
ለሚ፦ ለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ ወደ ሥራ በገባ በአጭር ጊዜ የሀገሪቱ ትልቅ የግንባታ አጋር መሆን መቻሉ ተገለጸ። ፋብሪካው ወደ ማምረት ሥራ ከገባበት መስከረም 2017 ዓ.ም ጀምሮ ባለፉት ስድስት ወራት ከ12 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ሲሚንቶ ለገበያ ማቅረቡም ተጠቁሟል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ፋብሪካውን ለመገናኛ ብዙኃን እና ለታዋቂ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ትናንት ባስጎበኘበት ወቅት፤ የኢስት አፍሪካን ሆልዲንግ ተወካይ አቶ አዳነ ዓለሙ እንደተናገሩት፤ ፋብሪካው ወደ ሥራ በገባ አጭር ጊዜ ውስጥ ከ12 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ሲሚንቶ ያመረተ ሲሆን፤ በእዚህም በኢትዮጵያ ትልቅ የግንባታ አጋር መሆን ችሏል፡፡ የመገናኛ ብዙኃንና የኪነጥበብ ባለሙያዎች ፋብሪካውን መጎብኘታቸው ከንግግር ባለፈ በፋብሪካው የተከናወኑትንና እየተከናወኑ ያሉትን ሥራዎች ለሕዝብ ለማድረስ ወሳኝ ነው፡፡
ፋብሪካው መንግሥት በልዩ ዓይን ከሚከታተላቸው ፕሮጀክቶች አንዱ መሆኑን የገለጹት አቶ አዳነ፤ በኢስት አፍሪካን ሆልዲንግና በቻይናው ዌስት ኢንተርናሽናል ሆልዲንግ ጥምረት የተገነባው ይህን ፋብሪካ ወደ ማምረት ሥራ መግባቱ የሀገሪቱን የሲሚንቶ ገበያ ማረጋጋት እንዳስቻለም አስረድተዋል፡፡
እንደ አቶ አዳነ ማብራሪያ፤ ፋብሪካው ወደ ሥራ ከገባበት መስከረም 2017 ዓ.ም አንስቶ በስድስት ወራት ከ12 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ሲሚንቶ አምርቶ ለገበያ አቅርቧል። በእዚህም በሲሚንቶ ገበያ ላይ ተፈጥሮ የነበረውን ችግር በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመፍታት አስተዋጽኦ አድርጓል። ይሄ የሆነውም፤ ለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ እና እህት ኩባንያው ድሬዳዋ ሲሚንቶ ፋብሪካ በአንድነት ከሀገሪቱ ሲሚንቶ ገበያ 46 በመቶውን በመያዛቸው ነው።
ፋብሪካው በተጠቀሱት ወራት ያመረተው ሲሚንቶ መጠን ገበያው በሚፈልገው ልክ የተመረተ መሆኑን የጠቀሱት አቶ አዳነ፤ ከገበያው አንጻር ሲታይ ትርፍ እያመረተ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ የፋብሪካው የማምረት አቅም በቀን 150 ሺህ ኩንታል መሆኑን ጠቅሰው፣ እያመረተ ያለው ገበያው በሚፈልገው ልክ ነው ብለዋል።
ኩባንያው የድሬዳዋ ሲማንቶ ፋብሪካና የለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ የሲሚንቶ ምርቶችን በመላ ሀገሪቱ ለማሰራጨት እንዲያስችለውም ኢስት አፍሪካን ናሽናል ዲስትሪቢዩሽን የተሰኘ እህት ኩባንያ አቋቁሞ ሲሚንቶው በመላ ሀገሪቱ እንዲዳረስ እየሠራ መሆኑን አመልክተዋል።
አቶ አዳነ አያይዘው እንደገለጹት፤ ፋብሪካው ከእዚህም በላይ ማምረት የሚችል ቢሆንም፤ አሁን ላይ ገበያውን ታሳቢ ባደረገ መልኩ እያመረተ ይገኛል፡፡ በቀጣይ ግን ገበያውን በማስፋት ከእዚህም በላይ ምርት ለገበያ ለማቅረብ አቅዷል። ፋብሪካው የሚገኝበት የአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የእንሳሮ ወረዳ መሬት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ንጉሳየሁ ሜሙዬ፣ የፋብሪካው ወደ ወረዳው መምጣት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን አስታውቀዋል።
“ፋብሪካው ለወረዳውና ለለሚ ከተማ ትልቅ ዕድል ይዞ መጥቷል” ያሉት አቶ ንጉሳየሁ፤ በእዚህ እድል ወረዳዋም ከተማዋም በከፍተኛ መነቃቃት ውስጥ ናቸው ብለዋል። የፋብሪካውን ወደ አካባቢው መምጣት ተከትሎ ወደ ንግዱ የሚገቡ በርክተዋል ሲሉም ጠቅሰዋል፡፡
በእዚህም ለሃያና ሰላሳ ዓመታት እንቅልፍ ውስጥ የነበረችው የለሚ ከተማ ነቅታ በዕድገት ጎዳና መጓዝ ጀምራለች በማለትም፤ የሥራ ዕድል ፈጠራው ከፍተኛ መሆኑን፣ አርሶ አደሩም ጭምር ወደ ንግድ ሥራ እየገባ እንደሚገኝም ተናግረዋል። ይሄን ጅምር ከማስቀጠል አኳያም፤ የወረዳዋም የከተማዋም አስተዳደሮች ከፋብሪካው ጋር አብረው እየሠሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል። በመሆኑም፣ በፋብሪካው ለሚቀርቡ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት በትኩረት እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል።
የመገናኛ ብዙኃንና የኪነጥበብ ባለሙያዎቹ የፋብሪካውን የተለያዩ ክፍሎች ጎብኝተዋል። ባለሙያዎቹ ጥያቄዎችን አንስተው በፋብሪካው አመራሮችና የየክፍሉ ኃላፊዎች ምላሽና ማብራሪያዎች ተሰጥቶባቸዋል።
ኃይሉ ሣህለድንግል
አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 17 ቀን 2017 ዓ.ም