አዲስ አበባ፦ በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ላይ እንዲኖር የሚፈለገው የኢንዱስትሪ ባለቤትነት እየመጣ አለመሆኑን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሁለተኛው ዓለም አቀፍ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኮንፈረንስ በትናንትናው ዕለት ሲከፈት ሚኒስትሯ ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም እንዳሉት፣ ዘርፉ በከፍተኛ ሁኔታ ከኢንዱስትሪ ጋር መተሳሰር ያለበት ቢሆንም እስከ አሁን በሚፈለገው ልክ እየመጣ አይደለም ብለዋል ።
እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ የቴክኒክና ሙያ አሰለጣጠን 70/30 ነው፤ ይህ ሲባል ደግሞ 70 በመቶው በእጅ የሚነካ እጃቸውን ከብረቱ ከእንጨቱ ጋር የሚያገናኙበት ሲሆን፤ 30 በመቶው ግን በክፍል ውስጥ የሚሰጥ ትምህርት ነው። ከዚህ አንጻር ኢንዱስትሪው ዘርፉን በባለቤትነት ሊመራ የሚገባውን ያህል እየመራው ካለመሆኑም በላይ ሰልጣኞችም በሥራ ላይ ሊያገኙት የሚገባን እውቀት እየጨበጡ አለመሆኑን ጠቁመዋል።
በየዓመቱ ይህንን መሰል ኮንፈረንስ ማድረግ ያስፈለገውም አካሄዱን ለመቀየር ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ለመጋራት ነው ያሉት ሚኒስትሯ፣ በዚህም የእነ ጀርመንና ጃፓን እንዲሁም በአገር ውስጥም በዘርፉ ጥሩ ሥራን የሰሩ የግልና የመንግሥት
ተቋማት ልምዳቸውን እንደሚያጋሩም ነው የጠቆ ሙት።
ሚኒስትሯ እንዳሉት የዘርፉ ትልቅ ችግር ቴክኒክና ሙያ ዝም ብሎ በክፍል ትምህርት ብቻ እንዲጠናቀቅ መደረጉ ነው፡፡ በእርግጥ በተለያዩ ማሰልጠኛ ተቋማት መጠነኛ የልምምድ ቦታዎችና ዎርክሾፖች አሉ። እነዚህ በቂ ባለመሆናቸው ከኢንዱስትሪው ጋር በጋራ ባለቤትነት የሥልጠና ፕሮግራሙን ከመቅረጽና ከመለየት ጀምሮ የማሰልጠን ሂደቱ ላይም መስራት ያስፈልጋል፤ ይህንን ለማምጣት ሙከራዎችና ጥረቶች ቢኖሩም በሚፈለገው ደረጃ አልደረሰም ።
የኢንዱስትሪው የባለቤትነት ሂደት ገና አልመጣም ያሉት ሚኒስትሯ፣ ይህንን ሥልጠና ከዚህ አንጻር ቃኝተን ተግባራዊ በማድረግና ሥራ ፈጣሪዎችን በማበ ረታታት የተሻሉ ብቃት ያላቸው ሰዎችን ለማውጣት ተሳስረን እንስራ የሚለውም ለውይይት እንደሚቀርብ አመልክተዋል።
«ኢትዮጵያ ለቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና አዲስ አይደለችም፣ ከጥንት ጀምሮ እነ አክሱም ላሊበላን ሌሎችን የእጅ ጥበብ ሥራዎችን ሰርታለች፤ ነገር ግን ዘመናዊ የሆነና ኢኮኖሚውን የሚለውጥ ለመሆን አልቻለም። ስለዚህ የሥራ ገበያውን ፍላጎት የሚያሟላ ሰልጣኝ እንዴት አድርገን እናውጣ? ተነሳሽነት ያለውና ለራሱም ሥራ የሚፈጥር ባለሙያ ማውጣት እንዴት ይቻላል የሚለው ላይ ሰፊ ምክክር ይደረጋል ።
ዓለም ሁሉ በኢኮኖሚ ውድቀት ሲሰቃይ እነ ጀርመንና ጃፓን ቀጥ ብለው የቆሙት በቴክኒክና ሙያ የታገዘ ኢኮኖሚ ባለቤት በመሆናቸው ነው፤ እኛም ከዚህ ብዙ መማር ይኖርብናል ብለዋል ።
በጂ.አይ.ዜድ ቀጣይነት ያለው የትምህርትና ሥልጠና ፕሮግራም ሥራ አስኪያጅ ኒኮላ ዳሜ በበኩላቸው፣ በአገሪቱ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ የመጣ ቢሆንም አሁንም ወጣቶች ዘርፍን መርጠውት እንዲቀላቀሉ በማድረጉ በኩል ሰፊ ሥራ ያስፈልጋል ብለዋል።
እንደ እርሳቸው ገለጻ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ዘርፉ እንዲያድግ ከተፈለገ የተለያዩ የዘርፉ ተዋንያን በጋራ ለመስራት መወሰን አለባቸው፤ በተለይም የግል ዘርፉ የመንግሥት ተቋማትን በሥልጠና አሰጣጥ፣ በካሪኩለም ቀረጻ፣ በትምህርትና ሥልጠና ግብዓት መሟላት ላይ በማማከር ቢሳተፉ የሚሰጠውም ሥልጠና ደረጃውን የጠበቀ ሰልጣኞችም ብቁ ይሆናሉ፤ በመሆኑም ይህንን ለማድረግ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
በኮንፈረንሱ ላይ ዓለም አቀፍ ልምድ ያላቸው የተለያዩ አገራት ተወካዮች በአገር ውስጥ ያሉ የግልና የመንግሥት ተቋማት ተሳታፊ የሆኑ ሲሆን በዘርፉ ያሉ ችግሮችን እንዲሁም መፍትሔያቸውን በተመለከተም የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች እንደሚቀርቡ ታውቋል።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 24/2011
እፀገነት አክሊሉ