“ኢትዮጵያ ሥርዓተ ምግብ ሽግግርን ለማሳካት በጊዜ የለንም መንፈስ እየሠራች ነው” – ጌታቸው ድሪባ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፡ኢትዮጵያ የሥርዓተ ምግብ ሽግግርን ለማሳካት በጊዜ የለንም መንፈስና በቁርጠኝነት እየሠራች መሆኑን በኢትዮጵያ የሥርዓተ ምግብ ሽግግርና ኒውትሪሽን ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ዋና አስተባባሪ ጌታቸው ድሪባ (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡

ጌታቸው(ዶ/ር) ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ ኢትዮጵያ የዜጎቿን የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ያስችላት ዘንድ ከሦስት ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ እያደረገች ያለውን የሥርዓተ ምግብ ሽግግር መርሃ ግብር ውጤታማ ለማድረግ ርብርብ እያደረገች ትገኛለች፡፡

መንግሥት ለመርሃ ግብሩ መሳካት የተለየ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ አመልክተው፤ በተለይም ከእርሻ ጀምሮ እስከ ተመጋቢው እስከሚደርስ ደረስ ያሉ የእሴት ሰንሰለቶችን ጤናማ ምቹና እርስ በርስ የሚደጋገፍ ከማድረግ አንጻር 16 ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በጋራ እንዲሠሩ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡

ሀገሪቱ ባለፉት ዓመታት የግብርናውን ምርትና ምርታማነት ከማሳደጉ ጎን ለጎን የተመረተው ምርት ጥራቱን ጠብቆ፣ በበቂ ሁኔታና በሚፈለገው ጊዜ ለሕዝብ እንዲደርስ በማድረግ የሥርዓተ ምግብ ሽግግሩ በአጭር ጊዜ እውን ሊያደርጉ የሚችሉ ሥራዎችን ስታከናውን መቆየቷን አብራርተዋል፡፡

ከሌማት ቱሩፋት ጀምሮ አረንጓዴ አሻራና ሌሎችም ለግብርናው ምርታማነት መጎልበት የተነደፉ መርሃ ግብሮች ውጤታማ በሆነ መልኩ እየተገበረች እንደምትገኝና ተጨባጭ ለውጥ እየታየ መሆኑን ጠቅሰው፤ በትራንስፖርት፣ ሎጅስቲክስና በሌሎችም የምግብ ሰንሰለቱ ማሳለጫዎች ላይ ያሉ ውስንነቶችን ለመፍታትና ለማስተካከል ሁሉም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በኃላፊነት እየሠሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

“ዋናው ጥረታችንም በተሻለ መልኩ የሥርዓተ ምግብ ሰንሰለቱን ተከትሎ እንዲሄድ ለማድረግ ነው” ያሉት ዋና አስተባባሪው፤ ይህም ሲባል አምራቹ፣ ነጋዴው፣ አቀነባባሪው፣ ቸርቻሪው፣ መሪው፣ ገዢው አብሮ እንዲጓዝ ለማድረግ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ግቡን ለማሳካት እያደረገች ያለችው የሚበረታታ ጥረት በዓለም ሀገራት እይታ ውስጥ መግባቷን አመልክተዋል። ለመጀመሪያ ጊዜ አፍሪካ ውስጥ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብ ሥርዓት ጉባኤ እንድታዘጋጅ የተመረጠችውም እያስመዘገበችው ባለው ውጤት መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

“ቅንጅት የባሕላዊና የትርክት ለውጥ ይፈልጋል” በማለት ተናግረው፤ በተለይም በኢኮኖሚ የበለፀጉ ሀገራት ድጋፋቸውን እያቆሙ ባሉበት በእዚህ ወቅት በውስጥ ያለውን ሀብትና አቅም በመጠቀም የሀገርን ብልፅግና ማፋጠን እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You