አዲስ አበባ፡- የኢፌዴሪ የፋይናንስ ደህንነትና መረጃ ማዕከል ማግኘትና በሕገ ወጥ መንገድ የወጣን ገንዘብና ንብረት መጠየቅና መጠቀም እንዲችል የጥምረቱ አባል የመሆን ፈቃድ አገኘ፡፡
የፋይናንስ ደህንነትና መረጃ ማዕከሉ ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፤ በሕገ-ወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ የማቅረብ፣ ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት የመሳሰሉትን መረጃ የመለዋወጥና የፋይናንስ ዩኒቶች ውጤታማ እንዲሆኑ ለማገዝ እንዲችል ሰኔ 26 ቀን 2011ዓ.ም ኔዘርላንድ ዘ ሄግ በተካሄደው 26ኛ የግሩፑ ፕሌነሪ ላይ የኢግመንት ግሩፕ የ164 አገሮች አባል እንዲሆን ተወስኗል፡፡
እንደ መግለጫው ማዕከሉ የኢግመንት ግሩፕ አባል ለመሆን ጥያቄ ያቀረበው ከ3ዓመት በፊት ሲሆን በስፖንሰር አድራጊ አገራት አማካይነት በአካል ጭምር ግምገማ እየተካሄደበት ከቆየ በኋላ መመዘኛዎቹን በማሟላቱ ፍቃድ ማግኘቱንና አባል ለመሆን መቻሉን ጠቅሷል።
ማህበሩ (ግሩፑ) የተመሰረተበት ዋና አላማ በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ የማቅረብ ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳትና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በመከላከልና በመቆጣጠር ሂደት ውስጥ መረጃን ያለቅድመ ሁኔታ በአባል አገራት ተቋማት መካከል መለዋወጥ ለማስቻል መሆኑን መግለጫው ያብራራል።
ይህንን ውሳኔ ተከትሎም ማዕከሉ ከአገሪቱ በሕገ-ወጥ መንገድ የወጣን ገንዘብና ንብረት የተመለከተ መረጃ ለመጠየቅና ለመጠቀም የሚያስችል ሙሉ መብት ስላለው የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በቁርጠኝነት ለመወጣት መዘጋጀቱን መግለጫው አብራርቷል።
ኤግመንት ግሩፕ የአገራት የፋይናንስ መረጃ ዩኒቶችን በአባልነት ያቀፈ ዓለም አቀፍ ኔትዎርክ ሲሆን፤ እ.አ.አ. በ1995 በቤልጅየም ብራሰልስ በአረንበርግ ቤተ-መንግሥት የተመሰረተ ነው።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 24/2011
እፀገነት አክሊሉ