
አዲስ አበባ፡– ኢትዮጵያ በርካታ የሚመራመሩ፣ ችግር ፈቺ የሆኑ እና ለብልፅግና መሠረት የሚጥሉ ሥራዎችን እንደምትፈልግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡ ጊዜው ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነት የሰፈነበት በመሆኑ የዜጎችን ብቃትና እኩል ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሁሉም ኃላፊነት መሆኑ ተጠቆመ።
10ኛው ከተማ አቀፍ የተማሪዎችና የመምህራን የሳይንስና የፈጠራ ሥራ አውደ ርዕይ “በፈጠራ ሥራ የተካነ ትጉህ ትውልድ ለሀገር ብልፅግና” በሚል መሪ ሃሳብ ከትናንት በስቲያ በወዳጅነት አደባባይ ተከፍቷል፡፡
ከንቲባ አዳነች አውደ ርዕዩን ሲከፍቱ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኢትዮጵያ በርካታ የሚመራመሩ፣ ችግር ፈቺ የሆኑ እና ለብልፅግና መሠረት የሚጥሉ ሥራዎችን ትፈልጋለች፡፡አውደ ርዕዩ በተማሪዎች መካከል ውጤታማ ውድድር በማካሄድ የፈጠራ ሥራን ያበረታታል፤ በከተማዋ እየተከናወነ ላለው መጠነ ሰፊ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ለውጦችም ዓይነተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል፡፡
በመዲናዋ በልዩ ትኩረት እየተከናወኑ ካሉ የለውጥ ማሳያዎች መካከል አንዱ የሆነው የትምህርት ሥርዓቱን ስብራቶች በመጠገን በቀለም ብቻ ሳይሆን በሚዳሰሱ የፈጠራ ሥራዎች የታነፀ ትውልድ የመገንባት ሥራዎች ተጨባጭ ፍሬዎች እያፈሩ እንደሚገኙም አመልክተዋል።
መምህራን የፈጠራ ሥራዎች ፣ ተማሪዎች ደግሞ የሀገር ለውጥ መሠረት ናቸው ያሉት ከንቲባዋ፤ ከተማዋን ለፈጠራ እና ምርምር ሥራዎች ምቹ እንድትሆን እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል። ተማሪዎች ከልጅነታቸው ጀምሮ የሚሠሯቸውን የፈጠራ ውጤቶች ማበረታታት የሳይንስ ፈጠራ ሥራዎች ለማሳደግ ጉልህ ሚና እንዳለውም አመልክተዋል፡፡
ትውልዱ ከሚማረው የቀለም ትምህርት ባሻገር በሚዳሰሱ የፈጠራ ሥራዎች እንዲታነጽ ማድረግ ተጨባጭ ፍሬ እንዲያፈሩ ይረዳዋል ያሉት ከንቲባዋ፤ ከተማ አስተዳደሩም በተማሪዎችና መምህራን የሚሠሩ የፈጠራ ሥራዎች ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲደርሱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስገንዝበዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ አውደ ርዕዩ የሚሠሩ የፈጠራ ሥራዎች የደረሱበትን ደረጃ ለኅብረተሰቡ ከማስተዋወቁ ባሻገር የፈጠራ ባለቤቶቹን ለተሻለ ሥራ የሚያነሳሳ መሆኑን አመልክተዋል።
ጊዜው ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነት የሰፈነበት በመሆኑ የዜጎችን ብቃትና እኩል ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሁላችንም ኃላፊነት ነው ያሉት ቢሮ ኃላፊው፤ በእዚህ ዘመን ለትምህርት ጥራት የሚመደብ ሀብት የሀገርን ሁለንተናዊ እድገት ለማፋጠን ጉልህ ድርሻ ያበረክታል ብለዋል ፡፡
የትምህርት ፖሊሲያችን ተማሪዎች አካባቢያቸውን እንዲያጤኑና እንዲገነዘቡ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመው፤ አውደ ርዕይው በክፍል ውስጥ የተማሩትን ትምህርት በተግባር ለመግለጥ እድል የሚፈጥር እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ የከተማዋ ነዋሪዎችም ለዕይታ ክፍት በሆነው አውደ ርዕይ በመገኘት የፈጠራ ባለቤቶቹን እንዲያበረታቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በትናንትናው ዕለት የተከፈተው 10ኛው ከተማ አቀፍ የሳይንስ የፈጠራ ሥራ አውደ ርዕይ እስከ ሚያዚያ 18 ቀን 2017 ዓ.ም ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ ተመላክቷል።
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 18 ቀን 2017 ዓ.ም