እግር ኳስና – ፖፕ ፍራንሲስ!

የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አቡነ ፍራንሲስ በሕይወት ዘመናቸው ከኃይማኖት አባትነታቸው ባሻገር በዓለማችን በተለያዩ መስኮች ተፅዕኖ በመፍጠር ገናና ስም አላቸው። አቡኑ በስፖርቱ መንደር በተለይም ከተወዳጁ እግር ኳስ ጋር ያላቸው ቁርኝትም ቀላል አይደለም።

ከዓለማችን የምንጊዜም ድንቅ የእግር ኳስ ኮከቦች ዲዬጎ ማራዶናና ሊዮኔል ሜሲ ሀገር ከሆነችው አርጀንቲና የተገኙ ታላቅ የኃይማኖት አባት ናቸው። ሀገራቸው ላፈራቻቸው ሁለቱ ኮከቦች ያላቸው ፍቅርም ትልቅ ነው። በአጠቃላይ ለስፖርት በተለይም ለእግር ኳስ ያላቸው በጎ አመለካከትም በስፖርቱ ዘርፍ እንዲታወሱ ያደርጋቸዋል።

ፖፕ ፍራንሲስ መጋቢት 13 ቀን 2013 266ኛው የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው ሲመረጡ 1 ሺህ 300 በሚጠጉ ዓመታት ውስጥ የመጀመሪያው ከአውሮፓ ውጭ ያሉ የቫቲካን መንበር የበላይ ጠባቂ ሆነዋል። ይህንንም ተከትሎ ሁሉ ነገራቸውን ከእግር ኳስ ጋር ማገናኘት የሚወዱት አርጀንቲናውያን “ሁለተኛው የእግዜር እጅ” ሲሉ ነበር ደስታቸውን የገለፁት። አርጀንቲናውያን የመጀመሪያው “የእግዜር እጅ” የሚሉት ዘመን አይሽሬው ኮከብ ማራዶና በ1986 የሜክሲኮ ዓለም ዋንጫ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ላይ እንግሊዝ ላይ በእጁ ግብ ያስቆጠረበትን ተዓምራዊ አጋጣሚ ነው።

ፖፕ ፍራንሲስ ለእግር ኳስ ያላቸው ፍቅር መታወቅ የጀመረውም የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው መመረጣቸውን ተከትሎ ነበር። የሀገራቸው ክለብ ሳን ሎሬንዞ የልብ ደጋፊም ናቸው። መመረጣቸውን ተከትሎ ይህ ክለብ ፖፕ ፍራንሲስ የክለቡን አርማ ይዘው የሚያሳይ ፎቶ ግራፍ በትዊተር ገፁ አጋርቶ ነበር። እሳቸውም የክለቡን አርማ ብቻ ሳይሆን የአባልነት ካርድ ይዘው ኖረዋል። የካርድ ቁጥራቸውም 88,235 ነው።

“ቅዱሳኖቹ” በሚል ቅፅል ስም የሚታወቀው ሳን ሎሬንዞ ክለብ አቡነ ፍራንሲስ ለታላቁ መንበር ከተመረጡ በኋላ ጠንካራ ተፎካካሪ መሆን ችሏል። እኤአ 2013 ላይ የሀገሩን ሊግ አሸንፏል። ከዓመት በኋላም የኮፓ ሊበርታዶሬስን ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ማንሳት ችሏል። በዚህም የክለቡ ኃላፊዎች ፖፕ ፍራንሲስን ለድጋፋቸው ከአንዴም ሁለቴ ዋንጫ ተሸክመው ቫቲካን ድረስ በመሄድ ምስጋና አቅርበዋል።

ፖፕ ፍራንሲስ በ88 ዓመታቸው ባለፈው ሰኞ ቫቲካን በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው አርፈው ትናንት ሥርዓተ ቀብራቸው ተፈፅሟል። ማረፋቸውን ተከትሎም ጥልቅ ኀዘኑን የገለፀው ከልብ የሚደግፉት ክለባቸው ነበር። ክለቡ ፖፕ ፍራንሲስ ልጅ እያሉ 1946 ላይ ቡድኑን ሲመለከቱ የተነሱትን ፎቶ ግራፍ “ሁሌም ከእኛ እንደ አንዱ ነው” ከሚል መግለጫ ጋር በኢንስታግራም ገፁ በማጋራት ኀዘኑን ገልጿል። ሳን ሎሬንዞ ክለብ አዲስ የሚያስገነባውን ስቴድየም “ፍራንሲስ” በማለት የመሰየም እቅድ እንዳለውም ተሰምቷል።

አቡነ ፍራንሲስ ልዩ ቦታ ከሚሰጡት ማራዶና ጋር በመንበራቸው እያሉ ሁለት ጊዜ በአካል ተገናኝተዋል። እኤአ 2014 ላይ በአንድ በጎ አድራጎት ጨዋታ ላይ በተገኛኙበትም ወቅት ማራዶና 10 ቁጥር ዝነኛ ማሊያው ላይ ፍራንሲስኮ በሚል ስማቸው በስፓኒሽ ቋንቋ ታትሞበት አበርክቶላቸዋል። ከዓመት በኋላ ሲገናኙም ማራዶና የአቡነ ፍራንሲስ አድናቂ መሆኑን ተናግሯል። እሳቸውም አርጀንቲናዊው ኮከብ 2020 ላይ ሕይወቱ ማለፉ በተሰማበት ወቅት ፀሎተ ፍትሀት አድርገውለታል።

የዘመናችን ሌላኛው የእግር ኳስ ንጉስ ሊዮኔል አንድሬስ ሜሲ የፖፕ ፍራንሲስን ህልፈት ተከትሎ በማህበራዊ ትስስር ገፁ “ዓለማችንን የተሻለች ስላደረክልን ሁሉ እናመሰግንሃለን፣ ሁሌም ትናፍቀናለህ” በማለት ኀዘኑን በኢንስታግራም ገፁ አስተላልፏል።

እጅግ ከሚያደንቁት ማራዶና እስከ ሜሲና ሌሎች በርካታ የእግር ኳስ ኮከቦችን፣ ትልልቅ የዓለም እግር ኳስ መሪዎችን በተለያዩ አጋጣሚዎች በመንበራቸው ተቀብለው በማነጋገርና ማሊያቸውን ለማስታወሻ በመውሰድ እግር ኳስንና ተፅዕኖ ፈጣሪነታቸውን ለበጎ ነገር እንዲጠቀሙበት ምክራቸውን ሲለግሱ የኖሩትን የአቡነ ፍራንሲስ ህልፈት ተከትሎ የስፖርቱ ዓለም ኀዘኑን እየገለፀ ይገኛል።

ከፊፋ እስከ ዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ መሪዎች፣ ከአንጋፋ እስከ ወጣት ከዋክብት ተጫዋቾች፣ ከታላላቅ የዓለማችን ክለቦች እስከ ሊጎች የኀዘን መግለጫዎችን አውጥተዋል። ባለፈው ሰኞም በ33ኛ ሳምንት መርሀግብር ሊካሄዱ የነበሩ አራት ጨዋታዎች የሴሪ ኧ ጨዋታዎችን ጨምሮ በጣሊያንና አርጀንቲና እስከ ታችኛው ርከን የሚካሄዱ ጨዋታዎች ተሰርዘዋል።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You