“የሕወሓት አመራር እድር መቆጣጠር ይፈልጋል፤ ማህበር መቆጣጠር ይፈልጋል፤ ቤተክርስቲያን መቆጣጠር ይፈልጋል” -አቶ ጌታቸው ረዳ የጠቅላይ ሚንስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚንስትር

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት፣ በቴሌዢዥን ጣቢያው አማካኝነት ከሰሞኑ በእንግዳ ፕሮግራሙ ከምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች የጠቅላይ ሚንስትሩ አማካሪ ሚንስትር ከአቶ ጌታቸው ረዳ ጋር፣ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሰፋ ያለ ቃለ ምልልስ አድርጓል። በዚህ ቃለ ምልልሱም በሀገራዊ ብሎም ክልላዊ ጉዳዮች፤ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ ብሎም በሰላምና ፀጥታ አጀንዳዎች፤ እንዲሁም ሕወሓትን የተመለከቱ ነጥቦች ተነስተዋል። እኛም ይሄንኑ የቴሌቪዥን ጣቢያውን ቃለ ምልልስ በሚከተለው መልኩ አቅርበነዋል።

ፋና ቴሌቪዥን፦ አቶ ጌታቸው አድማጭ ተመልካቾች ብዙ ጊዜ ስለ እርሶ ማወቅ የሚፈልጉት ነገር አለ፤ እንዴት ወደ ፖለቲካ ገቡ፤ እንዴት ወደ ፖለቲካ ተሳቡ፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ይላሉ?

አቶ ጌታቸው፦ ወደ ፖለቲካ የማይሳብ ሰው የለም። የሆነ ሁኔታዎች ውስጥ ኑር፤ ሀገር ውስጥ ኑር፤ የሆነ አካባቢ ኑር ሽፍት በል …ወደ ፖለቲካ የመሳብ ሁኔታ አለ። አሁን እያልክ ያለኸው እኔ እንደሚመስለኝ ወደ ተደራጀ ፖለቲካ እንዴት ገቡ የሚል ይመስለኛል። እኔ ለረጅም ጊዜ ከዩኒቨርሲቲ ከወጣሁ በኋላ አስተማሪ ነበርኩ። የድርጅት አባልም አልነበርኩም። ግን ዩኒቨርሲቲ በማስተምርበት ወቅት የማምንባቸው ነገሮች ነበሩ።

በዚያን ሰዓት የነበረው ገዥ ፓርቲ ካሉት አስተሳሰቦች ጋር የሚቀራረብ እምነት ነበረኝ። በዚህ ምክንያት አባል መሆን አለመሆኔን ሳላውቀው ጭምር እራሴን እንደ አባል ነበር የምቆጥረው። በሂደት ከማስተማር ሥራ ወጥቼ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማገልገል ስጀምር ፤ ስትራቴጂክ ፖሊሲ ምክር ነገር እንድሰጥ ነው የተመደብኩት። ግን በሂደት የፓርቲ አባል መሆን የተሻለ ያታግላል የሚል እምነት ከአለቆች ስለመጣ እንጂ በግሌ የፓርቲ አባል የመሆን ያን ያህል የተለየ ጉጉት፤ የተለየ እንቅስቃሴ አድርጌ አላውቅም።

በሂደት ያዩሁት ነገርም እኔ ወደ ሕውሓት አመራርነት የመጣሁበት ሂደት ያልተለመደ ሂደት ነው። ትልቅ ሥልጣን ከያዝኩ በኋላ ምናልባት በፓርቲ ስር ቢታገል ይሻላል በሚል የተመለመልኩ ነኝ። ስለዚህ በተለመደው ሂደት ከስር ጀምሮ እየተመለመለ፤ እያገለገለ፤ እየተኮተኮተ፤ ጎንበስ ቀና እያለ የመምጣት አይነት ሂደት አልነበረም።

ከከፍተኛ ኃላፊነት ነው የጀመርኩት ማለት ነው። እንደውም አስታውሳለሁ አንድ አሁን ውጭ ሀገር ያሉ ከፍተኛ የኢህዴግ ባለሥልጣን ለምንድ ነው እስካሁን አባል ያልሆንከው አሉኝ፤ አይ ድርጅታቹህ ታጋዮች ያልሆኑ ብዙ አባላት ስላሉት፤ አባላት ያልሆንን ታጋዮች እናስፈልጋችኋለን በሚል ነው ብዬ እንደ ቀልድ አንስቼላቸው ነበር።

ተደራጅቶ መታገሉ ጥሩ ነው የሚል እምነት ላይ ስለደረሰ፤ በዛ ደረጃ ነው የመጣሁት። አመጣጤ መሳብ ነው አለመሳብ ነው በሚል ሳይሆን፤ ኃላፊነት ውስጥ ከገባው በኋላ በድርጅቱ ውስጥ ብትታቀፍ የተሻለ ትታገላለህ በሚል ብዙ ሳላንገራግር ነው የተቀበልኩት። ይህ የተደራጀ ፖለቲካ ውስጥ የገባሁበት ሂደት ነው።

ፋና ቴሌቪዥን ፦ መልካም ፤ የፓርቲ አባል ከሆኑ በኋላ በፍጥነት ነው ተፅኖ ፈጣሪ አባል የሆኑት። ከበረሃ የመጣ ብቻ ነው የጀርባ አጥንት ያለው የሚል ባህል ባለው ድርጅት ውስጥ እንዴት ተሳካሎት፤ ምንስ ፈተና ገጠሞት?

አቶ ጌታቸው፦ እኔ የመጣሁበት ሂደት በጣም ያልተለመደ ነው። አባልነት በፈረምኩ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ነው ከፍተኛ አመራር ከሚባለው እርከን ውስጥ የገባሁት። ከፍተኛ አመራር ተብዬ ሥልጠና መውሰድ ከጀመርኩ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ነው የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የሆንኩት።

እንደገና ዓመት ከስድስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ሆንኩ። ለነባሮቹ ትንሽ ግር የሚያሰኝ ነበር። ግን ነባሮች ከምላቸው ውስጥ በጣም የማከብራቸው ሰዎች በዚህ ሂደት ድርጅቱ ይጠቀማል የሚል እምነት የነበራቸው ብዙዎች ነበሩ። አሁን ላይ በሕይወት ያሉም የሌሉም።

አንዳንዶች ደግሞ ይሄ አመጣጡ ለመኮርኮም የማይመች ስለሆነ፤ (ምክንያቱም የጡት አባትህ መታወቅ መቻል አለበት) ማነው መልምሎ ያመጣው፤ የሆነ ያጠፋ እለት ፤ ያኮረፈ እለት ማነው ተጠንቀቅ የሚለው፤ ወይ ከመስመር ልውጣ ያለ ቀን፤ ከመስመር ልውጣ ማለት እምነት ሳይሆን፤ ምናልባት መፋጠጥ ያበዛ ቀን ምንድ ነው ሊደረግ የሚችለው የሚል ስጋት ያለባቸው አሁንም አመራር ውስጥ ያሉ ሰዎች አሉ። ግን ደግሞ ሂደቱ የምርጫ ጉዳይ ስለሆነ ማስገደድ የሚችሉበት ሁኔታ አልነበረም።

ተጽኖ ፈጣሪነት ማዕከላዊ ኮሚቴ፤ ፖሊት ቢሮ ስለሆንኩ ብቻ ሳይሆን፤ ከዚያ በፊት በነበረኝ የመንግሥት ኃላፊነት አቅሜ የፈቀደውን ሁሉ ሀገሬን ያገለግላል ብዬ የማምንበትን ሁሉ፤ ድርጅቱም ሀገርን የማገልገል ዓላማ ይዞ ነው የሚንቀሳቀው ብለህ ስለምታምን የሚለውን ሁሉ ስሰጥ ስለነበረ፤ አቅሜ የፈቀደውን ሁሉ ሳደርግ ስለነበር፤ ያው በባህሬዬም የተሰማኝን ከመናገር ወደ ኋላ የምል ሰው ስላልነበርኩ የሆነ ነው።

ተጽኖ መፍጠር ተደማጭነት የሚባል ከሆነ የፓርቲው ከፍተኛ አመራር ሳልገባ ጭምር ከዚያ በፊት የመንግሥት ኃላፊነት ለማግኘት ጭምር እድሉ ገጥሞኝ ስለነበር ያን አጋጣሚ በደንብ የተጠቀምኩበት ይመስለኛል። እንዳልኩት ግን ብዙዎቹ የትጥቅ ትግል ውስጥ ያልተሳተፈን ሰው በተለይ የሕዋሓት አመራር ውስጥ አከርካሪ አለው ተብሎ አይታመንም።

የአከርካሪ ጉዳይ ያው አከርካሪ እንዳለን በተደጋጋሚ አሳይተናል። አከርካሪ የሌለው ተብሎ ከመጠርጠር በላይ ግን ቅድም እንዳልኩት የጡት አባቱ ማን እንደሆነ የማይታወቅ አመጣጡ እማይታወቅ፤ ከስር ትመለምለዋለህ። መልምለህ የሆነ ደረጃ ታሳድገዋለህ። እያሳደክ ሁኔታውን እያየህ፤ አፋሽ አጎንባሽ መሆኑን እያረጋገጥህ ነው የምታሳድገው በብዛት። ስለዚህ በዛ ባህል ከእምነትህ ይልቅ አገልጋይነትህ የበለጠ ተቀባይነት በሚያደርግ ባህል ውስጥ በእኔ መንገድ የመጡ ብዙ ሰዎች የሉም።

እንደተባለው ነው በአንድ ዓመት ከምናምን ጊዜ ውስጥ ማእከላዊ ኮሚቴ አባል ሆኜ ፤ ዓመት ከስድስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የፖሊት ቢሮ አባል ሆንኩ። ይሄ በድርጅቱ ታሪክ ውስጥም ስላልነበረ ነው። ትጥቅ ትግል ውስጥ ስላልተሳተፈኩ ብቻ ሳይሆን፤ እኔ ጋር ትጥቅ ትግል ሳይሳተፉ የፖሊት ቢሮ የገቡ ሰዎች እንዳሉ አውቃለው። ግን እኔ የምመዘንበት መንገድ አድራሻው የማይታወቅ ሰው፤ የመለመለኝ ሰው፤ ወይ እዛ ያደረሰኝ ሰው የማይታወቅ አጠራጣሪ ሰው ነው ብለው ይሰጋሉ።

አንዳንድ ጓዶች ብዙም ምቾት የማይሰማቸው ነበሩ። ግን እንዳልኩት በሕይወት የሌሉም ያሉም የእኔ በዛ ፍጥነት እዛ ላይ መድረስ ድርጅቱን የሚጠቅም ነው ብለው ሙሉ ድጋፍ የሚሰጡኝ ነበሩ።

ፋና ቴሌቪዥን ፦ የትግራይ ሕዝብና ሕውሓት አንድ ናቸው የሚል አባባል በአንዳንድ አካላት ዘንድ ይነሳል። አባባሉን ሁለት ወገኖች ለተለያየ ሁለት ዓላማ ሲጠቀሙበት ይታያል። አንደኛው የሃሳብ ብዘሃነትን የማቀበል የጠቅላይነት ባህሪ ያለው የሕወሓት አመራር ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ሌላው ሕዝቡን ከፓርቲው ጋር አንድ ላይ የፓርቲውን ህጸጽም፤ ችግርም አንድ ላይ ደርቦ ሕዝቡን የሚፈርጅ ፤ ሕወሓት ሕዝብ ሕዝብም ሕወሓት ነው፤ ትግራይ ሕዋሓት ሕወሓትም ትግራይ ነው ብሎ የሚፈርጅ አለ። በሁለቱም ፍረጃዎች ሕዝቡ አልተጎዳም ወይ? የእርሶ ምልከታ ምንድነው?

አቶ ጌታቸው፦ ሕዝቡ በሁለቱም ፍረጃ ውስጥ በጣም ተጎጂ ሆኗል። የመጀመሪያው የሕወሓት አመራር ስለሆንኩ አመራሩ የፈጠረው ተረት በጣም ምቹ በሆነ መንገድ ሕዝቡን በአንድ አይነት መንገድ ለመግዛት፤ ጠቅላይ የሆነ አስተሳሰብ ብለህ ያነሳኸው በፖለቲካው አስተሳሰብ “ቶታሊታሪያን” የሚባለው ነው።

የሕወሓት አመራር እድር መቆጣጠር ይፈልጋል፤ ማህበር መቆጣጠር ይፈልጋል፤ ቤተክርስቲያን መቆጣጠር ይፈልጋል። መቆጣጠር የማይፈልገው ባህል፤ የሕይወት መስክ የለም። ስለዚህ ይህን ለማድረግ በምታደርገው ጥረት ለይስሙላ ፓርቲዎች እንዲኖሩ እንኳን ብትፈልግም፤ ፓርቲዎች እንኳ ሳይቀር በአንድ ወይም በሌላ መልኩ የሕወሓት አመራር አስተሳሰብ ተጽእኖ ስር ናቸው። ይህንን ለማድረግ የሚጠቀምበት ሚዲያ ተቆጣጠራለህ ፤ ሁሉንም አይነት ተቋም ትቆጣጠራለህ አስተሳሰቡን።

አሁን የትግራይ ሕዝብ የገጠመው ጣጣ ምንድ ነው ሕወሓትን የራሴ ድርጅት ነው ብሎ የሚያምን በሚሊዮኖች የሚቆጠር የትግራይ ተወላጅ አለ፤ ነበረ። እንደአደረጃጀት የትግራይን ሕዝብ የተደራጀ ትግል ከመምራት አንፃር ትልቅ አስተዋፅኦ ያደረገው ድርጅት ቢኖር ሕወሓት ነው። የተደራጀ ትግል ከማድረግ አንጻርም ከዚያ በፊት የነበረው ትግል የተበታተነ ነበር። ከዛ አንፃር ይሔን በማድረጉ ድርጅቱ የተደራጀ ትግል ምልክት ( symbol) አድርጎ ከመውሰድ አንፃር የሚሰጠው ድጋፍ አለ። ያ ማለት ግን የሕወሓት አመራር ይህንን እያዛባ (abuse) እያደረገ ሥልጣኑን ለማራዘም ሲጠቀም ነበር። እዚህ ግባ የሚባል ለውጥ አላመጣም።

ያንን የመሰለ የተደራጀ ሕዝብ ይዘህ፤ ያንን የመሰለ ጠንካራ፤ ሥራ ወዳድ ሀገሩን የሚወድ ሕዝብ ይዘህ ትግራይን መድረስ የነበረበት ደረጃ ላይ ከማድረስ ይልቅ በታሪክ አጋጣሚ እጁ ላይ የገቡ አማራጮችን ሥልጣን እና ሥልጣንን ላይ ብቻ የተወሰነ ቡድንን ጥቅም ከማረጋገጥ አንፃር ብቻ እየመዘነ የመጣ አመራር ነው።

አመራር ውስጥ ለሕዝብ፣ ለሀገር ትልቅነት አስተዋፅኦ ያደረጉ መሪዎች ነበሩ። ምንም የሚያጠራጥር ነገር የለውም። እንደዛም ሆኖ ግን መጨረሻ ላይ ወደ ምን ወረደ? ወደ ጠባብ ቡድናዊ ፍላጎት ብቻ ትኩረት ያደረገ፤ የሕዝብ አጀንዳው አጀንዳው ያልሆነ፤ እኔ ያልኩት፤ ምን እንደሚል እንኳ ሳይታወቅ እኔ ያልኩት ብቻ ነው ትክክል የሚል፤ ከእንቅልፍ ባንኖ በተነሳ ቁጥር የሚመጡለት ጉዳዮችን የሕዝብ አጀንዳ እያስመሰለ የሚያደናግር፤ በሕዝብ ስም እየማለ እየተገዘተ ግን የሕዝብን አጀንዳ እና ጉዳይ ወደ ጎን ትቶ የራሱን ጥቅም የሚያሳድድ ሃይል ወደ መሆን ነው የመጣው አመራሩ። ይሔ ዝም ብሎ ውጭ ወጥተህ እገሌ እገሌ ብሎ ለመውቀስ ሳይሆን ሁላችንም ባለፍንበት ሂደት የሕዝበ አጀንዳን ከማስቀደም አንፃር ምን አደረግን? ብለን ማየት ተገቢ ነው የሚሆነው።

ሕወሓት እና ትግራይ አንድ ናቸው። የትግራይ ሕዝብ እና ሕወሓት አንድ ናቸው የሚለውን ማጭበርበሪያ አመራሩ ይጠቀምበታል። አመራሩ የሚጠቀምበት ከስርቆት፤ ከሌሎች በመንግሥት ሥልጣን ላይ ሆነህ ለምትፈፅማቸው በደሎች ተጠያቂ ላለመሆን ፤ የሚሠራቸውን ሥራዎች በሙሉ ከሕዝቡ እና ከሕዝቡ ይሁንታ በመነጨ እንደሚሠራቸው አድርጎ ለማሳመን ይሞክራል።

እውነታው ግን ምንድን ነው? የሚሠርቅ ባለሥልጣን እና የሚሰርቅ አመራር በሕዝብ ስም ሲምል እና ሲገዘት፤ ድርጅቴ ሕወሓት እና ሕዝቡ አንድ ነው ማለትም አንድ ነገር ነው። አመራሩ ራሱን የሕዝብ ወኪልም አድርጎ፤ ሕዝብንም እንዲሰግድለት አድርጎ፤ ሕዝብ አንድም ዓይነት የተቃውሞ ምልክት እንዳያሰማ አፍኖ፤ የስርቆት አጀንዳ ውስጥም በደም ተነክሮ ግን ደግሞ ሕወሓት እና ሕዝብ አንድ ስለሆንን ብሎ በዛ ማጭበርበሪያ ራሱን ነፃ ለማድረግ የሚሞክርበት ሁኔታ አለ። ይሄን አይነት አካሄድ ደግሞ በሥነፅሁፍ (lierature) ላይ ጆርጅ ኦርዌል የሚባል እንግሊዛዊ እንዳስቀመጠው፣ ከአንተ የተለየ እሳቤ እንዳይኖር (የተለየ ነገር እንዳታስብ) የሚያደርጉ ባህሎችን እርሱ (protective stupidity) የሚለውን አይነት ነው።

እናም የሕወሓት አመራር በመሠረታዊነት (essentially) ዜጎች የሚመስላቸውን ተናግረው እና ድርጅታቸውን ወቅሰው ወደ ትክክለኛ ቦታ የሚመለሱበት ሂደት እንዳይፈጠር ሚዲያን መቆጣጠር ብቻ ሳይሆን፤ ሁሉንም የአስተሳሰብ አደረጃጀቶችን በሙሉ ተቆጣጥሮ በዚህ መልኩ እንድትሰግድ ያደርግሃል። ሰው አሁን ብዙ ጊዜ የትግራይ ወጣት ሕወሓትን መንቀፍ በሚፈልግበት ጊዜ በአማርኛ ቢነቅፍ ብዙ ሰው ቅር ይሰኛል። ምክንያቱም የጓዳ ጉዳይ አድርገህ ነው የምታስቀምጠው።

የሕወሓት አመራር የሚፈልገው ይሔንን ነው። መወቀስ የሚፈልገውን ነገር፤ የትግራይ ተወላጅ መሮት አንገሽግሾት መናገር የሚፈልገውን ጉዳይ በሌላ ቋንቋ አትገልፅም ብቻ ሳይሆን፤ ወጣ ብለህ እንዳትጮህ የሚከለክል ሥርዓት ነው መትከል የሚፈልገው። ይሔ አደገኛ ነው። ከዚህ አንፃር በአንደኛው መንገድ የትግራይ ሕዝብ በእንደዚህ ዓይነቱ ፍረጃ ተጎጂ ነው።

በሁለተኛ ደረጃ ሰነፍ አስተሳሰብ የተጠናወተው ብዙ አለ። አንደኛ ደረጃ የትግራይ ሕዝብ በትግሉ ጥግ ያስያዛቸው አስተሳሰቦች አሉ። እውነት ለመናገር በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በተደራጀ ጦርነት ( resistance) ለውጥ የማምጣት ሂደት ውስጥ ትልቅ አስተዋፅኦ ያደረገ ሕዝብ ነው። በዚህ አጋጣሚ ከእንጀራቸው የተፈናቀሉ፤ ከሥልጣናቸው የተፈናቀሉ ወገኖች፣ ሃይሎች ፤ ሕዝብ በዚህ ደረጃ የሚጎዳ ሕዝብ የለም። የትግራይን ሕዝብ እንደ መሠረታዊ የችግራቸው ምንጭ አድርገው የሚቆጥሩ አሉ።

እነዚህ ሰነፍ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች ሕወሓት ወይም የሕወሓት አመራር ላይ ያላቸውን ችግር ( issue) ምክንያቱም ጥናት ይጠይቃል። ይሔን ለያይተህ ተንትነህ የሕወሓት አመራር ይህንን አደረገ የሕወሓት አባል ሳይሆን የሕወሓት ከፍተኛ አመራር ነው ብለህ መተንተን ትንሽ ጥረት የሚጠይቅ ስለሆነ እና ሰነፎችም ስለሆኑ ሕወሓትንም የትግራይ ሕዝብንም በአንድ ላይ አጃምለው ፤ ሕወሓትን ወይም የሕወሓት አመራርን ለማጥፋት ያላቸውን አጀንዳ የትግራይን ሕዝብ ከማጥፋት አጀንዳ ጋር አንድ ላይ አያይዘው ነው የሚንቀሳቀሱት። እንደዚህ ዓይነት ሰነፍ በጣም አደገኛ አስተሳሰብ እኩል የትግራይን ሕዝብ ለአደጋ ዳርጎታል።

የምናያቸው አጋጣሚዎች በሙሉ በተወሰነ ደረጃ ስርቆት ውስጥ የተሠማራ ሰው ሊኖር ይችላል። በተወሰነ ደረጃ ባለሥልጣን ሆኖ በደል የፈፀመ ሊሆን ይችላል። በልኩ ከመውሰድ ይልቅ፤ ሕዝብን እንደሕዝብ እየፈረጅክ ሕዝብ የኢትዮጵያ አካል ሳይሆን የኢትዮጵያ ችግር እንደሆነ ተደርጎ እንዲታሰብ በማድረግ በትግራይ ሕዝብ ላይ የደረሰ በደል እንዲፈጠር ትልቅ አስተዋፅኦ ያደረገ ፍረጃ ነው።

ሁለቱም ፍረጃዎች ከማንም ይምጣ ከማን የሕወሓት አመራር ያካሔደውም ሆነ ሌላው ይሔ ሰነፍ ይፈርጀው አሁንም የትግራይን ሕዝብ ተጎጂ የሚየደርግ ነው። ስለዚህ በሁለቱም መልኩ የትግራይ ሕዝብ የፖለቲካ ዕውነታ ( consciousness) ሁሉንም ሃሳቦች ማስተናገድ በሚችልበት ደረጃ እንደአዲስ መቀረፅ መቻል አለበት። ከሕወሓት አመራር ውጪ (beyond) ማሰብ መቻል አለበት።

ሕወሓት ራሱ ቀጣይነት እንዲኖረው ከተፈለገ እኔ ብቻ አውቅልሃለሁ ከሚል ያረጀ አስተሳሰብ ወጥቶ ወጣት ማስተናገድ የሚችል፤ የተለያዩ ጥያቄዎችን መመለስ እንደሚገባው የሚያምን የተለያዩ ሃሳቦችን ማስተናገድ እንደሚገባው በሚያምን አመራር መቀየር መቻል አለበት። ይህንን ባላደረክበት ሁኔታ አሁንም በተለመደው መንገድ ድሮ ጥቂት ሰዎች ፤እነገሌ እኮ ዓይናቸውን ጨፍነው 30 ዓመት ያሰባሉ ፤ አርባ ዓመት ወደ ፊት ያያሉ የሚባል ተረት አክትሟል።

እኔ ባለሁበት የህወሓት አመራር የየሳምንቱን መተንበይ አቅቶን፤ ሕዝብ ጦርነት ውስጥ ከገባ በኋላ በመስዋትነቱ የፈለገውን ርቀት ሊሔድ ይችል የነበረን አደጋ ቀልብሶ ወደ ሰላም ከመጣን በኋላ በየሳምንት የሚቀያየር፣ በየሳምንቱ አጋጣሚዎችን እያየ ልጠቀም የሚል አደገኛ አመራር እየሠጠን፤ ሰላሙንም ተጠቃሚ እንዳይሆን ፤የልማትም ተጠቃሚ እንዳይሆን ህልውናውንም አደገኛ ሁኔታ ላይ ከመፍጠር አንፃር ትልቅ አስተዋፅኦ ያደረገ አመራር ነው።

ይሔ አመራር አሁንም እኔ ነኝ የማውቅልህ ብሎ ሊቀጥል ይፈልጋል። እርሱ ሊሆን አይችልም። ከአሁን በኋላ ማጭበርበር አይቻልም። እኔ ቢያንስ ንሰሃ ገብቻለሁ። ይሔንን ወጣት እያጭበረበርኩ መኖር የምችልበት ጊዜ አክትሟል የሚል እምነት አለኝ። ከመጀመሪያው ይሔን አስብ ነበር። ከዛ በፊት የእዛ አመራር አካል ሆኜ ያጠፋሁዋቸውን ጥፋቶች ሃላፊነት ለመውሰድ ዝግጁ ነኝ።

ይሔ አመራር ግን ጦርነት ውስጥ ገብተን ያ ሁሉ ጣጣ ከተፈጠረ በኋላ፤ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ሰው ካለቀ በኋላ የሰላም አጋጣሚን ተጠቅሞ ሰላሙ በመስዋትነታችን የመጣ ነው። ሰላማችንን ማስጠበቅ መቻል አለብን፤ ሰላማችንን ለማስጠበቅ በየጊዜው መሞት የለብንም፤ በሕይወት ኖረን ሕዝባችንን ማገልገል የምንችልበትን ሁኔታ( environment) ተፈጥሯል። ይህንን እንጠቀም ብለን በወሰንበት ሰዓት ጭምር ስልጣኑን እና ጥቅሙን ብቻ የዘረፋ፤ ኔትወርኩን ማስጠበቅ ብቻ ማዕከል ያደረገ አመራር፤ አሁንም ሰላም ደፍርሶም ቢሆን፤ ሕዝብን ለአደጋ አጋልጬም ቢሆን ሕልውናዬን አስቀጥላለሁ ብሎ ሲፍጨረጨር በተግባር እየታየ ነው።

ይህንን አስተሳሰብ በመያዝ ነገ ከነገ ወዲያ መቀጠል አይቻልም ብቻ ሳይሆን፤ አሁን የትግራይ ወጣት ደርሶበት ባለ የንቃት ደረጃ በፈለግከው መልኩ ምክንያቱም ከእንደዚህ ዓይነት መከራ ሊያወጣህ ብቻ ሳይሆን ወደ ሌላ መከራ ሊያስገባህ የሚችልን አመራር በምን ተዓምር አመራር ብለህ ይዘህ ልትቀጥል የምትችለው? ይህንን ነገር ማስተካከል ባልቻልክበት ሁኔታ ሕወሓትም አንድ ዓመትም መቀጠል አይችልም፤ ሁለት ዓመትም መቀጠል አይችልም።

የሕወሓት ቀጣይነት ፤ሕወሓት ብቻውን አይመራም ብቻ ሳይሆን፤ የፖለቲካ ባህል ምህዳራችን መስፋት አለበት ብቻ ሳይሆን ፤ ሁሉም አስተሳሰቦች መስተናገድ አለባቸው ብቻ ሳይሆን፤ ሕወሓት ይቀጥል እንኳ ከተባለ ሕወሓት ራሱን ባልቀየረበት ሁኔታ ይህ አመራር ከራሱ ጥቅም ከዘረፋ ኔትወርኩ በላይ የሕዝብን አጀንዳ አጀንዳው አድርጎ ለመቀጠል ዝግጁ ባልሆንበት ሁኔታ አንድ አዳር መቆየት የሚችል አይመስለኝም።

የተቀየረ ሁኔታ ነው ያለው። እንዳልኩህ በዚህ ጥቅል ፍረጃ ምክንያት ሕዝባችን ያየውን መከራ በፍፁም መካድ የሚቻል አይሆንም። ለዕከሌ ለዕከሌ የሚተው ጥፋት ብቻም አይደለም። ከላይ ያነሳሁት የኦርዌል ( protective stupidity) አዎ! የራስ ሰው ያጠፋው ጥፋት እና ሌላ ሰው ያጠፋው ጥፋት በሚል ልትፈርጀው አትችልም። ፈፃሚው ማንም ሆነ ማን ሕዝብ ላይ የሚደርስ ማንኛውም ጥፋት፤ ጥፋት ነው። ስለዚህ ሁለቱም ፍረጃዎች የራሳቸው አደገኛ በትር አሳርፈዋል በትግራይ ሕዝብ ላይ የሚል ማየት ጥሩ ነው።

ፋና ቴሌቪዥን፡- በግጭቱ በአመዛኙ የትግራይ ክልል ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፤ በአማራና በአፋር ክልልም እንዲሁ ከባድ ጉዳት ደርሷል። በቅድሚያ እንደሰው፤ ቀጥሎም ደግሞ እንደሀር ተወላጅ በሁሉም ቦታ በደረሰው ጥፋት እንደማዘን መንስኤውን ገምግሞ ለማረም እንደመጣር ለፍትህ ሳይሆን ለቀጣይ ቁርሾ ፣ ለቀጣይ ቂም፣ ለቀጣይ መበቃቀል የመጠቀም አዝማሚያና ፕሮፖጋንዳ በስፋት ይሰማል። ይህ ለተጎጂዎችም፤ ለወደፊት አብሮነትም ያለው አንድምታው ምንድን ነው ይላሉ?

አቶ ጌታቸው፡– አንድ ነገር የጥፋት ፓሪቲ ለማስቀመጥ መሞከር ተገቢ አይደለም፤ ሁሌም። እንዳልከው እንደ ዜጋም በዚህ ጦርነት ውስጥ የራሱን አሉታዊም አወንታዊም ሚና እንደተጫወተ የፖለቲካ አመራር በትግራይ ሕዝብ ላይ የደረሰው በደል የአፋር፤ የአማራ በደል በማነሱ ወይም በመተለቁ ምክንያት መደብዘዝ አለበት ብለን አናምንም። ትልቅ በደል ተፈፅሟል፤ ትልቅ ጥፋት ተፈፅሟል። ስለዚህ የተፈፀመው ጥፋት አማራም ሆነ አፋርም ላይ የተፈፀመ ጥፋት እኩል ነው ሊያሳምመን የሚገባው።

ኢኳሊ ሊያሳምነን ይገባል ማለት ግን ብዙ ጊዜ ግሎሰ ኦቨር የማድረግ ነገር አለ፤ ምንድነው አይ ትግራይ ብቻ እኮ አይደለም የወደመው አማራም እኮ ወድሟል ብለህ ስትናገርና ኖ ጦርነቱ በሁሉም አካባቢዎች ውድመት አስከትሏል ብለህ ስትናገር ያለው ትርጓሜ የተለያየ ነው። ብዙ ጊዜ አንዳንድ መድረኮች ላይ የሚገባን ይህንን ያክል ጥፋት ገጥሞናል ብለህ ስትናገር አንዳንድ የፌደራል ሰዎች አማራም እኮ ጥፋት ተፈፅሟል ይላሉ። አዎ ተፈፅሟል። መፈፀሙን ማመን አለብኝ። መጠየቅ ካለብን እንጠየቅ እንጠየቅ ከሚሉት ሰዎች ውስጥ ነኝ እኔ።

በጠፋው ጥፋት ልክ መጠየቅ ካለብን መጠየቅ አለብን ከሚሉት ውስጥ ነኝ። ሶ እንዳልኩህ ነው ፓሪቲ አቻነት የመፍጠር ጉዳይ ሳይሆን በሁሉም አካባቢዎች የተፈጠረው ጥፋት መሆን አልነበረበትም ነው ብለን ወስደን ትግራይ ውስጥ የተፈጠረው ጥፋት በሚመለከት እኔ እንደትግራይ የሥራ ሃላፊ እነዚህ እነዚህ ጥፋቶች ተፈፅመዋል፤ እነዚህ እነዚህ ጥፋቶች መካስ መቻል አለባቸው፤ ከምንም በላይ ግን ፕሪቶሪያ ላይ የሰላም ስምምነት ስንፈራረም እኮ ያስቀመጥናቸው ነገሮች አሉ። ጥፋትን ለመካስ የሚያስችሉ፤ ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚያስችሉ፤ ሥራዎች እንሥራ ብለን ገብተናል።

እንዳልከው ግን ይሄ የሕወሓት አመራር ጥፋት ብቻ አይደለም፤ በየቦታው ይሄ የደረሰብን፤ እንደዚህ የፈፀሙብን ስለዚህ ነገ ከነገወዲያ እንበቀላለን የሚል አስተሳሰብ በብዙ ቦታ ይታያል። ሀገር በዚህ መልኩ አያድግም። እኔ የትግራይ ሕዝብ የመበቀል ፍላጎት የለውም፤ ይልቁንም በደሉን እውቅና ሰጥተህለት ወደ ሥራ መመለስ ብቻ የሚፈልግ ሕዝብ ነው። የተሰዋለትን ሕዝቦች ቁጥር በየቀኑ እየደጋገመ በተመሳሳይ ቁጥር ካልጨረስኩኝ ፤ ሁለት እጥፍ ካልጨረስኩኝ የሚል ሕዝብ አይደለም።

እዚህ ላይ ማረጋገጥ እችላለሁ። ህልውናውን ማረጋገጥ የሚፈልግ ሕዝብ ነው፤ ህልውናው ላይ የተጋረጠ ማንኛውንም አደጋ መስዋትነት ከፍሎ ለማረጋገጥ ዝግጁ የሆነ ሕዝብ ነው። ግን ደግሞ ከሌሎች ጎረቤቶቹ ጋር ፤ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በሰላም ለመኖር ደግሞ ሙሉ ዝግጁነት ያለው ሕዝብ ነው።

ይህንን ሕዝብ ለመምራት በታሪክ አጋጣሚ እድል የገጠመን ሰዎች ከዚህ አንፃር ምን ሠርተናል የሚለውን ነገር መጠየቅ ተገቢ ነው። ቁርሾን በማባዛት ላይ ነው የተጠመድነው? የበቀል ትርክት በማስቀመጥ ላይ የተጠመድነው? መጠየቅ መቻል አለበት። በዚህ አንፃር ነገ ከነገወዲያ ካልተበቀልን በስተቀር ሰላማችን አይመለስም ብሎ የሚስያብ ሰው አለ ከእኔ ወገንም ፤ ይሄ የሕዝብ አስተሳሰብ አይደለም።

ከሌላው ወገንም አሁንም አጋጣሚውን ተጠቅሞ ፤የትግራይን ሕዝብ መዳከም ግምት ውስጥ አስገብቶ የትግራይን ሕዝብ የጥቃት ሰለባ ከማድረግ ወደኋላ የማይመለስ ሌላም አለ። በአንድ አጋጣሚ ይሄ ሕዝብ ተዳኮሟል፤ ወይ መሬቱን ቆርሰን፤ ወይም ሕዝቡን አሰድደን አንድ ነገር እናደርጋለን የሚል በርካታ ሃይል አለ። ይሄ ከውጭም ከቅርብም እንደዚህ አይነት አስተሳሰብ የሚያራምዱ ወገኖች አሉ።

ዋናው አጀንዳችን መሆን መቻል ያለበት ይህንን ሰላም ማፅናት የምንችለው ለጦርነቱ ምክንያት የሆኑ አለመግባባቶች በሰላምና በሰላም ብቻ ሊፈቱ የሚችሉበትን ምህዳር እንደ አዲስ መመለሳቸውን በማረጋገጥ ነው። ይህንን አድርገህ እንደተባለው ነው የትግራይ ሕዝብ ተበድያለሁ ብሎ ስለሚያምን በብዛት በወጣቱ ዘንድ የሚቀነቀን የተነጣይነት አስተሳሰብ አለ። ይሄ አስተሳሰብ ለምን መጣ ብሎ መፈተሽ ነው ተገቢ የሚሆነው? ይሄ አስተሳሰብ ከፀረ ኢትዮጵያዊነት፣ ይህ አስተሳሰብ ከፀረ አንድነት ወዘተ ከሚሉ ጥቅል ፍረጃዎች ወጥተን ሕዝቡ ለእንደዚህ አይነት አስተሳሰብ ፤ ወጣቱ ለእንደዚህ አይነት አስተሳሰብ ያነሳሱት ምክንያቶች ምንድን ናቸው ብለን መለየትና እነዚህን ለማከም የሚያስችል ሥራ መሥራት ተገቢ ነው። እንደተባለው ሀገር በፈቃደኝነት ብቻ ሳይሆን በጋራ የመልማት ፍላጎትም ላይ መመሥረት መቻል አለበት።

አዲስ አበባ ውስጥ ያለ ደስ የሚል የልማት እንቅስቃሴ ትግራይ ውስጥም ሊደገም እንደሚችል የሚያስይ ከባቢ ካልፈጠርክ በስተቀር ፤ ባህርዳርም ሊደገም እንደሚችል፤ ደብረማርቆስም ሊደግም ፤ በየገጠሩም ሊደገም እንደሚችል ካላሳየህ በስተቀር ሰዎች በሚደረጉት አጓጊ እንቅስቃሴዎች ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉበት ተስፋ ካልፈጠርክ በስተቀር ኢትዮጵያ ሀገሬ የሚል ፍላጎት ስላለው ብቻ ሀገር ሊቀጥል አይችልም።

ስለዚህ እንደሕዝብ የትግራይ ሕዝብ የገጠመው ፈተና ትልቅ ፈተና ነው፤ የደረሰው ጥፋት እጅግ ከፍተኛ ነው። እንደተባለው ሌሎች አካባቢዎች የደረሰው ጥፋትም እኩል መወገዝ መቻል አለበት፤ እንዳይደገም ሁላችንም መጣር መቻል አለብን። አልፈን ሄደን ግን ለሕዝቡ የተበዳይነት፣ የተነጣይነት ስሜት መፈጠር ምክንያት የሆኑ የሚባሉ ነገሮችን አክመን የጋራ ህልም፤ የጋራ ግብ ይዘን መንቀሳቀስ የምንችልበትን ሁኔታ መፍጠር መቻል አለብን።

እንደተባለው ግን የቅያሜ ትርክት ይዞ መቀጠል ሀገር ያጠፋል፤ እንደ ትግራይ እንደሕዝብም የመበቀል ፍላጎት አይደለም ያለው። የመበቀል ፍላጎት አለኝ የሚል ሰው ከራሱ ጥቅም ጋር አያይዞ ሊያስበው የሚችለው ነገር ነው፤ ግን እንደሕዝብ አይደለም። እኔ የመበቀል ፍላጎት የለኝም ስል ምክንያቱም የመበቀል ፍላጎቴን ተግባራዊ ላድርግ ስል የትግራይን ወጣት ጭዳ አድርጌ ነው፤ የትግራይን ወጣት መስዋእት አድርጌ ነው። እሱን ምዕራፍ መዝጋት አለብን።

ለሀገሬ እኖራለሁ የሚል አስተሳሰብ እንዲኖረው የትግራይን ወጣት እናድርገው የሚል ነው የእኔ እምነት። ለሀገሬ እሞታለሁ እያልክ ዘላለም እየፎከርክ የምትቀጥልበት ሁኔታ መኖር የለበትም። ስለዚህ ለእኔ ህልውና፤ ለእኔ ሥልጣን፤ ለእኔ የዘረፋ ኔትወርክ ሲባል በትግራይ ሕዝብ ስም ጦርነት አካሂዳለሁ የሚል አደገኛ አስተሳሰብ በስፋት ስላለ በተወሰነ አመራር ደረጃ የሚንፀባረቅም ቢሆን ገዢ አስተሳሰብ ሆኖ እስከቀጠለ ድረስ ይሄ አደገኛ ነው።

በሌላ አካባቢም ቢሆን ይሄ ጥፋት ደርሶብናልና ይሄን ይሄን መበቀል እንፈልጋለን የሚል አደገኛ ኋላቀር አስተሳሰብ ይዞ እስከቀጠለ ድረስ ሀገር ሊቀጥል አይችልም። ስለዚህ ከዚህ መውጣት መቻል አለብን፤ ከዚህ መውጣጥ አለብን ሲባል ተጠያቂነትን ማረጋገጥ የለብንም ማለት አይደለም። ጌታቸው በአንደበቴ፣ በምላሴ፣ በጠመንጃ፣ በአፈሙዜ ያጠፋሁት ጥፋት ካለ እንደአመራር ለመጠየቅ ዝግጁ መሆን መቻል አለብኝ። ይህንን ማድረግ ማለት የመበቃቀል ትርክትን ማካሄድ ማለት አይደለም። ተጠያቂነት ማረጋገጥ ፍትህን ማረጋገጥ ነው፤ በመሠረታዊነት ማንኛውም በሕግና በሥርዓት የሚመራ ማህበረሰብ ማድረግ ያለበት ጉዳይ ነው።

መጠየቅ ያለብንን እንጠየቅ ማለት የመበቃቀል አጀንዳ እስከጌታ መምጫ ድረስ ይቀጥል ማለት አይደለም። የሕግ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች የሉም ማለት አይደለም፤ ይህንን ፍላጎት ነው ሕዝብ በማያጠፋ መልኩ መገረዝ ያለበት አስተሳሰብ። ይህ አስተሳሰብ አድሬስ መደረግ አለበት።

ፋና ቴሌቪዥን፡- በግጭቱ ወቅት እንደሚያውቁት ከጦርነት ሕግ ውጪ የተፈፀሙ ጥፋቶች እንዳሉ ይታወቃል፤ የደረሱ ከበቂ በላይ የሚሆኑ ጥፋቶች አሉ። የፌዴራል መንግሥት ደረስኩበት ባላቸው ልክ ተጠያቂ ያደረጋቸው የመከላከያ ሠራዊት አባላት እንዳሉ ይገልፃል፤ በሕወሓትና በታጣቂው ዘንድስ ምንም ጥፋት አልጠፋም? ከዚሁ ጋር ተያይዞ የትግራይ ሴቶችን፣ ታጣቂዎችን ጨምሮ፣ የሚታገሉትም ሴቶች ደጋግሞ የደፈሩ የገደሉ የትግራይን አካባቢ ብቻ ሳይሆን ሌላውንም አካባቢ በከፍተኛ ደረጃ ዝርፊያ የፈፀሙ እንዳሉ ይጠቀሳል፤ መጀመሪያ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ ወይ? ከዚሁ ጋር ተያይዞ ተጠያቂነትን ለማስፈን በእናንተስ በኩል ምን ተደረገ?

አቶ ጌታቸው፡- አሁን ትልቅ ጥፋት ነው የተፈፀመው፤ የፌዴራል መንግሥቱ ጥፋት የፈፀሙ ሰዎችን ቀጥቻለሁ ይላል፤ አልሟገትም በዚያ ጉዳይ፤ መቀጣት ያለባቸው መቀጣት መቻል አለባቸው። እንደተባለው የጥፋት አቻነት ማስቀመጥ ተገቢ ባይሆንም በእኛ በኩል የተፈፀሙ ጥፋቶች ካሉ፤ ይኖራሉም፤ መጠየቅ ባለብን ደረጃ መጠየቅ መቻል አለብን የሚል እምነት አለኝ። ታጣቂዎቻችንን በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት ከግንባር ሸሸ ብሎ የረሸነ ይኖራል። በዚያ ደረጃ መጠየቅ መቻል አለብን። መከላከያ በገባባቸው አካባቢዎች የወሰዳቸው የውር ድንብር ርምጃዎች ካሉ፤ አሉም፣ መጠየቅ መቻል አለበት።

ይሄ የመከላከያ ሠራዊት ወይም መከላከያ ሠራዊት ጎን ተሰልፎ የመጣ ሌላ ሃይል የፈፀሟቸው ሁሉም በደሎች ወይ የትግራይ ታጣቂዎች የተለያዩ አካባቢዎች ሄደው የፈፀሟቸው በደሎችን ግልፅ ሆነን መነጋገር መቻል አለብን። አንዱ ሌላውን ብቻ ተጠያቂ እያደረገ የሚሄድበት ሁኔታ መኖር የለበትም። እዚህ ውስጥ ግን የትግራይ ሴቶች ላይ የደረሰው መከራ ግን መቼም ቢሆን በምንም መልኩ ልታካክሰው በጣም የሚከብድ ነው። እንግዲህ የትግራይ ሴቶች የሚደርስባቸው መከራ አንደኛ ልጆቻቸው ወይም በትጥቅ ትግሉ ምክንያት በተደራራቢ ችግር ምክንያት ጉዳት ደርሶባቸው የሚጠፉባቸው ናቸው፤ ባሎቻቸው የሚጎዱባቸው ናቸው፤ እነሱ እንደሴቶች ተፈጥሮ የሰጣቸው ፀጋ መሆኑ ቀርቶ እርግማን ሆኖ የሚደፈሩበት ሁኔታ በስፋት ታይቷል።

እኔ እዚህ ውስጥ ማን ምን አጠፋ የሚባለው ነገር ያው እንደተባለው ነው ለምሳሌ አንድ ሁለት ቀን ገልጬው ይሆናል፤ እስከአሁን ግን ገልጬው አላውቅም ነበር። ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ባደረገው ጥናት ትግራይ ውስጥ የተፈፀሙ የፆታ ጥቃቶች በ 10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች የተደፈሩበት ሁኔታ ጥናት ስናደርግ 76 በመቶ ያህሉን የኤርትራ ሠራዊት ፈጽሞታል ይላል።

76 በመቶውን የኤርትራ ሠራዊት ፈጸመው ማለት 24 በመቶውን የፈጸመው ሌላው ወገን ተጠያቂ አይደለም ማለት አይደለም። አንድ ሰውም አንድ ጥፋትም ካለ ተጠያቂ ነው። ስለዚህ ፌዴራል መንግሥት በ24 በመቶው የሚሆኑት ፋኖ ወዘተ ሁሉም ተንጋግቶ ወደ ትግራይ የመጣ በመሆኑ ትግራይ ውስጥ የፈጸሟቸውን በደሎች ከማጣራት አንጻር የሚሰራው ሥራ ይሰራ ብለን ነበር።

አንድ ነገር ልንገርህ፤ መጀመሪያ አካባቢ በትግራይ ጦርነቱ እንደተከፈተ ከሦስት ሳምንት በኋላ ተበታትነን ነበር። ሠራዊቱም ተበትኖ ፤ እኛም ተበትነን ገጠር በምንገባባቸው አካባቢዎች ዓድዋ አካባቢ አዴ ኦሮ የሚባል ቦታ ብላክ ቦርድ ሰባብረውታል፤ ግን በትግረኛ ምን የሚል ተጽፏል 30 ዓመት ወደኋላ መልሳችሁናል ፤ 40 ዓመት ወደ ኋላ እንመለሳቹኋለን ይላል። የተደራጀ እንቅስቃሴ ይደረግ እንደነበር በየቦታው ስማችን የሚመለከት የሚጻፉ አንዳንድ የሚያስቅ የሚመስሉ ግን የተደራጀ ነገር ትኩረት ያደረገ የሚመስል ነገር ነበር። የትግራይን ሰው እንደ ሰው የማዋረድ ፍላጎት የነበረ አካሄድ እንደነበር መታወቅ መቻል አለበት። ስለዚህ 24 በመቶ ያህሉን የፈጸሙት ኃይሎችም መጠየቅ መቻል አለባቸው።

ይህንን የምገልጸው 76 እና 24 የማወዳደረ ጉዳይ ሳይሆን በትግራይ ሴቶች ላይ የተፈጸመው በደል እውነት ነው። እውነት ነው ብቻ ሳይሆን በደንብ ዓይናችንን አፍጠጠን ልናየው የሚገባ ነገር ነው። ከዚህ እውነታ ጋር ሳንታረቅ ሌላ ነገር ማለባበስ አያስፈልግም። እንፈታዋለን ግን በኤርትራ ሠራዊት ላይ ባደረግነው ጥናት ያረጋገጠነው ታውቆና በተደራጀ መንገድ የትግራይ ሰው የማንበርከክ፣ የትግራይን ሴቶች ቅስም የመስበር እንቅስቃሴ ይደረግ እንደነበር አረጋግጠናል።

ይህ ማለት የመከላከያ ሠራዊትና የፋኖ አባል ሆኖ ወጣቶችን በጅምላ የጨፈጨፈ ሰው የለም ማለት አይደለም፤ እሱም በሚጠየቅበት ደረጃ መጠየቅ አለበት። ልጃገረዶች ፣ ሴቶች፣ ባለትዳሮች የደፈረ የለም ማለት አይደለም፤ እሱም በተጠያቂነቱ ልክ መጠየቅ መቻል አለበት። እኔ እያልኩ ያለሁት ይህ በደል አልተፈጸመም እያልኩ አይደለም። የፈጸመው እርምጃ የሚወሰድባቸው አሉ።

ብዙን ጊዜ የትግራይ ሠራዊት ከፍተኛ አመራሮች ከተወሰኑት ሌቦች በስተቀር ሥርዓት ለማክበር ጥረት የሚያደርጉ ናቸው። ይህ መታወቅ አለበት። ሥርዓት ለማክበር በሚያደርጉት ጥረት አማራ ክልልና አፋር ክልል ላይ የመድፈር ወንጀል የፈጸሙ ሰዎች ላይ ርምጃ የወሰዱ የሠራዊት አመራሮች እንዳሉ አውቃለሁ።

ርምጃ መውሰድ ወይስ ለፍትሐ ማቅረብ ነው ትክክል የሚሆነው የሚለው የተለየ ጉዳይ ሆኖ በእኔ አረዳድ እንደዚህ አይነት በደል ሲፈጽሙ ርምጃ የተወሰደባቸው ታጋዮች እንዳሉ አውቃለሁ። ያ ማለት ባወቅኩት ልክ ብቻ አልቆመም ማለት አይደለም፤ ልዩ ጥፋቶችም ካሉ መመርመር መቻል መጠየቅ መቻል አለባቸው። ለዚህ ደግሞ ዝግጁ መሆን አለብን።

ከዘረፋና ከዘርፋ ውጭ ከበቀል ስሜት ውጭ ሌላ እምነት የሌላቸው የተወሰነ ውስን ቁጥር ያላቸው የሠራዊት አመራሮች አሉ። የራሳችንንም ታጋዮች ሳይቀር እነርሱ 90 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሆነው የሚመሩት ጦርነት ካቅማቸው በላይ ሆኖባቸው ያፈገፈጉ ሰዎችን ሳይቀር የሚረሽኑ ሰዎች አሉ። ይህንን እርግጠኛ ሆኜ እነግርሃለሁ። ይህንን የፈጸሙ ሰዎች እንዳሉ የማውቀውን ያህል በደል ሲፈጸም ደግሞ ርምጃ የወሰዱ ሌሎች አመራሮች አሉ። ሁሉንም በአንድ ሳጥን ውስጥ ማስቀመጥ አይቻልም። ለመጠየቅ ግን ዝግጁ መሆን መቻል አለብን።

አልተፈጸመም ብዬ መከራከር ጥፋት ነው። ስለዚህ እኔ በማውቀም ልክ በትግራይ ሴቶች ላይ የደረሰው መከራ በጣም ግዙፍ ነው። እንዳልኩህ ያቀረብኩልህ  ስታስቲክስ ተራ ስታስቲክስ ሳይሆን እውነት ነው። ስማቸው የሚታወቁ ሴቶች ዋጋ የከፈሉበት ነው፤ ግን ስማቸው የሚታውቁ አዛዦች ወስነውት የተደረገ ነው። በወሳኝ መልኩ እንዳልኩህ አሁን ላይ የኤርትራ ሠራዊት ወገናችን ነው ብለው የሚፎክሩ ሰዎች እሰማለሁ።

ቢያንስ ንሰሃ ይግባ መጀመሪያ ጥፋቱን ይቀበል። በፕሪቶሪያል ስምምነት መሠረት መከላከያ ትግራይ ውስጥ እንዲሰፍር ተስማምተን መጥተናል። ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር ያሉ ጥፋቶች ለመመርመርና ርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ ነን፤ ተጠያቂነት እናረጋግጥ ስንል ፈርመናል። በፈርመነው ልክ ተጠያቂነትን አረጋግጠናል ወይ መታየት ያለበት ጉዳይ ነው። ከተጠያቂነት ጋር ብቻ ሳይሆን ሲስተማቲክ በሆነ መንገድ ሕዝብ እንደ ሕዝብ እንዲንበረከክ ሕዝብ እንደሕዝብ እንዲጠፋ በተለይ ደግሞ ጾታዊ ጥቃት እንደ ጦር መሣሪያ ከመጠቀም አንጻር የተደራጀ ሥራ የሠራን ኃይል ወገኔ ነው ብዬ የምንቀሳቀስበት ምክንያት ሊኖር አይችልም።

ይህንን በደንብ ግምት ውስጥ ማስገባት ተገቢ ነው። ከተጠያቂነት አንጻር ትግራይ ውስጥ የተፈጠረው በደል ሌሎች አካባቢዎች እንደተፈጸመው በደል ሊደበዝዝ አይገባም። ትግራይ ውስጥ ብዙ በደል ስለተፈጸመ ደግሞ ሌሎች አካባቢዎች ምንም አይነት በደል አልተፈጸመም ተብሎ መወሰድ የለበትም።

ፋና ቴሌቪዥን፦ አቶ ጌታቸው እርሶ በተደጋጋሚ ሲሉ የሚደመጠው ነገር አለ። በወርቅ ዘረፋ በሰው ንግድ ኬላ ወጥሮ መዝረፍ በመሬት ወረራ ወዘተ ላይ የተሠማሩ ዋናዋና የታጣቂና የፖለቲካ አመራሮች እንዳሉና ይህም የሰላም ጠንቅ እንደሆነ በግልጽ ወጥተው ደፍረው የተናገሩበት ወቅት አለ። ይሄ እንደተጠበቀ ሆኖ ሁለት ጥያቄዎች ይነሳሉ። አንደኛው በቂ ጥናትና ማስረጃ ካለ ሕዝቡ በስም እንዲያወቃቸው ለምን አልተደረገም?

ሁለተኛው ደግሞ ለምን በሕግ አልተጠየቁም? እንደዚህ የሚታወቁ ከሆነ ይህንን ያህል አምርረው የሚቃወሙት ነገር በተደጋጋሚ ገልጸዋል። እዚህ አካባቢ ያለው ነገር ምንድነው?

አቶ ጌታቸው፦ ቅድም ያልኩህ “ፕሮቴክቲቭ ስቱፒዲቲ ” የመደበቅ አባዜ ፖለቲከኞችን ያጠቃል እንደኔ። እንደእኔ አይነቱን የበደሉ አካል የነበረ በጦርነት ወቅት ግን የተፈጠረውን ጥፋት በሰላም ስምምነት ማክተም አለበት ብቻ ሳይሆን የትግራይ ሕዝብ ካሁን በኋላ ተገዶ ካልሆነ በስተቀር ፈልጎ ወይም በአንድም በሌላ መልኩ በፖለቲካ አመራር ሰበብም ይሁን በሌላ ምክንያት ጦርነት ውስጥ መግባት የለበትም የሚል እምነት ያለኝን ሰው ጭምር እንዲህ አይነት ወንጀሎች እየተፈጸሙ አንድነታችን ጥንካሬ ነው ብለን ስለምናምን የመደበቅ አባዜ ሁላችንም ነበረብን።

አንድነት ኃይል ነው ይባላል። አንድነት ሁልጊዜ ኃይል እንደማይሆን የምታውቀው ለምሳሌ የከሰል እሳት በተጠጋጋ ቁጥር አቅማቸው ይዳከማል፤ እሳት ፍም ባስጠጋጋሁ ቁጥር አንዱ አንዱን ነው የሚያጠፋው። ስለዚህ ሁል ጊዜ አንድነት ኃይል አይደለም። የትግራይ ሕዝብ ከቁጥሩ በላይ አቅም እንዲኖረው ያደረገ ተደራጅቶ የመንቀሳቀስ ባህል ያለው ሕዝብ ነው። ይህንን የመንቀሳቀስ ባህል ለግል ጥቅማቸው ሊጠቀሙበት የሚፈልጉ ኃይሎች ካሉ ግን እነዚህን ከማስወገድ ውጭ የትግራይ ሕዝብ አንድነት ጥንካሬ ሆኖ ሊቀጥል አይችልም። ስለዚህ ከዚህ አንጻር ይሄ አንድነት በሚል ተረት ረዥም ጊዜ ተቃቅፎ የመቀጠል ልክ እንደ ከሰል እርስ በእርስ የምትጠፋፋበትን ሂደት የሚያስቀጥል ሂደት አካል ነበርኩ እኔ።

አንድ ምሳሌ እነግርሃለው ፤ የወርቅ ንግድ ፤ ብዙ ሰው የወርቅ ንግድ የፕሪቶሪያው ስምምነት ከተፈረመ በኋላ የጀመረ የሚመስለው ሰው አለ። ጦርነት ውስጥ በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ እኔ የማምንበትን ትግል ነው የታገልኩት ብዬ ነው የማምነው ፤ በዛ በማምንበት ትግል ውስጥ የትግራይ ሕዝብን አጀንዳ ይዘው የታገሉ ብዙ የጦር መኮንኖች አሉ።

እነሱ ለሠሩት ሥራ ያለኝ ክብር በፍጹም ሊቀንስ አይችልም። ግን ደግሞ ገና ገና ጦርነቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን ይበላ በነበረበት ወቅት ሳይቀር ምሽግ ለመቆፈር ብለን የወሰድነውን እክስካቫተር ወርቅ ለመልቀም ይጠቀሙበት የነበሩ አዛዦችም አሉ። ይህን እናውቃለን። ሲዋሹ በጣም ነው የሚገርሙኝ። እኔ እስካሁን የዋሸሁት ይበቃኛል። እስካሁን የታገስኩት ይበቃኛል። ሰው ሲሸጡ የሚኖሩ ሰዎች አሉ።

ኤርትራዊ መሸጥ ንብረት ነው የሚባለው። ‹‹ንብረት›› አውርደናል፤ አውርዷል ነው የሚባለው። ሰው ታፍንና አውርደናል ነው የሚባለው። ዓላማው የኤርትራን ሠራዊት እናፍርሰው የሚል ነበር በእኛ በኩል። የኤርትራን ሠራዊት ለማፍረስ ግን ሰዎች እንዲመጡ ማድረግ ነው። የኤርትራን ሠራዊት የማፍረስ ዘመቻ ጀምሬያለሁ ብሎ ይህን የሚመራውን ወገን ገንዘብ ያላቸውን ሰዎች ብቻ ነው ማፍረስ የሚችለው ስለዚህ የደሃ ልጅ ወጥሮ ሊዋጋ ይገደዳል።

ከያዝክ በኋላ 27 ወጣት አንድ ቤት ትዘጋና ውጭ ቤተሰብ አላቸው የሚባሉ ሰዎች አካውንት እየተጠየቀ እያንዳንዱ ሰው በትንሹ አራት ሺ ዶላር እንዲያስገባ ተደርጎ 20 ሰው ካፈንክ 80 ሺህ ዶላር ታስገባለህ። በዚህ የውጭ አካውንት ከፍተው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን እየሸጡ እያገቱ ይህ በኤርትራውያን የተጀመረው ወደ ትግራይ ተወላጆችም ዞረ ይህን አመራር የሚሰጡ ከፍተኛ አመራሮች አሉ። ይህን አጥንተን ለሕግ እንዲቀርቡ ሁለት ዓመት ሆኗል። እሱን በኋላ እመጣበታለሁ …

ይህንን የሚመራ የመረጃ ሃላፊ ርምጃ እንዲወሰድበት ወይ ከሥራ እንዲነሳ ብለን ወስነን ስናበቃ ይህን ለማስፈጸም ሃላፊነት የሚሰጣቸው ሰዎች የኔ ሰዎች ናቸው፤ የጸጥታ አመራሮች ናቸው ። የጸጥታ አመራር በባህሪው ጥፋት ያጠፋም ያላጠፋም የመተጋገዝ ባህሪ አለው።

ወርቅ ንግድ ውስጥ የገባ አሁን ለትግራይ ነጻነት አሁንም አስከ መጨረሻው እሰዋለሁ እያለ የሚፎክር ጀነራል አለ። ወርቅ ንግድ ነው ያለኸው ነው መባል ያለበት። እነ ምግበ የሠሩት ጀግንነት የወጣት መስዋእትነት መሠረት አድርጎ የመጣ ጀግንነት ነው። እነዛን ወጣቶች ለስደት በሚዳርግ ደረጃ ወደ ተራ የወርቅ ንግድ ገብተው ሲያበቁ የስርቆት ተግባራቸውን፤ የትግራይ ግዛት አንድነት የማረጋገጥ አድርገው ሲሉት፤ እንደገና ለሌላ መስዋእትነት ይህን ወጣት ሊዳርጉት ሲንቀሳቀሱ ማየት ፤ እነ ሃይለሥላሴ የተዘረፈ ብር ነው ፤ብር ከመንግሥት ከዝና የወጣ ብር በመቶ ሚሊዮን ብር የዘረፉ ሰዎች አሁን በትግራይ ሕዝብ አንድነት ስም የትግራይን ወጣት ከኤርትራም ጋር አብሬ ለማገዶነት እዳርገዋለሁ ብሎ ሲፎክር በጀግንነት ስም ነው የሚለው።

እንዳልኩህ ከልባቸው ሕዝባቸውን ሊያገለግሉ የሚፈልጉ መኮንኖች አሉ ፤ ከልባቸው ሰላም የሚፈልጉ አሉ። እነ ምግበ እና ሃይለሥላሴ በወንጀል ተነክረው ድንገት የሆነ ሰላም ከተፈጠረ አደጋ ውስጥ ተጠያቂ እሆናለሁ ብለው የሚያስቡ ሰዎች ግርግሩ እንዲያልቅ አይፈልጉም ወደዛም ቢሆን እንሄዳለን፤ ዝግጅት ይደረጋል ይሉሃል። የትግራይን ሕዝብ ለሌላ ጦርነት ለመማገድ።

ምን መሰለህ እየታሰበ ያለው፤ የፌዴራል መንግሥት የወደብ አጀንዳ …ወዘተ በሚል ድንገት ውጊያ ይገጥመናል በሚል ስጋት ውጊያው ትግራይ ውስጥ እንዲሆን ለማድረግ የሚያስችል ስትራቴጂ ነው ተቀይሶ ያለው። ይህ የፌዴራል መንግሥቱ ትግራይ ውስጥ ተቀርቅሮ ይዳከማል፤ በትግራይ ሕዝብ ወጣት መስዋዕትነት እንድናለን የሚል አስተሳሰብ የወለደው ነው። ሰላም መፈጠር መቻል አለበት፤ በኢትዮጵያም በኤርትራም መካከል ጦርነት መፈጠር የለበትም፤ የኔ እምነት ነው።

የኤርትራ ሕዝብ ለአደጋ መዳረግ የለበትም፤ የኔ እምነት ነው። ግን መምረጥ ካለብኝ የትግራይ ሕዝብ ድጋሚ የጦር አውድማ የሚሆንበት ሁኔታ ግን እስከ መጨረሻው ድረስ እንዳይሆን እታገላለሁ። ይሄን ለማድረግ በምናደርገው ትግል እንቅፋት የሆኑት ወርቅ ንግድ ላይ የተሠማሩት ዘራፊዎች ናቸው። ግንባር አዛዥ ነኝ ይልሃል፤ የሆነ ነገር ያወራል። ወርቅ ሲዘርፍ ነው የሚውለው፤ 2014 ነው የምነግርህ።

2014 ወጣቶች በየግንባሩ በሚተናነቁበት ሰዓት፤ ቀላል ምሳሌ ልንገርህ፤ ዳባት፣ ደባርቅ አካባቢ ሊማሊሞ ውጊያ ይመራ የነበረ ሰው፤ ሩቅ ርቀት ሆኖ ውጊያ ይመራ የነበረ ሰው፤ በተመሳሳይ ሰዓት በኤክስካባተር ወርቅ እየቆፈረ ይሸጥ ነበር። ይሄ ኔት ወርክ ነው፤ ይሄ ፖለቲከኛውም አለበት። ጥቂቶች እኮ ናቸው ዘረፋ ውስጥ የገቡት።

ልንገርህ፤ ኮምቦልቻ አካውንት ነበር፤ እኔ አሁን በዚያን ሰዓት በእኛ ውሳኔ ነው፤ ውሳኔው ትክክል ነው ብዬ የማምነው። ገንዘብ ያስፈልገናል፤ ያው ጦርነት እያደረግን ነው። ገንዘብ ያስፈልገናል ተብሎ ባንኮች ውስጥ የነበሩ፤ የግል ባንኮች አንኳን የመንግሥት ግን መውሰድ አለብን የሚል ፖለቲካሊ ወሰንን። እኔ እንደማውቀው አራት ቢሊዮን ነው፤ አካውንት ውስጥ የነበረው፤ ይሄን ማረጋገጥ ትችላለህ ብሄራዊ ባንክ። ምክንያቱም የመጣልኝ ወረቀት አለ ከብሄራዊ ባንክ። የጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ከሆንኩ በኋላ፤ ምን እንደተፈጠረ ባንኮቹ ውስጥ ግልፁልን የሚል ነበር።

አካውንት ውስጥ ያለውን ገንዘብ እንዲሰበስቡ ከተመደቡት ሰዎች መሀል፤ አንደኛው የግንባር አዛዥ የሚባለው ሃይለሥላሴ በቢሊዮን የሚቆጠር፤ ኢንፋክት አንድ ቢሊዮን አካባቢ ነው የወሰደው። እርሱ ስር ተፍ ተፍ የሚሉ የእሱ አገልጋዮች የሆኑ የተወሰነ ድርሻቸውን የወሰዱ አሉ። አብዛኛው ሰውም ትግሉ ለትግራይ ህልውና ካለው ጥቅም አንፃር ብቻ ነው የተሳተፈው። ገንዘብ አገኝበታለሁ ብሎ የተሳተፈ የለም። ስለዚህ ሁሉም አይደለም በአንድ ላይ የሚታየው።

በዚያ ውስጥ ይሄን ያስተባብር የነበረ፤ ሰሞኑን በቁጥጥር ስር እንደዋለ ሰምቻለሁ፤ ውጪ ነው የነበርኩት ሰምቻለሁ። በራሳችን ጥናት፤ እኔ አይደለሁም ያደረኩት ያንን ጥናት ዶክተር ደብረፂዮን በሚመራው ጥናት ይህ ሁሉ ዝርዝር አለ ተቀምጧል። ዝርዝር ተቀምጦ ለምሳሌ ይሄ ሃይለ የሚባለው ሰው፤ እኔ ልንገርህ ሃይለ እንትን ብቻ አይደለም የሚሠራው፤ እኔ በማውቀው በሚገባ ባረጋገጥኩት ሰነድም ጭምር፤ የወርቅ ማሽኖችን ሲያስገቡ ነው የሚውሉት፤ የፖለቲካ አመራሩም የወርቅ፤ እነዚህ የምልህ ሰዎች ከፌዴራል ሰዎች ጋር ይነጋገራሉ። ልንገርህ፤ ሀጢያቱ ብዙ ነው።

የፌዴራል ሰዎች ጋር ማሽን ሲያዝባቸው እናንተን የመሰለ ሰው እኮ የለም እያሉ እየተለማመጡ ማሽን ሊያስለቅቁ ይሞክራሉ። ይሄ ዝርዝር መረጃ ነው ያለኝ። ይህንን የኔ ምከትል ያውቃል፤ የፀጥታ ሃላፊው ጋር ተነጋግረን እርምጃ እንውሰድ፤ ለፍርድ ይቅረቡ፤ የተደረገ ጥናት ነው የምነግርህ። በተደረገው ጥናት እገሌ ይሄን ያክል ይሄን ያክል 300 ሚሊዮን ወስዷል በቁጥጥር ስር ይዋል። ይሄ እገሌ እገሌ ይሄን ያክል ማሽነሪ ወስዷል፤ በቁጥጥር ስር ይዋል የተባለውን ርምጃ እንውስድ ካልን ሁለት ዓመት ሆነን።

የመውሰድ ፍላጎት አንዳንድ ጊዜ ፖለቲካሊ የምታያቸው ነገሮች አሉ፤ ትግል ውስጥ ትልልቅ አስተዋጽኦ ያላቸው ስም ሌሎችንም ይዞ እንዳይጠፋ በሚል ያልነው፤ ቅድም ያልኩህ የውሸት አንድነት ለማስቀጠል ባደረግነው ጥረት፤ መጨረሻ ላይ ግን የውሸት አንድነት ማስቀጠልም አይደለም፤ የመረረኝ ሰዓት ርምጃ መወሰድ አለበት ባልኩበት ሰዓትም ርምጃ እንዲወሰድ ዶክመንት አቅርቤም ሳይቀር ተግባራዊ አልተደረገም።

አሁን ያለው እኔን ክደሃል የሚለኝ አመራር ወንጀለኞቹን ዋናዎቹ የራሱ ሥርዓት አድርጎ ነው የሚቆጥረው። ግንኙነቱ የወንጀል ኔትወርክ ነው፤ የወርቅ ንግድ ውስጥ የሚሳተፈው ጀነራል ዋና የሚተማመንበት መሠረት፤ በግልፅ እኮ ባለፈው ሲናገር ሰምታችሁታል፤ አይ አሁን አሁን የራሳቸን ሰው ስለመጣ ጌታቸውን እንዳደናቀፍነው ማደናቀፍ የለብንም ይላል። ምክንያቱም ጌታቸውን ያደናቅፍ እንደነበር ያውቃል፤ ጌታቸውን የሚያደናቅፍበት ምክንያት የስርቆት ኔትወርኩ አካል ስላልሆንኩ ነው። ሌላ ምክንያት የለም።

እኔ ላይ የሚያገኙት አካውንት የለም፤ እኔ ላይ ሚያገኙት መሬት ካርታ የለም። በዚህ ምክንያት ሁሏም፤ ልንገርህ አንዳንዴ በጣም የሚያሳዝነኝ፤ ፌዴራል ጋር ያላቸውን ጉዳይ፤ መሬት አስመልስልን፤ እንዲህ በልልን ምናምን የሚባል፤ እኔን ሸምግልልን ይሉኛል። ይሄን ሲፎክሩ የምትሰማው ውሸት ነው። ምክንያቱም አብዛኛው የሠራዊት አመራር በሰላም የትግራይ ህልውና እስከተረጋገጠ ድረስ ሌላ ጥይት የመተኮስ ፍላጎት የለውም።

ተገዶ ከገባ ይዋጋል፤ ምንም ጥያቄ የለውም። ተገድዶ ማለት ተጭኖበት ከሆነበት። ከዚህ ውጪ እነዚህ የሚፎክሩት የወርቅ ንግዳቸውን፣ ዘረፋቸውን ለማስቀጠል፤ የዘረፉትን በቁጥር ነው የምነግርህ፤ በቁጥር። እነ ሃይለሥላሴ ሌላ ነገር የለውም። እኔ ውጪ ሀገር ሄድህ ታከም ብዬ በተደጋጋሚ ጠይቄዋለሁ፤ ቪዛ አስርቸለታለሁ አይደለም። የተወሰኑትን ይዥያቸው ወጥቼ አውቃለሁ። እንዲታከሙ። እንዲያርፉ እፈልጋለሁ፤ የከፈሉት መስዋዕትነት ያክል የሚተካ አንድ ነገር፤ ግን አዲስ አበባ መምጣት፤ ንብረት ይሰጣል። መቶ ሚሊዮን ምናምን ሸጫለሁ፤ ይላል። በተግባር የተረጋገጠ። ግን የተዘረፈ ነው የምነግርህ።

ሁሉም የሠራዊት አመራሮች ዘርፈዋል የሚል መልእክት እያስተላለፍን ነው የመጣነው። ውሸት ነው። ሃይለሥላሴን መጥቀስ እያቃተን፤ ሃይለሥላሴን መጠየቅ እያቃተን፤ አንደኛ ፎካሪ ሆኖ እርሱ በተለየ ለትግራይ ሕዝብ የሚቆረቆር ሆኖ እንዲቀርብ እናደርጋለን። ምግበን መጠየቅ እያቃተኝ እርሱ የተለየ የሚቆረቆር ሆኖ፤ ግን በዚህ ጉዳይ ውስጥ ገብቶ የማያውቅ ሌላ ጀነራል ከእነርሱ ጋር ጀነራሎች ወርቅ ንግድ ውስጥ ገብተዋል፤ ወዘተ ይባላል።

ወርቅ ንግድ ውስጥ የገቡትን በይፋ መጠየቅ ስላልቻልን፤ ሁሉም በይፋ ሕዝባቸውን የሚያገለግሉትንም ሰዎች ሳይቀር ጀነራሊ፤ ለምን አላቀረብናቸውም ለተባለው፤ አንደኛ ይሄ ሲያደናቅፍ የኖረው ፖለቲካል ሊደርሺፕ፤ ተጠያቂ እንዲሆኑ አይፈልግም። ተጠያቂ እንዲሆኑ የማይፈልግበት ምክንያት እራሱም ተጠያቂ ስለሆነ ነው።

የወንጀል ኢንተር ፕራይዝ ነው ይሄ። ከትግራይ ሕዝብ ህልውና ጋር የሚያገናኝ ምንም ነገር የለውም፤ እንዳልኩህ ነው፤ አሁን ጌታቸውን ከሥልጣን አስወግደነዋል። ስለዚህ የፌዴራል መንግሥቱም በቃ ወደሌላ ነገር መግባት ስለማይችል ከኤርትራ ጋር ያለውንም ግንኙነት ተጠቅመህ የወርቅ ንግድ ማጧጧፍ፤ ኮንትሮባንድ ማጧጧፍ ነው፤ ዋናው አሁን ፍላጎት ያለው፤ በፖለቲካ ሊደርሽፑም የምትላቸው ጥቂት ሰዎችም ቢሆኑም። ግን ተረታቸው ምንድን ነው ለትግራይ ሕዝብ ህልውና አንዴ ምእራብን እናስመልሳለን አንዴ ደቡብን እናስመልሳለን..ማፈሪያ ነው። ከራስህ ሕዝብ ጋር ተዋግተህ አይደለም የምታስመልሰው ፤ በሰላም የሚያልቅበትን ነገር ሁሉ ማሟጠጥ መቻል አለብን ነው።

በወንጀል የሚጠየቅ ሰው ፤አንዳንዴ ይገርመኛል መስዋእትነት ምናምን ሁሉ ውሸት ነው። ምንም የመስዋእትነት ፍላጎት የላቸውም፤ መሰዋት አይፈልጉም በወጣቱ መስዋእትነት ነው ትርፍ ማትረፍ የሚፈልጉት። በመሠረቱ እንዲጠየቁ ብለን ጥናት ተደርጎ ተረጋግጦ እኔ በመጨረሻ ከስድስት ወር በፊት ለፍትህ ቢሮ እና ለፖሊስ የተወሰኑትን ዶክመንቶች ለጸረሙስና እንዲገቡ አርጌያለሁ። በተግባር ይጠየቃሉ ሌላ ጉዳይ ነው ።

ለምሳሌ በዚህ ጉዳይ ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ የነበረው የሰዎች ዝውውር ላይ መያዝ አለበት ብለን የምናስበው ሰው ወደ ውጪ ሀገር ወጥቷል። ሌሎች አሉ አሁንም ንግዱ ተጧጡፎ እንዲቀጥል፤ ቅድም እንዳልኩህ ነው በዚህ የኤርትራ ሠራዊትን ማፍረስ አይቻልም። ምክንያቱም ገንዘብ ያለው ሰው ብቻ ነው በዚህ ሊወጣ የሚችለው። ወጣቶች ፤ መዋጋት የማይፈልጉ ግን ታፍነው ገንዘብ አውርዱ እንዳይባሉ በዛው ስቃይ ውስጥ መቀጠልን ይመርጣሉ።

የየኤርትራን ሠራዊት እናፈርሳለን በሚል ግን በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች “ሊትራሊ” ተሸጠዋል። ይህ የትግራይ ሰዎችንም ይጨምራል። ሀብት አለው የሚባል ሰው የትግራይ ተወላጆች ሳይቀሩ ፤ አንዳንዴ የሚያደርጉት ምንድነው ገንዘብ የሚቀበሉት ሳያበቃ የትራንስፖርት ሳይቀር ራሳቸው አውቶብስ ተከራይተው የትራንስፖርት ከእያንዳንዱ ሰው አስር አስር ሺህ ብር መቀበል የት አካውንት ፤ መተፋፋር የለም እገሌ የሚባል አካውንት ውስጥ ሊገባ ይችላል። አዲስ አበባ ያለ አካውንት ውስጥ ሊሆን ይችላል፤ ካናዳ ሀገር ያለ አካውንት ውስጥ ሊገባ ይችላል።

ይህ ሁሉ በዝርዝር በምናውቀው ሁኔታ ነው ምንም አይነት ርምጃ ልንወስደው ያልቻልነው ፤ ለምን አንወስድም። እንግዲህ አንድ ሰው ዱላ ይዞ የሆነ ነገር ማድረግ አይችልም። ይህንን ማስፈጸም ሃላፊነት ያለባቸው ሰዎች አሉ። እነርሱ እርስ በእርስ አንዱ አንዱን እየተከላከለ የሚቀጥልበት ቅድም እንዳልኩህ ነው። እማዝነው ትልቅ መሥዋዕትነት መክፈል ብቻ ሳይሆን ሕዝባችን አሁንም ምንም አምስት ሳንቲም ሰባራ ሳንቲም ሳያገኙ እያገለገሉ ያሉ ሰዎች ሳይቀር እንደ ጥፋተኞች እንደ ከዳተኞች የሚቆጠሩበት ኢንቫይሮመንት ከመፍጠር ጋር በተያያዘ እኔ ጥፋት ፈጽሜያለሁ እላለሁ።

ኃይለሥላሴ ነው የሰረቀው ብዬ መናገር ስችል ጠቅላላ የሠራዊት አመራር ተጠርጣሪ የሚሆንበት ሁኔታ ከመፍጠር አንጻር ምግበ ነው የሰረቀው ማለት ፤ ተወልደ ነው ይህንን ያደረገው ማለት ስንችል ይህንን ባለማለታችን ምክንያት ሁሉም የትግራይ የጦር የጸጥታ አመራር ተጠርጣሪ የሚሆንበትን ኢንቫሮመንት ከመፍጠር አንጻር የራሴ አስተዋጽኦ አድርጌያለው እላለሁ። ግን ደግሞ የእኔ አቅም ሊምትድ ነች። እንደ አመራር ይህ ይህ ጥፋት ተፈጽሟል ይህ ይህ ርምጃ ይወሰድ ብለህ ትዕዛዝ ትሰጣለህ።

እንደተባለው ዱላ ይዤ እገሌን እገሌን ብዬ መቼስ አርጩሜ ይዤ እንትን የምልበት ሁኔታ የለም። ስለዚህም መዋቅሩ ፖለቲካ አመራሩ የሚባለው አሁን ሥልጣን ጠቅልዬ ይዤያለሁ ብሎ የሚያስበው አመራር ይህንን የወንጀል መዋቅር “የክራይም ኔትወርክ” ማስቀጠል ነው የሚፈልገው። አሁን ከፋኖ ጋር አብሬ፤ ከእገሌ ጋር አብሬ የሚል ፉከራ ትሰማለህ። ያችን የክራይም ኔትወርክ ለማስቀጠል እንጂ የፋኖ አጀንዳ ከትግራይ ሕዝብ አጀንዳ ጋር ምን ያህል ይገናኛል ብሎ ተንትኖ አይደለም። ውሸት ነው።

እውነት ለመናገር የኤርትራ መንግሥትና ፋኖ ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር ግጭት ውስጥ የገቡት ትግራይ ላይ የተጀመረው ጦርነት በፕሪቶሪያል ስምምነቱ ጋብ ስላለ ነው። ስለዚህም የተጀመረውን ዘመቻ ማጠናቀቅ አልቻልንም የሚል ነው። ይኸም በይፋ የተነገረ ነው።

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ እኮ “ተሆሊፍና” ይህ ሰውዬ አደናቀፈን ፤ ዘመቻችንን እስከ መጨረሻው መቀሌ ተገብቶ የትግራይ ሕዝብ ወደ ሁሉም ዓለማት ተበትኖ፤ የሚሞተው ሞቶ ትግራይ የሚባል ኢንትቲ የሚጠፋበት ሁኔታ አጀንዳ ይዞ የመጣ ኃይል ፤አሁን ከዚህ ኃይል ጋር መሠረታዊ የሆነ ስምምነት ፈጥረህ የትግራይን ሕዝብ ጥቅም ማረጋገጥን ማዕከል አድርገህ ነው መንቀሳቀስ ያለብህ።

የትግራይን ሕዝብ ብሔራዊ ጥቅም ማዕከል ካደረግህ ቢያንስ ቢያንስ ከፌዴራል መንግሥት ጋር የጀመርከውን አሟጠህ ለመጨረስ ነው መንቀሳቀስ ያለብህ። ከሌላ ኃይል ጋር አይደለም የምትሠራው። ቢያንስ የሚታወቅ ስምምነት አለ ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር ፤ የኢትዮጵያ አካል ነህ ግን ደግሞ ዓለም የሚያውቀው ስምምነት ፈጽመሃል። ይሄ ኃይል ግን ጓደኛዬ ይለኛል የብርሃን ልጆች በብርሃን ነው የሚንቀሳቀሱት። በጨለማ መንቀሳቀስ የሚፈልግ ኃይል ብርሃን ከበራ በጣም ይጨንቀዋል።

ሰላም ለእንደነዚህ አይነት ሰዎች፤ ለእንደነዚህ ክሪሚናል ኢንተርፕራዝ አደጋ ነው የሚሆነው። የማጋለጫ ብርሃን ነው የሚሆነው። ስለዚህ ግር ግር በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ከመፍጠር ውጪ ሌላ ሥራ አለን ብሎ የማያምን ፤ ጥቂት ሰዎች እንደፈለጋቸው የሚዘውሩት ግን አብዛኛው ቅን ኃይል ሆስቴጅ የሆነበት ሁኔታ ነው ያለው። የፖለቲካ አመራር ውስጥ ሁሉም አይደለም፤ ጥቂት ሰዎች ናቸው ይህንን የወንጀል ኔትወርክ እስከ መጨረሻው ማስቀጠል የሚፈልጉት።

በቃ ሀገሬ ነጻ ወጥቷል ተብሎ የወርቅ ማሽን እያስገቡ ነው። እንዳልኩህ ነው እኔ እንኳን በማውቀው ልክ ማሽኖችን አስዤያለሁ። ስልክ ሲደዋወሉ በነበረኝ መረጃ መሠረት የገሌ ማሽን የገሌ ማሽን እነዚህ ሰዎች እኮ ናቸው ሲፎክሩ የምንሰማቸው ማሽን ሲያስገቡ ፌዴራል መንግሥት የሆነ አካል ጋር ደውለው የሆነ እቃ እንደዚህ እንደዚህ ገብቶ አስለቅቁልን ሲሉ አያፍሩም።

በቀጥታ ስልካቸው ነው የሚደውሉት፤ ይህ የምልህ እኔ የትግራይ ሕዝብ ተጨማሪ የጦርነት ሰላባ እንዳይሆን የትግራይ ወጣት ይህንን የወንጀል ኢንተርፕራዝ ማፍረስ ላይ መረባረብ መቻል አለበት። ጥቂት አባላት ነው ያሉት። ግን በትግራይ ሕዝብ ስም ስለሚምሉና ስለሚገዘቴ ከምንም ነገር በላይም ቅድም እንዳልከው የትግራይ ሕዝብ ከሕልውናው ጋር በተያያዘ ሕወሓትና ሕወሓት ነው መፍትሄው የሚል ትርክት ፈጥረው ብዙ ስላደናገሩ ብዙ ነው የሚመስሉት ፤ግን ጥቂት ናቸው።

አብዛኛው የትግራይ አመራር ሰላሙን ይፈልጋል ብቻ ሳይሆን ስርቆት ውስጥ የለም። ስርቆት ውስጥ የገቡት ጥቂት ሰዎች ግን ሆስቴጅ አድርገውታል ሁሉንም። እኛም ራሳችን መጠየቅ ያለባቸው እገሌ እገሌ ብለን እንደመጠየቅ፤ ልንገርህ የመጀመሪያ ጥናት ስናደርግ የሕወሓት ሊቀመንበር ሰባት ሰዎች ነን በዚሁ ጉዳይ ላይ የምንወያየው። ይህ ነገር ዝርዝር ባናየው። ምክንያቱም ትልልቅ የጦር መሪዎች እዚህ ዘርፍ ውስጥ ስለተገኙ ጉዳችን እንዳይወጣ ብለናል። እኔም ራሴ የምር ተስማማሁበት።

ኋላ ፕሬዚዳንት ከሆንኩ በኋላ አትሊስት ምስጢሩን ማወቅ አለብኝ። ይቅረብልኝ ወረቀቱ አልኩና እንደተቀበልኩ ያየሁት አሁን በቁጥጥር ስር ውለዋል የተባሉት ሰውዬ ሰኔ 14 ቀን 2014 ዓ.ም ነው ዶክመንቱን የተወያየንበት። ጀነራል በሆነ መንገድ፤ ዝርዝሩን አላየንም። ምክንያቱም ሊቀመንበሩ ምን አሉ ዝርዝሩን ብናይ ትልልቅ ሰዎች እዚህ ውስጥ ኢንፕልኬት ይሆናሉ። ይህ ሰኔ 14 ቀን 2014 ዓ.ም የሆነውን ነው የምነግርህ።

ሐምሌ 14 ቀን 2014 ዓ.ም ሌሎች ሰዎች ብዙ ፖለቲካ ልዩነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ እንደ ፈለጌ የማያዜዋቸው ሰዎች የሆነ ወንጀል ፈጽመዋል ብለው በሙስና ወንጀል እንዲያዙ ተደረገ። ስለዚህ በሕጉና በተደረገው ጥናት መሠረት ርምጃ ወሰድን አሉን ሊቀመንበሩ። ትክክል ብዙ አልስማማበትም ነበር በሰዎቹ መታሰር ግን ጥፋት አጥፍተው ከሆነ መጠየቅ አለባቸው ነው የምለው። ከዚያ ወዲያ በሆነ አጋጣሚ ነሐሴ 10 ቀን ወደ ኤክስተርናል አፌር ሄድ ብዙ ጊዜ የእንትን ሥራውን ነው እንጂ የምሠራው የቢሮ ሥራውን የሚሠሩት ሌሎች ሁለት ሰዎች የሚያግዙኝ አሉ።

አንደኛው አምባሳደሩ ስለሆነ ይህ አሁን በቁጥጥር ስር የዋለ የሚባለው ኃይለ ሊባኖስ ከሊቀመንበሩና ከምክትል ሊቀመንበሩ ጋር ተነጋግሬ ውጪ ሀገር እንድሄድ ስለተወሰነ እንግሊዝ እንድገባ ድጋፍ ይጻፍልኝ ብሎ ደብዳቤ ግጥም አድርጎ ጻፈ። አሁን እኔ ኃላፊ መሆኔን አያውቅም። ወደኔ መጣ ደብዳቤው። እኔ ምንም የማውቀው ነገር የለኝም። ምንድነው ያልኩት እኛ አውሮፕላኖችን እናስገባ ስለ ነበረ ከውጪ። ይህ ምስጢር ማንም ሰው መስማት የለበትም።

እንኳን ለአውትሳይደር የፖለቲካ ቢሮ አባላት የምንባለው ፤ ሴንትራል ኮማንድ የምንባለው ሰባት አባላት መሀል ይህንን የተወሰነ ሰው ብቻ እንዲያውቀው ነው ተወስኖ የነበረው። እናም ወረቀት ሲመጣ ወደ ሊቀመንበሬ ጋር ሄድሁ። ምን ነካችሁ እናንተ ለማንም ሰው ነው እንዴ አውሮፕላን ይመጣል ትሄዳላችሁ እያላችሁ የምትወስኑት። ስለዚህ ሰውዬው ከምክትል ሊቀመንበሯ ጋር አላውቅም የጋብቻ ይሁን የሌላ አይነት ግንኙነት ፤ ብቻ የቅርብ ግንኙነት አላቸው። ወይ አላውቅም እንደዚያ ይባላል በኋላ ነው የሰማሁት።

ወረቀቱን ካየሁ በኋላ ነሐሴ 14 ምሽት በመጣ ፍላይት ሱዳን ገብቷል። እኔ ፕሬዚዳንት ከሆንኩ በኋላ መቼ ማለት ነው ሚያዚያ 2015 ላይ ዶክመንቴን ስቀበል ያስደነገጠኝ ያኔ ነው።

ሰኔ 2014 ላይ 300 ሚሊዮን ወስዷል ፤ ከኮንቦልቻ ከመጣ ገንዘብ፤ 300 ሚሊዮን ብር አጉድሏል ስለዚህ በቁጥጥር ሥር ይዋል የተባለ ሰውዬ ነሐሴ 14 ውጪ ሀገር እንዲሄድ ፈቅደውለታል። በምን ምክንያት። ይህንን በሁሉም ስብሰባ አንስተነዋል፤ ለምን እየዋሸን እንቀጥላለን፤ ማንንም አይደለም። ይህንን ስናገር እገሌን ለመውቀስ አይደለም። እንደ ሰረቀ ተጠርጣሪ ነው ተብሎ፤ ተጠርጣሪ ነው ሳይሆን ሰርቋል፤ ተጣርቷል ተብሎ በቁጥጥር ስር ይዋል የተባለ ሰው ነው፤ በቁጥጥር ሥር ይዋል የተባለ ሰው፤ ከሁለት ወር በኋላ ሌሎችን አስረህ እርሱን ወደ ውጪ እንዲወጣ ማድረግ ፤ምክንያቱ ምን አደርጉ ጸረ ሙስና ይህንን፤ አትሊስት ፤ ውጪ ስላለ ክስ በዚህ ላይ መሥርቱ በሌሎቹ ላይ መመሥረት እንኳን ባንችል ስል ፤ይህ የክራይም ኔትወርክ ፋይናንስ ኦዲተር የሚባሉ ሰዎችን ሎቦ አድርጎ ተሳስተን ነው እንጂ ተቀብለነው ነበር የሚል ፋይንዲንግ እየሠሩ እያሉ ነው የወጣሁት።

Recommended For You