ተፅዕኖ ፈጣሪው የካቶሊካውያኑ አባት ሲታወሱ

የሮማ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ፖፕ ፍራንሲስ ሥርዓተ ቀብር ዛሬ ይፈፀማል፡፡ በ88 ዓመታቸው ባለፈው ሰኞ ዕለት በትንሳኤ ማግሥት ያረፉት ሊቀ ጳጳሱ፣ ላለፉት 12 ዓመታት በመላው ዓለም የሚገኙ ከአንድ ቢሊዮን በላይ ካቶሊኮች የሃይማኖት አባት ሆነው ቤተክርስቲያኗን መርተዋል፡፡

ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ የሮማ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲ ያንን የመሩ የመጀመሪያው ላቲን አሜሪካዊ፣ ከአሜሪካ ክፍለ ዓለም የተገኙ የመጀመሪያው የቤተክርስቲያኗ ሊቀ ጳጳስ፣ ከሶሪያዊው ሊቀ ጳጳስ ሳልሳዊ ግሪጎሪ በኋላ (ከ1272 ዓመታት በኋላ) ከአውሮፓ ውጪ ተወልደውና አድገው ለቤተክርስቲያኗ መሪ የሆኑ የመጀመሪያው ሊቀ ጳጳስ፣ ለቫቲካን ቅዱስ ጴጥሮስ መንበር የበቁ የመጀመሪያው ኢየሱሳዊ (Jesuit) እንዲሁም ከደቡባዊው የዓለም ክፍል የተገኙ የመጀመሪያው የቤተክርስቲያኗ ሊቀ ጳጳስ ናቸው።

የተወለዱት በታኅሣሥ ወር 1929 ዓ.ም ቦነስ አይረስ፣ አርጀንቲና ውስጥ ነው፡፡ ከፋሺስቱ ቤኒቶ ሙሶሊኒ አገዛዝ አምልጠው አርጀንቲና የገቡት ወላጆቻቸው ያወጡላቸው ስማቸው ሆርጌ ማሪዮ ቤርጎግሊዮ ነበር፡፡ የእግር ኳስ አፍቃሪ እንዲሁም የታንጎ ዳንስ ወዳጅ ነበሩ፡፡ በአንድ የምሽት ክበብ ውስጥ አሳላፊ እንዲሁም በአንድ ፋብሪካ ውስጥ ደግሞ ኬሚስት ሆነውም ሠርተዋል፡፡ በ1950 ዓ.ም የኢየሱሳዊያን ኅብረትን (Jesuits) ከተቀላቀሉ በኋላ ፍልስፍናን፣ ሥነ ጽሑፍን እና ሥነ ልቦናን አጥንተዋል፡፡

በ2005 ዓ.ም የሮማ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ሆኑ፡፡ በቫቲካን ቅዱስ ጴጥሮስ ሰገነት ላይ ቆመው ሊቀ ጳጳስ ቤኔዲክት 16ኛ በፈቃዳቸው የለቀቁትን ርዕሰ ሊቃነ ጵጵስና ተቀበሉ፡፡ ገና ወደ ጵጵስናው ሲመጡ ጀምሮ ነገሮችን በተለየ መልኩ ሲተገብሩ ይስተዋላሉ። ሽብርቅርቅ-ሽቅርቅር ያለና ከልክ ያለፈ ድግስ ምቾት አይሰጣቸውም። ሰው ሰው የሚል ነገር ይመርጣሉ። ወደ ነዳያን ይቀርባሉ። ለአብነት ያህል ቫቲካን ለጳጳሳት የምታቀርበውን ውድ ሊሞዚን ፊት ነስተውታል። ሌሎች ካርዲናሎችን በሚያመላልሰው የሕዝብ አውቶቡስ መሳፈርን መርጠዋል። በእዚህ ቀለል ያለ የሕይወት ዘይቤያቸውም ከአንድ ቢሊዮን ለሚልቁ ምዕመኖቻቸው ምሳሌ ለመሆን ሞክረዋል። “ለድሆች የምትቆም ኩርምት ያለች ቤተክርስቲያን ትማርከኛለች” በሚለው አነጋገራቸው ይታወቃሉ።

ቀልድ አዋቂ የነበሩትና ቀለል ያለ ሕይወትን የሚመርጡት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ከድሮም ጀምሮ በአውሮፕላን ሲጓዙ በአንደኛ ደረጃ ማዕረግ ክፍል ውስጥ አይቀመጡም። ከተራው ሕዝብ ጋር (በኢኮኖሚ ክፍል) መሳፈርን ይመርጣሉ። ለድሃው ድምጽ በመሆንም ይታወቃሉ፡፡ ከአንግሊካን ሉተራን እና ሜቶዲስት እምነት መሪዎች ጋር በጋራ መሥራታቸው ያስመሰግናቸዋል። እርሳቸው በመሩት ፀሎት ላይ የእስራኤል እና የፍልስጤም መሪዎች በጋራ እንዲገኙ ማድረጋቸውም ተደንቆላቸዋል። ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ ከእዚህ ቀደም ባልተመደ ሁኔታ 140 ካርዲናሎችን ከአውሮፓ ውጪ ከሆኑ ሀገራት ሹመዋል። በአክራሪ ሙስሊሞች ጥቃቶች ምክንያት እስልምናን ማውገዝ ልክ አለመሆኑን መናገራቸውም የሚጠቀስ ነው። ማንኛውም ጥቃት፣ ጥቃት አድራሹን እንጂ ሃይማኖትን እንደማይወክል አስተምረዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ወግ አጥባቂም ናቸው። በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ የማያወላዳ አቋም አላቸው። ለምሳሌ በሐኪም እርዳታ በፍቃድ የሚፈጸም ሞት እና ጽንስ ማቋረጥን በጽኑ ይቃወማሉ። የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያንንም ቢሆን እጇን ዘርግታ መቀበል እንዳለባት ቢናገሩም፤ በሁለት ተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ውስጥ ልጅን በጉዲፈቻ ማሳደግ ግን ሕጻናትን መበደል እንደሆነ አስተምረዋል፡፡ ሴት ቀሳውስት ጳጳሳት ሆነው ሊሾሙ አይገባም የሚል አቋምም አላቸው። የእርግዝና መከላከያ መጠቀምንም ያወግዛሉ። በአንድ ወቅት በፊሊፒንስ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር “የእርግዝና መከላከያ ቤተሰብን የሚያፈርስ ነው” ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ተወዳጅ የሆኑትን ያህል ነቀፌታም አላጣቸውም። በታሪካቸው ጥቁር ጠባሳ ተብሎ የሚነሳው በአርጀንቲና ካርዲናል ሳሉ ለወታደራዊው መንግሥት አጎብድደዋል የሚለው ክስ ነው። በተለይም በወታደራዊው አገዛዝ ታፍነው በተወሰዱት እና ብዙ ስቃይ ባሳለፉት ሁለት ቀሳውስት ዝምታን መርጠዋል ተብለው በብርቱ ይወቀሳሉ፡፡ እርሳቸው ግን “አልሆነልኝም እንጂ ቀሳውስቱ እንዲለቀቁ ከመድረክ ጀርባ ብዙ ሠርቻለሁ፡፡ በወቅቱ በይፋ መናገር በጣም ከባድ ነበር” ብለዋል፡፡ ይሁንና በእዚያ ዘመን ብዙ ሰዎች ከአሰቃቂው ወታደራዊ አገዛዝ እንዲሸሹ ዕድሎችን አመቻችተዋል።

አባ ፍራንሲስ በዘመናቸው ትልቁ ፈተና የሆነባቸው በዓለም ዙሪያ በቀሳውስት ተፈጽመዋል የሚባሉ የሕጻናት ጥቃቶችን በበቂ ሁኔታ አልተከላከሉም የሚለው ክስ ነው። በእዚህ ጉዳይ ላይ ከሊቀ ጳጳሱ ጋር ለዓመታት የዘለቀ ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ የቆዩት በዋሽንግተን የሊቀ ጳጳሱ መልዕክተኛ የነበሩትና በቫቲካን የተወገዙት ካርሎ ማሪያ ቪጋኖ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

አባ ፍራንሲስ የወግ አጥባቂነታቸውን ያህል ከቤተ ክርስቲያኒቱ የተገፉትን በማቅረብም ይታወቃሉ። ጥብቅ የቤተክርስቲያን ሕግጋትን በሚከተሉት ጳጳሳት የሚመረጡትን ያህል ለዘብ ያለ አመለካከታቸውም ልዩ ያደርጋቸዋል፡፡ ለተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ያሳዩት ርህራሄ የእዚህ ማሳያ ተደርጎ ይጠቀሳል። ይህ ድርጊታቸውም ከአንዳንድ የሃይማኖቱ አባቶች ጋር አለመግባባት ውስጥ ከቷቸዋል፡፡

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ በመላው ዓለም በነበራቸው ተፅዕኖ ፈጣሪነታቸውም ይታወሳሉ። ሊቀ- ጳጳስ ፍራንሲስ ባለፈው ዓመት 2024 እስያን ሲጎበኙ በምሥራቅ ቲሞር የሚኖሩ ሰዎች በአጠቃላይ አደባባይ ወጥተው ነበር የተቀበሏቸው። በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ኪንሻሳ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ደግሞ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ቫቲካን ባላት ተፅዕኖ ምክንያት የካቶሊክ ቤተ- ክርስቲያን ሊቃነ ጳጳሳት ከ184 ሀገራት እና ከአውሮፓ ኅብረት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያደርጋሉ። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድምጽ መስጠት ባይችሉም የቋሚ ታዛቢነት ሚናም አላቸው። ይህም በድርጅቱ ውይይቶች ላይ በመሳተፍ አቅጣጫ ማስያዝ የሚችሉበት አቅም ይሰጣቸዋል።

እ.አ.አ በ2015 የፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ሲፈረም ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ ሀገራት ለአየር ንብረት ለውጥ በቂ ትኩረት አልሰጡም ብለው ተችተዋል። ሀገራት ምድርን ለማትረፍ ጥረት እያደረጉ እንዳልሆነ እና “በትዕቢት የተሞላ ችላ ባይነት” እንዳሳዩ ተናግረው ነበር። ከእዚህ በተጨማሪም እ.አ.አ በ2014 በአሜሪካና በኩባ መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲታደስ ለማድረግ ሊቀ ጳጳሱ የተጫወቱት ሚና አይዘነጋም። ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ ለሁለቱም ሀገራት ደብዳቤ በመጻፍና በቫቲካን ምሥጢራዊ ውይይት በማዘጋጀት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱ እንዲታደስ አስችለዋል። የወቅቱ የሀገራቱ ፕሬዚዳንቶች ባራክ ኦባማ እና ራውል ካስትሮ በአደባባይ ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስን አመስግነዋል።

አባ ፍራንሲስ በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳትነታቸው ዘመን ብዙ የካቶሊክ እምነት ተከታዮች ወዳሏት አፍሪካ አህጉር አምስት ጉዞዎችን አድርገው 10 ሀገራትን ጎብኝተዋል፡፡ በ2019 ወደ ደቡብ ሱዳን ተጉዘው ፕሬዚዳንት ሳልቫኪርና ምክትል ፕሬዚዳንት ሪክ ማቻር ሰላም እንዲያወርዱ የፖለቲከኞቹ እግር ላይ ተደፍተው ሲማጸኑ መታየታቸው የሚዘነጋ አይደለም። ቤተክርስቲያኗ ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት በብዙ መልኩ እንዳሻሻሉትም ይነገርላቸዋል፡፡

አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You