
አዲስ አበባ፡– አብዛኛው ሥራዎቻችን ተሰናስነውና ተደምረው ሲታዩ የኢትዮጵያ ማንሰራራት እውን እየሆነ እያየነው እየመጣን መሆኑን ያመላክታሉ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከከፍተኛ አመራሮች ጋር አብረው የቡልቡላ ፓርክን በጎበኙበት ወቅት በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክትም፤ኢትዮጵያ የምትነሳበት ዘመን የሚጣለው መሠረት በሁሉም መስክ ነው። በእርሻ ስንዴና ቡና ፣ በማዕድን ወርቅ ፣ በኢንዱስትሪ ኢትዮጵያ ታምርት እንደምንለው እንዲሁም በቱሪዝም በርካታ ሥራዎች እንደተሠሩት ፤ በቴክኖሎጂ የሞባይል ባንኪንግ፣ በቅርቡ የተመረቀው የመሶብ
የአንድ አገልግሎት ማዕከልና የጥራት መሠረተ ልማት አብዛኛው የተቋም ግንባታ ሥራችን ተሰናስኖና ተደምሮ ሲታይ የኢትዮጵያ ማንሰራራት እውን እየሆነ እያየነው እየመጣን እንደሆነ ያመላክታል ብለዋል።
በሁሉም መስኮች እየታየ ነው። የዚህ ስኬት አስገራሚ ምልክት የቡልቡላ ፓርክ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ይህ ዓመት የኢትዮጵያ የማንሰራራት ዓመት ነው ባልነው መሠረት እየመጣ ያለው ለውጥ ይበል የሚያስብል ነው።” ሲሉ ገልጸዋል።
በተለያዩ መስኮች እያከናወንን ያለነው የተቋም ግንባታ እና ልማት ጥረታችን የሀገራችን ማንሰራራት ግልፅ ምልክት እንደሆነ ጠቁመው ይህ ስኬት በሁሉም መስኮች እየታየ ነው። የዚህ ስኬት አስገራሚ ምልክት የቡልቡላ ፓርክ ነው ብለዋል።
በአንድ ወቅት የቆሻሻ መጣያ የነበረ ሥፍራ በጥቂት ወራት ውስጥ ዋጋው ከፍ ወዳለ የሕዝብ መጠቀሚያ ተቀይሯል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የቦሌ ክፍለ ከተማ አመራሮች በራሳቸው ተነሳሽነት ከግሉ ዘርፍ ጋር በመተባበር ብሎም ማኅበረሰቡን በማስተባበር አስደናቂ ሥራ ሠርተዋል። የባለቤትነት መንፈሱ እና ቀድመው አስበው የመሥራት ተነሳሽነታቸው በሁሉም ዘርፍ መቀዳት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
እዚህ ሥፍራ የፈሰሰው ሀብት የዛሬውንም የነገውንም ትውልድ ያገለግላልና የአካባቢው ነዋሪ እንዲንከባከበው ጥሪ አቀርባለሁ። ባለድርሻ አካላት ሁሉ ደግሞ ይህን ጥረት በተቀሩት የከተማችን እና የሀገራችን ክፍሎች አሳድገው እንዲተገብሩ አደራ እላለሁ ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ከቦሌ ኤርፖርት ካርጎ ቡልቡላ እስከ አቃቂ ድልድይ በራስ አቅም የተገነባ ከ20 ሄክታር በላይ የሚሸፍን ሥራ የተሠራ ሲሆን ይህም የቡልቡላ ፓርክን ጨምሮ የአረንጓዴ ሥፍራዎች ፣ የመንገድ አካፋይ፣ ደረጃቸውን የጠበቁ ዘመናዊ የእግር ኳስ ሜዳዎች እንዲሁም በርካታ መሠረተ ልማቶች የተሠሩበት ሥፍራ እንደሆነ ተገልጿል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 23 ቀን 2017 ዓ.ም