
አርባ ምንጭ:- የሲቪል ምዝገባ ሥርዓት ዘመኑን የዋጀ ፣ ጥራቱን የጠበቀ እና ተደራሽ እንዲሆን እየተሠራ እንደሚገኝ የኢሚግሬሽን ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ገለጹ ።
የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ አዋጅን አስመልክቶ መመሪያዎች፣ ረቂቅ ደንብና የአፈፃፀም መመሪያና ግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ በአርባምንጭ ከተማ ከትናንት በስቲያ ሲካሄድ እንደገለጹት ፤ የማንነት ግንባታ ሥርዓትን በተሟላ ደረጃ እውን ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል ። ይህም የአገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋ፣ ተደራሽ ፣ ግልፅ እና ውጤታማ ማድረግ የሚያስችል ሲሆን አፈፃፀሙ ሕገ-መንግሥቱን መሠረት ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል ።
ዋና ዳይሬክተሯ የምዝገባ ሥርዓትን ማሻሻል ዘለቄታዊ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ የመልካም አስተዳደር መርሆዎችና አሠራሮች በሁሉም ዘርፍ ተግባራዊ እንዲሆን ለማድረግ የሚያስችል ነውም ብለዋል።
ዘመናዊ የሕዝብ አስተዳደር ሥርዓት የሀገሪቱን ሕገ መንግሥታዊ መርሆዎችና ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸው ዓለምአቀፍ ስምምነቶች ላይ የተመሠረተ እና ለመልካም አስተዳደር ሥርዓት ግንባታ መሠረት የሆነ ነው ብለዋል።
የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ ሥርዓት አዋጅ ከዚህ ቀደም ፀድቆ ወደ ሥራ የተገባ መሆኑን ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሯ፤ በትግበራ ወቅት ማካተት የሚገባቸውን ቁልፍ ጉዳዮች ባለማካተቱ እና የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት የማያስችል ሆኖ ባለመገኘቱ የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ አዋጅ 1370/2017 ተሻሽሎ በሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት መጽደቁን አውስተዋል።
አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በሕገ መንግሥት እውቅና የተሰጣቸውን መሠረታዊ የዜጎችን መብትና ነፃነት በማክበርና በማስከበር ፣ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በአግባቡ ለመተግበር ዘመናዊ የሕዝብ አስተዳደር ሥርዓት አስፈላጊነትን ወይዘሮ ሰላማዊት በመድረኩ ጠቅሰዋል ።
የሲቪል ምዝገባ ማጠናከር ከዲጂታል መታወቂያ ጋር በጥምረት የሚሠራ እንደሆነ ጠቁመው፤ አንድ ሰው አንድ ማንነት ብቻ እንዲኖረው ከማድረግ ባሻገር ሕገ ወጥነትን በመቀነስ ረገድ ትልቅ ድርሻ የሚኖረው ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል ። በመድረኩ ላይ የሲቪልና የቤተሰብ ምዝገባ ረቂቅ መመሪያ በመድረኩ ላይ ቀርቦ ገለፃ አድርጓል።
በመድረኩ ላይ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ አቶ ዲማ ነጋዎ ፣ የአርባ ምንጭ ከተማ ዞን አስተዳዳሪ (ዶ/ር) ደምሴ አድማሱ ተገኝተዋል ።በቅርቡ የፀደቀውን የሲቪልና የቤተሰብ ምዝገባ አዋጅ አስመልክቶ አዋጁን ለማስፈፀም በተዘጋጀው ረቂቅ ደንብና የአፈፃፀም መመሪያዎች ውይይት እና ግብዓት የማሰባሰብ ሥራ ተሠርቷል፡፡
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 20 ቀን 2017 ዓ.ም