አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ በካንሰር የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በጤና ሚኒስቴር የሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ አቶ ሌሊሳ አማኑኤል በተለይም ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤ በኢትዮጵያ በካንሰር የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መጥቷል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ 19 ሚሊዮን የሚሆኑ አዳዲስ የካንሰር ታማሚዎች እንደሚገኙና በኢትዮጵያ ደግሞ 80 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በየዓመቱ በካንሰር እንደሚያዙ አማካሪው ጠቁመዋል። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ በየዓመቱ 53 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች በካንሰር እንደሚሞቱ ተናግረዋል፡፡
ይህም በኢትዮጵያ በካንሰር የሚያዙና በዚሁ በሽታ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ስለመምጣቱ ጠቋሚ ነው ያሉት አማካሪው፤ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ካንሰርን በሚመለከት በህብረተሰቡ በኩል ከፍተኛ የእውቀትና ግንዛቤ ማነስ በመኖሩ ነው ሲሉ ገልፀዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ደረጃ ሰዎች የሚያዙት በሳምባ ካንሰር ነው ያሉት አማካሪው፤ ከሳምባ ካንሰር ቀጥሎ በጡትና የአንጀት ካንሰር የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱን አመልክተዋል። በኢትዮጵያም በሳምባ ካንሰር የሚያዙ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ ቢሆንም በጡትና በአንጀት ካንሰር የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ግን ጭማሪ እያሳየ መምጣቱን ጠቁመዋል።
የካንሰር ተፈጥሯዊ መነሻዎች የእድሜ መግፋትና የዘረመል ሁኔታዎች ቢሆኑም በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታዎች ዋናዎቹና ትልቅ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ መንስኤዎች ሲጋራ ማጨስ፣ ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ የአልኮል መጠጦችን አብዝቶ መጠቀምና የአየር ንብረት ለውጦች መሆናቸውን አማካሪው ገልፀዋል፡፡
ካንሰርን ለመከላከል በጤና ሚኒስቴር በኩል የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውንም አማካሪው ገልፀው፤ ከክልል ጤና ቢሮዎች ጋር በመሆን የተለያዩ መመሪያዎችን፣ ስትራቴጂክ ሰነዶችን በማዘጋጀት ለተፈፃሚነታቸው እየተሠራባቸው እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡ በፖሊሲው ውስጥም የመጀመሪያና ሁለተኛ ጤና ህክምናዎች ተካተው እየተሠራበት እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
በተመሳሳይ የካንሰር ህክምና የሚሰጥባቸው ተቋማት ተደራሽ እንዲሆኑ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን የጠቀሱት አማካሪው፤ የካንሰር ታካሚዎች በትልልቅ ሆስፒታሎች ከሚያገኟቸው ህክምናዎች በተጨማሪ በጤና ጣቢያዎችም ህክምናውን እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የካንሰር መድኃኒቶች በሀገር ውስጥ ተመዝግበው እንዲገቡ እየተደረጉ መሆናቸውንም አማካሪው ጠቁመው፤ በርካታ መድሃኒቶች በመንግሥትም በኩል እየገቡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ የካንሰር ስፔሺያሊስት ሀኪሞችን አሰልጥኖ የመመደብ ሥራም ከዚሁ ጎን ለጎን እየተሠራ እንደሆነም አማካሪው ጠቅሰዋል፡፡
ከመድሃኒት ክህምና በተጨማሪ የጨረር ህክምና መሣሪያዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ መደረጋቸውንም አማካሪው ተናግረው፤ ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን ያሟሉ የጨረር ህክምና አገልግሎት የሚሰጡ አራት ትላልቅ ጤና ተቋማት እንዳሉም ጠቁመዋል፡፡
የካንሰር ህክምናን መንግሥት ብቻውን ሊሰጥ እንደማይችል በመገንዘብ እንደ ተስፋ አዲስ የካንሰር ህሙማን ማእከልና በልሻ ፋውንዴሽንን የመሰሉ የግል ካንሰር ህክምና ተቋማትን መደገፍና ሌሎችም በዚህ ህክምና ዘርፍ እንዲገቡ ማበረታት እንደሚያስፈልግ አማካሪው ጠቁመዋል፡፡
አስናቀ ፀጋዬ