የኮንስትራክሽን ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት ትኩረት ሊሰጥ ይገባል

አዳማ:- ከውጭ የሚገቡ የኮንስትራክሽን ዘርፉን ግብአቶች በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት የተቀመጠውን እቅድ ለማሳካት አሁንም በትኩረት መሥራት እንደሚገባ ተገለጸ፡፡ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ሥራዎች የኮንስትራክሽን ዘርፉን ተኪ ምርቶች ከ20 በመቶ ወደ 50 በመቶ ማድረስ መቻሉ ተጠቁሟል፡፡

የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ከኢትዮጵያ አርክቴክቸር ሕንጻ ግንባታና ከተማ ልማት ተቋም እንዲሁም ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚክ ማህበር ጋር በመተባበር የጥናትና ምርምር ውጤቶችን የጋራ ለማድረግ የሚያስችል የውይይት መድረክ ሰሞኑን በአዳማ ከተማ አካሂደዋል።

የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ታምራት ሙሉ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ሴራሚክ፣ መስታወትና መሰል የኮንስትራክሽን ምርቶችን በተወሰነ ደረጃ ሀገር ውስጥ ብታመርትም በአጠቃላይ ሀገሪቷ በሁሉም መስኮች በውጭ የግንባታ ግብዓቶች ላይ ጥገኛ መሆኗ አሁንም በስፋት ይስተዋላል።

ይህን ሁኔታ ለመቀየር የዘርፉን ግብአቶች በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ባለፉት አራት እና አምስት ዓመታት በተከናወኑ ተግባሮች የሀገር ውስጥ ምርቶች አጠቃቀምን ከ20 በመቶ ወደ 50 በመቶ በማድረስ ለውጥ ማምጣት መቻሉን አስታውቀዋል፡፡ ይህን ለውጥ በ10 ዓመቱ የልማት ግብ 80 በመቶ ለማድረስ ከታቀደው አኳያ አሁንም ብዙ መሥራት እንደሚገባ አመላክተዋል።

ሀገሪቷ የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ በምታስገባበት ጊዜ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ እንደሚያሳድር ገልጸዋል። በብዙ ድካም የተገኙ የግብርና ምርቶች ወደ ውጭ ተልከው የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ መልሶ ብረት መሰል የኮንስትራክሽን ግብአቶችን ከውጭ ለመግዣ እንደሚውል አመልክተዋል፡፡

ይህም ለሀገር ኢኮኖሚ ከፍተኛ ተግዳሮት መሆኑን ጠቅሰው፤ ለሀገር ውስጥ ምርቶች ትኩረት ሰጥቶ በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባ አመላክተዋል።

የሀገር ውስጥ አምራቾችም ገበያው ሲመቻችላቸው ምርታማነታቸውን ማሳደግ እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመው፤ ምርቶቻቸው ጥራታቸውን የጠበቁና በሚፈለጉ አማራጮች የሚያቀርቡ እንዲሆኑ ማድረግ እንዳለባቸውም አሳስበዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ አምራቾቹ በዋጋም ተወዳዳሪ ለመሆን የማምረት አቅማቸውን መጨመር አለባቸው።

ይህ ካልሆነም ሰዎች ከውጭ ወደ ማምጣት ሊያዘነብሉ የሚችሉ በመሆኑ በእዚህ ላይ ሊሠሩ ይገባቸዋል። በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አሶሴሽን ተመራማሪ፣ አማካሪና የሥልጠና ኃላፊና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ሲሳይ ደበበ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የሀብት አጠቃቀም ላይ ለአንድ ዓመት ጥናት ተደርጓል፡፡ ከኮንስትራክሽን ግብአቶቹ ከ35 እስከ 40 በመቶ የሚሆኑት በውጭ ምንዛሪ የሚገቡ ናቸው፡፡

ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ማህበር ጥናት ያቀረቡት ሰለሞን እንድሪያስ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በሀገር ውስጥ ያሉ የግንባታ ግብአቶችን በመለየት የአሠራር ሥርዓት ለመዘርጋት ያለመ ጥናት መደረጉን አስታውቀዋል።

በጥናቱ የአቅርቦት ሰንሰለት ዋነኛ ችግር መሆኑ ታይቷል ሲሉም ጠቅሰው፤ በፋብሪካ ገብተው ፕሮሰስ የሚደረጉ ምርቶች የሚጠቀሙ ጥሬ እቃዎች የእሴት ሰንሰለቱ አካል መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ለእነዚህ የእሴት ሰንሰለቶችም 38 ባለድርሻ አካላት በጥናቱ መለየታቸውን ገልጸዋል። የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር፣ የማዕድን ሚኒስቴር እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ዋነኛ ባለድርሻ አካላት መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

የከተማ መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ የትምጌታ አስራት፤ በሁሉም ረገድ በሀገር ውስጥ ምርት በውስጥ አቅም መጠቀም እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በዓመት በአማካይ አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ የኮንስትራክሽን ግብአቶችን ከውጭ እያስገባች መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የጥናት ውጤቶቹም በመረጃ እና በእውቀት ላይ በመመሥረት የፖሊሲ አቅጣጫ ለመቅረፅ እንደሚያግዙ ሚኒስትር ዴኤታው አመላክተዋል ። የጥናቶቹ ውጤቶች የሀገር ውስጥ የኮንስትራክሽን ግብአት ምርት በዘላቂነት በመጨመርና የውጭ ጥገኝነት ለመቀነስ የሚያስችል መሆኑንም ጠቁመዋል።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You