
የማዕድን ሀብቶች በርካታ ዓይነቶች ናቸው። በአብዛኛው በማዕድንነት ሲጠቀሱ የሚታዩት እንደ ወርቅ፣ ብረት፣ የከበሩ ድንጋዮች፣ ኦፖል፣ የድንጋይ ከሰል፣ እምነበረድና ግራናይት ያሉት ናቸው። ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በግብዓትነት የሚያገለግሉት እንደ ድንጋይ፣ አሸዋና ሲሚንቶ ያሉትም በዚሁ ዘርፍ ይጠቃለላሉ።
እንደ እምነበረድ፣ ግራናይት፣ ድንጋይ እንዲሁም ለሲሚንቶ እንዲሁም ለሴራሚክ ማምረቻ በግብዓትነት የሚያገልግሉ በርካታ ማዕድናት እንዳሉ ይታወቃል። እነዚህ የማዕድን ዓይነቶች እሴት እየተጨመረባቸው ለግንባታ እንዲውሉ ይደረጋል፡፡
ድንጋይ እየጠረበ፣ እየተከሰከሰ፣ እየተፈጨ እና በተለያዩ መልኩ ለግንባታ አገልግሎት እንደሚውል ይታወቃል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ እንደ ድንጋይ ባሉት ማዕድናት ላይ እሴት በመጨመር የበለጠ ውብ በማድረግ ለግንባታ ማሳመሪያነት በስፋት እንዲውሉ እየተደረገ ነው። ድንጋይን በዘመናዊ መልኩ በማስዋብ የተለያዩ ቅርጻ ቅርጾች በመስጠት ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ ተለምዷል።
ኃይለሥላሴና ጓደኞቹ የድንጋይ ቅርጻ ቅርጽ ሕብረት ሥራ የሽርክና ማህበር በዚህ ሥራ ከተሠማሩት መካከል ይጠቀሳል። ወጣት ኃይለሥላሴና አራት ጓደኞቹ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 በተለምዶ የካ አባዶ ኮንዶሙኒየም በድንጋይ ቅርጻ ቅርጽ ማውጣት ሥራ ላይ ተሠማርተው እየሠሩ ናቸው። ሥራውን ተደራጅተው ነው የጀመሩት። በ2012ዓ.ም 120 ካሬ የመሥሪያ ቦታ ተመቻችቶላቸው ወደ ሥራ ገብተዋል።
የማህበሩ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ኃይለሥላሴ ጣሰው እንደሚለው፤ ማህበሩ ሥራውን ሙሉ ለሙሉ የጀመረው በ2013 ዓ.ም ነው። ከመደራጀታቸው በፊት በእጅ፣ በግራይንደርና በቀላል ማሽኖች የሚሠሩ የድንጋይ ቅርጻ ቅርጾችን ያወጡ ነበር። በብረታ ብረት ሥራው ላይ ልምድ ስለነበራቸው እና ቀላል ማሽኖችን በመሥራት ድንጋይ እንዲቀርጡ አድርገዋል። ‹‹እኛ በብረታ ብረት ልምዱ ስለነበረን ሙያችንን ተጠቅመን ማሽኖቹን ከግራናይትና ከማርብል ድንጋይ እንዲቀርጡ በማድረግ መሥራት ጀመርን ›› ይላል፡፡
የድንጋይ ቅርጻ ቅርጽ ሥራው ምንም ዓይነት ኬሚካል ያልተቀላቀለበትን የተፈጥሮ ድንጋይ በመጠቀም እንደሚሠራ ይገልጻል። በአካባቢው ላይ የሚገኘውን ድንጋይ ቅርጻ ቅርጽ በማውጣት እንደሚያስውቡ ጠቅሶ፤ የአራት ኪሎው ቤተመንግሥት አጥር፣ ፒያሳ፣ የቅርስ ጥገናዎችና የመሳሰሉት ሥራዎች ድንጋይ በማሰዋብ የተሠሩ መሆናቸውን ይገልጻል። ከኮሪደር ልማቱ ጋር የተያያዙ ብዙ ሥራዎች እየተሠሩበትና ሪልስቴቶች የዚህ ድንጋይ ተጠቃሚ መሆናቸውን ያመላክታል፡፡
እነዚህ የተፈጥሮ ድንጋዮች ከምድር የሚገኙ ሀብቶች ስለሆኑ ሁሉም ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ። ነገር ግን በማሽን ሊቀረጽ የሚችለውንና ከሲሚንቶ ጋር መዋህድ የሚችለውን የድንጋይ ዓይነት መለየት ያስፈልጋል። ድንጋዩ ከአዲስ አበባ ከተማ በስልሳና በሰማንያ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በብዛት ይገኛል። በጣፎ፣ ገብረ ጉራቻና ጫንጮ የሚገኝ ሲሆን፣ የወለንጪቲ አካባቢ ድንጋይ ደግሞ ባለ ቀለም ነው። በተለምዶ የአምቦ ድንጋይ የሚባለውም እንዲሁ ለእዚህ ሥራ የሚያስፈልግ የድንጋይ ዓይነት ነው።
ከድንጋይ አቅርቦት ጋር በተያያዘ የገበያም፣ የሥራም ክፍተት እንዳለ ተናግሮ፣ ሥራው ብዙም ያልተለመደና የተደራጁ አቅራቢ ማህበራት የሌሉት ነው ሲሉ ኃይለሥላሴ አመልክቷል። ከባለይዞታ ጋር በመስማማት ድንጋይ እያቀረቡ ያሉት ግለሰቦች ናቸው። በማህበራት ደረጃ ተደራጅተው የሚያቀርቡ ቢኖሩ ራሱን የቻለ ትልቅ የሥራ እድል እንደሚፈጠር አስታውቋል።
ድንጋዩን በጥልቀት መቆፈር ሳያስፈልግ በቀላሉ ማውጣት እንደሚቻል ጠቅሶ፣ ቅርጽ ወጥቶለትና ተውቦ ለተለያዩ አገልግሎቶች እንዲውል እንደሚደረግ ያመለክታል። የማህበሩ አባላት ሁሉም የተለያዩ ሙያዎች እንዳሏቸው፣ ይህን ሙያቸውን ተጠቅመው ለድንጋዩ ቅርጽ እያወጡ መሆናቸውን ይገልጻል። አብነትም ‹‹ቶርኖ›› የተሰኘው ማሽን ለብረት መቁረጫ ተብሎ የተሠራ ቢሆንም፣ ያንን ማሽን ኃይል እንዲቆጥብና ትልቅ ድንጋይ ተሸክሞ እንዲቆርጥ አድርገው መሥራታቸውንም ተናግሯል፡፡
አሁን የተለያዩ በሴንቲ ሜትር፣ በካሬ ሜትር እና በፒስ የቅርጻ ቅርጽ ሥራዎች እየሠሩ መሆናቸውን ይገልጻል። ማህበሩ ወጥ ሜዳማ ቦታ ላይ ከሚዘረጋ፣ በካሬ የሚላካ ክላዲንግ የሚባለው የሕንፃ የውጭኛ ክፍል ማስዋቢያን የማምረት አቅሙ በቀን 126 ካሬ መሆኑን ጠቅሰው፣ ሆኖም ማህበሩ በሦስት ፈረቃ ሃያ አራት ሰዓት የማምረት እድሉ ቢያገኝ አሁን ያለውን የማምረት አቅም እጥፍ ማድረግ እንደሚችል ያስረዳል።
ቅርጻ ቅርጽ የወጣለት ድንጋይ ለሕንፃዎች፣ ለቅርሶች እና ለአጥሮች፣ ለመሬት ምንጣፍ፣ ለግርግዳ፣ ለሕንፃዎችና ለመሳሰሉት ማስዋቢያነት ይውላል። የሕንፃ የደረጃ መወጣጫዎች በቅርጻ ቅርጽ በተዋቡ ድንጋዮች ሊሠሩ ይችላሉ። የቅርጻ ቅርጽ ሥራው አንዴ ከተገጠመ ከማጽዳት በስተቀር ቶሎ ቶሎ መጠገን የማይፈልግ፣ በእሳት ተቀጣጣይ ያልሆነ፣ በቀላሉ የማይፈራርስ መሆኑንም አመልክቷል።
እነዚህን ቅርጻቅርጽ የወጣላቸው ድንጋዮች በማምረት ከውጭ የሚመጡትን እንደ አሉሚኒየም ክላዲንግ ዓይነት፣ ሞዛይክ ቀለሞችንና ግራናይቶችን ማስቀረት ተችሏል ሲል ሥራ አስኪያጁ አብራርቷል፡፡
እሱ እንዳለው፤ ቅርጻ ቅርጽ የወጣለት ድንጋይ በብዙ መልኩ ተመራጭ ነው። አልሙኒየምም ቢሆን በቀላሉ ይለቃል፤ በእሳትም ተቀጣጣይ ነው፣ ቅርጻ ቅርጾቹ ከእንጨት ቢሠሩም ተሰባሪና ተቀጣጣይ ሊሆኑ ይችላሉ። ከብረትም ቢሠሩ በመዛጋቸው አይቀሬ ነው። ይህ ድንጋይ ከቅርብ አካባቢ የሚገኝና ቅርጻ ቅርጹም በሀገር ውስጥ ሊሠራ የሚችል፣ ለመጠገንና ለማቆየት ምቹ ሲሆን፣ እነዚህ ሁሉ በብዙ ምክንያቶች ተመራጭ እንዲሆን እንደሚያደርጉት ያብራራል።
የድንጋይ ቅርጻ ቅርጽ በድሮ ጊዜ በእጅ ይሥራ እንደነበር ጠቅሶ፣ ይህ ሥራ ብዙ ጊዜ እንደሚወስድም ኃይለሥላሴ አመልክቷል። አሁን ግን ቴክኖሎጂ በመጠቀም በአንድ ጊዜ ብዙ ማምረት ይቻላል። ማሽኖቹ ለድንጋዩ የሚያስፈልገውን ቅርጽ ሰጥተው ወዲያውኑ ሊያወጡት ይችላሉ። በቀን ብዙ ካሬ ማምረት ይቻላል። ለአንድ ባለ አስራ ሁለት ፎቅ የሚሆኑ የሕንፃ ክላዲንግ፣ ሀንድሊሩን እና ልዩ ልዩ ጌጣጌጥ የተሠራላቸውን ድንጋዮች በአንድ ቀን የማምረት አቅም አለን ይላል፡፡
በሀገሪቱ የድንጋይ ላይ ቅርጻ ቅርጽ ሥራ ቢኖርም፣ ምርቱን የሚጠቀሙት ጥሩ ኑሮ ላይ የሚኖሩ ብቻ ናቸው ሲል አመልክቶ፣ ይህን ድንጋይ መጠቀም እምብዛም አልተለመደም ነበር ብለዋል። በፈረንሳይ፣ ጣሊያንና በመሳሰሉት ሀገራት የድንጋይ ቅርጻ ቅርጽ ሥራዎች ያዩ ሰዎች በአብዛኛው ወደ ድንጋይ ቅርጽ ሥራ እየተመለሱ ያሉበት ሁኔታ እንዳለ ሲናገሩ እንደሰማ ገልጾ፤ የኮሪደር ልማቱም የድንጋይ ሥራ ጎልቶ የወጣበትና እየተለመደ የመጣበት መሆኑን ያስረዳል።
የድንጋይ ቅርጻ ቅርጽ ሥራውን ስንጀምር ለድንጋይ ከነበረው አመለካከት አንጻር ሲታይ አሁን ብዙ መሻሻል ታይቷል ሲል ገልጾ፣ አሁን ሰዎች ውበት ጥንካሬ እና ተፈጥሯዊ ነገሮች በደንብ ተለማምደዋል ይላል። ቀደም ሲል ይህንን ሥራ ይረዱ የነበሩት በውጭ የነበሩ ወይም በተለያዩ አጋጣሚ የውጭውን ዓለም ያወቁ ውስን ሰዎች ብቻ እንደነበሩ ተናግሯል።
አሁን አብዛኛው ሰው በመንግሥት በከተሞች ላይ እየተካሄደ ባለው የኮሪደር ልማት አማካኝነት ይህን የማዕድን ሀብት እየተረዳ መምጣቱን ጠቅሰው፣ ምንድነው? የትነው የሚሠራው? እያሉ መጠየቅ ጀምረዋል ይላሉ። ይህም ልምምዱም ሆነ ፍላጎቱ በደንብ እንዳለ ያሳያል። አብዛኛውን ሰው የድንጋይ ላይ ቅርጻ ቅርጽ በሀገር ውስጥ ሲያይ ከውጭ ሀገር እንደመጣ አድርጎ ሲያሰብ እንደነበረ አመልክቷል። ‹‹ይህ በእናንተ በሀገር ውስጥ የሚሠራ ነው ወይ ›› በማለት በመደነቅ እንደሚጠይቁም ይገልጻል።
ሥራው ልዩ ልዩ ማስዋቢያ ፍሬሞችንም እንደሚጠቀም ተናግሮ፣ ይህ ሁሉ ተሰልቶም ድንጋዩ ዋጋ እንደሚወጣለት ያስረዳል። ይህ ሲሆን አንዱ ቪላ ቤት ላይ የወጣው ዋጋ ሌላው ላይ ላይሠራ ይችላል ያለው ኃይለሥላሴ፣ ማህበሩ የድንጋይ ላይ ቅርጻ ቅርጾችን ከመሸጥ አንስቶ ወሰዶ እስከ መግጠም ያለውን ሥራ ይሠራል ብሏል።
ይህንንም አብነት ጠቅሶ ሲያብራራ ለጥ ያለ ቦታ ላይ የሚገጠም ባለቅርጻ ቅርጽ ድንጋይ ዋጋ ከ800 እስከ 920 ብር እንደሚሸጥ አስታውቋል። ‹‹ሥራው አድካሚ ቢሆንም ዋጋው ተመጣጣኝ የሚባል ነው፤ ባደከመን መጠን ባይከፍለንም ጥሩ ሥራ ነው፤ ገበያም አለው። ገበያው ብዙ በማምረት መሸጥ እንደሚያስችል አስታውቋል።
ደንበኞች በማህበራዊ ሚዲያዎች በሚያዩዋቸው ቤቶች ላይ ያሉ የድንጋይ ቅርጻ ቅርጾችን የሚመስል ቅርጻ ቅርጾችን እንድንሠራላቸው ይፈልጋሉ የሚለው ኃይለሥላሴ፤ መቶ በመቶ ያንን ማስመሰል ባይቻልም እንኳን በመቅዳት ተቀራራቢ ተደርጎ የሚሠራበት ሁኔታ እንዳለም ይጠቁማሉ። ለእነዚህ ሥራዎችም የእያንዳንዱ ሥራ ሂሳብ ከተሠራ በኋላ ዋጋ እንደሚወጣለትም ይናገራል፡፡
ከሥራው የሚያገኙትን ልምድ በመውሰድ ሥራቸውን እያሻሻሉና እያዘመኑ መምጣታቸውንም ይናገራል። ‹‹ሥራው ራሱ እያስተማረን እኛ ሥራውን እየሠራን፤ ሥራው እኛን እያሠራን፣ በደንብ መስመር እያሲያዘንና እያስተካከለን እያሻሻልን መጥተናል፤ ደንበኞቻችንም ለመሳብ በምናደርገው ጥረት ተጨማሪ ልምዶችን እየቀሰምን የተሻለ ሥራ ለመሥራት ችለናል ሲል አብራርቶ፣ ሥራውን ከጀመርን ሦስት ዓመት ተኩል ገደማ ሆኗል፤ ምርቶቹን የማቅረብ አቅማችንንም ሆነ ፍጥነትም በሚገባ አሻሽለናል›› ብሏል፡፡
ከማህበሩ ምርቶችን ተጠቃሚ ከሆኑ ደንበኞች መካከል ቪላ ቤት ያላቸው ባለሀብት፣ የሪል ስቴት ባለቤቶች፣ ፊት ለፊት ላይ ሕንጻ የሚገነቡ ሰዎችና ደረጃ አንድና ሁለት የኮሪደር ልማት የሚሠሩት ኮንትራክተሮችና ሌሎችም እንዳሉ ይጠቅሳል፡፡
ኃይለሥላሴ፣ ‹‹መንግሥት የማምረቻ ቦታ ሰጥቶ እንድንሠራ እንዲሁም ለብዙ ዜጎች የሥራ እድል እንድንፈጥር አድርጓል፤ ለዚህም ምስጋና እናቀርባለን›› ብሏል። ከዚህ የበለጠ ለመሥራትና ሀገሪቷንም ለመጠቀም ሥራው ድጋፍ ሊደረግለት እንደሚገባ አመልክቶ፣ ‹‹አሁን ላይ የገበያ እጥረት ባይኖርብንም በሙሉ አቅም እየሠራን አይደለም፤ በግማሽ አቅማችን ውስን ሥራ እየሠራን ነው›› ብሏል። ምክንያቱም ማምረቻ ቦታው ያለው በመኖሪያ መንደር /ኮንዶሚኒየምና አፖርትመንት/ አጠገብ ነው፤ ድምጹ አካባቢውን ይረብሻል፤ በዚህ የተነሳ ያለንን አቅም ተጠቅመን ማምረት አልቻልንም ሲል አብራርቷል። መንግሥት ይህንን ችግር ተመልክቶ የተሻለ የሥራ ቦታ ቢሰጣቸው የተሻለ ሊሠሩ እንደሚችሉም ጠቁሟል።
የትኛው ሥራ ላይ ተግዳሮት እንዳለ በመለየትና የሚያጋጥሙንን ተግዳሮቶች በመፍታት አሸንፈን አሁን ላለንበት ደረጃ ላይ ደርሰናል የሚለው ሥራ አስኪያጁ፣ ካጋጠሟቸው ተግዳሮቶች ትምህርት በመቅሰም ወደፊት መጓዝ እንደቻሉም አስታውቋል፡፡
ሥራው የድምጽ፣ የፍሳሽና የአቧራ ብክለት እንደሚያስከትል ጠቁሞ፣ ከመኖሪያ መንደር ራቅ ያለና መሠረተ ልማት የተሟላለት የማምረቻ ቦታ ማስፋፊያ እንደሌለ አመልክቷል። ይህ ችግር ዋነኛ ተግዳሮት ሆኖባቸው እንደቆየም ተናግሯል።
የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትና እንደ ብረታ ብረት፣ አውቶሞቲቭና ያሉት ዘርፎች ያለባቸው የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ሌላው ተግዳሮት መሆኑን ጠቁሟል። በዚህ የተነሳም ድርጅቱ የሰው ኃይል እያሰለጠነ መሆኑንም ተናግሯል። ሥራው በሰፊ ማስፋፊያ ቦታ ላይ ቢሠራ በጣም ብዙ ማምረት እንደሚያስችል አስታውቆ፣ ለብዙ ሥራ አጥ ዜጎችም የሥራ እድል እንደሚፈጥር አስታውቋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ በቅርቡ ባዘጋጀው መድረክም ድርጅቱን ከአነስተኛ አምራች ወደ መካከለኛ አምራችነት እንዲሸጋገር ተደርጓል። ወደ መካከለኛ አምራችነት በመሸጋገራችንም መንግሥት ተጨማሪ የቤት ሥራ ሰጥቶናል ይላል፤ ድጋፍና ክትትል እየተደረገልን ብዙ እንድናመርትም ይጠበቃል ሲል ኃይለሥላሴ ተናግሯል።
ሥራው መንግሥት ትኩረት ቢሰጠውና ቢሠራበት ለብዙ ዜጎች ቀጥተኛ እና ተዘዋዋሪ የሥራ እድል እንደሚፈጥር ኃይለሥላሴ ጠቁሞ፣ ‹‹እኛም በሥራው የተሠማሩ ዜጎችን ለማሰልጠን ዝግጁ ነን›› ብሏል።
ማህበሩ ማህበራዊ ኃላፊነት እየተወጣ እንደሚገኝም ጠቅሷል። ማዕድ በማጋራትና ፖሊስ ጣቢያዎችን በመሥራት ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ጠቅሶ፣ ተረፈ ምርቱን ለመሰብስብ የሚጠቀምባቸውን ሎደሮች የአካባቢውን ቆሻሻ እንዲያነሱ እንደሚያደርግም ይገልጻል። ባለፉት ሦስት ወራትም በማህበሩ ስም የአቅመ ደካሞችን ቤት ለመገንባት የ50ሺ ብር ድጋፍ ማድረጉን አስታውቋል።
የማህበሩ የማስፋፊያ ቦታ ችግር መፍትሔ የሚያገኝ ከሆነ ምርቱን በሦስትና አራት እጥፍ በማሳደግ ለብዙ ዜጎች የሥራ እድል በመፍጠር ብዙ መሥራት እንደሚቻል ሥራ አስኪያጁ ጠቁሞ፣ ከውጭ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች መተካት እንደሚቻል አስታውቋል። ውድ የሆኑ ቀለሞችን ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ በዚህ ምርት መተካት እንደሚቻልም ጠቁሟል።
በቀጣይ ማህበሩ ወደ ከፍተኛ አምራችነት ለመሸጋገር የሚያደረገውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል ሲል አስታውቆ፣ ሦስት የአፍሪካ ሀገራት ጥያቄ እንዳቀረቡለትም ገልጿል፤ ምርቶቹን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ አቅዶ እየሠራ መሆኑንም ተናግሯል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17 ቀን 2017 ዓ.ም