
አዲስ አበባ፡- የሚኒስትሮች ምክር ቤት የውጭ ዜጎች የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት ወይም ባለይዞታ የሚሆኑበትን አግባብ ለመደንገግ የወጣው ረቂቅ አዋጅና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ፡፡
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው 44ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ማሳለፉን አስመልክቶ እንዳስታወቀው፤ የውጭ ዜጎች የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት ወይም ባለይዞታ የሚሆኑበትን አግባብ ለመደንገግ የወጣው ረቂቅ አዋጅ ምክር ቤቱ የተወያየበት አጀንዳ መሆኑን ጠቁሞ፤ የዜጎችን የመሬት ይዞታ የማግኘትና የመጠቀም መብት በማያጣብብ መልኩ ለውጭ ዜጎች ሕጋዊ አሠራር መዘርጋቱ የውጭ ካፒታል በሀገራችን ሥራ ላይ እንዲያውሉ ለማበረታታት፣ የቤት ልማት እና ተደራሽነትን ይበልጥ ለማነቃቃት፣ የመኖሪያ ቤት ፍላጎት እና አቅርቦት ሚዛን ለማስጠበቅ እና ለዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ትልቅ ጠቀሜታ የሚኖራቸው በመሆኑ ምክር ቤቱ በረቂቅ አዋጁ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል ብሏል፡፡
ሌላው ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው ከጣሊያን ሪፐብሊክ መንግሥት እና ከዓለም አቀፍ የልማት ማህበር ጋር በተፈረሙ ሁለት የፋይናንስ ድጋፍ ስምምነቶች ላይ መሆኑን ጠቁሞ፤ ከጣሊያን ሪፐብሊክ መንግሥት የተገኘው የ11 ሚሊዮን 500 ሺህ ዩሮ ለአካባቢያዊና አረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት የበጀት ድጋፍ ፕሮግራም ማስፈፀሚያ የሚውል ሲሆን የ 16 ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ 30 ዓመት ተከፍሎ የሚጠናቀቅ መሆኑን ተብራርቷል::
ከዓለም አቀፍ የልማት ማህበር የተገኘው 38 ሚሊዮን 100 ሺህ ኤስ.ዲ.አር ለመማር ማስተማር ማጎልበቻ የትምህርት ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ማስፈፀሚያ የሚውል መሆኑን አመልክቶ ዜሮ ነጥብ 75 በመቶ የአገልግሎት ክፍያ የሚከፈልበት ሆኖ 6 ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ38 ዓመት ተከፍሎ የሚጠናቀቅ መሆኑን አመልክቷል:: ምክር ቤቱም ብድሮቹ ምንም አይነት ወለድ የማይታሰብባቸው እና ከሀገራችን የብድር አስተዳደር ፖሊሲ ጋር የሚጣጣሙ መሆናቸውን በማረጋገጥ ረቂቅ አዋጆቹ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ በሙሉ ድምጽ መወሰኑን አስታውቋል::
ምክር ቤቱ ሌላው የተወያየው በአፍሪካ ፋይናንስ ኮርፖሬሽን መቋቋሚያ ስምምነት ማጽደቂያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው ያለው መግለጫው፤ ኮርፖሬሽኑ ትኩረቱን በመሠረተ ልማት፣ በተፈጥሮ ሀብት እና በኢንዱስትሪ ዘርፍ ልማት ላይ በማድረግ ለግል አልሚዎችና ለመንግሥት አካላት የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ ለመስጠት የተቋቋመ ነው:: ሀገራችን በአባልነት መቀላቀሏ ለግሉ ዘርፍ ተጨማሪ የፋይናንስ ሀብት በማቅረብና የግል ዘርፉን የማይተካ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽነት ሚና በማሳደግ ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ለማፋጠንና ድህነትን ለመቀነስ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ ምክር ቤቱ በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ መወሰኑን ገልጿል::
ሌላው ምክር ቤቱ ለአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ ንግድ ቀጣና ስምምነት የዕቃዎች ቀረጥ ምጣኔ ቅነሳን ለማስፈፀም በቀረበ ረቂቅ ደንብ ላይ መወያየቱን አንስቶ፤ ስምምነቱ በአባል ሀገራት መካከል ንግድ እንዲስፋፋ፣ የገበያ ትስስሩ እንዲጠናከር፣ የእሴት ሠንሰለቱ እንዲጎለብት እና የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ማበረታታት የሚያስችል ነው:: በአባል ሀገሮች መካከል የሚደረጉ ግብይቶች በታሪፍ ምክንያት ሳይደናቀፉ የእቃዎች ፍሰት የተሳለጠ እንዲሆን ከአባል ሀገራት በሚመጡ እቃዎች ላይ የጉምሩክ ታሪፍ ምጣኔ ለይቶ መወሰን አስፈላጊ መሆኑን በመወያየት ምክር ቤቱ ደንቡ በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ተፈፃሚ እንዲሆን በሙሉ ድምጽ ወስኗል ብሏል::
ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየው በትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ለሚሰጡ አገልግሎቶች እና በኢ.ፌዴ.ሪ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ለሚሰጡ አገልግሎቶች የሚከፈሉ የአገልግሎት ክፍያዎችን ለመወሰን በቀረቡ ሁለት ረቂቅ ደንቦች ላይ መሆኑን ጠቁሞ፤ ተቋማቱ አገልግሎት ለመስጠት የሚያወጡትን ወጪ በመሸፈን፣ ገቢያቸውን አሳድገው ጥራት ያለው አገልግሎት በመስጠት የተገልጋይ ርካታ ማሳደግ የሚያስችል የደምበኞችን አቅም ባገናዘበ መልኩ የአገልግሎት ክፍያ መወሰን አስፈላጊ ይሆናል:: ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቦቹ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ በነጋሪት ጋዜጣ ታትመው ከወጡበት ቀን ጀምሮ በሥራ ላይ እንዲውሉ በሙሉ ድምጽ መወሰኑን ይፋ አድርጓል::
በመጨረሻም ምክር ቤቱ የተወያየው ከኦስትሪያ መንግሥት ጋር የተፈረመውን የአየር ትራንስፖርት ስምምነት ለማፅደቅ በቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው ያለው የሚኒስትሮች ምክር ቤት መግለጫ፤ የስምምነቱ መጽደቅ የሁለቱን ሀገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክር፣ ለአየር መንገዳችን ተጨማሪ የገበያ ዕድል የሚፈጥር ከመሆኑም ሌላ የሀገራችንን ንግድና ኢንቨስትመንት በማበረታታት፣ የወጪ ንግዱን በመደገፍ፣ ቱሪዝምን በማስፋፋት፣ የሥራ ዕድል በመፍጠርና በውጭ ምንዛሪ ግኝት ረገድ ትልቅ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ ምክር ቤቱ በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ መወሰኑን አመልክቷል::
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 24 ቀን 2017 ዓ.ም