ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተከናወነ ንቅናቄ ለግድቡ ግንባታ አንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር ተሰበሰበ

አዲስ አበባ፦ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በመላው ሀገሪቱ እንዲሁም ኢትዮጵያውያን ባሉባቸው የዓለም ሀገራት በሙሉ በህብረተሰብ ተሳትፎ ዙሪያ ትልቅ የንቅናቄ ሥራ ተሠርቶ አንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ጊዜያዊ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ጊዜያዊ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ፍቅርተ ተዓምር ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳሉት፤ ህብረተሰቡ ለህዳሴው ግድብ ግንባታ እያሳየ ያለው ተሳትፎ አሁንም ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ በዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ አንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር ማዋጣት ችሏል ብለዋል፡፡

በመሠረቱ ህብረተሰብ ያልተሳተፈበት የልማት ሥራ ውጤታማ ይሆናል ብሎ ማሰብ ከባድ ነው የሚሉት ወይዘሮ ፍቅርተ፤ ይብዛም ይነስም ህብረተሰቡ ዐሻራውን ያኖረበት የእኔ ነው ብሎ ያመነበት የልማት ሥራ ውጤቱ አመርቂ ይሆናል፡፡ እንደ አጋጣሚ ወይም ደግሞ አስፈላጊ ሆኖ የህዳሴው ግድብ በራሳችን አቅም የሠራነው ከህጻን እስከ አዋቂ ፣ ከደሃ እስከ ሀብታም፣ ከምሁራን እስካልተማረው፣ ከነጋዴ እስከ ገበሬ ሁሉም የአቅሙን ያዋጣበት ፤ ያዋጣበት ብቻም ሳይሆን በአይነ ቁራኛ የሚጠብቀው ሥራ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

ግድቡ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ እስኪመረቅ ድረስ የሕዝቡ አንድነትና ህብረብሔራዊነት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ያሉት ወይዘሮ ፍቅርተ፤ ለወዳጆቻችን ጥንካሬና ውጤታችንን ፤ በጎ ሳይመኙልን ለቆዩትም አንድ ከሆንን ምንም የሚያሸንፈን ነገር እንደሌለ የምናሳይበት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

እንደ ወይዘሮ ፍቅርተ ገለጻ፤ የግድቡ ግንባታ ብዙ ውጣውረዶችን አልፎ የነቃ የህብረተሰብ ተሳትፎ ታክሎበት በከፍተኛ የመንግሥት ትኩረት ተሠርቶ የሲቨል (የኮንስትራክሽን) ሥራው ተጠናቋል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም የኮርቻ ግድቡና የዋናው ግድብ ግንባታም ሙሉ በሙሉ አልቋል ካሉ በኋላ በሚቀጥለው አዲስ ዓመት 2018 ዓ.ም መጀመሪያ አካባቢ መንግሥትና ሕዝብ በጋራ ሪቫን ይቆርጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቅሰዋል፡፡

እፀገነት አክሊሉ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You