
“ለሠራተኞች ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየተሠራ ነው”– የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፡– መንግሥት ላቀረብናቸው ጥያቄዎች አስቸኳይ ምላሽ ይስጠን ሲል የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ጠየቀ። የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በበኩሉ ለሠራተኞች ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየተሠራ ነው ብሏል።
የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ የዓለም ሠራተኞች ቀንን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፤ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጋር በተደረገው ውይይት ጥያቄያችን ተቀባይነት አግኝቶ ለሚመለከታቸው ሚኒስትሮች አቅጣጫ ተሠጥቷል። በዚህም የተወሰኑ ጥያቄዎች ምላሽ ያገኙ ቢሆንም መሠረታዊና ቁልፍ የሆኑ የሠራተኛ ጥያቄዎች አልተመለሱም ብለዋል።
እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፤ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል የሚወስን የደመወዝ ቦርድ እንዲቋቋም በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ተደንግጓል። የደመወዝ ቦርድ ማቋቋሚያ ደንብ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ባለመውጣቱ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መግባት አልተቻለም።
በ2017 ዓ.ም በጋራ የሥራ ዕቅድ ውስጥ የገባና አንድ ዙር የተወያየንበት ቢሆንም ከችግሩ አንገብጋቢነት አንፃር ትኩረት ተሰጥቶት ደንቡ ወጥቶ ቦርዱ ቶሎ እንዲቋቋም አጥብቀን እንጠይቃለን ብለዋል።
ከዚህም ሌላ የሠራተኞችን በነጻነት የመደራጀት መብት በማስመልከት ላነሳነው ጥያቄ በተሰጠው አቅጣጫ መሠረት ተቀናጅተን እየሠራን እንገኛለን ያሉት አቶ ካሣሁን፤ በማደራጀቱ ላይ ትኩረት እንደተሰጠው ሁሉ የተደራጁ ማህበራትን በማይቀበሉና የማህበር አመራር አባላት ላይ ሕገ-ወጥ ርምጃ በሚወስዱ አሠሪዎች ላይ መንግሥት ሕጋዊ ርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል።
በተቋማት የሥራ አካባቢ ደህንነትና ጤንነትን በተመለከተ በአግባቡ የሥራ ቁጥጥር ማድረግ ባለመቻሉ በርካታ ዜጎች ላይ የአካል ጉድለትና የሕይወት ማጣት ችግሮች በየቀኑ በስፋት እንደሚከሰት አመልክተው፤ ቁጥጥር ለማድረግ በሕጉ መሠረት ኃላፊነት የተሠጣቸው አካላት ተገቢውን ሥራ እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዳንኤል ተሬሳ በጉዳዩ ላይ ለኢፕድ በሰጡት ምላሽ እንዳሉት፤ መንግሥት በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳዮች ላይ በርካታ ሪፎርሞችን እያካሄደ ይገኛል።
ደመወዝን በሚመለከት በተለያዩ ሀገራት በተለያየ መንገድ ይቀመጣል፤ የመጀመሪያው በአሠሪና ሠራተኛ መካከል በሚደረግ ምክክር፣ ሌላኛው መንገድ ደግሞ በመንግሥት፣ በሠራተኛና አሠሪ መካከል በሚደረግ ስምምነት ይሆናል።
ሦስተኛው መንገድ ደግሞ እንደ ሀገር ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ማስቀመጥ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህን ለማድረግ ከሥራው ደረጃ (ስታንዳርዱ)ና ባህሪው አንጻር ለየትኛው ሥራ ዘርፍ ስንት መከፈል አለበት የሚለውን ለመወሰን በርካታ ጥናቶችን ማካሄድ ይጠበቃል ብለዋል።
ባለፈው አንድ ዓመት መንግሥት በጉዳዩ ላይ ጥናት ሲያካሂድ እንደቆየ አመልክተው፤ የአሠሪና ሠራተኛ አዋጁ ባስቀመጠው መሠረት ገለልተኛ የደመወዝ ቦርድ መቋቋም እንዳለበት ገልጸዋል።
ይህን ገለልተኛ የደመወዝ ቦርድ ለማቋቋም ዝግጅት እየተደረገ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ የቦርዱ ማቋቋሚያ ረቂቅ ደንቡ ተዘጋጅቶ ከአሠሪና ሠራተኛ ማህበራት ጋር የመጀመሪያ ዙር ውይይት ተደርጎበታል። በአጭር ጊዜ ሰነዱ አስፈላጊ ሂደቶችን አልፎ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ እንዲጸድቅ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ደንቡ ጸድቆ ቦርዱ ቢቋቋምም በጥናት ላይ ተመስርቶ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ለመወሰን በቀጣይነት የሚከናወኑ በርካታ ሥራዎች መኖራቸውንም ጠቁመዋል።
ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል የሚወስነው ዝቅተኛውን ስለሆነ መወሰኑ በራሱ የሠራተኛውን ጥቅም ለማስከበር ያግዝ ይሆናል እንጂ ብቸኛ መፍትሔ እንደማይሆን ጠቅሰው፤ በሀገሪቱ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ቢወሰን እንኳን በአሠሪና ሠራተኛ የሁለትዮሽ ውይይት የሚሠሩ ሥራዎች ቀጣይነት ይኖራቸዋል ብለዋል።
በሌላ በኩል ሠራተኛው በነጻነት እንዲደራጅ መንግሥት ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ ነው ያሉት አቶ ዳንኤል፤ በአሠሪና ሠራተኛ መካከል የሚፈጠር አለመግባባት ምርታማነት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድር ነው። የማኅበራቱ መደራጀት ዋና ዓላማውም በጋራ ጉዳዮች ላይ እንዲመካከሩ ለማስቻል መሆኑን ገልጸዋል፡
መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ሠራተኞችም አሠሪዎችም እንዲደራጁ ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ መሆኑን አንስተው፤ ከሁለቱም አካላት ጋር የጋራ እቅድ ታቅዶም ወደ ሥራ ተገብቷል። ከተቀመጠው ሕግ ውጪ የሚንቀሳቀሱ አካላት ካሉም ርምጃ እንደሚወሰድ ጠቁመዋል።
በሥራ ላይ የሚያጋጥሙ ጉዳቶችን ለመቀነስም ሥራዎች እንደሚሠሩ የጠቆሙት አቶ ዳንኤል፤ በእያንዳንዱ ኢንዱስትሪ ውስጥ የሙያ ደህንነትና ጤንነት ሥርዓት እየተዘረጋ ነው። በዚህም ከአሠሪና ከሠራተኛ ተውጣጥቶ በሚዋቀር ኮሚቴ ያሉ ችግሮችን እየተፈቱ የሚሄዱበት ሁኔታ እየተፈጠረ መሆኑን አብራርተዋል።
በዚህ ዙሪያ ያለውን የባለሙያዎች ችግር ለመቅረፍም በሁለት ዩኒቨርሲቲዎች በሙያ ደህንነትና ጤንነት ላይ በዲግሪ ደረጃ ሥልጠና እየሰጡ ነው፤ በቴክኒክና ሙያ ተቋማትም አጫጭር ሥልጠና የወሰዱ ባለሙያዎች ስጋት ባለባቸው ኢንዱስትሪዎች ላይ ተቀጥረው እንዲሠሩ እየተደረገ ነው ብለዋል።
የዓለም ሠራተኞች ቀን (ሜይዴይ) በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ136ኛ በሀገራችን ደግሞ ለ50ኛ ጊዜ ዛሬ ሚያዝያ 23 ቀን 2017 ዓ.ም ይከበራል።
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 23 ቀን 2017 ዓ.ም