በአክሲዮን ሽያጩ በ121 ቀናት ውስጥ 3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ ተቻለ

በኢትዮ ቴሌኮም አክሲዮን ሽያጭ ከ47 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ተሳትፈዋል

አዲስ አበባ:– በኢትዮ ቴሌኮም የአክሲዮን ሽያጭ በ121 ቀናት ውስጥ 3 ነጥብ 2 ቢሊዮን የተከፈለ ገንዘብ መሰብሰብ መቻሉ ተገለጸ። በኢትዮ ቴሌኮም በ10 በመቶ የአክሲዮን ሽያጭ ከ47 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ፤ ኢትዮ ቴሌኮም ለኢትዮጵያውያን ለሽያጭ ያቀረበውን የ10 በመቶ ድርሻ አፈጻጸም አስመልክቶ ትናንት ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ ከጥቅምት 7 ቀን 2017 እስከ ታሣሥስ 25 ቀን 2017 ዓ.ም የመጀመሪያው ዙር የአክሲዮን ሽያጭ ሲካሄድ ቆይቷል። ተጠቃሚዎች እንዲራዘም በጠየቁት መሠረትም፤ እስከ የካቲት 7 ቀን 2017 ዓ.ም የአክሲዮን ሽያጩ ተራዝሟል። በእዚህ ሂደት በመጀመሪያው ዙር 43ሺህ 848 ኢትዮጵያውን 8 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሼሮችን በመግዛታቸው 2 ነጥብ 64 ቢሊዮን ሀብት ተሰብስቧል። በሁለተኛው ዙር 3ሺህ 529 ዜጎች አንድ ነጥብ 87 ሼሮችን ገዝተዋል። በድምሩም 47 ሺህ 377 ኢትዮጵያውያን 10 ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሼር መግዛታቸውን ሥራ አስፈፃሚዋ አስታውቀዋል።

በአጠቃላይ ከተሸጠው ሼር ሦስት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር ሀብት መሰብሰቡን አመልክተው፤ ከ30 እስከ 100 ሼሮች የገዙ የማህበረሰብ ክፍሎች 30ሺህ 14 መሆናቸውን እና ከ3ሺህ እስከ 3ሺህ 333 ሼሮች የገዙ 712 መሆናቸውንም አብራርተዋል።

በሂደቱም 3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የተከፈለ ገንዘብ የተሰበሰበ ሲሆን፤ 10 ነጥብ 7 ሚሊዮን የአክሲዮን ድርሻዎች መሸጣቸውን ተናግረዋል።

ሽያጩ ሙሉ በሙሉ በዲጂታል መንገድ በቴሌ ብር አማካኝነት የተፈፀመ መሆኑን የገለጹት ሥራ አስፈፃሚዋ፤ የዲጅታል ግብይት ሥርዓትን ማለማመድ መቻሉንም ተናግረዋል። በኢትዮ ቴሌኮም አክሲዮን ሽያጭ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ኢንቨስት ለማድረግ የሚፈልጉ ባለሀብቶች አለመሳተፋቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይ ባለ አክሲዮኖችን የማነጋገር ሥራ እንደሚሠራ እና ይህንንም ለማድረግ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን መብት ሰጥቷል ያሉት ወይዘሪት ፍሬህይወት፤ ሕጉም ይህንኑ እንደሚፈቅድ ነው። በሂደቱ ከባለአክሲዮኖች የሚጠየቅ ማረጋገጫ እና የሚያስፈልጉት ዶክመንቶች እንዲሟሉ በማድረግ ባለቤትነታቸው እንዲረጋገጥ ወደ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን እንደሚላክም ጠቁመዋል።

የሼር ባለቤቶችም በካፒታል ገበያ መሸጥ እና መግዛት ወደሚችሉበት አሠራር እንደሚገቡ አመልክተዋል።ኩባንያው ቀሪ አክሲዮኖች በተመለከተ ዝርዝር የሽያጭ ሂደቱን በቀጣይ የሚገልፅ መሆኑን ጠቁሟል፡፡

ጥቅምት 6 ቀን 2017 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮ ቴሌኮምን 10 በመቶ የአክሲዮን ሽያጭ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You