስቲያናቱ ላይ ያለውን መጠለያ (ሼልተር) የማንሳት መርሃ ግብር በተመለከተ ጉዳዩ የጥናት እና የዲዛይን ሥራ በመሠራት ላይ ነው፤ ነገር ግን ጥያቄውም ለሚመለከተው አካል በተደጋጋሚ አሁንም እየቀረበ ነው:: መንግሥትም ለማንሳት በጥረት ላይ ነው:: የማንሳት ሥራውም በችኮላ የሚሆን አይደለም፤ ከባድ ጥንቃቄን የሚጠይቅ ነው:: የመዘግየቱም ምክንያት ይህ መሆኑ ቢታወቅም የሼልተር ይነሳልን ጥያቄ እንደ ከተማ ግን አንገብጋቢው ጥያቄያችን ነው ብለዋል::
መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 24 ቀን 2017 ዓ.ም