በኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ ግብይት ይጠበቃል

-ኤክስፖው ከሚያዝያ 25 እስከ 29 ቀን 2017 ዓ.ም ይካሄዳል

አዲስ አበባ፡– በ2017 ኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ ግብይት እንደሚጠበቅ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ። ኤክስፖው ከሚያዝያ 25 እስከ 29 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚካሄድ ተጠቁሟል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል የዘንድሮውን ኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ አስመልክተው ትናንት በሰጡት መግለጫ

እንዳሉት፤ በኤክስፖው ከስድስት ሺህ በላይ የግብይት ትስስር እንደሚኖር ይታሰባል። በዚህም ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ ግብይት ይፈጸማል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።

በኤክስፖው ላይ 161 ከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች፣ 100 አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን ጨምሮ ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ 288 የሚደርሱ ተሳታፊዎች እንደሚኖሩ ጠቅሰው፤ ከ120 ሺህ በላይ ጎብኚዎች ኤክስፖውን ይጎበኛሉ ተብሎ እንደሚገመትም አመላክተዋል።

ባለፈው ዓመት ከሰባት ሀገራት የመጡ የኢትዮጵያን ምርት የፈለጉና የገዙ ደንበኞች እንደነበሩ አስታውሰው፤ በዚህ ዓመት ከዚህ ከፍ ያለ ቁጥር እንደሚጠበቅ አንስተዋል።

በኤክስፖው በሰባት የተለያዩ ክላስተሮች የተከፋፈሉ ምርቶች እንደሚቀርቡ አመልክተው፤ የቆዳ፣ የጨርቃ ጨርቅ፣ የምግብና መጠጥ፣ ኬሚካል፣ ስጋና ወተት፣ ማሽንና ቴክኖሎጂ እንዲሁም ፋርማሲዩቲካል ምርቶች እንደሚቀርቡ ጠቅሰዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ ባለፉት ዓመታት ገቢ ምርትን ለመተካትና ወጪ ምርትን ለማሳደግ ስትራቴጂ ተቀርጾ ሲሠራ ቆይቷል። በዚህም 96 አይነት ምርቶችን ለመተካት ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል። በዚህም እንደሀገር እየሠሩ ካሉ ሌሎች ሥራዎች ጋር ተደምሮ የንግድ ሚዛንን በማጣጣም በኩል ከፍተኛ ውጤት ተመዝግቦበታል።

በ2014 ላይ ዓመቱን ሙሉ 318 ሚሊዮን ዶላር ተኪ ምርት መመረቱን አስታውሰው፤ በተያዘው ዓመት ዘጠኝ ወራት ሦስት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን መተካት ተችሏል።ይህን ጨምሮ ሌሎችም ሥራዎች የንግድ ሚዛኑን በ10 ነጥብ አንድ በመቶ እንዲጣጣም አድርጎታል ብለዋል።

የሀገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች የገበያ ድርሻም 2013 ከነበረበት 30 በመቶ ወደ 41 በመቶ በላይ ከፍ ማለቱን አቶ መላኩ ገልጸዋል።

የዘንድሮው የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ የኢትዮጵያን ምርት ማስተዋወቅ፣ የሀገር ውስጥ ምርት የመጠቀም ባህልን ማሳደግ፣ የገበያ ትስስር መፍጠር፣ የምርት ጥራትን ማሻሻል እና ፈጠራን ማበረታታት የሚሉ ዓማዎችን ይዞ እንደሚካሄድ ሚኒስትሩ ጨምረው ገልጸዋል።

ኤክስፖው ለመላው ኢትዮጵያውያን የተዘጋጀ ትልቅ ድግስ ነው ያሉት አቶ መላኩ፤ የሚቀርቡ ምርቶችን ስናይም አጠቃላይ የኢትዮጵያን አቅም የሚያሳይ ነው። ሁሉም ዜጎች ኤክስፖውን እንዲጎበኙና ግብይት እንዲፈጽሙ ጥሪ አቅርበዋል።

ኤክስፖው ከሚያዝያ 25 እስከ 29 ቀን 2017 ዓ.ም ባሉት ተከታታይ አምስት ቀናት በአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል እንደሚካሄድ ተመላክቷል።

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You