ቆጮን በአዲስ አቀራረብ ከቂጣ ወደ ኬክ

ዜና ሀተታ

እንሰት በኢትዮጵያ ደቡብ እና ደቡብ ምዕራብ አካባቢዎች በስፋት ለምግብነት ይዘወተራል:: ነገር ግን ቆጮ አዘጋጅቶ ለምግብነት ለማዋል ሥራው አድካሚ ከመሆኑ፤ ባለፈ ለማዘጋጀት በአማካኝ ከሁለት ወር የበለጠ ጊዜ የሚወስድ መሆኑ ሌላኛው ተግዳሮት ሆኖ ቆይቷል::

አብዛኛው የማህበረሰብ ክፍል ቆጮን የሚያውቀው በሶስት ዓይነት አሠራር ብቻ ነው:: ነገር ግን አሁን ከአርባምጭ ዩኒቨርሲቲ ለማህበረሰቡ በተቸረ የፈጠራ ሥራ ቆጮን ፍቆ ላማጠናቀቅ የሚውሰድው ጊዜ ከአንድ ቀን ወደ 40 ደቂቃ፤ ለምግብነት ለማዋል ከሁለት ወር ወደ ሰባት ቀን ዝቅ እንዲል እንዲሁም፤ በአዲስ አቀራረብ ከቂጣ እስከ ኬክ ለመሥራት ተችሏል::

እንደ ሀገር ከ25 እስከ 30 የሚጠጋ ሚሊዮን ሕዝብ ቆጮ የሚጠቀም በሆንም ከአሠራር እና እሴት ከመጨመር አንጻር ክፍተቶች መኖራቸውን በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ እና የሉሲ እንሰት መሥራችና ባለቤት አዲሱ ፍቃዱ (ዶ/ር) ይናገራሉ::

አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ በየዓመቱ በማህበረሰቡ ዘንድ ያሉ ችግሮች ምንድናቸው የሚለውን በጥናት ይለያል የሚሉት ተመራማሪው፤ ከእንሰት ተክል ቆጮ ማዘጋጀት አቅም የሚጠይቅ፤ እንደልብ መጠቀም አለመቻሉ እና ሀገሪቱም ከእንሰት የሚገባትን ጥቅም አለማግኘቷን ከዛሬ 10 ዓመት በፊት ዩኒቨርሲቲው በሠራው ጥናት ማረጋገጡን ይገልጻሉ::

አዲሱ (ዶ/ር) እንደሚናገሩት፤ እንሰት ለምግብነት ማዘጋጀቱ እጅግ በጣም አድካሚ፤ ጊዜ የሚወስድ እና ጥራቱን የጠበቀ አለመሆኑ እንደ ዋና ችግር የሚጠቀስ ነው:: በሌላ በኩል እንሰት ተፍቆ የሚብላላበት ጊዜ ረጅም ከመሆኑ የተነሳ፤ መሬት ውስጥ ተቀብሮ ሁለትና ሶስት ወር ያህል ይቆያል::

መሬት ውስጥ ተቀብሮ በሚብላላበት ወቅት ደግሞ ለዝናብ፤ ለጎርፍ ይጋለጣል፤ እንዲሁም ከአፈር ጋር ንኪኪ ስለሚፈጥር የምግብ ደህንነቱን አጠያያቂ ያደርገዋል:: ከቂጣ፤ ከፍርፍር እና ከቡላ ገንፎ ውጭ እሴት ተጨምሮ ሌሎች የምግብ አይነቶችን አለመሠራታቸው ሌላኛው እንደ ክፍተት የሚነሳ ጉዳይ መሆኑንም ያነሳሉ::

እነዚህን ችግሮች በማጤን ዩኒቨርሲቲው ወደ መፍትሄ ሃሳብ መሄዱን የሚናገሩት ተመራማሪው፤ በቀላሉ እናቶች መጠቀም የሚችሏቸውን ማሽኖች በመሥራት ለማህበረሰቡ እየተሰራጨ ይገኛል፤ የእንሰት እርሾ በማበልጸግ ቆጮ ለማዘጋጀት የሚፈጀው ጊዜ ከሶስት ወር ወደ ሰባት ቀን መውረዱን ያስረዳሉ::

እንደ ኦሮቶ አይነት እቃዎችን በማዘጋጀት እንሰት ከተፋቀ በኋላ ጉድጓድ ውስጥ እንዳይቀበር መፍትሄ ለማዘጋጀት ተችሏል:: ከዚህ በፊት ቆጮ ከሶስት ምግቦች ውጭ የማይታወቅ ሲሆን፤ አሁን ላይ የቆጮ ዱቄት እንዲዘጋጅ በማድረግ የቆጮ ኬክ፤ ኩኪስ እና ዋፍል እየተዘጋጀ መሆኑን ያስረዳሉ::

ከዚህ በፊት አንድ ቆጮ ፍቆ ለማጠናቀቅ አንድ ቀን የሚፈጅ ሲሆን፤ በዘመናዊ መልክ የተዘጋጀው ማሽን አንድ እንሰት በ40 ደቂቃ ውስጥ ፍቆ ያጠናቅቃል፤ ቃጫው ከሚበላው ይለያል፤ ማሽኑ ከመሬት ውስጥ የሚወጣውን ሀምቾ የሚባለውን የእንሰት ክፍል እንደሚያደቅም ያስረዳሉ::

ቆጮን እርሾ ጨምሮ በእቃ ማዘጋጀቱ የምግብ ደህንነቱ እንዲጠበቅ ያደርጋል የሚሉት ተመራማሪው፤ መሬት ውስጥ በሚቀብርበት ወቅት አየር ስለሚገባበት በዘመናዊ መልክ ከተዘጋጀው ጋር ሲነጻጸር ይጠቁራል:: ሌላው በመሬት ተቀብሮ በሚዘጋጅበት ወቅት ይባክናል ይላሉ::

ለአብነትም አንድ ሰው መቶ ኪሎ ቆጮ ቢያዘጋጅ በአማካኝ 34 ኪሎ ግራም ያህል ይባክናል:: ነገር ግን በዘመናዊው አሠራር የተዘጋጀው እንሰት ሁሉ ምግብ ሆኖ ስለሚወጣ፤ ሁለት ኪሎ ግራም እንኳን እንደማይባክን ያስረዳሉ::

ቆጮ በዱቄት መልክ እንዴት እንደሚዘጋጅ የሚናገሩት ተመራማሪው፤ የቆጮ ሊጥ ከተዘጋጀ በኋላ በምግብ ማድረቂያ እንዲደርቅ በማድረቅ ይፈጫል:: በቀጣይ ምርቱን በኩባንያ ደረጃ ለማምረት በስፋት ማድረቅ የሚያስችል ማድረቂያ ማሽን ከቻይና ለግዢ ማዘዛቸውንም ይጠቁማሉ::

እሳቸው እንደሚሉት፤ ቆጮ በዱቄት መልክ መዘጋጀቱ የምግብ ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን፤ ከቦታ ቦታ በቀላሉ ለማጓጓዝ፤ ሳይበላሽ በአማካኝ እስከ ሁለት ዓመት እንዲቆይ እና በቀላሉ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ያስችላል::

ኢትዮጵያ በስፋት ቆጮ ኤክስፖርት ታደርጋለች:: ነገር ግን ቆጮው ተጋግሮ ነው ለውጭ ገበያ የሚቀርበው ፤ ይህ ደግሞ የምግብ ደህንነቱን አደጋ ላይ ይጥላል:: በዱቄት መልክ መዘጋጀቱ ጥራቱን በጠበቀ መንገድ በስፋት ኤክስፖርት በማድረግ የበለጠ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ያስችላል ይላሉ::

የሲዳማ፤ የጅማ፤ የሀረር ቡና ተብሎ በተለየ መልኩ እንደሚሸጠው፤ ቆጮንም ብራንድ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው:: ከዚህ በፊት የጋሞ እና የወላይታን ቆጮ ብራንድ የማድረግ ሥራ የተሠራ ሲሆን፤ በቅርቡ ከባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን የወሊሶን ቆጮ ብራንድ መደረጉን ይገልጻሉ::

አዲሱ (ዶ/ር) እንደሚሉት፤ እንደ ዩኒቨርሲቲ ልክ እንደ ወፍጮ ቤት ማህበረሰቡ የራሱን እንሰት አዘጋጅቶ በማምጣት እንዲያስፈጭ የሚደረግ ሲሆን፤ በሌላ መልኩ ደግሞ ዱቄትና የተለያዩ እሴት የተጨመረባቸውን ምግቦች በማዘጋጀት ለገበያ ይቀርባል:: በዚህም በማህበረሰቡ ዘንድ ያለው አቀባበል አበረታች ነው::

የምርምር ውጤቱ የማህበረሰቡን ችግር መሠረት ያደረገ እና ድካም የሚቀርፍ ግኝት ነው የሚሉት አዲሱ (ዶ/ር) ፤ ከዚህ በፊት የቆጮ ዱቄት፤ ኩኪስና ኬክ ገበያ ላይ አይታወቅም:: ነገር ግን አሁን ላይ ከምርምር ግኝት አልፎ ወደ ገበያ በስፋት እየገባ ይገኛል ይላሉ::

አሁን ላይ ዓለም አቀፍ የምግብ ኩባንያዎች ፍላጎት ማሳየት ብቻ ሳይሆን፤ ቆጮን በስፋት በማምረት ለዓለም አቀፍ ገበያ እንዴት ነው ማቅረብ የሚቻለው በሚሉ ጉዳዮች ከእኛ ጋር በሰፊው ድርድር እያደረጉ ነው ሲሉ ይጠቁማሉ::

ከአፍሪካ ህብረት ጋር በመሆን ቴክኖሎጂውን በስፋት የማዳረስ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ በመግለጽ፤ በተለይ ሴቶችን ማበረታታት የሚፈልጉ አካላት አብረው እንዲሠሩ ጥሪያቸውን ያቀርባሉ::

ዓመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You