ስለ ሌሎች የተሰጠ

አስተውሎ ላየው የዓመታት የሕይወት ፈተና በመላ አካሉ ይነበባል። ልብሶቹ ንጹህ ሆነው አያውቁም። የመልካም ጠረን ባለቤት አይደለም። እርሱ ስለሌሎች ደስታና መዝናናት እንጂ ስለራሱ ግዴለሽ ይሉት አይነት ነው። አንዳንዴ ከአስፓልት ዳር ሲተኛ የሞት ያህል እንቅልፍ ይጥለዋል። ዝናብ ጸሀዩ ይወርድበታል፤ ቆሻሻ ጎርፉ ያልፍበታል። ማንም ግን ነገሬ ሳይለው ሰዓታት ያልፋሉ።

መጠጥ ካናወዘው ድካሙ በነቃ ጊዜ ግን ዓላማውን አይዘነጋም። የጠወለገ፣ ፊቱ የጠቆረ ገጽታው ድንገት ይፈካል፣ አካሉ ይበረታል። ግራቀኙን እያየ አንደበቱን ሲቃኝ አድናቂ ተመልካቹ በአስተውሎት ያየዋል። የማይለወጥ ድምጸት ፣ የማይነጥፍ ችሎታ፣ የማይሰለች ቅላፄ ። ሁሌም የእሱ ድንቅ ሀብቶች ናቸው ።

ብርሃኑ ዓለሙ በአካሉ ላይ የሚስተዋል ጉዳት አለው። በተለይ አንድ እግሩ የዓመታት መለያው እንደሆነ ዓመታትን አብሮት ዘልቋል። ተወልዶ ባደገበት የአምቦ ከተማ እስከ ስምንተኛ ክፍል መማሩን የሚገልጸው ጎልማሳ የውስጡን ስሜት ከእሱ በቀር የሚያውቅለት የለም። እሱ ተጎሳቅሎ ለሌሎች ደስታ ያድራል። እሱ እየከፋው ለሌሎች ፈገግታ ያበራል። በራሱ ዓለም ‹‹ብሬክስ›› ሲል በሰየመው የግል ሙዚቃ ባንድ ወጪ ወራጁን እያዝናና እያስፈገገ የዕለት ገቢውን ያገኛል።

ብርሃኑ አዲስ አበባ መኖር ከጀመረ በርካታ ዓመታት ሆኖታል። መገኛዎቹ በከተማዋ ዋና ዋና ስፍራዎችና ብዙሃን በሚጓጓዙበት አውቶቡሶች ውስጥ ነው። በተፈጥሮ የተቸረው ልዩ ችሎታ በድንቅ ሙዚቃዎቹ ብቻ አይገታም። በቀላሉ መለየት አስኪያቅት የታዋቂ ጋዜጠኞችን ድምጽ ያስመስላል። እንስሳትና የዱር አውሬዎችን ድምጽ ሳይሳሳት ያሰማል።

ብርሃኑ በልጅነቱ በግቢው በርካታ ዶሮዎችን ያረባ ነበር። ይህ አጋጣሚ ታዲያ ልዩ ችሎታውን ፈልጎ እንዲያገኝ እድል ፈጠረለት። በእጁ የሚያድጉ ዶሮዎችን ድምጽ ጠንቅቆ አወቀ። የሴትና አውራ ዶሮዎችን ባህርይ በወጉ ሲረዳ ማንነታቸውን ተዋርሶ እንደእነሱ መሆን ቻለ። የፈረንጆቹን ከአበሾቹ እየነጠለ ድምጻቸውን ማስመሰል ያዘ። ጥረቱ ከሙከራ በላይ ሆኖ አድናቆትን አላበሰው።

የልጅነት ጊዜው ከሙዚቃ ቤቶች ደጃፍ አላራቀውም። አዳዲስ ዘፈኖች ሲወጡ ከግጥም እስከ ቅላጼ ጠንቅቆ ማጥናት ልማዱ ሆነ። በተለያዩ ቋንቋዎች የሚዜሙ ሙዚቃዎች ለብርሃኑ የድንቅ ችሎታው ማሳያዎች መሆናቸው አልቀረም። የሁሉንም ድምጸት ውል ሳይስት በአግባቡ ማስመሰሉን ቻለበት።

ሕይወትና ኑሮው አዲስ አበባ ከሆነ ወዲህ የአካል ጉዳቱ ችግር እንደሌሎች ሮጦ እንዲያድር ዕድል አልቸረውም። አብሮት ያደገው ድንቅ ችሎታው ግን ከውስጡ አልራቀም። በየደረሰበት ሁሉ የሚጠቀምበት፣ ብዙሃንን የሚያስደምምበት መተዳደሪያው ሆነ እንጂ።

ብርሃኑ ከአንገቱ አንጠልሎት የሚዞረው ሳጥን መሳይ ካርቶን በርካቶች በችሎታው ሲደመሙ የእጃቸውን የሚጥሉበት የገንዘብ ማኖሪያው ነው። ከሳንቲም ጀምሮ ዳጎስ እስከሚል ገንዘብ ድረስ ሲጠራቀምበት ይውላል። ይህ ገቢ ለእሱ የዕለት ጉርሱና መተዳደሪያው እንደሆነ ዓመታትን ዘልቋል።

ብርሃኑ ‹‹ብሬክስ›› ሲል በሰየመው የግል ባንዱ በርካቶችን ሲማርክና ሲያዝናና ይውላል። እሱ ይህን ያድርግ እንጂ ችሎታው ብቻውን ለማንነቱ የተረፈ ጸጋ እንዳላኖረለት በድፍረት መናገር ይቻላል። እንዳለመታደል ሆኖ ይህ ድንቅ ችሎታው የሕይወቱን መስመር አንዳች አልቀየረለትም። በርካታ ዓመታትን በተመላለሰባቸው የአዲስ አበባ አውቶቡሶችና ጎዳናዎች ዛሬም ድረስ ታሪኩ አልተለወጠም።

ብርሃኑ ከልጅነት እስከ ዕውቀት በሚታወቅበት ችሎታው ሌሎችን ሲያስደስትና ሲያዝናና ይውላል። ለእሱ ሕይወት የተረፈ ጥቂት እንጥፍጣፊ ተስፋ ግን የውስጥ ምልክቱ መሆን አልቻለም። ይህ አይነቱ ማንነትም የኑሮው መልክ በሌላ የሕይወት ገጽ እንዲገለጥ አስገድዷል።

ዛሬ የእሱ ችሎታ የሚፈጥረው ልዩ ስሜት ለሌሎች ደስታን ያቀብላል። የአፍታ ጨዋታና ፈጠራውም በርካቶችን በአድናቆት ሲያስደምም ይውላል። ማለዳውን ለሌሎች ፈገግታና ሳቅ የሚያውለው ብርሃኑ በሬዲዮና ቴሌቪዥን የሚሰማቸውን ዜናና ማስታወቂያዎች እየቀያየረ ያስደምጣል። እንስሳትና ነፍሳቶችን በሰውኛ እያናገረ መልዕክቶች ያስተላልፋል። የድሮና የዘንድሮ ህጻናትን ድምጽ በለቅሶ ያዋዛል። ይህን ሲያደርግ የማስመሰል አንደበቱን ያለ አንዳች ስብራት በጥንቃቄ አጥንቶ ነው። አስገራሚ ችሎታውን የሚያዩ በርካቶች ታዲያ ሁሌም እጃቸውን በአፋቸው ጭነው በአድናቆት ይደመማሉ።

ብርሃኑ ከትናንት እስከ ዛሬ ድንቅ ችሎታው አልደበዘዘም። በየጊዜው ወቅቱን መሠረት አድርጎ መረጃዎችን ለአድናቂዎቹ ያደርሳል። ከእጁ የማትነጠለው አሮጌ ሬዲዮኑም ለየዕለት ስኬቱ እገዛዋ የላቀ ነው። ብርሃኑ አድናቂዎቹ የት እንደሚገኙ ጠንቅቆ ያውቃል። የሁልጊዜ ምርጫው በሆነው የከተማ አውቶቡስም ሾፌሮችና ትኬት ቆራጮች በሚገባ ያውቁታል።

የከተማ አውቶቡስ ማለት ለብርሃኑ የውስጡ ስሜቱ መተንፈሻ ፣ የችሎታው ማሳያ ና የዕለት ጉርሱ ማስገኛ ነው። ሁሌም ለዓላማው ። ወደ ውስጥ ሲዘልቅ ተጠቃሚውን ጨምሮ ሠራተኞቹ ፊት አያጠቁሩበትም። ጉዳተኛ እግሩን የሚያዩ አንዳንዶች አገባቡ ለልመና ቢመስላቸውም ቆይተው ችሎታውን ሲያዩ አድናቆትን ይቸሩታል። በተደሰቱበት ቆይታ እንደምስጋና በሚቸሩት ገንዘብ ቅር አይሰኙም።

ብርሃኑ ከእጇ ላይ የተቀነጠሰችውን ዕድሜ ጠገብ ማይክ/መነጋገሪያ/ ቢጤ ይዞ ብቅ ሲል የአብዛኞቹ ገጽታ በፈገግታ ይዋዛል። ውስጣቸውም በደስታ ዘና ይላል። ጥቂት አይሏቸው ተመልካቾች ደግሞ ለብርሃኑ አርቀው አሳቢዎች ናቸው። ድንቅ ችሎታውን ሲያዩ መልካሙን ሁሉ ይመኙለታል። ዛሬን ከቆመበት ጠርዝ አሻግረው ነገውን በበጎ ያልሙታል።

ብርሃኑም ቢሆን በማንነቱ ተስፋ አይቆርጥም። በየቀኑ በአዳዲስ መረጃዎች፣ ችሎታውን እያሳደገ ከተመልካቾቹ መሃል ይከሰታል። ስለሰዎች ደስታ የተፈጠረው ይህ ብርቱ ሰው አንዳንዴ የሚገኝበትን ስፍራ ላስተዋለ እንደሰው ልብን መስበሩ አይቀርም። መጠጥ ባዳከመው ጊዜ ከአስፓልት ዳርቻ ወድቆ ጊዜውን ያሳልፋል።

መጠጥ ክብርን ያስጥላል። ማንነትን ያወርዳል። ከዕውቀት ችሎታ አጣልቶ የውስጥ አቅምን ይነጥቃል። ብርሃኑ ከመጠጥ ሲወዳጅ ምናልባትም ራሱን ለመርሳት፣ ውሎውን ለመዘንጋት ይሆናል። ይህን እውነት የሚያውቅ የሚረዳው ራሱ ባለቤቱ ብቻ ነውና።

ባለፈው ዓመት የተካሄደው የፎከስ ኦን አቢሊቲ የአጭር ፊልም ውድድር ግን ብርሃኑን የዘነጋው አይመስልም። ማንነቱና የሕይወት ገጽታው የሳባቸው መልካም ዓይኖች የዚህን ድንቅ ሰው ችሎታ በካሜራ ሌንሶች አስቀርተው የኑሮውን ሀቅ ከነሰንኮፉ ‹‹እነሆ›› ብለውታል።

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You