ከአንድ ዓመት በፊት 66 አካባቢ የነበረው የፓርቲዎች ቁጥር ባለፈው አንድ ዓመት ከእጥፍ በላይ አድጎ አሁን 133 ደርሰዋል። አንዳንድ ፖለቲ ከኞችና የፓርቲ ኃላፊዎችም በኢትዮጵያ የአገር ፓርቲ ብቻ ሳይሆን የቤተሰብም የፖለቲካ ድርጅቶች መኖራቸውን በማንሳት ቁጥሩ የሚገርም እንዳልሆነም
ይናገራሉ።
የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳሸን መፍላት በፖለቲካ ሊሂቃን ዘንድ «የፖለቲካ ግሽበት» ሲሉት ሌሎች ክስተቱን «የተለያዩ ሃሳብ በማንጸባረቅ በአገሪቱ ዴሞክራሲንና ለዜጎች የተለያዩ አማራጭ የማቅረብ ዕድል» ይሉታል። የፓርቲዎቹ መብዛት «ዕድል» ወይስ «ግሽበት» መሆኑን የሚለየው በፓርቲዎች የሃሳብ አማራጭ ፕሮግራም ነው።
የአዲስ ዘመን ጋዜጣ የፓርቲዎቹ ቁጥር መብዛት «ዕድል» ወይስ «የፖለቲካ ግሽበት» የሚለውን ለማየት በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተመዝግበው ሕጋዊ ሰውነት ካላቸው ከ68 ፓርቲዎች መካከል የ60ዎቹን ፕሮግራም መርም ሯል።
ፕሮግራማቸውን ከመረመርነው
60 የአገር አቀፍና የክልል ፓርቲዎች ላይ እንደተመለከትነው ፓርቲዎቹ በዋና ዋና ጉዳዮችን ተመሳሳይ፣ ተቀራራቢ እንዲሁም በርካታ ፓርቲዎች ደግሞ ፕሮግራሞቻቸውን አንዱ ከሌላው የተገለበጠ ዓይነት መሆኑን በሚያስብል ደረጃ ነው።
ፕሮግራማቸውን ከመረመርነው 60 ፓርቲዎች መካከል ለምሳሌ 59 ፓርቲዎች በኢትዮጵያ መኖር አለበት የሚሉት የሥርዓተ መንግሥት አወቃቀር ፌዴራላዊ መሆን እንዳለበት አስቀምጠዋል። አንድ ፓርቲ ብቻ አገሪቱ አሀዳዊ ሥርዓት መከተል እንዳለበት ያስቀምጣል።
የክልል አወቃቀርን በተመለከተ ሁሉም ፓርቲዎች በሚባል ደረጃ አገሪቱ መዋቀር ያለባት መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥን፣ የሕዝብ አሰፋፈርን፣ ለአጠቃላይ የልማት ሥራ አመቺነትን፣ ባህልና ታሪክን፣ የብሔር ብሔረሰቦችን የራስን በራስ የማስተዳደር መብትን፣ ለብሔራዊ መግባባት አመቺነትን መሠረት አድርጎ መካለል እንዳለባቸው ያምናሉ። በፓርቲዎች ፕሮግራም ላይ ልዩነት በእነዚህ ጉዳዮች ቅደም ተከተል ላይ ብቻ ነው።
ኢኮኖሚን በሚመለከትም የፓርቲዎቹ ፕሮ ግራም ሁሉም በሚባል ደረጃ የነፃ ገበያን ሥርዓት እንደሚከተሉ አስቀምጠዋል። በኢኮኖሚው ውስጥ መጠኑ የተለያየ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት እንደሚኖርም የፓርቲዎች ፕሮግራም ልዩነት ያሳያል። የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ላይ ሁሉም ፓርቲዎች ተመሳሳይነትም አላቸው። በኢኮኖሚው ፕሮግራማቸው ላይ ልዩነት አለ ከተባለም በተቃዋሚዎችና በገዥው ፓርቲ ፕሮግራሞች ላይ በመሬት ባለቤትነት «የግል» እና «የመንግሥት» መሆን አለበት የሚለው ልዩነት ነው ጎልቶ የሚታየው። ሌላው ጉዳይ ላይ ግን በፓርቲዎቹ ጥቅል ፕሮግራም ላይ የጎላ ልዩነት አለ ለማለት ያስቸግራል።
በማህበራዊ ዘርፍ ላይ ተመሳሳይ ነው። በትምህርት ዘርፍ በገዥውና በተቃዋሚዎች ከሚታዩ የትምህርት ደረጃዎቹ ውጪ መሠረታዊ ልዩነት የለም። በዳሰስናቸው 60 ፓርቲዎች የትምህርቱ ዘርፍ በግልና በመንግሥት እንደሚካሄድ ያስቀምጣሉ። ሁሉም ጥራት ያለው ትምህርት ለማምጣት፣ የትምህርት ፕሮግራም ቀረጻ፣ የሰው ኃይል ማብቃት፣ ግብዓት ማቅረብና ዘርፉን ከፖለቲካ ነፃ በማድረግ የበቃ ዜጋ ለማፍራት እንደሚሰሩ የሚያመላክት ሲሆን፤ በፓርቲዎቹ ፕሮግራም መሠረታዊ ልዩነት አይታይም።
የፓርቲዎቹ ፕሮግራሞች በጤና ረገድ በሽታን መከላከልና ማከምን የተመሰረተ ፕሮግራም አላቸው። አገልግሎቱም በመንግሥትና በግል እንደሚቀርብ ያስቀምጣሉ። በፓርቲዎቹ ፕሮግራም ላይ ያለው ልዩነት የቅደም ተከተል ጉዳይ ብቻ ነው። ገዥው ፓርቲ በፕሮግራሙ መከላከልን ሲያስቀድም አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሁለቱን በእኩል መሰራት አለባቸው ሲሉ፣ ሌሎች ደግሞ ህክምና ላይ የሚያተኩሩም አሉ።
የውጭ ጉዳይ ፖሊስን በተመለከተ በጥቅሉ ተመሳሳይ ነው ማለት ይቻላል። በሁሉም ፓርቲዎች የኢትዮጵያን ጥቅም ማስጠበቅ፣ በሌሎች አገሮች ጥቅም አለመግባት፣ ከጎረቤትና ከአፍሪካ አገራት ጋር ጥቅምን መሠረት በማድረግ መስራት እና ዓለም አቀፍ ሕግን ማክበር የሁሉም ፓርቲዎች ፕሮግራም ማጠንጠኛ ተመሳሳይ ነው።
የአገር መከላከያን በተመለከተም በፓርቲዎቹ ፕሮግራም ሁሉንም ብሔር ብሔረሰቦች የሚወክል፣ ከፖለቲካ ገለልተኛ የሆነ፣ የአገሪቱን ሉዓላዊነት የሚያስጠብቅ እና በሳይንሳዊ ውትድርና የበቃ መከላከያ መገንባት ሁሉም ፓርቲዎች ለማራመድ በፕሮግራማቸው አስቀምጠዋል። በመከላከያ በልዩነት ደረጃም ከተነሳ በወታደር ቁጥር ላይ ያለው የአንዳንድ ፓርቲዎች ልዩነት ያሳያል።
የ60ዎቹ ፓርቲዎቹ ፕሮግራም በጥቅሉ ሲመረመር ልዩነቱ እጅግ የጠበበ ነው። የአብዛኞቹ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ልዩነት የቃላት፣ የፕሮግራም ማብራሪያ ስፋትና ጥበት፣ አልፎ አልፎ ያሉ ልዩነቶች ካልሆነ በስተቀር ተቀራራቢ ናቸው። የገዥው ፓርቲ የኢህአዴግ አራቱ አባል ድርጅቶችና የአጋር ድርጅቶች ከስያሜና ከሚያስተዳድሩት አካባቢ በፕሮግራማቸው ላይ ከሰጡት ትኩረት ውጪ በጥቅሉ ተመሳሳይ ናቸው። በድምሩ በፓርቲዎቹ ፕሮግራም ጫፍ የወጣ የሃሳብ ልዩነት አይታይም። ታዲያ በሌለ የሀሳብ ልዩነት ለምን 133 ፓርቲ ደረሱ?
የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ ሊቀመንበሩ አቶ ቶሎሳ ተስፋዬ፤ የበርካታ ፖለቲካ ፓርቲዎች ፕሮግራም ተመሳሳይ መሆኑን ያምናሉ። ኦሮሚያን ጨምሮ በክልሎች የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች የበለጠ ተቀራራቢ መሆኑን እንደሚያውቁ ይናገራሉ።
እሳቸው እንደሚሉት ተቀራራቢ ፕሮግራም ይዞ ለመለያየታቸው ምክንያቱ የፓርቲ አመራሮች በሥልጣን ላይ ሙጭጭ ማለትና የሥልጣን ጥመኝነት፣ አንድነት ከተፈጠረ ሥልጣን አጣለሁ የሚሉ፤ በፓርቲዎች መካከል የአለመተማመን ችግርና ሌሎች መንስዔ መሆናቸውን ያመላክታሉ።
የፓርቲዎች መብዛት ጥቅም የለውም የሚሉት ሊቀመንበሩ የዚህ አገር ችግር የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሳይሆን የፖለቲካ መሪዎች ናቸው። «ፓርቲዎች ተሰባስበናል ብለን መግለጫ በሰጠን ማግስት በወራት እንበተናለን» ያሉት አቶ ቶለሳ፣ በዚህም ባለፉት ዓመታት ፓርቲዎች ችግር አልፈቱም ብለዋል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ፤ ብዙ ፓርቲዎች ተመሳሳይና አንዳንዶቹም የተገለበጠ የሚመስል ፕሮግራም አላቸው። የፓርቲዎች ቁጥር 133 ደርሰዋል የሚባለው የቤተሰብ ማህበር የሚመስሉ ፓርቲዎችም ተቆጥረው ነው። አንድም ክልል ላይ ቢሮ ያልከፈቱ ቀደም ባለው ጊዜ ኢህአዴግ አንጃ እየፈጠረ ዋናዎቹን እያሰረ ሌሎቹን በወረቀት ህልውና የሰጣቸው ናቸው ይላሉ።
እንደነዚህ ያሉ ፓርቲዎችን ፓርቲ ብሎ መቁጠር እንደሚከብድ የሚያነሱት ዶክተር ደሳለኝ፤ በኢትዮጵያ መንግሥት እና ገዥው ፓርቲ ስለሚፈልጋቸው፤ ምርጫ ቦርድም ቁጥጥር ስለማያደርግ ተፈልፍለዋል። ሆኖም ፓርቲ የሆኑና ያልሆኑትን ሕዝብ ስለሚያውቃቸው ፓርቲ ቢባሉም ድምጽ አያገኙም። ከዚህ በፊትም እየተወዳደሩ ድምጽ አለማግኘታቸው ታይቷል።
የምዕራብ ሱማሌ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ሆርሲ ዶል፤ የአንዳንድ ፓርቲዎች ፕሮግራም ተመሳሳይ መሆኑን ያምናሉ። እስካሁን ውህደት የለም። ከዚህ በኋላ ቅንጅት፣ ግንባርና ውህደት በመፍጠር የፓርቲዎች ቁጥር እንደሚቀንስ ተስፋቸውን ያመላ ክታሉ።
በሱማሌ ክልል አምስት የሚሆኑ ፓርቲዎች መኖራቸውን የሚያመላክቱት ሊቀመንበሩ ግንባርና ውህደት ለመፍጠር ተቀራርቦና አብሮ ለመስራት ማሰባቸውንም አንስተዋል። ተቀራርቦ መስራት ካልተቻለም ዴሞክራሲዊ ሥርዓትና ምርጫ ካለ በውድድር የተሻለውን ሕዝብ በመምረጥ የማያስፈልጉት እንደሚከስሙ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር እና የመድረክ ምክትል ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፤ በበኩላቸው የፓርቲ መብዛት ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ መሆን የለበትም። አቅም ሲያጡ በእራሳቸው ጊዜ ይከስማሉ። ፓርቲ በዛ ብሎ ትልቅ ችግር አድርጎ መደጋገም ተገቢ አይደለም ይላሉ።
«ከመንግሥት ለፓርቲዎች የሚያደርገው ድጋፍ እና መራጩ ሕዝብ ጠቃሚ ሃሳብ የያዙትን ፓርቲዎች ተረድቶ ለመምረጥ አያስቸግርም?» ስንል ላነሳነው ጥያቄ ፕሮፌሰር በየነ፤ መንግሥት መደገፍ ከፈለገ መስፈርት አውጥቶ የሚያሟሉትን መደገፍ ይችላል። ሕዝቡም ቢሆን የሚጠቅመውን አማራጭ ፓርቲ መምረጥ ይችላል። ፓርቲ በዛ እያሉ እንደሞኝ መደጋገም አስፈላጊ አይደለም ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ናትናኤል ፈለቀ፤ ፓርቲዎች 133 እንደሆኑ ቢነገርም በተግባራቸው ከ20 በላይ ፓርቲዎች አሉ ለማለት አይቻልም የሚሉት ኃላፊው፣ ማንም ሰው ፓርቲ ጥራ ቢባል ከአምስትና ከአስር በላይ መጥራት አይችልም። በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ እየተነሱ ፓርቲ መመስረት ተገቢ አይደለም። መሆን ያለበት ትንሽና ሰፊ ድንኳን ያላቸው እና የብዙሃንን ሃሳብ የሚራመድባቸው መሆን ነው ያለባቸው። በሂደትም ይህን እንደርስበታለን። ብዙ ፓርቲዎች ከአዜማ ዓይነት ፓርቲዎች ጋር ይዋሃዳሉ። ሌሎችም ደጋፊ ሲያጡ በእራሳቸው ጊዜ ይከስማሉ። ምርጫ ቦርድም ሕጉን እየተከታተል መፈጸም ሲጀምር ቁጥራቸው እያነሰ ይሄዳል በማለት ቁጥራቸው እንደሚቀንስም ይናገራሉ።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 24/2011
አጎናፍር ገዛኸኝ