“የመሶብ መጀመር ለኢትዮጵያ ሕዝብ ትልቅ የምስራች ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፡- መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መጀመር ለኢትዮጵያ ሕዝብ ትልቅ የምስራች ነው፤ ኢትዮጵያ በዚህ ማዕከል ላይ ጨምራ እና አስፋፍታ ለዜጎች ሁሉ የተሻለ የአገልግሎት አሰጣጥን ታረጋግጣለች ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ምረቃን አስመልክተው በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መጀመር ትልቅ ርምጃ መራመዳችንን ያሳያል። በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ ዜጎቻችን ላይ ምሬት የሚፈጥሩ አሠራሮችን ፈትሾ ማስተካከል ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ ነው። ለዚህ ቁርጠኝነታችን አንዱ ማሳያ የሆነውን መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን መርቀናል ብለዋል።

ይህን አዲስ ማዕከል የሚገልጡ ሶስት ቁልፍ አላባውያን አሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የቆየ እና የተጎዳ ህንፃን ወደ ዘመናዊ እና ሥነ ውበታዊ ደረጃው ለሥራ ከባቢ አስደሳች ወደ ሆነ ህንፃ መለወጡ አንዱ ነው። አገልግሎቶችን ለመሰተር እና ለማቀናጀት በሀገር ውስጥ የለማ ሶፍትዌር በሥራ ላይ መዋሉ ብሎም በታደሰ አመለካከት ብቁ እና ክብር የሞላበት አገልግሎት የሚሰጡ ወጣቶች መዘጋጀታቸው ሌሎቹ አላባውያን ናቸው ሲሉ ጠቅሰዋል።

12 ተቋማት በአንድ ጣሪያ ሥር 40 የተለያዩ አገልግሎቶችን መስጠት የጀመሩ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህም ዜጎች ጊዜያቸውን እንዲቆጥቡ እና አገልግሎቶችን በተሻለ ውጤታማ መንገድ ለማግኘት እንደሚያግዝ ነው የገለጹት።

እንደዚህ ያሉ ሥርዓቶችን ማበልፀግ ለዜጎች የተለያዩ የአገልግሎት ርካታ መታጣቶች ምላሽ በመስጠት በሂደት ለሰፊው ማኅበረሰብ ርካታ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ምረቃ ትልቅ ርምጃ መራመዳችንን ያሳያል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በዚህ ማዕከል ላይ ጨምራ እና አስፋፍታ ለዜጎች ሁሉ የተሻለ የአገልግሎት አሰጣጥን እንደምታረጋግጥ አመልክተው፤ የዚህ ዓመት የኢትዮጵያ የማንሰራራት ጅማሮ ነው ስንል አንዱ የሕዝብ ምሬትና ቅሬታ ያሉባቸውን ዘርፎች ዘላቂ በሆነ መንገድ በሚፈታ መልኩ ሪፎርም ማካሄድ ነው ብለዋል።

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ገለጻ፤ ዛሬ መሶብ ተወልዷል። መሶብ የአንድ አገልግሎት ማዕከል መስጫ ነው። ይህም በንግድ ፈቃድ፣ በገቢዎች፣ በኦዲት ፓስፖርትና መሰል አገልግሎቶች የሚሰሙ ምሬቶችን መፍታት የሚያስችል ነው። ማዕከሉም ሥራ የሚያቀላጥፍበት፣ ሌብነት የሚጠፋበት፣ ኢንቨስትመንት የሚስፋፋበት እንዲሆን ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።

ለኢትዮጵያ ሕዝብ መንግሥታዊ አገልግሎቶችን ማዘመንና ማቀላጠፍ ቃል የገባንበት ጉዳይ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህንም በመሶብ ተረጋግጧል ብለዋል። በቀጣይም የመሶብን የአንድ ማዕከል አገልግሎት ወደ ሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎችና ከተሞች ለማስፋፋት በትኩረት እንደሚሠራም አመልክተዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You