በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አነሳሽነት፣ በሕዝቡም ይሁንታ የተጀመረው አገራዊ የችግኝ ተከላ መርሃግብር ችግኞች ባለቤት ኖሯቸው ለውጤት እንዲበቁ የሚያስችል መሆኑ እየተገለጸ ነው፡፡
በያዝነው ክረምት አራት ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ እስካሁን ከ3ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ ችግኝ ተተክሏል፡፡ ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ ቀን በአንድ ጀንበር 200 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ 23 ሚሊዮን ሕዝብ የተሳተፈበት 353 ነጥብ 6 ሚሊዮን ችግኝ መትከል ተችሏል፡፡
የችግኝ ተከላው (አረንጓዴ አሻራው) የተራቆተውን መልከዓ ምድር የማዳንና በደን ልማት ላይ ለተንጠለጠለው የኢትዮጵያ ብልጽግና ምስጢር መፍቻ እንዲሁም የዘላቂ ልማት ጉዞ ሃዲድ መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባ ምሑራን ያሳስባሉ፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ሕይወት ተመራማሪው ፕሮፌሰር ለገሰ ነጋሽ እንደሚሉት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕዝቡ በደን ልማት እንዲሳተፍ ባቀረቡት ጥሪ መሠረት ሕዝቡ ባለቤት ሆኖ የችግኝ ተከላ ሥራውን መጀመሩ በእጅጉ ያስደስታል፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ በብዙ ነገር ሀብታም ብትባልም፤ ዛፎቿ ባለቤት አጥተው ምድሪቱ በመራቆቷ የዛፍ ድሃ ሆናለች፡፡ አሁን የተጀመረው ሥራ ግን ችግኞችን በመትከል፣ በመጠበቅና በመጠቀም ዛፎች ባለቤት እንዲያገኙ ያደረገ መሆኑ ሥራው የሚበረታታ፤ ዘላቂነት ኖሮትም ውጤት የሚያመጣ ይሆናል፡፡
በአካባቢ ደንና አየር ንብረት ኮሚሽን በደን መመንጠር የሚመጣ አማቂ ጋዝ ልቀት ፕሮጀክት (ሬድ ፕላስ) ሴክሬታርያት ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ ዶክተር ይተብቱ ሞገስ እንደሚናገሩት፤ አንድ አጀንዳ ሆኖ ኢትዮጵያውያንን ያሰባሰበው የችግኝ ተከላ መርሃግብር በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ የልማት ሥራ ውስጥ ትልቅ ድርሻ አለው፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ የዝናብ ጥገኛ ከሆነው ግብርናዋ ጀምሮ፣ የኃይል አቅርቦቷ፣ ቱሪዝሟ፣ የመጠጥ ውሃዋ፣ አጠቃላይ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎቿ በደን ሀብት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡
«የዚህ ዓመት የችግኝ ተከላ ከሌሎቹ ዓመታት የሚለይበት የራሱ ባህሪ አለው፡፡ ከእነዚህ አንዱ አገራዊ አጀንዳ ተደርጎ መያዙ ሲሆን፣ ችግኞቹ ሲዘጋጁም ሆነ እንዲተከሉ ሲደረጉ ግልጽ በሆነ መመሪያ ነው፡፡ ደረጃውን የጠበቀ ችግኝ በተገቢው ሁኔታ ባለቤት ኖሮት ከተተከለና እንክብካቤ ከተደረገለት ለውጤት የማይበቃበት ምክንያት የለም» ሲሉ ዶክተተር ይተብቱ ይገልፃሉ፡፡
እንደ ፕሮፌሰር ለገሰ ገለጻ ደግሞ፤ የኢትዮጵያ የልማት ችግሮች ሁሉ ሰንኮፍና እንብርት የደኖች መመናመን ነው። በዚህ ሂደት የአገር በቀል ዛፎች ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል።
ምክንያቱም እነዚህ ዛፎች አንደኛ፣ ረዥም ዕድሜ በመቆየት በትውልድ ቅብብሎሽ አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆን፣ ሁለተኛ የመሬትን ለምነት በማሳደግ ለኢትዮጵያ ግብርና የድርሻቸውን የሚያበረክቱ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ዝግባ ተተክሎ ከ500 እስከ አንድ ሺ ዓመትና ከዚያም በላይ የሚቆይ ነው፡፡ የአገር በቀል ዛፎች ደግሞ የኢትዮጵያ የውሃ ምንጮች፣ የስብጥር ብዝሃ ሕይወት መከሰቻ፣ የአፈር ለምነት ማህጸኖች ናቸው፡፡ ቱሪስቶች ጭምር ወደ ኢትዮጵያ ሊመጡ የሚችሉት የአገር በቀል ዛፎች ሲኖሩ ነው፡፡
ሁለተኛው ጉዳይ ለመጠቀም ከማሰብ በፊት ኢትዮጵያ ቅድሚያ ማተኮር ያለባት እየፈራረሰ ያለውን መልከዓ ምድሯን መመለስ ላይ ነው፡፡ የካርቦንም ሆነ መሰል የሽያጭ ግኝቶች ላለው ሁኔታ ትርጉም አይሰጡም፡፡ በመቶ ዓመታት ሂደት በተፈጠረ የደን መመናመን መልከዓ ምድሯ ፈርሷል፤ አፈሯ ታጥቧል፤ ትውልዱም እየጫጨ ነው፡፡
ይህ ደግሞ አገር በቀል ዛፎች ለአፈር ሊለግሱ የሚገባቸውን 17 ያህል ንጥረ ነገሮች አፈር ማግኘት ባለመቻሉ የመጣ ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ መልኩ ሥራው ተጠናክሮ ከቀጠለ ደግሞ ይህን ችግር ለመፍታት የሚቻልበትን ዕድል ይፈጥራል፡፡ ምክንያቱም ይህ ሲሆን የአፈር ለምነትን መጠበቅ፣ ውሃን ማጎልበትና ሌሎች ተያያዥ የኢኮኖሚ ልማቶችን ማከናወን እንደሚቻልም አስረድተዋል፡፡
ዶክተር ይተብቱ እንደሚሉት፤ ደን አልምቶ ከካርበን ሽያጭ ገቢ ማግኘት ከተፈለገ ሊገኝ ይችላል፡፡ ይህ ግን ትንሽ ነው። ዋናው ነገር ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ለራሳቸው በቅተው ለሰው መትረፍ የሚችሉበትን ዕድል መፍጠር መቻሉ ነው። ስለዚህ የችግኝ ተከላ ሥራው ሲከናወን ዋናው ነገር ከካርበን ሽያጭ መጠቀምን ታሳቢ በማድረግ ሳይሆን የኢትዮጵያን ዘላቂ ልማትና ብልጽግና ምስጢር በውስጡ የያዘ መሆኑን በመገንዘብ ሊሆን ይገባል፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ግብርና፣ መስኖ፣ የኃይል ልማትና የመሳሰሉት የደን ልማትና ዝናብ ላይ የተንጠለጠለ ነው፡፡
ለምሳሌ ደን ዝናብን በማምጣት በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ የልማት ጉዞ ውስጥ የማይተካ ሚና አለው፡፡ በሌላ በኩል ግን ራሱ ደኑ በቀጥታ (በቡና፣ በጣውላና መሰል ሀብቶች) ለኢኮኖሚው የሚያበረክተው አስተዋጽዖ በርካታ ነው፡፡
እንደ ፕሮፌሰር ለገሰ ንግግር፤ የችግኝ ተከላው ጥሪ፣ ከአፄ ምኒልክ የአድዋ ጦርነት ወቅት ከነበረው የክተት አዋጅ ጋር የሚነጻጸር ነው፡፡ በወቅቱ ወራሪ ጠላትን ከኢትዮጵያ ለማስወገድ ንጉሱ አዋጅ አወጁ፤ ሕዝቡም ወጣ፤ ወራሪም ተሸንፎ ተወገደ፡፡
አሁንም ኢትዮጵያ በደን እጦት ተራቆተች፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ለሕዝቡ መልዕክት አስተላለፉ፤ ሕዝቡም በዚህ መልኩ ምላሽ ሰጠ፡፡ በአሁኑ ወቅት የመጣው ውጤትም በቀላሉ የመጣ ሳይሆን ከምሑራን ጀምሮ ሲባል የነበረ፤ ነገር ግን ሀሳብ የሚያዳምጥ መሪ ሲገኝ ወደተግባር የገባ ነው፡፡ በመሆኑም ሥራው ለብዙ ዓመታት ስር የሰደደን ችግር መፍታት ላይ ሊያተኩር ይገባል፡፡
ኢትዮጵያ ከ50 ዓመት በፊት የደን ሽፋኗ ከ40 በመቶ በላይ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይህ ቁጥር ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ ወደ ሦስት በመቶ ዝቅ ማለቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ደኑ እንዲያገግም ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ተግባሮች ሽፋኑ ወደ 15 በመቶ ከፍ ማለቱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ከወራት በፊት በዚህ የክረምት ወቅት በሀገሪቱ አራት ቢሊዮን ችግኞች እንደሚተከሉ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ በዚህም እያንዳንዱ ሰው በነፍስ ወከፍ 40 ችግኞችን እንደሚተከል ይጠበቃል፡፡
ፕሮፌሰር ለገሰ እንደሚሉት፤ሥራው ዘላቂና ውጤታማ እንዲሆን መስራት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ዛፎች ባለቤት እንዲያገኙ ከማድረግ ጀምሮ ይህ ሥራ የሚመራበት መሬት የረገጠ ፖሊሲ ማውጣት፤ በደን ላይ ያሉ ሕጎችንም ማሻሻል ይገባል፡፡ እነዚህ ሕጎችም ሕዝብ ዛፍ ተክሎ ሲያሳድግ ሊሸለምና ሊበረታታ ብሎም እውቅናም ሊያገኝ የሚችልበትን አካሄድ ጭምር የያዘ ሊሆን ግድ ይላል፡፡ ፖሊሲዎችም ሲወጡ በቢሮ ውስጥ ወንበር ላይ ቁጭ ብሎ ሳይሆን፤ በየቢሮው ያሉ ኃላፊዎች ጭምር ወጥተውና በተጨባጭ በየቦታው ያለውን ችግር አይተው መፍትሄ በሚያመጣ መልኩ ሊሆን ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ባለፈም የሚተከሉ ችግኞችን መምረጥ፤ ለአገር በቀሎቹ ትኩረት መስጠት ይገባል፡፡
ዶክተር ይተብቱ እንደሚሉት፤ ሥራውን ቀጣይና ዘላቂ ለማድረግ እንደ ሕዝብም ሆነ እንደ መንግሥት አሁን የተፈጠረውን አብሮ የመስራት ጥምረት ማስቀጠል ይገባል። የተመረጡ ተቋማትም ለዚሁ ስኬት ተቀናጅተው እየሰሩ ያሉትን ሥራ የበለጠ በማጠንከር ቢያንስ በቀጣይ አስር ዓመታት ያክልም በዚህ ዓይነት ንቅናቄ ሕዝቡን መምራትና መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሥራውንም በበቂ ባለሙያዎች መምራትና መደገፍም ይገባል፡፡
በዚህ መልኩ መጀመሪያ አገርን የማዳንና በደን የመሸፈን ሥራ መስራት፤ ከዚህ በኋላም ለሌላው የመድረስ ደረጃ ላይ መድረስ ይቻላል፡፡ በጥቅሉ በተራቆተች አገር ከሚከናወነው የእርሻ መር ኢኮኖሚ ጉዞ በተጓዳኝ ደን መር ልማት ማከናወን የግድ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 24/2011
ወንድወሰን ሽመልስ