ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ሳምንቱን በውጤት አሳልፈዋል

በሳምንቱ መጨረሻ በርካታ የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድሮች ሲካሄዱ ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም በተሳተፉባቸው የተለያዩ ውድድሮች ውጤታማ ሆነው አሳልፈዋል።

በጎዳና ላይ የሩጫ ውድድሮች ረጅም ዕድሜን ያስቆጠረው የቦስተን ማራቶን ትናንት ከመካሄዱ አስቀድሞ የተከናወነው የ5 ኪሎ ሜትር ውድድር ዘንድሮ ለ15ኛ ጊዜ ሲካሄድ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ገላ ሃምቢሴ አሸናፊ ሆናለች።

ከአሜሪካ ከተሞች መካከል በአትሌቲክስ እውቅ የሆነው ቦስተን 129 ዓመት ካስቆጠረው ዝነኛ የማራቶን ውድድሩ ዋዜማ በተለያዩ ርቀቶች ፉክክሮችን ያስተናግዳል። በእዚህም በርካታ የዓለም ስመጥርና ከዋክብት አትሌቶች ይሳተፋሉ። በእነዚህ የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድሮችም ጤና ላይ ትኩረት ያደረጉ መልዕክቶች ይዞ የሚካሄደው የቦስተን 5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር ላይ የተካፈሉ 9ሺ137 ሯጮች ርቀቱን ማጠናቀቃቸውን የውድድሩ አዘጋጆች አስታውቀዋል።

በእዚህ ርቀት በሴቶች በቀዳሚነት ያጠናቀቀችው አትሌት ደግሞ ወጣቷ ኢትዮጵያዊት አትሌት ገላ ርቀቱን 14:53 በሆነ ሰዓት ማጠናቀቅ ችላለች። የ22 ዓመቷ የመም(ትራክ) ተወዳዳሪ የሆነችው ይህች አትሌት በተያዘው ዓመት ትኩረቷን የጎዳና ላይ ውድድሮች ላይ ያደረገች ሲሆን፤ ከወር በፊት በፈረንሳይ ሊል በተካሄደ የ10 ኪሎ ሜትር ውድድር ላይ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ ይታወሳል። ይኸውም የዘንድሮውን የቦስተን 5 ኪሎ ሜትር ውድድር በድል እንድትወጣ አስችሏታል። ይሁን እንጂ በውድድሩ ቀላል ፉክክር አልገጠማትም። ከኬንያዊቷ አትሌት ግሬስ ሎይባች ጋር ብርቱ ፉክክር አድርጋ በተቀራረበ ልዩነት በሁለት ሰከንዶች ብቻ ቀድማት አሸናፊ ለመሆን ችላለች። ቴይለር ሮይ የተባለችው አሜሪካዊት አትሌትም በተመሳሳይ ሁለት ሰከንዶችን በመዘግየት ሦስተኛ ደረጃ ይዛ አጠናቃለች።

በመካከለኛና ረጅም ርቀት የመም ውድድሮች ተሳትፏቸው ስኬታማ በመሆን የሚታወቁት ኢትዮጵያዊያኑ አትሌቶች ጽጌ ገብረሰላማ እና አትሌት ለምለም ኃይሉ ደግሞ ተከታትለው በመግባት አራተኛና አምስተኛ ደረጃን ይዘው ፈፅመዋል። በእዚሁ ርቀት በወንዶች መካከል በተደረገው ውድድር ኤርትራዊው አትሌት ዳዊት ረዳኢ የእንግሊዝና ኬንያ አትሌቶችን አስከትሎ በመግባት አሸናፊ ሲሆን፤ ኢትዮጵያዊው አትሌት አባቢያ ሲምባሳ አራተኛ ደረጃን ይዟል።

በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች የተካፈሉበት ሌላኛው ውድድር የሻንጋይ ግማሽ ማራቶን ሲሆን፤ በሴቶች አስደናቂ ብቃት የታየበትም ነበር። በማራቶንና ዳይመንድ ሊግ ውድድሮች ይበልጥ የምትታወቀው የቻይናዋ የንግድ ከተማ ሻንጋይ በግማሽ ማራቶንም በዓለም አትሌቲክስ የወርቅ ደረጃ የተሰጠውና ከፍተኛ ፉክክር የሚታይበት ፉክክር ታስተናግዳለች።

15ሺ ሯጮችንና ከሌሎች ዓለማት የተሰባሰቡ በርካታ ኢሊት አትሌቶችን ባሳተፈው የዘንድሮው የሻንጋይ ግማሽ ማራቶን ውድድር በወንዶች ኬንያዊያን አትሌቶች የበላይነት ይዘው አጠናቀዋል። በሴቶች ደግሞ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ፍታው ዘራይ 1ሰዓት ከ06 ደቂቃ ከ36 ሰከንድ በሆነ ሰዓት በቀዳሚነት አጠናቃለች። በድንቅ ብቃት ውድድሩን የፈጸመችው ኢትዮጵያዊቷ አትሌት የቦታውን ክብረወሰን በማሻሻል ጭምር ስታሸንፍ፤ ተፎካካሪዎቿን በአራት ደቂቃዎች ልዩነት ቀድማ መግባትም ችላለች። ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊ አዲሴ ጨቅሉ ደግሞ አራተኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀች አትሌት ሆናለች።

በተመሳሳይ እዚያው ቻይና በተካሄደ ሌላኛው የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድርም ኢትዮጵያዊቷ አትሌት አሸናፊ ሆናለች። ሃርቺንዶ በተሰኘው የማራቶን ውድድር በሴቶች መካከል በነበረው ፉክክር አትሌት ብዙዓለም ጨቅሌ ስታሸንፍ፤ 2ሰዓት ከ30 ደቂቃ ከ33 ሰከንድ ርቀቱን ያጠናቀቀችበት ሰዓት ሆኖ ተመዝግቦላታል። ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ጸሃይ ገብሬ ደግሞ ስድስት ሰከንዶችን በዘገየ ሰዓት ሁለተኛ ደረጃን ልትይዝ ችላለች። በተመሳሳይ በወንዶች በኩል ኢትዮጵያዊው አትሌት ሞላልኝ ፋንታሁን በ2 ሰዓት ከ12 ደቂቃ ከ39 ሰከንድ በሆነ ሰዓት በመሮጥ ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀ አትሌት ሆኗል።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 14 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You