ሩሲያና ዩክሬን ይስማሙ ይሆን?

“ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ” ተብሎ ተሰይሞ የነበረውና በጥቂት ጊዜያት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተነግሮለት ከሦስት ዓመታት በፊት የተጀመረው የሩሲያ-ዩክሬን ግጭት፤ ዛሬም ሕይወት እየቀጠፈና ንብረት እያወደመ ቀጥሏል። አሜሪካና የአውሮፓ አጋሮቿ ለዩክሬን ያቀረቡት በመቶ ቢሊዮኖች የሚቆጠር ወታደራዊ ድጋፍ ዩክሬን ተጨማሪ ግዛቶቿን በሩሲያ እንዳትነጠቅ ስለማገዙ ቢገለፅም ጦርነቱ እንዳይባባስ ማድረግ ግን አልቻለም።

“ምርጫውን ካሸነፍኩ ጦርነቱን በአንድ ቀን አስቆመዋለሁ” ብለው ሲፎክሩ የነበሩት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ጦርነቱን ማስቆሙ እንኳን በአንድ ቀን በዘጠና ቀናትም አልተሳካላቸውም። በእርግጥ ፕሬዚዳንቱ የነጩን ቤት መንበር ከተረከቡ ጊዜ ጀምሮ ጦርነቱን ለማስቆም ጥቂት የማይባሉ ጥረቶችን አድርገዋል። በእዚህ ጥረታቸውም የሩሲያ፣ የዩክሬንና የአሜሪካ ተወካዮች የተሳተፉባቸው የጋራና የተናጠል ውይይቶች ተካሂደዋል። የ30 ቀናት ተኩስ የማቆም እቅድ ይፋ ተደርጓል በተፋላሚዎቹ እንዲሁም በተፋላሚዎቹና በአሜሪካ መካከል አንዳንድ ስምምነቶች ተደርገዋል፤ ትራምፕና ፑቲን በቀጥታ በስልክ ተወያይተዋል።

“እኔ ጦርነቱን ለማስቆም እየጣርኩ ነው፤ በጣም ጥሩ ውጤት እየታየ ነው፤ ይህ አስቀያሚ ጦርነት መቆም አለበት” ሲሉ የሚደመጡት ፕሬዚዳንት ትራምፕ፤ የጠበቁትን ያህል ውጤት ባያገኙም ተፋላሚዎቹን በውድም በግድም ስምምነት ለማስፈረም ጥረዋል።

አንዳንድ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ጦርነቱን ለማስቆም የተሞከሩት ጥረቶች ተፈላጊውን ውጤት ማምጣት ባለመቻላቸው በሁኔታው ሳይሰላቹ እንዳልቀሩ ተገልጿል። የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ከዩክሬን የአውሮፓ አጋሮች ጋር በፓሪስ ከተወያዩ በኋላ ባደረጉት ንግግር፤ የአሜሪካ የሰላም ጥረት ፍሬ የማያፈራ ከሆነ ሀገራቸው ከተኩስ አቁምና ከሰላም ስምምነት አደራዳሪነት ሚናዋ ልትወጣ እንደምትችል ገልጸዋል። “የምናገረው ስለጥቂት ቀናት ጉዳይ ነው። በፍጥነት መወሰን ይኖርብናል። የተኩስ አቁም ላይ የማይደረስ ከሆነ ጥረታችንን እንተወዋለን። አሜሪካ የምታተኩርባቸው ሌሎች ጉዳዮች አሏት” ብለዋል።

ፕሬዚዳንት ትራምፕም ይህን የሩቢዮ ሃሳብ ደግመውታል። ፕሬዚዳንቱ አሜሪካ ከሩሲያ-ዩክሬን አደራዳሪነት ሚናዋ ልትወጣ እንደምትችል ባስጠነቀቁበት ንግግራቸው፣ ሞስኮ ወይም ኪዬቭ ተኩስ የማቆሙን ጥረት አስቸጋሪ የሚያደርጉት ከሆነ ሀገራቸው ጦርነቱን ለማስቆም የምታደርገውን ጥረት ልታቋርጥ እንደምትችል ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ይህን ያህል ጥረት ቢያደርጉም አውዳሚው የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት ግን የመባባስ እንጂ የመቀዝቀዝ ምልክት አልታየበትም። ለእዚህም ነው ብዙ የጂኦ-ፖለቲካ ተንታኞች “ሩሲያና ዩክሬን የመስማማት ተስፋ አላቸው? ዘላቂ የተኩስ አቁም ብሎም የሰላም ስምምነትስ ይፈራረሙ ይሆን…?” ብለው አበክረው የሚጠይቁት።

የውጭና የደህንነት ጉዳዮች ተንታኙ ስቴቨን ፒፈር፣ የፕሬዚዳንት ትራምፕ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ ለሩሲያ ያደላ አካሄድን እየተከተሉ እንደሆነ ያምናሉ። “ዊትኮፍ ተፋላሚዎቹ ስምምነት ላይ እንደሚደርሱ በተደጋጋሚ ቢገልጹም፣ ይህ ተስፋቸው በምን ዓይነት እቅድ ገቢራዊ እንደሚሆን ግልጽ አይደለም። ንግግሮቻቸው ሁሉ ለሞስኮ የወገኑ ናቸው። ኪዬቭ ደግሞ ይህን ዓይነት አካሄድ ትቀበላለች ተብሎ አይጠበቅም” ይላሉ።

ፒፈር እንደሚገልጹት፣ ሩሲያ የተኩስ አቁም ለማድረግ ዳተኛ እየሆነች ነው። ዊትኮፍ አሜሪካ ባቀረበችው የ30 ቀናት የተኩስ አቁም እቅድ ላይ ከፑቲን ጋር ያደረጉትን ውይይት “ውጤታማና መፍትሔ ተኮር” ብለው ቢገልጹትም፤ ሩሲያ ከውይይቱ ከአንድ ወር በኋላ እንኳ የተኩስ አቁም ለማድረግ ፍላጎት አላሳየችም።

ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከሳምንታት በፊት አሜሪካ ስላቀረበችው የተኩስ አቁም እቅድ ሲናገሩ፤ ሀገራቸው ተኩስ የማቆምን ሃሳብ በአወንታዊነት እንደምትቀበለው ገልጸው፤ ግልጽ ምላሽና ማብራሪያ የምትፈልግባቸው ጉዳዮች እንዳሉ ገልጸው ነበር። “ግጭትን ለማስቆም ተኩስ አቁም ማድረግ ትክክለኛ ሃሳብ ነው። ሩሲያም በመርህ ደረጃ ተኩስ ማቆምን ትደግፋለች። ነገር ግን ከአሜሪካ ጋር ልንወያይባቸው የሚገቡ ጉዳዮች አሉ” ያሉት ፑቲን፣ ሞስኮ የተኩስ አቁም ስምምነቱን እንድትተገብር መሟላት ስላለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ዘርዝረው ነበር።

በዩክሬን ወታደሮች ተይዞ የነበረው የሩሲያው ኩርስክ ግዛት ጉዳይ የፑቲን አንዱ ቅድመ ሁኔታ ነው። ዩክሬን የተኩስ አቁም ጊዜውን መሣሪያ ለመሰብሰብ እና ኃይል ለማደራጀት ልትጠቀምበት ትችላለች ብለውም ይሰጋሉ። ይህ እንዳይሆንም ዋስትናው ምን እንደሆነ ጠይቀዋል። “የተኩስ አቁም ስምምነቱ ተቆጣጣሪ ማን ነው?” የሚለው ጉዳይም የፑቲን ሌላው ቅድመ ሁኔታ ነው።

በሩሲያ የተያዙ የዩክሬን ግዛቶች ጉዳይም ሁለቱ ሀገራት ስምምነት ላይ እንዳይደርሱ ትልቅ እንቅፋት የሚሆኑ ናቸው። ዩክሬን ከሦስት ዓመታት በፊት በተጀመረው ጦርነት የተያዙባት ግዛቶቿ ብቻ ሳይሆኑ ከ11 ዓመታት በፊት በሩሲያ የተያዘችባት የዩክሬሚያ ግዛትም እንድትመለስላት ትፈልጋለች። ሩሲያ ደግሞ በፍፁም ይህ እንደማይሆን በተደጋጋሚ አሳውቃለች።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከሁለት ወራት በፊት ለጋዜጠኞች በሰጡት ገለጻ፣ ዩክሬን በሩሲያ የተወሰዱባትን ግዛቶች የማስመለስም ሆነ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ኔቶ(NATO) አባል የመሆን እድል ላይኖራት እንደሚችልና ሀገሪቱ ከሦስት ዓመታት በፊት በተጀመረው ጦርነት ያጣቻቸውን አንዳንድ ግዛቶቿን በድርድር የማስመለስ እድል ያላት ቢሆንም ከ11 ዓመታት በፊት የነበረው ድንበር ግን ይመለሳል ብሎ መጠበቅ እንደማይገባ ተናግረው ነበር። አሜሪካ የመጨረሻ አማራጭ ብላ ሰሞኑን ያቀረበችው የሰላም እቅድም ዩክሬን ክሪሚያ የሩሲያ አካል ስለመሆኗ እውቅና እንድትሰጥ የሚጠይቅ እቅድ እንደተካተተበት ተገልጿል።

ዩክሬንና አጋሮቿ የዩክሬንን ግዛቶች ለሩሲያ አሳልፎ መስጠት የማይታሰብ እንደሆነ በተደጋጋሚ ገልጸዋል። የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ሀገራቸው በሩሲያ የተያዙ ግዛቶቿን በፍጹም የሩሲያ አካል አድርጋ እንደማትቆጥር በአጽንዖት ተናግረዋል።

በለንደን ኪንግስ ኮሌጅ (King’s College London) የመከላከያ ጥናት ተመራማሪ ማሪና ሚሮን፣ የትራምፕ አስተዳደር ዩክሬን በድርድሩ ላይ ያላት አቅምና የወሳኝነት ሚና ዝቅተኛ መሆኑን በግልጽ እያሳየ እንደሆነ ይገልጻሉ። “ተኩስ አቁሙ እስከሚተገበር ድረስ ጊዜ መውሰዱ አይቀርም። ይህ ደግሞ ሩሲያ ኩርስክን መልሳ ለመቆጣጠር የሚያስችል ጊዜ ይሰጣታል። ይህም የዩክሬንን የመደራደር አቅም ያዳክመዋል” ይላሉ።

ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም ኢኮኖሚያዊ ጫናዎችን በአማራጭነት የሚጠቀሙት ፕሬዚዳንት ትራምፕ፤ ሩሲያ ጦርነቱን ለማስቆም ለሚወስዱት ርምጃ ተባባሪ ካልሆነች ተጨማሪ ማዕቀቦችን እንደሚጥሉባት ዝተዋል። ይህ ዛቻ ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ እስካሁን ድረስ 22ሺ ገደማ ማዕቀቦች ለተጣለባት ሩሲያ አስደንጋጭ ርምጃ ይሆናል ተብሎ አይጠበቅም። ይህ አካሄድ ደግሞ ጦርነቱን ከማራዘም ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም።

ከእዚህ በተጨማሪም የአሜሪካ፣ የአውሮፓ (ፈረንሳይ፣ እንግሊዝና ጀርመን)ና የዩክሬን ባለሥልጣናት ከቀናት በኋላ በለንደን ሊያደርጉት የነበረው ውይይት መራዘሙም ተፋላሚዎቹ በቀላሉ ከስምምነት ላይ አይደርሱም የሚሉ ወገኖችን ሃሳብ የሚያጠናክር ሳይሆን አይቀርም።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ አሜሪካ ከሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት የተኩስ አቁምና የሰላም ስምምነት ጥረት እንድትወጣ የሚያደርጉ ከሆነ፣ ዩክሬን ከአሜሪካ የምታገኘውን ከፍተኛ የጦር መሳሪያ፣ የገንዘብና የመረጃ ድጋፍ ልታጣ ትችላለች። ትራምፕ “የምትስማሙ ከሆነ በፍጥነት ተስማሙና ይህን አስቀያሚ ጦርነት አቁሙ፤ አለበለዚያ አሜሪካ ለማይመለከታት ጦርነት ገንዘቧን የምታፈስበት ምንም ምክንያት አይኖራትም” የሚለው ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያቸው ይህን የሚያመለክት ይመስላል። ይህ ደግሞ ተፋላሚዎቹ ስምምነት ላይ እንዳይደርሱና አውዳሚው ጦርነትም እንዲቀጥል ያደርጋል።

አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን  ሚያዝያ 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You