
ሀገራችን የረጅም ዘመን የሀገረ መንግሥት ታሪክ ካላቸው ጥቂት የዓለም ሀገራት በቀዳሚነት የምትጠቀስ ናት። በእነዚህ ረጅም ዘመናት ውስጥም በደግም፤ በክፉም የሚጠቀሱ ሰፊ ታሪኮች ባለቤት ናት። ከሁለም በላይ በየዘመኑ የነበሩ ትውልዶች ከቀደመ ሀገራዊ የከፍታ ትርክት ተነስተው ያንን ዘመን ለመመለስ የሚያስችል በቁጭት የተሞላ መነሳሳት ነበራቸው። ይህ መነሳሳት በሕዝቡም ዘንድ የሚስተዋል ሀገራዊ አጀንዳ ሆኖ ዘመናት ተቆጥረዋል።
በዘመናት መካከል እንደ ሀገር ገነን ከመጣንባቸው ሥልጣኔዎች/ የአክሱም የላሊበላ… ወዘተ/ ወርደን የመጣንበት የማነስ ሀገራዊ እውነታ፤ የየዘመኑን ትውልድ አንገት ያስደፋ፤ በብዙ ቁጭት ለሀገራዊ ትንሳኤ እንዲነሳሳ መነቃቃትን የፈጠረ ነው። መነቃቃቱን ወደ ተጨባጭ ልማት መለወጥ የሚያስችል የፖለቲካ ባሕል አለማዳበራችን፤ ዛሬም ድረስ ሀገራዊ ፈተና ሆኖ ብዙ ዋጋ እያስከፈለም ይገኛል።
እንደ ሀገር ያለን ገና ያልተነካ የተፈጥሮ ሀብት፣ ተስማሚ አየር፣ ሰፊ የሚለማ መሬት፣ ውሃ እና አምራች የሰው ኃይል ወደ ቀደመው ከፍታችን ለመመለስ በትውልድ መካከል የነበረውን እና አሁንም ያለውን መነቃቃት ተጨባጭ ልማት ለማድረግ ትልቅ አቅም እንደሚሆኑ፤ ከትናንቶች መማር የሚያስችል ልብ እና ማስተዋል መፍጠር ከቻልን የዘመናት የታሪክ ትርክቶቻችንም የመመለስ ጉዟችንን እንደሚያቀሉት የብዙዎች እምነት ነው።
በተለይም የፖለቲካ ባሕላችን ላይ ያለውን ተግዳሮት መሻገር የሚያስችል የፖለቲካ ተሃድሶ፤ ዘመኑን የሚመጥን የትውልድን ተለውጦ የመገኘት መሻት የሚሸከም የአስተሳሰብ ልዕልና መገንባት የሚያስችል ትውልዳዊ ዝግጁነት መፍጠር ከቻልን አሁናዊ ዓለም አቀፍ እውነታዎች ሀገራዊ ትንሳኤያችንን ለማፋጠን እንደ መልካም አጋጣሚ የሚወሰዱ፤ ትውልዶች የናፈቁትን ሀገራዊ ከፍታ ተጨባጭ ለማድረግ አቅም የሚሆኑ ናቸው።
ለዚህ ደግሞ ባለፉት ስድስት ዓመታት እንደ ሀገር የመጣንበትን ተለውጦ የመለወጥ መንገድ በአግባቡ ማጤን፤ በዚህ የለውጥ ሂደት ለተገኙ ስኬታማ ተሞክሮዎች ተገቢውን ትርጉም ሰጥቶ መገምገም ተገቢ ነው። በተለይም ለውጡ ይዞት የመጣውን አዲስ የፖለቲካ እሳቤ/ባህል አጠቃላይ ከሆነው የትውልድ ወደ ቀድመ ከፍታ የመመለስ መሻት ጋር አስተሳስሮ ማየት ወሳኝ ነው። እንደ ሀገር የምንፈልገውን ብልፅግና እውን ለማድረግም ቀዳሚ የቤት ሥራ ነው።
ሁሉ እያለን ወደ መሻታችን እንዳንጓዝ እና ወደቀደመው ከፍታችን እንዳንመለስ በዘመናት መካከል እንደ ጥላ ሲከተለን የኖረው፤ ትናንት ላይ ቸንክሮ ያቆመን አክሳሪ የፖለቲካ ባሕላችን ስለመሆኑ ብዙ መናገር አይፈልግም። “በአሸናፊ ተሸናፊ” ትርክት የሚሰላው የፖለቲካ ባሕላችን እርስ በርሳችን እንዳንደማመጥ ከማድረግ ባለፈ፤ የውጭ ኃይሎች መሻታችንን ተጨባጭ ማድረግ የምንችልባቸውን ዕድሎች እንዲያጨልሙ፤ የጥፋት ተልዕኳቸው በእኛ ላይ ፍሬ እንዲያፈራ አቅም ሆኗቸዋል።
በተለይም ታሪካዊ ጠላቶቻችን የኛን መበልጸግ/ወደ ከፍታችን መመለስ የህልውናቸው ስጋት አድርገው ከመውሰዳችው ጋር በተያያዘ እንደ ሀገር ያለንን ህልውና ከመገዳደር የሚቦዝኑበት አንዳች ደቂቃ ይኖራቸዋል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው። እነዚህ ጠላቶቻችን ትናንት ያደረጉንን ትተን አሁን ድህነትን ታሪክ ለማድረግ የጀመርነውን ጥረት ለማሰናከል እየሄዱበት ያለውን የጥፋት መንገድ ቆም ብሎ ማሰብ ተገቢ ነው።
ከለውጡ ማግሥት ጀምሮ ያጋጠሙን ፈተናዎች እና ተግዳሮች፤ የእነዚህ ጠላቶቻችን የአደባባይ ሴራ ውጤቶች ናቸው። ከእያንዳንዷ ግጭት፤ የጥፋት ትርክት እና ትርክቱ ከፈጠረው ግራ መጋባት፣ ሁከት እና ብጥብጥ፤ ሞት፣ ስደት እና መፈናቀል በስተጀርባ አሉ። ዕድሉን ከሰጠናቸው ወደፊትም ይኖራሉ።
እነዚህ ጠላቶቻችን ለውጡን እና ለውጡ የተሸከመውን የትውልዶች መሻት የቱን ያህል በውስጥም በውጭም እየተፈታተኑት እንደሆነ፤ የቱን ያህል ዋጋ እንዳስከፈሉን እና እያስከፈሉን እንደሆነ ዓይናችንን ከፍተን ልንመለከት ይገባል፤ እየተገዳደሩት ያለው የእዚህን ትውልድ ብቻ ሳይሆን የብዙ ትውልዶችን መሻት መሆኑንም ማስተዋል ያስፈልጋል። ይህንን ስለራሳችን፣ ስለልጆቻችን እና ልጅ ልጆቻችን ስንል ልናደርገው የሚገባ ትውልዳዊ ፤ ታሪካዊ አደራ ነው።
ይህን ማድረግ መቻል በብዙ ትውልዶች ባለተስፋ ሆና ያለፈችውን ሀገራችንን የተስፋዋ ባለቤት የማድረግ ጅማሬ ነው፤ በየዘመኑ የነበሩ ትውልዶች ከቀደመው ሀገራዊ የከፍታ ትርክታችን ተነስተው ያንን ዘመን ለመመለስ የፈጠሩትን የቁጭት መነሳሳት፤ ለዚሁ የከፈሉትን ዋጋ አክብሮ የመቆም ቁርጠኝነት ነው። በብዙ ፈተናዎች ውስጥ እየተለወጠች ያለችን ሀገራችንን የለውጥ ጉዞ የማስቀጠል “አልፋ እና ኦሜጋም” ነው!
አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 19 ቀን 2017 ዓ.ም