
ዜና ሐተታ
ብዙ የፈጠራ ሥራዎች መነሻቸው ተግዳሮት ነው ይባላል፡፡ ለዚህ ይመስላል አበው ‹ችግር ብልሃትን ይወልዳል› ብለው የሚተርቱት፡፡ የመምህር ዮሴፍ መሐመድ የፈጠራ ሥራ ከላይ ያነሳነውን ሃሳብ የሚያጠናክር ነው፡፡ መምህሩ በልደታ ክፍለ ከተማ መዝገበ ብርሃን ትምህርት ቤት የሚያስተምሩ ሲሆን፤ በአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ በተዘጋጀው ዓውደ ርእይ ላይ ቤት ለመሥራት የሠሩትን የብሎኬት ማምረቻ ማሽን ይዘው ቀርበዋል፡፡ መምህር ዮሴፍ ማሽኑን ለመሥራት መነሻ የሆናቸው ቤት ለመሥራት የሚወጣው ከፍተኛ ወጪ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡
ወጪውን ለመቀነስም የተለያዩ የፕላስቲክ ውጤቶችን በግብዓትነት መጠቀምን ምርጫቸው አድርገዋል፡፡ ይህም ዋጋ ከመቀነስ ባለፈ በአካባቢ ላይ ብክለት የሚያስከትሉ ቁሳቁሶችን በመቀነስ ጠቀሜታውን በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ይሉት ዓይነት ያደርገዋል ይላሉ፡፡
መምህራን ሁሌም ለተማሪዎቻቸው አርአያ መሆን እንዳለባቸው የሚጠቅሱት መምህር ዮሴፍ፤ የፈጠራ ሥራቸው ተማሪዎች ለሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶች ችግር ፈቺ ፈጠራዎችን በመሥራት በራሳቸው መፍትሔ መስጠት እንዳለባቸው የሚያመላክት እንደሆነም ያነሳሉ::
ማሽኑ አካባቢ ላይ ብክለት የሚያስከትሉ እንደ ፌስታል ያሉ ፕላስቲኮች፣ የማዳበሪያ ከረጢቶች፣ የቴሌቪዥንና የቴፕ ከቨር እና የመሳሳሉትን አንድ ላይ በማቅለጥና ቅርጽ በማውጣት ተገጣጣሚ የፕላስቲክ ብሎኬት መመረታቸውን ጠቅሰው፤ ብሎኬቱም ጠንካራ፣ ቢወድቅ በቀላሉ የማይሰበር ለብዙ ዓመታት አገልግሎት ሊሰጥ የሚችል እንደሆነም ይገልጻሉ::
አሁን ለግንባታ የሚውለው ብሎኬት ከ30 እስከ 40 ዓመት ቢያገለግል ነው የሚሉት መምህሩ፤ እሳቸው የሠሩት የብሎኬት ማምረቻ የሚያመርተው ምርት አደጋ ተቋቋሚነቱም ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለእሳት በቀላሉ የማይበገር መሆኑንም አብራርተዋል::
ብሎኬቱን ለተለያዩ አገልግሎቶች ማዋል እንደሚቻልም ጠቁመዋል:: በኮሪዶር ልማቱ የመጸዳጃ ቤቶችን ለመሥራት፣ ለዶሮ ርባታ ቦታዎች፣ ለመኖሪያ ቤቶች ግንባታና ፓርቲሽን መከፋፈያነት ሊውል እንደሚችልም አመላክተዋል::
ቴክኖሎጂውን እንደ ሀገር ብዙ በመሥራት ማሳወቅ እንደሚገባም አመልክተው፤: ሞልዱን በመቀያየር የተለያዩ ብሎኬቶችና ሌሎች ጠንካራ ነገሮችን መሥራት ይቻላል ይላሉ::
ማሽኑ ፕላስቲኮችን አንዴ ካቀለጠ በኋላ ሙሉ ቀን ከሠራ ከ200 እስከ 300 ብሎኬቶች ሊያመርት እንደሚችል የሚጠቁሙት የፈጠራው ባለቤቱ፤ አንድ ብሎኬት ለመሥራት ከሁለት እስከ ሦስት ኪሎ የፕላስቲክ ተረፈ ምርቶች ሊያስፈልጉ ይችላሉ:: ለምርቱ የሚያገለግሉት ግብዓቶች በአካባቢው ይገኛሉ:: እነዚህን ሰብስበን በማቅለጥ ለብሎኬት መሥሪያነት ማዋል እንደሚቻል ያነሳሉ::
ማሽኑን ወደ ገበያ በማውጣት ለሕብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ድጋፍ የሚያደርጉ አካላት ትብብር እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፤ መንግሥትም ሆነ የግል ባለሀብቶች የፈጠራ ሃሳቡን በመደገፍ ማሽኑ ተግባር ላይ እንዲውል እንዲያግዟቸው ጥሪ አቅርበዋል::
ተማሪ ፉአድ ገቢም የዚህ ዓውደ ርእይ ሌላኛው ድምቀት ሆኖ ተከስቷል:: ተማሪው በቂሊንጦ ቁጥር ሁለት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የአራተኛ ክፍል ተማሪ ነው:: ከልጅነቱ ጀምሮ ሞተር ሳይክል እንዲኖረው ይመኝ ነበር:: ተመኝቶ ግን አልቀረም በአካባቢው በቀላሉ የሚያገኛቸውን ግብዓቶች ተጠቅሞ የራሱን ሞተር ሳይክል መሥራት ችሏል::
ከልጅነቱ ጀምሮ ቁሳቁስን በመነካካት፣ በመፈታታትና መልሶ በመገጣጠም እየሞከረ ማደጉ ሥራውን እንዳቀለለለት ጠቅሶ፤ በቴሌቪዥን መስኮትና በአካባቢው ላይ የሚመለከታቸው ነገሮች ለፈጠራ ሃሳቡ መነሻ እንደሆነው ያነሳል:: ሞተር ሳይክሉ ከተለመዱ ሞተር ሳይክል አይነቶች ይለያል ይላል::
በተለይ ለልጆች ምቾች እንዲሰጥና በቀላሉ መቆጣጠር የሚቻል እንዲሆን አድርጎ እንደሠራው ጠቅሶ፤ በሰዓት 12 ኪሎ ሜትር መጓዝ ይችላል:: ሞተር ሳይክሉ የወዳደቁና የተጣመሙ ብረታ ብረቶችን በመጠቀም እንደሠራው ያወሳል::
ሪሞቱ ከሌሎች ሞተር ሳይክሎች እንዲለይም ያደርገዋል የሚለው ተማሪ ፉአድ፤ ያለመቆጣጠሪያ ሪሞቱ ሞተር ሳይክሉን ማሽከርከር አይቻልም:: ይህም ሰዎች ሞተሩን አቁመው ቢሄዱ እንዳይሰረቁ እንደሚረዳ ይገልጻል::
ሞተር ሳይክሉን ለማሽከርከር የሚያስችል መመሪያ ማንዋል ማዘጋጀቱን አስታውሶ፤ ይህን የፈጠራ ሥራ አሳድጎ መኪና የመሥራት ህልም ሰንቋል::
ድጋፍ የሚያደርግለት አካል ቢያገኝ የፈጠራ ሥራውን ለማሻሻልና ሌሎች ፈጠራዎችን ለመሥራት እንደሚፈልግ አመላክቷል::
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 24 ቀን 2017 ዓ.ም