አዲስ ዘመን:- የገቢዎች ሚኒስቴር በቅንነትና በፍትሐዊነት አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር የሕዝብን ገንዘብ ለመሰ ብሰብ የወጣውን ሕግ ለማስከበር ጠንካራ እርምጃ እንደሚወስድ አስታወቀ።
ሚኒስትሯ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉትቆይታ መስሪያቤታቸው በአገሪቱ ላይ ፍትሐዊ የግብር አሰባሰብ ሥርዓት ለማስፈን በከፍተኛ ቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይም ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲውል የሕዝብን ገንዘብ ለመሰብሰብ የወጣውን ሕግ ለማስከበር ጠንካራ እርምጃ እንደሚወሰድ ገልጸዋል፡፡
የታክስ ሕጉን የማስከበር ሥራ ራሱን በቻለ ሚኒስትር ዴኤታ እየተመራ መሆኑን የገለፁት ሚኒስትሯ፤ የኢንተሊጀንሲና የምርመራ ሥራው በዳይሬክተር እንዲመራ በመደረጉ ዘንድሮ 189 ያህል አከፋፋይ ጅምላ ሻጮችና ዕቃ አስመጪዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ያለ ደረሰኝና ያለ ሕጋዊ የሽያጭ ሥርዓት ዕቃ በማከፋፈላቸው እርምጃ መወሰዱን ፤ 11 ሚሊዮን ብር የሚገመት አስተዳደራዊ ቅጣት መቅጣት መቻሉንም አስረድተዋል።
የታክስ ሕግን ከማስከበር አንጻር የእኛ አገር ሕግ የላላ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ ሌላው አገር ላይ ለአሠራርና ለአገልግሎት በጣም ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል፤ አጭበርብሮ ለተገኘ ግን ምንም ምህረት የለም። በዚህ ደረጃ ሕጉን እናስከብር ብለን ስንነሳ ነጋዴውን እንዳዋከብንና እንዳስጨነቅን በመቁጠር የገባውም ያልገባውም አስተያየት ይሰነዝራል፤ ይህ ሁኔታ ለአገር አይጠቅምም ብለዋል።
«አገሪቱ የጋራችን ናት ሌላ አገር የለንም፤ በሚሰበሰበው ግብር ነው እንደእነ አሜሪካ። ቻይናና ሌሎች የበለጸጉ አገሮች ለውጥ ልናመጣ የምንችልባቸው ሥራዎች የሚከናወኑትና ፍትሐዊነት ማስፈን የምንችለውም የታክስ ሕጉ መከበር ሲችል ነው» ብለዋል ሚኒስትሯ። (ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ያካሄዱትን ሙሉ ቃለ ምልልስ በገፅ 8 ይከታተሉ)
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 24/2011
እፀገነት አክሊሉ