ኢትዮጵያ በዓመት 500 ሺህ ቶን ማር የማምረት አቅም እንዳላት ተጠቆመ

-ዓለም አቀፍ ዘላቂ የንብ ሀብት ልማት ፎረም በጅማ ከተማ ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ፡– ኢትዮጵያ በዓመት በአማካኝ 500 ሺህ ቶን ማርና 50 ሺህ ቶን የንብ ሰም የማምረት አቅም እንዳላት የግብርና ሚንስቴር አስታወቀ። የዓለም አቀፍ የንብ ቀን እና ሁለተኛው ዓለም አቀፍ ዘላቂ የንብ ሀብት ልማት ፎረም ከግንቦት 12 እስከ 14 ቀን 2017 ዓ.ም በጅማ ከተማ ይካሄዳል።

የግብርና ሚንስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) ትናንት በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በማርና ሰም ምርት ከአፍሪካ በቀዳሚነት ቦታ የምትገኝ ሀገር ናት። በዓመት በአማካኝ 500 ሺህ ቶን ማርና 50 ሺህ ቶን የንብ ሰም የማምረት አቅም አላት።

እንደ ሚንስትር ዴኤታው ገለጻ፤ ለዓለም አቀፍ የንብ ቀንና ለሁለተኛው ዓለም አቀፍ ዘላቂ የንብ ሀብት ልማት ፎረም የእንስሳትን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ሀገራዊ የሌማት ትሩፋት ፕሮግራም ተቀርጾ በመሠራቱ ከፍተኛ እምርታ እየታየ ይገኛል። በሌማት ትሩፋት ፕሮግራም በትኩረት እንዲሠራባቸው ከተለዩ ተግባራቶች አንዱ የንብ ሀብት ልማት ሥራ ነው ብለዋል።

ምቹ ሥነ-ምህዳር፣ ተስማሚ የአየር ንብረት እና ከአንድ ሺህ በላይ የንብ ቀሰም እጽዋቶች መኖራቸው ለማርና ሰም ምርትና ምርታማነት ተጠቃሽ ናቸው ያሉት ፍቅሩ (ዶ/ር)፤ በተጨማሪም ሥራውን የሚደግፉ የመንግሥት አሠራር ሥርዓቶችም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ እያስመዘገበች ባለው እድገት መነሻነት ዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ የግብርና ኮንፍረንሶችን እያስተናገደች እንደምትገኝ ጠቁመው፤ ኢትዮጵያ ባላት የንብ ሀብት ፀጋ እና መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ልዩ ትኩረት ጉባዔውን እንድታዘጋጅ እድል አግኝታለች ነው ያሉት።

የዓለም አቀፍ የንብ ቀንን እና ሁለተኛው ዓለም አቀፍ ዘላቂ የንብ ሀብት ልማት ፎረም ከግንቦት 12 እስከ 14 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ በጅማ ከተማ ይካሄዳል ብለዋል።

ፎረሙን ኢትዮጵያ ከተባበሩት መንግሥታት የምግብና የእርሻ ድርጅት (FAO) ጋር በመተባበር እንደምታዘጋጀው አመልክተው፤ የሀገሪቱን በጎ ገፅታ የማስተዋወቅ፣ ልምዷን በማካፈልና ከሌሎች ሀገሮች ተሞክሮ በመውሰድ በዘርፉ እየተመዘገበ ያለውን እምርታ ይበልጥ ለማጎልበት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

የፌዴራልና የክልሎች የሥራ ኃላፊዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የዓለም እና የሀገራችን የዘርፉ ምሁራን፣ የንብ አናቢዎችን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት በፎረሙ እንደሚሳተፉ ጠቁመው፤ ይህም በዘርፉ ልምድ ለመቅሰም እና የገበያ ትስስር ለመፍጠር ዕድል ይሰጣል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ንብ አናቢዎች እና ከ12 ሚሊዮን በላይ ህብረ ንቦች እንደሚገኙ ጥናቶች ማመላከታቸውን ከሚንስቴሩ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You