የሎጅስቲክስ አገልግሎት ሰጪዎች ተወዳዳሪ ተቋማትን መገንባት እንደሚጠበቅባቸው ተጠቆመ

አዲስ አበባ፡የሎጅስቲክስ አገልግሎት ሰጪዎች በዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆኑ ተቋማትን መገንባት እንደሚጠበቅባቸው የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር አስገነዘበ። በሎጅስቲክስ ዘርፍ የሰለጠነ ባለሙያ እጥረት ለዘርፉ ዕድገት ፈተና መሆኑ ተመላከተ።

የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዴንጌ ቦሩ ከሎጅስቲክስ ዘርፍ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር የምክክርና የልምድ ልውውጥ መድረክ ትናንት ሲካሄድ እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ ያሉ የሎጅስቲክስ አገልግሎት ሰጪዎች በዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆኑ ተቋማትን መገንባትና በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይወሰኑ ወደ ጎረቤት ሀገራትም ተሻግረው መሥራት ይጠበቅባቸዋል።

ዘርፉን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ እንደ ተግዳሮት ከሚነሱት ቀዳሚ ጉዳዮች መካከል የሠለጠነ የሰው ሃይል እጥረት አንዱ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ዛሬም ድረስ ስለ አቅርቦትና ተያያዥ ጉዳዮች በቂ የትምህርት ዝግጅትና እውቀት ያለው ባለሙያ በመንግሥትም ሆነ በግሉ የዘርፍ በበቂ ሁኔታ አለመኖሩንም ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅት በዩኒቨርሲቲዎች እየተሰጠ ያለው የሎጀስቲክስ ትምህርትም ተመሳሳይነት ያለው ካለመሆኑ ባሻገር የተግባር ሥልጠና የሚያካትት እንዳልሆነ ጠቁመው፤ በዚህም የተነሳ በዘርፉ ተመርቀው የሚወጡ ተማሪዎች በቂ እውቀትና ክህሎት አላቸው ለማለት አያስደፍርም። በዚህ ረገድ ትምህርትና ሥልጠና የሚሰጡ ዩኒቨርሲቲዎችና ተቋማትም የተቀናጀ አካሄድ ሊከተሉ ይገባል ነው ያሉት።

ይህም የሎጅስቲክስ አገልግሎትን ሙያ ወጥነት ያለው እውቀትና ክህሎት እንዲቀስሙ የሚያስችል መሆኑን አመልክተው፤ ለዚህም በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመመካከር ዓለም የደረሰበትን ደረጃ መነሻ ያደረገ ተመሳሳይ ትምህርት እንዲሰጥ እየሠራን እንገኛለን ብለዋል።

ከዚህ መነሻነትም በኢትዮጵያ ያሉ የሎጀስቲክስ አገልግሎት ሰጪዎች በዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆኑ ተቋማትን መገንባትና ከሀገር ወጥተው በጎረቤት ሀገራትም ለመሥራት ዕቅድ ይዘው መንቀሳቀስ እንደሚኖርባቸው ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።

በዘርፉ የሚስተዋሉ ክፍተቶችንና ተግዳሮቶችን ለመሙላት የሚያስችል አቅም ለመፍጠርም የሎጅስቲክስ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅትና በትብብር መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

የፓን አፍሪካ ግሎባል ሎጅስቲክስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ኤልሳቤጥ ጌታሁን በበኩላቸው ፤ የሰው ሀብት ልማት ላይ በትኩረት ካልተሠራ የዘርፉን ውጤታማነት ማረጋገጥ አይቻልም ብለዋል።

ወይዘሮ ኤልሳቤጥ እንዳብራሩት፤ እስከ ቅርብ ጊዜ እንደ ሀገር በሎጅስቲክስ መስክ የተማረ የሰው ሃይል ማግኘት አስቸጋሪ ነው። ይህንን በመገንዘብ የፓን አፍሪካ ግሎባል ሎጅስቲክስ ከብዙ ዓመታት በፊት ጀምሮ ዛሬም ድረስ በራስ አቅም ለሠራተኞቹ ሥልጠናን እየሰጠ ይገኛል።

በአሁኑ ወቅት በዘርፉ ሥልጠናና ትምህርት እየሰጡ ያሉ ተቋማት ቁጥር እየጨመረ የመጣ መሆኑን ያስታወሱት ሥራ አስፈጻሚዋ፤ አሁንም ቢሆን ግን ዘርፉ ከሚፈልገው አኳያ በቂ የሚባል አይደለም። በመሆኑም ዓለም አቀፍ ግንኙነት በመፍጠር ዓለም በደረሰበት ደረጃ የእውቀትና የክህሎት ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎች ማፍራት የሚጠበቅ እንደሆነ አመልክተዋል። ይህ ደግሞ ለትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር ብቻ የሚተው ባለመሆኑ ዩኒቨርሲቲዎችና በዘርፉ የተሰማሩ ተቋማት በቅንጅት መሥራት የሚጠበቅባቸው መሆኑን ጠቁመዋል።

ራስወርቅ ሙሉጌታ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You