ከትራምፕ ውሳኔዎች ጋር የሚፋጠጡት አዲሱ የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር

በካናዳ የተደረገውን ምርጫ የ‹‹ሊበራል ፓርቲ›› (Liberal Party of Canada) አሸንፏል። ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ጆሴፍ ካርኒ ፓርቲያቸው ድል እንደቀናው አውጀዋል። በምርጫው የምክር ቤት ወንበራቸውን የተሸነፉት የተቃዋሚው ‹‹ኮንሰርቫቲቭ›› ፓርቲ (Conservative Party) መሪ ፒየር ፖሊየቭ ፓርቲያቸው በምርጫው መሸነፉን አምነው፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ካርኒ የመልካም ምኞት መግለጫ አስተላልፈዋል። በዚህም መሠረት የካናዳ ሊብራል ፓርቲ ለአራተኛ ጊዜ ሀገሪቱን በጠቅላይ ሚኒስትርነት ለመምራት የሚያስችለውን ድምጽ አግኝቷል።

የሀገራትና የተቋማት መሪዎችም ለጠቅላይ ሚኒስትር ካርኒ የ‹‹እንኳን ደስ አለዎት›› መልዕክት እያስተላለፉ ይገኛሉ። ለአብነት ያህል የፈረንሳይ፣ የብሪታኒያ፣

ከትራምፕ ውሳኔዎች ጋር የሚፋጠጡት አዲሱ የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር የአውስትራሊያ፣ የኔዘርላንድስ፣ የዩክሬን፣ የህንድ፣ የአውሮፓ ኅብረትና የኔቶ መሪዎች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹እንኳን ደስ አለዎ›› ካሉ በኋላ፣ ከካናዳ ጋር በወዳጅነትና በጋራ ተጠቃሚነት መርሆች አብሮ ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸውላቸዋል። ቻይናም ከካናዳ ጋር ያላትን ግንኙነት በመከባበር፣ በእኩልነትና በጋራ ተጠቃሚነት መርሆች መሠረት ማሻሻልና ማጠናከር እንደምትፈልግ በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቷ በኩል ገልፃለች።

ማርክ ካርኒ ከድሉ በኋላ ለደጋፊዎቻቸው ባደረጉት ንግግር እንደተጠበቀው በአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ርምጃዎች ላይ አተኩረዋል። ‹‹አሜሪካ መሬታችንን፣ የተፈጥሮ ሀብታችንን እና ሀገራችንን ትፈልጋለች። ፕሬዚዳንት ትራምፕ ሊሰብረንና ሊቆጣጠረን ይፈልጋል፤ ያ ደግሞ በጭራሽ ፈጽሞ አይሆንም›› በማለት ለደጋፊዎቻቸው ተናግረዋል። ‹‹ካናዳ በታሪክ እጥፋት ላይ ትገኛለች›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ከአሜሪካ ጋር የነበረን የቆየ የትብብር ወዳጅነት አብቅቷል›› ብለዋል።

ሀገራቸው ከአውሮፓ እና ሌሎች አጋር ሀገራት ጋር ያላትን ወዳጅነት አጠናክራ እንደምትቀጥልም አስታውቀዋል። ካናዳ ከአሜሪካ ጋር የምታደርገውን የንግድ ጦርነት በድል እንደምትወጣውም ጠቅላይ ሚኒስትር ካርኒ ቃል ገብተዋል። ‹‹ለካናዳ የተሻለውን ለማስገኘት ባለን ነገር ሁሉ እንፋለማለን። ለታላቋ ሀገራችን ነጻ የሆነ መጻዒ ጊዜ እንፈጥራለን›› ብለዋል።

ከ20 ሚሊዮን በላይ ካናዳውያን ድምፃቸውን የሰጡበት ምርጫ፣ የመራጮች ቀዳሚ አጀንዳዎች በካናዳ ሉዓላዊነትና ምጣኔ ሀብት ላይ ትልቅ አደጋ ደቅነዋል የተባሉት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ርምጃዎች ናቸው። ፕሬዚዳንት ትራምፕ በካናዳ ምርቶች ላይ የጣሉት ታሪፍ እና ፕሬዚዳንቱ ካናዳ 51ኛዋ የአሜሪካ ግዛት እንደምትሆን ደጋግመው የተናገሩት ዛቻ መራጮች ድምፃቸውን ለየትኛው ፓርቲ መስጠት እንዳለባቸው በመወሰን ረገድ ትልቅ ሚና እንደነበራቸው ተገልጿል።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ጎረቤታቸው ካናዳ 51ኛዋ የአሜሪካ ግዛት መሆን እንዳለባት መናገራቸውና በካናዳ ምርቶች ላይ ታሪፍ መጣላቸው ሊብራል ፓርቲ እንዲያሸንፍ ማድረጉም ተገልጿል። ማርክ ካርኒ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት ላይ ብቻ ሳይሆን በሉዓላዊነቷም ላይ አደጋ መደቀናቸውን በመግለጽ የመራጮችን ልብ ማሸነፍ ችለዋል። ዶናልድ ትራምፕ ይህንን አቋማቸውን ይፋ ከማድረጋቸው በፊት የወግ አጥባቂው ተወዳዳሪ ፒየር ፖሊየቭ ያሸንፋሉ ተብሎ ይገመት ነበር።

ማዕቀብ ለመጣል፣ ታሪፍ ለመጨመር፣ ርዳታዎችን ለማቋረጥ እና ስምምነቶችን ለመሰረዝ ፈጣን ርምጃዎችን የሚወስዱት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ፕሬዚዳንታዊ ምርጫውን ካሸነፉ ከአንዳንድ ሀገራት ወደ አሜሪካ በሚገቡ ምርቶች ላይ ታሪፍ እንደሚጨምሩ ሲዝቱ ነበር። እንደዛቱትም የነጩን ቤት መንበር እንደተረከቡ ከአንዳንድ ሀገራት ወደ አሜሪካ በሚገቡ ምርቶች ላይ የታሪፍ ጭማሪ ማድረጋቸውን ገልፀው እንደነበር ይታወሳል። ከእነዚህ ሀገራት መካከል አንዷ ደግሞ ጎረቤታቸው ካናዳ ናት።

ይሁን እንጂ ይህን ውሳኔያቸውን አንድ ጊዜ ሲያራዝሙት፣ ሌላ ጊዜ እንደገና ሲመልሱት ቆይተዋል። በእርግጥ ፕሬዚዳንት ትራምፕ በመጀመሪያ የሥልጣን ዘመናቸው በፈረሙት የአሜሪካ፣ ካናዳና ሜክሲኮ ነፃ የንግድ ስምምነት (US-Mexico-Canada Trade Agreement – USMCA) መሠረት አንዳንድ ምርቶችን ከታሪፍ ጭማሪው ነፃ የማድረግ ርምጃ ወስደዋል። ካናዳም ከአሜሪካ በሚገቡ ምርቶች ላይ የታሪፍ ጭማሪ እንደምታደርግ አሳውቃ፣ ተመጣጣኝ ያለችውን ርምጃ ወስዳለች።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ለታሪፍ ጭማሪው የሚያነሷቸው ምክንያቶች ከአደንዛዥ መድኃኒቶችና ከሕገ ወጥ ስደተኞች እንዲሁም ከንግድ ሚዛን ኢፍትሃዊነት ጋር ተያያዥነት እንዳላቸው ሲገልፁ ቆይተዋል። ፕሬዚዳንት ትራምፕ የአሜሪካ ጎረቤቶች ካናዳና ሜክሲኮ ሕገወጥ ስደተኞችና እንደፌንታኒል (Fentanyl) ያሉ አደገኛ መድኃኒቶች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ቁጥጥር አያደርጉም የሚለውን የመረረ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል። ከዚህ በተጨማሪም ፕሬዚዳንቱ ‹‹አሜሪካ በጎረቤቶቿና በሌሎች የሩቅ ሀገራት ለበርካታ ዓመታት ስትበዘበዝ ኖራለች፤ በሀገራቱና በአሜሪካ መካከል ያለው የንግድ ሚዛን ኢፍትሃዊና አሜሪካን የጎዳ ነው›› የሚል አመለካከትም አላቸው።

ሀገሪቱን ላለፉት አስርት ዓመታት የመሩት የሊብራሉ ፓርቲው ጀስቲን ትሩዶ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ምንም ለውጥ ባለማሳየታቸው በፓርቲው ደጋፊዎች ዘንድ ቅሬታ ተፈጥሮ ነበር። ፓርቲውም ትሩዶን የባንክ ባለሙያ በሆኑት ማርክ ካርኒ ከተካ በኋላ ‹‹አስደናቂ›› የተባለውን የምርጫ ውጤት አግኝቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ካርኒ እስከ ግንቦት 18 አዲስ ካቢኔ ያዋቅራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ካናዳ ከአጠቃላይ የወጪ ንግዷ 75 በመቶ የሚሆነውን የምትልከው ወደ አሜሪካ ነው። ይህ የምጣኔ ሀብት አሃዝ ከትራምፕ የማዕቀብ ውሳኔ ጋር ሲተያይ የፕሬዚዳንቱ የታሪፍ ውሳኔ በካናዳ ምጣኔ ሀብት ላይ ቀላል የማይባል ተፅዕኖ እንደሚኖረው ግልጽ ነው። ስለሆነም የአሸናፊው የ‹‹ሊብራል›› ፓርቲ ሊቀ መንበርና የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ የሚጋፈጡት ከዚህ እውነት ጋር ነው።

የምጣኔ ሀብት አለመረጋጋት፣ በተለይም የመኖሪያ ቤት ዋጋ መናር፣ ላለፉት 10 ዓመታት ካናዳን በጠቅላይ ሚኒስትርነት ያገለገሉት ጀስቲን ትሩዶ፣ ከካናዳ ሊብራል ፓርቲ (Liberal Party of Canada) ሊቀ መንበርነትና ከሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ኃላፊነታቸው እንዲለቁ አስገድዷቸዋል። ይህ ችግር ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትርም ከባድ ፈተና እንደሚሆንባቸው ይጠበቃል።

ለፖለቲካ ቅርብ አልነበሩም ተብለው የሚወቀሱት የሀርቫርድና የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲዎች ምሩቁ ካርኒ ግን ካናዳ የፕሬዚዳንት ትራምፕን የታሪፍ ጦርነት እንደምታሸንፍ ቃል ገብተዋል። የ60 ዓመቱ የቀድሞው የካናዳ ባንክ (Bank of Canada) እና የባንክ ኦፍ ኢንግላንድ (Bank of England) ገዥ ካርኒ፣ የቀውስ ጊዜያት አመራር የመስጠት እንዲሁም ችግር የገጠመውን ኢኮኖሚ ከችግር አውጥቶ ጠንካራ የማድረግ ብቃት እንዳላቸው ይናገራሉ።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እንደሚያስረዱት፣ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በየጊዜው ይፋ የሚያደርጓቸው የታሪፍ ጭማሪዎች ለዋጋ ንረት፣ ለምጣኔ ሀብት መዳከምና ለዓለም አቀፍ የንግድ ጦርነት ያስከትላሉ። የታሪፍ ጭማሪው ለአሜሪካውያን ሸማቾች የምርቶች ዋጋ እንዲንር ያደርጋል፤ በካናዳም የምጣኔ ሀብት መቀዛቀዝ ይፈጥራል። ታላላቅ የፋይናንስና የኢንቨስትመንት ተቋማትን የመሩት የ60 ዓመቱ ካርኒና ፓርቲያቸው ለዚህ የሚሰጡት ምላሽ ወደፊት የሚታይና የካናዳውያንን ሕይወት የሚወስን ከባድ ትግል ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You