
– ከተመዘኑት ውስጥ 33 ሺህ 704 ሠልጣኞች ብቁ መሆናቸውን አረጋግጧል
አዲስ አበባ፡- በ2017 በጀት ዓመት በዘጠኝ ወራት 66 ሺህ 508 ለሚሆኑ የመንግሥትና የግል የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ሠልጣኞች የሙያ ብቃት ምዘና ማድረጉን የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ሥልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣን አስታወቀ። ከተመዘኑት ውስጥ 33 ሺህ 704 የሚሆኑት ብቁ መሆናቸውን እንዳረጋገጠ ጠቁሟል።
የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ሥልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣን የቴክኒክና ሙያ ብቃት ምዘና አገልግሎት ዝግጅትና አሰጣጥ ዳይሬክተር ወይዘሮ ራሄል ማሞ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ ዓምና ከተሠራው የሙያ ብቃት ምዘና ይልቅ የዘንድሮው ቀዝቀዝ ብሏል። ይህ የሆነበት ምክንያት የምዘና ስትራቴጂ ቁጥሩ ስለተቀየረ ነው ብለዋል፡፡
በዚሁ አዲስ የምዘና ስትራቴጂ ቁጥር መሠረት ባለሥልጣኑ በ2017 በጀት ዓመት በዘጠኝ ወራት ውስጥ ለ66 ሺህ 508 ሠልጣኞች የሙያ ብቃት ምዘና ማድረጉንና ከዚህ ውስጥ ወደ 33 ሺህ 704 የሚሆኑት ብቁ መሆናቸውን እንዳረጋገጠ ተናግረዋል። ይህም ከተመዘኑት የቴክኒክና ሙያ ሠልጣኞች ውስጥ 59 ነጥብ 9 ከመቶ የብቃት ምጣኔውን እንደሚያሳይ ዳይሬክተሯ ጠቁመዋል።
ምዘናው ከተጀመረበት ከ2000 ዓ.ም አንስቶ እስካሁን ድረስ ባጠቃላይ ባለሥልጣኑ ከ አንድ ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ምዘና ማካሄዱንም ዳይሬክተሯ ገልፀዋል፡፡
ዓምና ደረጃ በደረጃ ያሉ የቴክኒክና ሙያ ሠልጣኞች ይመዘኑ እንደነበር ያስታወሱት ዳይሬክተሯ፤ ሆኖም የሙያ ብቃት መመዘኛ ፖሊሲው መቀየሩን ተከትሎ ዘንድሮ ተጠቃሎ ደረጃ አራት ላይ እንዲመዘኑ መደረጉን ተናግረዋል።
በዚሁ መሠረት ደረጃ በደረጃ የነበረው ምዘና እዛው ሠልጣኞች ባሉበት ተቋም ውስጥ እንዲሰጥ መደረጉንና ይህን ምዘና ካጠናቀቁ በኋላ የመጨረሻው ደረጃ ላይ ሲደርሱ ተቋሙ ምዘናውን እንደሚያካሂድ ጠቁመዋል። በዚሁ መሠረት ዘንድሮ ለ66 ሺህ 508 ሠልጣኞች የመጨረሻውን የደረጃ አራት የሙያ ብቃት ምዘና ማድረጉን ዳይሬክተሯ አብራርተዋል።
በዘንድሮው በጀት ዓመት የመጣውን አጠቃላይ የቴክኒክና ሙያ ሠልጣኝ መቶ ከመቶ ለመመዘን እቅድ መያዙን የተናገሩት ዳይሬክተሯ፤ አሁን ባለው ደረጃ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ለምዘና የመጣው የቴክኒክና ሙያ ሠልጣኝ ቁጥር ግን 66 ሺህ 508 መሆኑን ገልፀዋል። በቀሪዎቹ ወራትም የመጣውን ሁሉ ተመዛኝ ተቀብሎ በማስተናገድ ሙሉ በሙሉ እቅዱን ለማሳካት ባለሥልጣኑ እየሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
የኢንዱስትሪ ተቋማት ለምዘና ክፍት አለመሆንና በባለቤትነት ሥራውን አለማገዝ፣ መዛኞችን በደምብ አጥርቶና አሳትፎ ያለመላክ እና በተመዛኞች በኩል ስለምዘና ያለው አመለካከት ደካማ መሆንና ከምዘና ይልቅ አቋራጭ መንገዶችን መፈለግ በምዘና ሂደት እየገጠሙት ያሉ ችግሮች መሆናቸውንም ዳይሬክተሯ አመልክተዋል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 19 ቀን 2017 ዓ.ም