ባለሥልጣኑ ሁሉንም የደንብ ጥሰቶች ለመከላከል ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያደርግ ገለጸ

አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ሁሉንም የደንብ ጥሰቶች ለመከላከል ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያደርግ ገለጸ። ተቋሙ የደንብ መተላለፎች እንዳይፈጸሙ ግንዛቤ ማስጨበጥን እንጂ ቅጣትን መሠረት ያደረገ ሥራ እንደማይሠራም ተጠቁሟል።

የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን የሥልጠና እና ቅድመ መከላከል ዘርፍ ኃላፊ አቶ ንጋቱ ዳኛቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ ፤ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ሁሉንም የደንብ ጥሰቶች ለመከላከል ክትትልና ቁጥጥር ያደርጋል። የከተማ አስተዳደሩ ቅጣት ከመጣል ይልቅ መከላከል ሥራ ላይ አተኩሮ ይሠራል።

ተቋሙ ከወንዝ ዳርቻዎች ልማት ጋር ተያይዞም በከፍተኛ ትኩረት ለህብረተሰቡ ግንዛቤ መስጠት ላይ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ንጋቱ ፤ ተቋሙ ግለሰቦችን መቅጣትን ዓላማው እንዳላደረገም ተናግረዋል።

በወንዝ ዳርቻዎች እና በኮሪዶር ልማቱ ላይ የሚፈጸሙ የደንብ መተላለፎችንም ለመከላከል የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እየተሠራ ባይሆን እና በቅጣት ላይ ብቻ ትኩረት ቢደረግ ከፍተኛ ገቢ መሰብሰብ እንደሚቻልም ገልጸዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ የሚያወጣቸውን ደንቦች ህብረተሰቡ እንዳይተላለፍ አስቀድሞ የማሳወቅ ሥራ ይሠራል የሚሉት ኃላፊው ፤ የደንብ መተላለፎች ሲፈጸሙ ህብረተሰቡ ላይ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና የጤና ጉዳት እንደሚከተል ጠቅሰዋል፡፡

ለአብነትም የደንብ ቁጥር 180/2017 በሚተላለፉ ግለሰቦች የወንዞች ብክለት ይፈጸማል፤ ይሄውም የጤና ጉዳት እንዲከሰት መንስኤ ይሆናል። ለዚህም ህብረተሰቡ የደንብ መተላለፎችን ሊከላከሉ እና ከመፈጸም ሊቆጠቡ ይገባል ብለዋል፡፡

እንደ ኃላፊው ገለጻ፤ ከትምህርት ቤቶች ጋር በጋራ በመሆን የደንብ መተላለፎች እንዳይፈጸሙ የማስገንዘብ ሥራ ይሠራል። በዚህም ለውጥ መጥቷል። ቅጣቶችን እና የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎችን አቀናጅቶ እየሠራ ነው። ተቋሙ ከወንዝ ጋር የፍሳሽ ማስወገጃዎቻቸውን ያገናኙ የትምህርት ተቋማት፣ ክሊኒኮች፣ ሆስፒታሎች፣ ፋብሪካዎች እና ሪልስቴቶች ሴፍቲ ታንከር እንዲገነቡ የምክር እና የቴክኒካል ድጋፍ እያደረገ ነው። በመኖሪያ ቤቶችም የፍሳሽ ማስወገጃ ታንከሮች እንዲዘጋጁ ለማድረግ እየተሠራ ነው።

የቁም እንስሳት የኮሪዶር ልማቱን እንዳያበላሹ፣ የተረፈ ምርቶች ከተማው ላይ እንዳይጣሉ፣ ቆሻሻዎችም የከተማዋን ውበት እንዳያጠፉ ለማድረግ ከጽዳት አስተዳደር ጋር በቅንጅት እየተሠራ ነው፡።

በሕገወጥ ንግድ ከሚወረሱ ንብረቶች ጋር ተያይዞ መንግሥት ራሱን የቻለ አሠራር አለው የሚሉት የባለሥልጣን መሥሪያቤቱ ኃላፊ፤ ከተወረሰ በኋላ የጨረታ ሂደት እንደሚፈጸምም ገልጸዋል።

መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You