ነጻ አውጪነት ነፍሰ-ገዳይነት አይደለም!

 

የሰው ልጅ የፍጥረት ታሪክ ውስጥ ወንድም ወንድሙን መግደል የጀመረው ቅናት በፈጠረው መነሳሳት እና የልብ ድንዳኔ እንደሆነ ቅዱስ-መጽሐፍ ያስረዳል። ቃየል በወንድሙ አቤል ላይ አንድ ብሎ የጀመረው ይህ ነፍስ የማጥፋት ወንጀል፤ በዘመናት መካከል በተለያዩ ምክንያቶች እስከ ዛሬ እንደቀጠለ ነው። የሰው ልጅ አንድ የባሕሪ መገለጫ ሆኖም እየተወሰደ ነው።

በእርግጥ ነፍሰ ገዳይነት የሕግም የሞራልም ተጠያቂነት የሚያስከትል ፤ በማኅበረሰቦች የተወገዘና በፈጣሪም ዘንድ ጸያፍ የሆነ ተግባር ነው። ነፍሰ-ገዳይነት ምንም ዓይነት ምክንያት ቢሰጠው እና የትኛውንም አይነት ቀለም ቢቀባ ለውዳሴ የሚበቃ አይደለም። ይልቁኑ ከሰው ልጅ ፍጥረታዊ ማንነት ፣ከአምላኩ ከተጋራው በጎ መንፈስ እና ሕሊና አኳያ በብዙ የሚወገዝ ነው።

ከፍጥረት ማግስት ጀምሮ ተለዋዋጭ ከሆነው የሰው ልጅ ያልተገራ ፍላጎት ፣ ፍላጎቱ ከተገዛበት የልብ ድንዳኔ፣ ድንዳኔው ከፈጠረው የአመጽ መንገድ አኳያ፤ ባለንበት ዘመን ነፍስ ገዳይነት የተለያዩ አዎንታዊ ምክንያቶች እየተሰጡት እና እየተበረታታ፣በአንዳንድ የሳቱ እና ጠርዝ የለቀቁ ጽንፈኛ እሳቤዎች እየተደገፈ ተወዳሽ የሆነበት እውነታ ላይ ደርሷል።

በተለይ በነጻ አውጪነት ስም የሚካሄዱ በደመ ነፍስ የሚገዙ፤ የሰው ልጅ ሰብአዊ እሴቶች ጋር ገና ከጅምሩ የተፋቱ የአመጽ /የጥፋት እንቅስቃሴዎች በዘመናት መካከል የሰውን ልጅ ብዙ ያልተገባ ዋጋ አስከፍለውታል። ከሰውነት ልኬቱ ወጥቶ የማያስበ እስኪመስል ድረስ ለያዥ ለገላጋይ የማይመች አድርገው በራሱ ፍጥረታዊ ማንነት ላይ በፍጹም ተቃርኖ እንዲቆም አስገድደውታል።

ነጻነት በመገዳደል መንገድ ላይ የሚገኝ የተሰወረ እንቁ አይደለም ፤በወንድም ደም የሚዋጅ አማልክታዊ ስጦታም አይደለም። ከፍጥረታዊ ስሪት ጋር የተቆራኘ በአስተሳሰብ ልእልና የምንቀዳጀው ፣በደረስንበት መጠን የምንኖረው፣ በኖርነው መጠን ጣዕሙን የምናጣጥመው ፣ ለፍጥረታዊ ማንነት የተገዛ ሰብአዊ ፍላጎት ነው።

ስለ ነጻነት ጠበቃ ሆኖ ለመቆም ከሁሉም በላይ ይህንን እውነት በአግባቡ መረዳት ፣ ለእዚህ እውነት የተገዛ ማንነት መፍጠር እና መላበስ ያስፈልጋል። ከእዚህ ውጪ ነጻነት በብዙ የፖለቲካ ዲስኩር ወይም በጠብመንጃ አፈሙዝ በሚካሄድ የትጥቅ ትግል ተጨባጭ የሚደረግ አይደለም። ይህን እውነታ ንቆ አደርጋለሁ ብሎ ማመን የጥፋት “አልፋ እና ኦሜጋ” ነው። የሚያስከፍለውም ያልተገባ ዋጋ ለግምት የሚከብድ ነው።

በእዚህ መንገድ ነጻነትን ለማኅበረሰብ ተጨባጭ ለማድረግ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የተደረጉ ጥረቶች ማኅበረሰብን የግጭት አዙሪት ውስጥ ከመክተት እና መውጪያ መንገድ ከማሳጣት ያለፈ ትርጉም ያለው ፍሬ አፍርተው አልታዩም። በማህበረሰብ ውስጥ የልብ ድንዳኔ እና ተስፋ ቢስነትን ከመፍጠር ያለፈ ከነጻነት የሚመነጭ ማኅበረሰባዊ ማንነት መፍጠር አላስቻሉም።

ለእዚህ ደግሞ እኛ ኢትዮጵያውያን ብዙ ተሞክሮዎች ያሉን ሕዝቦች ነን። በየዘመኑ የነበሩ የትውልዶችን የለውጥ መንፈስ እና ተለውጦ የመገኘት ሕልም የተናጠቁ የጠብመንጃ ትግሎች፤ እንደ ሕዝብ ትናንቶች ላይ ተቸንክረን፤ የትናንት ናፋቂዎች እንድንሆን አድርገውን ኖረዋል። በማኅበረሰብ ውስጥ የልብ ድንዳኔ እና ተስፋ ቢስነትን በመፍጠር ነገዎቻችንን አጥርተን እንዳናይ፤ በእነሱም ተስፋ እንዳናደርግ ፈተና ሆኖብንም ቆይተዋል ።

ይህ ለዘመናት እንደ ሀገር ነገዎቻችንን ሲያጨልም የነበረ ርግማን ላለፉት አስርት ዓመታት የነጻ አውጪነት ካባ ለብሶ ፣ የሕዝባችንን የዕለት ተዕለት ሕይወት ፈተና ውስጥ ከትቷል፤ እንደ ሀገር ያለንን ሕልውና በብዙ ተገዳድሯል፤ ትውልድን ያልተገባ ዋጋ በማስከፈልም ሀገራዊ ድባቴ ፈጥሮ ቆይቷል።

በነፃ አውጪነት ስም የተለበጠ ነፍሰ ገዳይነት ፣ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በተለያዩ የውጭና የሀገር ውስጥ ጸረ ሰላም ተዋንያን የሕዝባችንን የለውጥ መንፈስ እና ተለውጦ የመገኘት መሻት በብዙ እየተፈታተነው ነው። ከትናንት በነጻነት ስም የብዙ ተስፈኞችን ሕይወት ገብረው የሥልጣን ርካብ የተቆናጠጡትን ጨምሮ የእነሱ መንገድ ተስፈኛ የሆኑ ብዙዎች ዛሬ የገዛ ወንድሞቻቸውን እየገደሉ ስለነጻነት ሲደሰኩሩ ምንም ሀፍረት አይታይባቸውም።

እልፍ ሲሉም በተጨባጭ መገለጫቸው የሆነውን ነፍሰ ገዳይነት ፣የነጻነት ትግል ስትራቴጂ አድርገው ለመስበክ ሲሞክሩ ፤ በእዚህ ደረጃ ለደነደነ ልባቸው እና ከእዚህ ለሚመነጨው ነፍሰ ገዳይነታቸው የጽድቅ ትርጓሜ ፤የሕዝባዊነት አልፋ እና ኦሜጋ አድርገው ለመስበክ ሲሞክሩ ማየት እና መስማት የተለመደ ሆኗል።

ይህ የጥፋት መንገድ ማኅበረሰብን የግጭት አዙሪት ውስጥ ከመክተት እና መውጪያ መንገድ ከማሳጣት ያለፈ ትርጉም የለውም። በማኅበረሰብ ውስጥ የልብ ድንዳኔ እና ተስፋ ቢስነትን ከመፍጠር ያለፈ ከነጻነት የሚመነጭ ማኅበረሰባዊ ማንነት መፍጠር የሚያስችል ማንንም ከምንም ነጻ ማውጣት የሚያስችል አይደለም። በአጠቃላይ ነፍሰ ገዳይነት በጸረ-ሕዝብነት በታሪክ የሚያስጠይቅ እና ማንም ሊያወግዘው የሚገባ በትውልድ ተስፋ ላይ ያነጣጠረ ወንጀል ነው!

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You