አዲስ አበባ፡- የሥራ ፈቃድ ቢኖራቸውም በተቀመጠላቸው የሕግ አግባብ ባለመስራታቸው ሕገወጥ ተግባር ፈፅመው በተገኙ 19 አሠሪና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን የቂርቆስ ክፍለ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡
የክፍለ ከተማው የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አልማው ኃይሉ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ኤጀንሲዎቹ ሕጉ በማይፈቅደው ሁኔታ ከተቀጣሪዎች
ላይ ገንዘብ በመቀበል፣ በአካልም ሆነ በዕድሜ ክልላቸው ለሥራ ያልደረሱ ሕፃናትን በማዘዋወርና በተለያዩ ሥራዎች ላይ በማስቀጠር፣ ሴቶችንና ሌሎች ዜጎችን ወደ ሥራ ማሰማራት በተከለከሉባቸው የሥራ አካባቢዎች በማስገባት፣ የአገር ውስጥ ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ ሆነው በውጭ አገር ሥራና ሠራተኛ እንደሚያገናኙ በማስመሰል ከተፈቀደላቸው የሥራ መስክ ተላልፈው በሕገወጥ ድርጊት ውስጥ ተሳትፈው የተገኙ እንዲሁም ለሠራተኞች ደህንነት ዋስትና እንደማይሰጡ የተረጋገጠባቸው 19 ኤጀንሲዎች እንዲታሸጉ ተደርጓል፡፡
እንደ ጽሕፈት ቤት ኃላፊው ማብራሪያ በግልጽ ቦታ ላይ መገኛ አድራሻቸውን ብሎም ማስታወቂያዎችን ያለማድረግና ቢሯቸው የሚጠበቅበትን መስፈርት ከማሟላት ጋር ተያይዞ ጉድለቶች የተስተዋለባቸው ኤጀንሲዎች ላይም ተመሳሳይ እርምጃ ተወስዷል፡፡ ኤጀንሲዎቹ ሕግን ተላልፈው በፈፀሟቸው ተግባራት ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚመጡ ሕፃናትን ጨምሮ በርካታ በዕድሜ ለጋ የሆኑ ዜጎችን ለጉልበት ብዝበዛ ዳርገዋል፡፡
ኤጀንሲዎቹ ከቀጣሪው አካል ለአገልግሎት ክፍያ ገንዘብ የመቀበል መብት እንዳላቸው፤ ነገር ግን ከሥራ ፈላጊው ገንዘብ መቀበል እንዳሌለባቸው በሕግ የተደነገገ ቢሆንም፤ ህጉን ጥሰው ገንዘብ ከተቀበሉ በኋላ ተገቢውን አገልግሎት ባለመስጠታቸው፤ ሕብረተሰቡንም ለእንግልት በመዳረጋቸው በርካታ ቅሬታዎች በመቅረባቸው እርምጃው እንደተወሰደባቸውና ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ እንደሚገኝ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
ኃላፊው በቀጣይ መሠል ችግሮች እንዳይከሰቱ ጽሕፈት ቤቱ ኤጀንሲዎቹ የሚጠበቅባቸውን መስፈርት ማሟ ላታቸውን በተመለከተ ቅድመ ምዘናዎችን በማድረግ ትክክለኛውን ሥራ ለመሥራት ማሟላት የሚጠበቅባቸውን መስፈርት አሟልተው ሲገኙ ብቻ የሥራ ፈቃድ እንደሚሰጣቸው ጠቁመው፤ ወደ ሥራ ከገቡ በኋላ ደግሞ ሕጉን ተላልፈው ዜጎችን ለጉዳት መዳረጋቸው ሲደረስበትና በችግሩ ተሳታፊ እንደሆኑ ጥቆማ ሲደርስ አስፈላጊው እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል፡፡
ኃላፊው ከዚህ ቀደም ጠንከር ያለ የሕግ ተጠያቂነት ባለመኖሩ በርካታ ችግሮች እንደሚታዩና አድራሻ የሌላቸው ኤጀንሲዎች የሕግ ቁጥጥር ሲደረግባቸው አሽገው ይጠፉ እንደነበር ጠቅሰው፤ አከራዮች የተከራዮችን አድራሻ፣ ተያዥ እንዲሁም አስፈላጊ ግዴታዎች መሟ ላታቸውን አረጋግጠው የቤት ኪራይ ውል የሚያስሩበትን አሠራር በመዘርጋት ችግሮችን ለማቃለል ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ፣ ከአገልግሎት ተቀባዩና ከሕብረተሰቡ ጋር በቅንጅት መሥራት እንደሚያስፈልግና እያንዳንዱ ዜጋ የችግሩ ሰለባ እንዳይሆን ከመንግስት ጎን ሆኖ ሊሠራ እንደሚገባም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 24/2011
ፍዮሪ ተወልደ