
ያለ ኢንዱስትሪዎች ዕድገት የአንድ ሀገር ዕድገት እና ብልፅግና ሊረጋገጥ አይችልም፡፡ ኢንዱስትሪዎች ሊያድጉና ለሀገራዊ ዕድገትም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችሉት ምርት እና ምርታማነትን ሊጨምሩ የሚችሉ ግብዓቶችን ከማቅረብ ባሻገር በኢንዱስትሪዎቹ ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩ ሠራተኞች አቅም በፈቀደ መጠን መሠረታዊ ፍላጎቶቻቸው ሲሟሉ ነው፡፡
መንግሥት በቀየሰው የኢንዱስትሪ ስትራቴጂ አምራች ኢንዱስትሪዎች ምርታማ እንዲሆኑና ከውጭ የሚገቡ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት ትኩረት አድርጓል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 40 በመቶ የሚሆነውን ፍላጎቷን በሀገር ውስጥ ምርት መሸፈን ችላለች፡፡
ሆኖም ካለው ፍላጎት አንጻር ይህ ቁጥር ወደ 80 በመቶ ማደግ የሚገባው በመሆኑ መንግሥት ይህንን ትልም ለማሳካት የሚያስችለውን ስትራቴጂ አስቀምጦ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ በተለይም የኢንዱስትሪ ዘርፉ ምርት እና ምርታማነትን ሊጨምሩ የሚችሉ ግብዓቶችን በማቅረብና የኃይል እርቅቦትን ተደራሽ በማድረግ ለጥቅል ሀገራዊ ምርት አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ላይ ይገኛል።
እየተደረጉ ባሉ ድጋፎችም የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም እያደገ መጥቷል፡፡ በአማካኝም የኢንዱስትሪዎች የማምረት እቅም 56 በመቶ ደርሷል፡፡ እስከ 70 በመቶ ድረስ አቅማቸውን የሚጠቀሙ አምራች ኢንዱስትሪዎችም ተፈጥረዋል፡፡ ድጋፉ ቀጣይነት ያለው በመሆኑም የኢንዱስትሪዎች ምርትና ምርታማነት መጨመሩ የማይቀር ነው፡፡
ሆኖም የኢንዱስትሪዎችን ምርታማነት ማረጋገጥ የሚቻለው ግብዓቶችን በማሟላት እና የተለያዩ ድጋፎችን ከማድረግ ጎን ለጎን የሀገሪቱን አቅም ባገናዘበ መልኩ በኢንዱስትሪው ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞችን መሠረታዊ ጥያቄዎችን በመመለስ ጭምር ነው፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ኢንዱስትሪዎች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ሠራተኞች በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ውስጥ በመሰማራት ለኢንዱስትሪው እድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ይገኛሉ፡፡ ሆኖም እያበረከቱት ያለውን ሀገራዊ አስተዋጽኦ የሚመጥን እና የኑሮ ውድነቱን መቋቋም የሚያስችል ክፍያ ሲያገኙ አይታዩም፡፡
ይልቁንም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄደው የኑሮ ውድነት በሠራተኛው ላይ የበረታ ጫና በማሳረፍ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ደግሞ ሠራተኛው በሚፈለገው መልኩ አምራች እንዳይሆን እና ኢንዱስትሪውም የሚጠበቅበትን ሀገራዊ አስተዋጽኦ እንዳይወጣ እንቅፋት መሆኑ የማይቀር ነው፡፡
ስለዚህም አሁን ያለውን የኑሮ ውድነት የሚመጥን እና ለተመጣጣኝ ሥራ ተመጣጣኝ ክፍያ መክፈል የሚለው ጉዳይ በጥናት መታየት ይኖርበታል፡፡ ዝቅተኛ የደመወዝ መነሻ ወለል ለመትከልም በኢንዱስትሪው ውስጥ ከሚገኙ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር መነጋገር እና በጋራ መሥራት ወሳኝ ነው፡፡
በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ በ2011 ዓ.ም የደመወዝ ወለል እንዲወሰን የሚጠይቅ የአሰሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ወጥቷል። አዋጁን መተግበር የሚያስችል ደንብ ባለመውጣቱ፤ አዋጁ አራት ዓመት ቢያስቆጥርም እስካሁን ተግባራዊ ባለመሆኑ በርካታ ሠራተኞች ለችግር ተዳርገዋል ሲባል እየተሰማ ነው፡፡ በኢንዱስትሪውም አስተማማኝ ሰላም እንዳይሰፍን እንቅፋት እነደሆነም ይገለጻል፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎንም በአሠሪዎች በኩል የሠራተኞችን የመደራጀት መብት መንፈግ እና የሙያ ደህንነትና ጤንነት ሕጎችን አለማክበር ይታያል፡፡ በሠራተኛውም በኩል ቢሆን የኢንዱስትሪው ምርታማነት ጠንክሮ ከመሥራት አንጻር ውስንቶች ይታያሉ፡፡ በአጠቃላይ የሥራ ቦታ ሰላም እንዲሰፍን ሁሉም አካላት መብትና ግዴታቸውን በውል ሊረዱ ይገባል፡፡ አንዱ የሌላውን መብት ማክበር መቻል ይኖርበታል፡፡ ስለዚህም በኢንዱስትሪው ውስጥ ያሉ አካላት ችግሮቻችውን በአግባቡ ለይተው ኢንዱስትሪው ለሀገር እድገት እና ብልፅግና የሚጫወተውን ሚና በላቀ መልኩ እንዲወጣ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ይህ ሲሆን በአሠሪ እና ሠራተኛው መካከል ጤናማ ግንኙነት ይፈጠራል፤ የሠራተኛው ርካታ ይጨምራል፤ ሀገራዊ የማምረት አቅም ይጎለብታል፤ ተወዳዳሪ ሀገራዊ ምጣኔ ሀብት ለመገንባትም ይረዳል፤ የተረጋጋ የኢንዱስትሪ ሰላም ለመፍጠርም ምቹ ይሆናል፡፡
ኢትዮጵያም በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ የሆኑ የኢንዱስትሪ ምርቶችን አምርታ ለመሸጥ እንዲሁም ከውጭ የሚገቡ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት የጀመረችው መንገድ የበለጠ ቀና ይሆናል፡፡ በዚህም የሀገሪቱ ዕድገት እና ብልፅግና ይረጋገጣል!
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 23 ቀን 2017 ዓ.ም