በሕገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ ከ59 ሺህ ሊትር በላይ ነዳጅ ተያዘ

አዲስ አበባ፡- በመዲናዋ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት በሕገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ ከ59 ሺህ 944 ሊትር በላይ ነዳጅ መያዙን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሀቢባ ሲራጅ የቢሮው የ2017 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወር አፈጻጸም ሪፖርት ግምገማ ሰሞኑን ሲካሄድ እንደተናገሩት፤ በዘጠኝ ወራት በኮንትሮባንድ እና በሕገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ 47ሺህ 311 ሊትር ቤንዚን፤ 12ሺህ 444 ናፍጣ እና 189 ሊትር ነጭ ጋዝ በድምሩ ከ59 ሺህ 944 ሊትር በላይ ነዳጅ መያዝ ተችሏል።

እንዲሁም 48 ኬሻ ቡና በተደረገ ቁጥጥር በመያዝ አሠራሩን ጠብቆ እንዲሸጥ መደረጉን አመልክተው፤ በዚህም ነዳጅን ጨምሮ ከ10 ሚሊዮን 207 ሺህ ብር በላይ ለመንግሥት ገቢ ተደርጓል ብለዋል።

ኃላፊዋ እንደገለፁት፤ ሕገወጥ የነዳጅ ዝውውርን ለመቆጣጠር በተከናወኑ ተግባራት ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር መሠረታዊ መሻሻል ታይቷል። የንግድ ሕገ ወጥነትን ለመከላከል በተደረገው የቁጥጥር ሥራ መቶ በመቶ ሕገ ወጥ ነጋዴዎችን ወደ ሕጋዊ መስመር መመለስ ተችሏል፡፡

በ340 ሺህ 553 የንግድ ድርጅቶች ላይ የበር ለበር ክትትል በማድረግ የንግድ ሕገ ወጥነትን ለመከላከል መታቀዱን የገለጹት ወይዘሮ ሀቢባ፤ በዘጠኝ ወራት በ375 ሺህ 989 የንግድ ድርጅቶች ላይ ክትትል መደረጉን አስረድተዋል፡፡

በሶስተኛው ሩብ ዓመት ለ80 ሺህ 687 ዜጎች አዲስ የንግድ ሥራ ፈቃድ ለማውጣት የተቻለ ሲሆን፤ በዚህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ለ12 ሺህ 729 ዜጎች ተጨማሪ አገልግሎት ለመስጠት ተችሏል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ኃላፊዋ እንደገለጹት፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የበዓል ወቅት ልዩ የገበያ ውሎዎችን ጨምሮ በቅዳሜና እሁድ ገበያ፤ 541 ሺህ 871 ኩንታል የሰብል ምርት፤ ከሁለት ሚሊዮን 469 ሺህ ኩንታል በላይ አትክልትና ፍራፍሬ፤ እንዲሁም 265 ሺህ 798 የቁም ከብት ለገበያ መቅረቡን አስረድተዋል፡፡

መንግሥት ድጎማ የሚያደርግባቸውን የፍጆታ እቃዎች በተመለከተም፤ 226 ሺህ 563 ኩንታል ስኳር፤ ሶስት ሚሊዮን 186 ሺህ 269 ሊትር የምግብ ዘይት እና ከ266 ሚሊዮን 407 ሺህ በላይ ዳቦ መሰራጨቱን ተናግረዋል፡፡

የነዳጅ ስርጭት ጉድለት ለመከላከል የተጀመረውን የቁጥጥር ሥራ ማጠናከር፤ እሴት የማይጨምሩ ደላሎችን ከንግድ ሥርዓቱ በማስወጣት አምራች እና ሸማቹን ማገናኘት እና የምርት አቅርቦት በስፋት እንዲኖር ማድረግ ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡

ዓመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You