አዲሱ የአውሮፕላን ማረፊያ ምን በረከት ይዞ ይመጣል?

ዜና ትንታኔ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ግዙፍ ያለውን የአውሮፕላን ማረፊያ በሰባት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ዶላር ወጪ ሊገነባ መሆኑን አስታውቋል። አየር መንገዱ ግንባታውን ለማስጀመር ዳር ከተባለ ዓለም አቀፍ ኩባንያ ጋራ የመግባቢያ ስምምነት የተፈራረመ ሲሆን፤ ግንባታው በሁለት ምዕራፎች ተከፍሎ እንደሚገነባም ገልጿል።

በመጀመሪያው ምዕራፍ 60 ሚሊዮን ተጓዦችን ማስተናገድ የሚችለው የአውሮፕላን ማረፊያ ይገነባል። የመጀመሪያው ምዕራፍ ሲጠናቀቅ ደግሞ 50 ሚሊዮን ተጓዦችን የሚያስተናግደው ሁለተኛው ምዕራፍ ይገነባል። የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ በአምስት ዓመት ውስጥ ማለትም እስከ 2022 ዓ.ም ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ በቢሾፍቱ አቅራቢያ ይገነባል የተባለው ግዙፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሦስት ሺህ 500 ሔክታር መሬት ላይ የሚያርፍ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ ግዙፍ የአየር መንገድ አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ስኩዌር ሜትር ላይ የሚያርፍ የመንገደኞች ተርሚናል፣ 126 ሺህ 190 ስኩዌር ሜትር ላይ የሚያርፍ ለአየር መንገዱ ድጋፍ የሚሰጡ ተቋማት እንዲሁም 100 ሺህ ስኩዌር ሜትር ላይ የሚያርፍ የጭነት አገልግሎት መስጫ እንደሚያካትት ገልጸዋል።

አዲሱ በቢሾፍቱ አቅራቢያ የሚገነባው አውሮፕላን ማረፊያ ከአዲስ አበባ ቦሌ አየር ማረፊያ ጋር በፈጣን መንገድ እንዲሁም በፈጣን ባቡር እንደሚገናኝ ተናግረዋል።

የሚገነባውን የኤርፖርት ሲቲ ስፋት እና ጠቀሜታ ለመረዳት አሁን ያለውን የቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያን የመሠረተ ልማት ውስንነት ግምት ውስጥ ማስገባት አስፈላጊ ነው ያሉት አቶ መስፍን፤ የአየር መንገዱ ዕድገት በጨመረ ቁጥር ለአውሮፕላን ማረፊያው የተለያዩ የማስፋፊያ ሥራዎች ሲከናወኑ ቢቆይም፤ በዓመት 25 ሚሊዮን ተጓዦችን ማስተናገድ በሚችልበት የመጨረሻ አቅሙ ላይ መድረሱን አቶ መስፍን አስታውቀዋል።

ከእዚህ መነሻነትም የአየር መንገዱን እድገት እና የመንገደኞችን ቁጥር መጨመር ታሳቢ ያደረገ ግዙፍ አውሮፕላን ማረፊያ (ኤርፖርት ሲቲ) መገንባት የግድ መሆኑን በማመን ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረው፤ አውሮፕላን ማረፊያው ከትራንስፖርት አገልግሎት ባለፈ ሆቴሎችን፣ የገቢያ ማዕከሎችን፣ የቢሮ ቦታዎችን እና የመኖሪያ አካባቢዎችን የሚያጠቃልል ትልቅ “የኤርፖርት ሲቲ” ዋና አካል እንዲሆን ታስቦ የሚገነባ መሆኑን ጠቁመዋል።

ለመሆኑ የኤርፖርት ሲቲው መገንባት ከንግድ አንፃር ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ምን ሊሆን ይችላል? ስንል የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎችን ጠይቀናል።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ሞላ አለማየሁ (ዶ/ር) ለኢፕድ እንደገለጹት፤ ኤርፖርት ሲቲው ተገንብቶ ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያ በዓመት 125 ሚሊዮን መንገደኞችን በአየር ትራንስፖርት ማስተናገድ ትችላለች። 100 ሚሊዮኑ በኤርፖርት ሲቲው የሚስተናገዱ ሲሆን፤ ቀሪዎቹ 25 ሚሊዮን ደግሞ በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ይስተናገዳሉ።

ይህም ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ጋር ያላት የንግድ ግንኙነት እንዲቀላጠፍና ከፍተኛ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንድትሆን ያደርጋታል ያሉት ሞላ (ዶ/ር)፤ በእዚህም ዓለም አቀፍ ባለሀብቶች የሀገሪቱን እምቅ አቅም እንዲመለከቱ በማድረግ የንግድ አማራጮች በግልጽ እንዲታዩ ሰፊ እድል ይፈጥራል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በቀላሉ የሚበላሹ የግብርና ምርቶችን ወደ ሌሎች ሀገራት የምትልከው በአየር ትራንስፖርት ነው። ከእዚህ አንፃር የቢሾፍቱ ኤርፖርት ሲቲ መገንባት የካርጎ አቅምን የሚጨምር በመሆኑ የሚበላሹ ምርቶችን በብዛት ወደ ውጭ ሀገር ለመላክና ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት ይረዳል ብለዋል።

ከቡና ምርት ቀጥሎ አበባን ወደ ውጭ የመላክ አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን አንስተው፤ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ንግድ ላይ ተወዳዳሪ በሆነችባቸው ምርቶች ላይ በልጣ እንድትገኝ የኤርፖርት ሲቲው መገንባት ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።

ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባው ምርት ወደ ውጭ ከሚላከው አንፃር ዝቅተኛ ነው። ይህም ሀብት ወደ ውጭ ሀገራት እንዲሄድ በማድረግ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ ይገኛል ያሉት ሞላ (ዶ/ር)፤ ኤርፖርት ሲቲው አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ውጪና ገቢ ንግድን ለማመጣጠን እንደሚረዳ ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን እያሳደገች ትገኛለች። ይህም የግብርና ምርቶችን ወደ ውጭ ሀገራት የሚልኩ አርሶ አደሮችን በተለይ በቡናና በአበባ ምርት ላይ የተሰማሩትን እንደሚጠቅም ገልጸው፤ አርሶ አደሮችና ነጋዴዎች ሌሎች የኤክስፖርት አማራጮችን እንዲመለከቱ እድል እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

አሁን ያለው የቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ያለው አቅም ኢትዮጵያ ወደፊት ከሚያስፈልጋት አቅም ጋር ሲነፃጸር ዝቅተኛ እንደሚሆን ገልጸው፤ አሁን ላይ የኢትዮጵያን የወደፊት አቅም የሚመጥን አየር ማረፊያ ለመገንባት የሚደረገው ጥረት ጊዜውን የዋጀ እና ሀገሪቱን የሚመጥን ተግባር መሆኑን ነው የተናገሩት።

የምጣኔ ሀብት ምሁሩ ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኤርፖርት ሲቲው በዓመት መቶ ሚሊዮን መንገደኞችን ማስተናገድ ይችላል ማለት በንግድ ዘርፉ ላይ የሚኖረው ሚና ቀላል የሚባል አይደለም። ከእዚህ አንፃር ኤርፖርት ሲቲው ራሱን የቻለ የኢኮኖሚ ዞን የመሆን እድል እንዳለው ጠቁመዋል።

በተለይ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና እየተስፋፋ በሚሄድበት ጊዜ የአየር ትራንስፖርት ተፈላጊነት ይጨምራል ያሉት ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አሁን ባለበት ሁኔታ ወደ ኢትዮጵያ ስድስት ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የንግድ እንቅስቃሴ እንደሚያመጣ መረጃዎች ያሳያሉ ነው ያሉት።

ከእዚህ በመነሳት ኤርፖርት ሲቲው የኢትዮጵያን የንግድ እንቅስቃሴን በእጥፍ ሊያሳድግ እንደሚችል የጠቆሙት ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር)፤ ኤርፖርት ሲቲው በውጭ ምንዛሪ ግብይት የሚፈጸም በመሆኑ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እንደሚያስገኝ ተናግረዋል።

ይህም ሀገሪቱ በውጭ ንግድ ላይ ተወዳዳሪ እንድትሆን በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተናግረው፤ በተለይ የሕክምና ቁሳቁሶችን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለማንቀሳቀስ የአየር ትራንስፖርት ተመራጭ መሆኑን አንስተው፤ በእዚህ ረገድ ኤርፖርት ሲቲው ተመራጭ እና አትራፊ የሚሆንበት እድል እንዳለ ገልጸዋል።

በኤርፖርት ሲቲ ውስጥ ተሳፋሪዎች ጊዜ ሲኖራቸው ተዘዋውረው እቃ የሚገዙበት ሁኔታ ይፈጥራል። በተለይ ደግሞ በኤርፖርት ሲቲው በርካታ አውሮፕላኖች የሚኖሩ ከሆነ የአየር ትራንስፖርት እና የጭነት የማጓጓዣ ዋጋ የሚቀንስ በመሆኑ ከመርከቦች ክፍያ ጋር ተቀራራቢ ሊሆን ይችላል ነው ያሉት።

የኤርፖርት ሲቲ መሠረተ ልማት መገንባት ከፍተኛ በጀት የሚፈልግ ፕሮጀክት ነው። ወደ ፊት ከሚገኘው ጠቀሜታ አኳያ ፕሮጀክቱን በፍጥነት ማጠናቀቅ እንደሚገባ አመላክተው፤ ኤርፖርት ሲቲው የኢትዮጵያን የአቪዬሽ አቅም በሦስት እጥፍ ያሳድጋል ተብሎ ይጠበቃል ነው ያሉት።

እንደ ምሁራኑ አገላለጽ፤ አውሮፕላን ማረፊያው የኢትዮጵያን የንግድ እንቅስቃሴ ለማሳለጥ ዓይነተኛ ሚና ይኖረዋል።ዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ኢንቨስት እንዲያደርጉ እንደ ማግኔት ጎትቶ የሚሰብ ነው። ይህም የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ዕድገት ዘላቂና አስተማማኝ ያደርገዋል። የሥራ ዕድልም ያሰፋል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 15 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You