ትራምፕ የሶሪያን ማዕቀብ እንደሚያነሱ ቃል ገቡ

ከሳዑዲ ጋር የ 142 ቢሊዮን ዶላር የጦር መሣሪያ ስምምነት የደረሱት ትራምፕ የሶሪያን ማዕቀብ ሊያነሱ መሆኑን ገለጹ። የአሜሪካው ፕሬዚዳንት በሶሪያ ላይ ተጥሎ የቆየውን ማዕቀብ በሙሉ ለማንሳት ቃል ገቡ።

ፕሬዚዳንቱ በሪያድ ባደረጉት ንግግር አሁን ጊዜው ሶሪያ ወደፊት፣ “ወደ ታላቅነት የምትጓዝበት ዕድል” መሆኑን ተናግረዋል። ትራምፕ በመጀመሪያው ቀን የሳዑዲ ዓረቢያ ቆይታቸው 142 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የጦር መሣሪያ ስምምነት የተፈራረሙ ሲሆን፤ እንዲሁም የሳዑዲው ልዑል አንድ ትሪሊዮን ያወጣሉ ያሏቸው ሌሎች ኢንቨስትመንቶችም ላይ ከስምምነት ደርሰዋል።

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሀገራቸው ከሳዑዲ አረቢያ የበለጠ “ሌላ ጠንካራ አጋር” እንደሌላት ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ባለመው የመጀመሪያው የውጭ ሀገር ጉዟቸው ላይ ተናግረዋል። ዶናልድ ትራምፕ በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸውም ሳዑዲ ዓረቢያ የመጀመሪያዋ የውጭ ሀገር ጉዟቸው መዳረሻ ነበረች። የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ከዚህ በኋላ ኳታርን እና የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስን ይጎበኛሉ።

አሜሪካ ለሳዑዲ አረቢያ 142 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የጦር መሣሪያ ሽያጭ ለመፈጸም የተፈራረመች ሲሆን፣ ይህም እንደ ዋይት ሐውስ ገለጻ ዋሺንግተን እስከ ዛሬ ከፈጸመችው ሁሉ ትልቁ “የመከላከያ ትብብር ስምምነት” ነው። በፕሬዚዳንቱ የሪያድ ጉብኝት ወቅት ለዓመታት በእርስ በእርስ ጦርነት በወደመችው ሶሪያ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንደሚነሳ መገለፁ ሌላው ትልቅ ዜና ነው።

በፕሬዚዳንት አህመድ አል ሻራ የተመሩት የሶሪያ አማፂያን የባሻር አል አሳድን መንግሥት ከሥልጣን ያወረዱት በታኅሣሥ ወር ነበር። ፕሬዚዳንት ትራምፕ በሪያድ በተካሄደ የኢንቨስትመንት ፎረም ላይ በሳዑዲ ዓረቢያው አልጋ ወራሽ ልዑል ሞሐመን ቢን ሳልማን ጥያቄ መሠረት ውሳኔ ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል። “ለልዑሉ ምን ማድረግ እችላለሁ” ያሉት ትራምፕ በፎረሙ ላይ የተገኙ እንግዶች በሳቅ አጅበዋቸዋል።

ከአስርት ዓመታት በፊት የተጣለው ማዕቀብ የታለመለትን ዓላማ በሚገባ መምታቱን ተናግረው፣ ነገር ግን አሁን ጊዜው ሀገሪቱ ወደ ፊት የምትሄድበት ነው ብለዋል። ይህ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ውሳኔ ሀገሪቱ ወሳኝ የፖሊሲ ለውጥ ማድረጓን ያሳያል። አሜሪካ በአውሮፓውያኑ 1979 የሶሪያን መንግሥት አሸባሪነትን የሚደግፍ ስትል የፈረጀች ሲሆን በ2004 ደግሞ ማዕቀብ ጥላለች።

እኤአ በ2011 የእርስ በእርስ ጦርነት ሲቀሰቀስ ደግሞ ሶሪያ ተጨማሪ ማዕቀቦች ተጥሎባታል። የሶሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሳድ አል ሺባኒ በኤክስ ገጻቸው ላይ ይህንን የአሜሪካ መንግሥት ውሳኔ ሶሪያን ዳግም ለመገንባት በሚደረገው ጥረት “አዲስ ጅማሮ” እንደሚሆን ተናግረዋል።

የዋይት ሐውስ ባለሥልጣናት ትራምፕ ረቡዕ ዕለት ከሶሪያው ፕሬዚዳንት አል ሻራ ጋር አጭር ቆይታ ለማድረግ መስማማታቸውን ገልጸዋል። ትራምፕ እና የሳዑዲው ልዑል በኃይል፣ በመከላከያ፣ ማዕድን እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ስምምነት ተፈራርመዋል።

ትራምፕ የሶሪያን አዲስ መንግሥት ለመደገፍ የተጣለውን ማዕቀብ ማንሳታቸውን ሲያስታውቁ ይህ ርምጃ የተወሰደው በሞሐመድ ቢን ሳልማን ጥያቄ መሠረት መሆኑ ተገልጿል። አሜሪካ በሶሪያ ላይ ለአስርት ዓመታት ጥላ የቆየችው ማዕቀብ በቀድሞው ፕሬዚዳንት ባሻር አል አሳድ ላይ ጫና ለመፍጠር እና ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳት ለማድረስ በሚል ነበር።

ትራምፕ የሶሪያውን ፕሬዚዳንት አህመድ አል ሻራን ረቡዕ ዕለት ያገኟቸዋል ተብሎ ይጠበቃል። ትራምፕ ከእስራኤል ጋር ያለውን ቀጣናዊ ግንኙነት ለማሻሻል እና ኢራን ላይ ጫና ለመፍጠር ከሳዑዲ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር ይፈልጋሉ።

ሁለቱ ሀገራት የተፈራረሙት ስምምነት የአሜሪካ የአየር እና የሚሳዔል መከላከያ ኩባንያዎችን፣ የአየር ኃይል እና የህዋ፣ የባሕር ኃይል ደህንነት እና የኮሙዩኒኬሽንን እንደሚያካትት ዋይት ሐውስ አስታውቋል።

የሮይተርስ የዜና ወኪል ምንጮች በሁለቱ ሀገራት መካከል በተፈረመው ስምምነት ወቅት ሎክሄድ ኤፍ-35 የተሰኘው የውጊያ አውሮፕላን ተነስቶ የነበረ ቢሆንም በስምምነቱ ውስጥ ስለመካተቱ ግን የታወቀ ነገር የለም ብለዋል።

የሳዑዲው ልዑል በቀጣይ አንድ ወር ውስጥ ሁለቱ ሀገራት የሚፈራረሙትን ስምምነት ጨምሮ አጠቃላይ አንድ ትሪሊዮን ዶላር የሚደርስ ስምምነት መደረጉን ተናግረዋል። ሳዑዲ ዓረቢያ ከአሜሪካ የጦር መሣሪያ ገዢ ደንበኞች መካከል ቀዳሚዋ ናት። ሁለቱ ሀገራት ላለፉት አስርታት ጠንካራ ወዳጅነት የፈጠሩ ሲሆን፤ ሳዑዲ ነዳጅ ስታቀርብ አሜሪካ ደግሞ ጦር መሣሪያ በመሸጥ ግንኙነታቸውን አጠናክረዋል።

ትራምፕ በጉዟቸው በጉዳዩ ላይ ምንም ያላሉ ሲሆን፣ ቢን ሳልማንን “አስደናቂ ሰው” ሲሉ አንቆለጳጵሰዋል። አክለውም “በጣም እንደምንዋደድ አምናለሁ” ብለዋል ትራምፕ።

ትራምፕ በመካከለኛው ምሥራቅ ስላለ ደህንነት ሳይሆን ኢንቨስትመንት ላይ ባተኮረው በዚህ ጉዟቸው ከሪያድ ወደ ኳታር ረቡዕ ዕለት የሚሄዱ ሲሆን ሐሙስ ደግሞ የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስን ይጎበኛሉ። የአሜሪካውን ፕሬዚዳንት በርካታ የሀገሪቱ የንግድ ሰዎች ያጀቧቸው ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል በአስተዳደራቸው ውስጥ ሹመት የተሰጠው የቴስላ ኃላፊ ኤለን መስክ፣ የኦፕን ኤአይ ሳም አትማን፣ የብላክ ሮክ ላሪ ፊንክ እና የብላክስቶን ስቴፈን ስዋርዝማን ይገኙበታል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You