
ህንድ በፓኪስታን ላይ ጥቃት ለመሰንዘር መዘጋጀቷን የሚያመለክቱ ታማኝ የደህንነት መረጃዎች እንዳገኙ የፓኪስታን የማስታወቂያ ሚኒስትር ገልፀዋል። ሚኒስትሩ አታውላህ ታራር ህንድ ባለፈው ሳምንት የተፈፀመውን የፔልጋም ጥቃትን ምክንያት አድርጋ በፓኪስታን ላይ ጦርነት ለመክፈት እየተዘጋጀች እንደሆነ ተናግረዋል። ‹‹ማንኛውም ዓይነት የወረራ ተግባር ከባድ ምላሽ ይኖረዋል። በቀጣናው ለሚፈጠር አደገኛ ክስተት ህንድ ሙሉ ኃላፊነቱን ትወስዳለች›› ብለዋል። ሚኒስትሩ ‹‹ታማኝ›› ላሉት የደህንነት መረጃ ተጨባጭ ማስረጃ እንዳላቀረቡና ዝርዝር ነገር ከመናገር መቆጠባቸው ተገልጿል።
የሀገሪቱ የመከላከያ ሚኒስትር ካዋጃ መሀመድ አሲፍ በበኩላቸው፣ ህንድ ጥቃት መሰንዘሯ እንደማይቀር ለ‹ሮይተርስ› የዜና ወኪል ተናግረዋል። ፓኪስታን በህልውናዋና በደህንነቷ ላይ አደጋ የሚፈጥር ሁኔታ ከተከሰተ የኑክሌር ጦር መሣሪያዎቿን እንደምትጠቀምም አስጠንቅቀዋል።
የህንድ መንግሥት ግን የፓኪስታን ሚኒስትሮች በተናገሩት ላይ እስካሁን በይፋ የሰጠው መግለጫ የለም። ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ባለፈው ሳምንት የጥቃቱ ፈፃሚዎች ለሕግ እንደሚቀርቡና የሀገሪቱ የጦር ሠራዊት ምን ማድረግ እንዳለበት እንደሚያውቅና የመወሰን ነፃነትም እንዳለው ተናግረዋል። ‹‹ህንድ እያንዳንዱን አሸባሪና ደጋፊውን ትለያለች፣ ትከታተላለች፣ ትቀጣለች። ይህን መላው ዓለም ይወቅ›› በማለት የጥቃቱን ፈፃሚዎች እንደሚበቀሉ ቃል ገብተዋል። የመከላከያ ሚኒስትሩ ራጅናት ሲንግ በበኩላቸው፣ ህንድ የምትቀጣው ጥቃቱን የፈፀሙትን ብቻ ሳይሆን ያቀዱትንም ጭምር እንደሆነ ተናግረዋል።
ባለፈው ሳምንት ህንድ በምትቆጣጠረው የካሽሚር ግዛት ውስጥ በምትገኘው ፔልጋም በተፈፀመ ጥቃት 26 ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ ለወትሮውም በቋፍ የነበረው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በእጅጉ ሻክሯል። 25 ህንዳውያንና አንድ ኔፓላዊ ከሆኑት ከሟቾቹ መካከል አብዛኞቹ ቱሪስቶች እንደነበሩ ተገልጿል። ‹‹ሬዚስታንስ ፍሮንት›› (The Resistance Front – TRF) የተባለው ታጣቂ ቡድን ለጥቃቱ ኃላፊነቱን ወስዷል።
ህንድ ጥቃቱን የፈፀመውን ቡድን ያሰለጠነችውና ያስታጠቀችው ፓኪስታን እንደሆነች በጽኑ ታምናለች። ቡድኑ ከሃሳብ ጀምሮ የመሣሪያና የሥልጠና ድጋፍ ያገኘው በፓኪስታን የመከላከያና ደህንነት መሥሪያ ቤት አማካኝነት እንደሆነ ገልፃለች። በተጨማሪም ፓኪስታን ውስጥ ከሚገኙ ሌሎች ታጣቂ ቡድኖች ጋር ግንኙነት አለው ብላለች። ፓኪስታን በበኩሏ በድርጊቱ እጇ እንደሌለበት ገልፃ፣ ጥቃቱ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ ጠይቃለች።
ጥቃቱን ተከትሎ ሁለቱ ሀገራት በየፊናቸው ከአፈሙዝ መልስ ያሉ ምጣኔ ሀብታዊና ዲፕሎማሲያዊ ርምጃዎችን ወስደዋል። ህንድ ከፓኪስታን ጋር የሚያዋስናትን ድንበር ዘግታለች። ፓኪስታን ለመስኖ እርሻዋ ከሚያስፈልጋት ውሃ ውስጥ 80 በመቶ ያህሉን ከምታገኝበት የኢንደስ ውሃ ስምምነት (Indus Waters Treaty (IWT) መውጣቷን አውጃለች። አንዳንድ ፓኪስታናውያን ህንድን ለቀው እንዲወጡም ቀነ ገደብ አስቀምጣለች። ፓኪስታን በበኩሏ ድንበሯንና የአየር ክልሏን መዝጋቷን አስታውቃለች። ከህንድ ጋር ያላትን የንግድ ልውውጥም አቋርጣለች። ከዚህ ባሻገር በሁለቱ ሀገራት ድንበር አቅራቢያ የተኩስ ልውውጦች መደረጋቸውም ተሰምቷል።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሁለቱ ባለኑክሌር ሀገራት የገቡበትን ፍጥጫ እንዲያረግቡ እየጠየቀ ነው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ከፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትርና ከህንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ባደረጉት ውይይት፣ ሀገራቱ መጥፎ ውጤቶችን ሊያስከትሉ የሚችሉ መፋጠጦችን እንዲያረግቡ አሳስበዋል።
አሜሪካም ሁለቱ ሀገራት ኃላፊነት የተሞላበት አካሄድን እንዲከተሉ ጠይቃለች። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርኮ ሩቢዮ ሀገራቱ ነገሮችን ከማባባስ እንዲቆጠቡ መምከራቸውን መሥሪያ ቤታቸው አስታውቋል። ሌሎች ሀገራትም ውጥረቱን ለማርገብ ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
ህንድና ፓኪስታን በአወዛጋቢውና ከፍተኛ ስትራቴጂካዊ ጥቅም እንዳለው በሚነገርለት የካሽሚር ግዛት ምክንያት ፍጥጫ ውስጥ ኖረዋል። በግዛት ይገባኛል የሚወዛገቡት ሁለቱ ጎረቤቶች ካሽሚርን ተከፋፍለው እያስተዳደሩ ቢሆንም፣ ሙሉውን ግዛት ለመጠቅለል ባላቸው ፍላጎት ምክንያት ሦስት ታላላቅ ጦርነቶችን አድርገዋል፤ በርካታ ግጭቶችንም አስተናግደዋል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 23 ቀን 2017 ዓ.ም