
በ1993ዓ.ም የሲድኒ ኦሊምፒክ የ10ሺ ሜትር ርቀት ጀግናው አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ ማሸነፉን ተከትሎ ከስመጥር የጎዳና ላይ ሩጫዎች መካከል አንዱ የሆነው ግሬት ኖርዝ ራን የግማሽ ማራቶን ውድድር ተሳትፎ ጥያቄ ቀረበለት። አትሌቱ ግን እሺታውን ከማሳወቁ አስቀድሞ ለሩጫው አዘጋጆች ይህን መሰል የጎዳና ላይ ሩጫ በኢትዮጵያ ማካሄድ እንደሚችሉ ጠየቀ። የአትሌቱና የአዘጋጆቹ ንግግር በስምምነት በመጠናቀቁም በቀጣዩ ዓመት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ሩጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ተከናወነ።
የጀግናውን አትሌት ርምጃ የተከተሉ ብዙ ሺዎችም በየዓመቱ የዚህ ሩጫ ተሳታፊዎች በመሆን ኢትዮጵያ የሯጮች ሃገር መሆኗን አስመሰከሩ። የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ በበጎ በማስተዋወቅ ተስተካካይ ያልተገኘለት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ሀገርን አልፎ በአፍሪካ ደረጃ ባለው ዕውቅና ቀዳሚ ሲሆን፤ በዓለም አቀፍ ደግሞ ተወዳጅ ከሆኑት 10 ሩጫዎች መካከል የሚካተት ነው። ለተተኪ አትሌቶች የውድድር ዕድል በመፍጠርና ሺዎች ሩጫን የኑሮ ዘይቤያቸው እንዲያደርጉ ከማስቻልም በላይ የውጪ ዜጎችን ጭምር የሚስብ ግዙፍና ተናፋቂ የጎዳና ሩጫ ነው።
የኢትዮጵያ ኩራት የሆነው ሩጫ በዓለም አትሌቲክስ ሌቭል ባገኘበት ማግስት ደግሞ የብር እዮቤልዩ ለማክበር በቅቷል። በመጪው ዓመት ኅዳር 14 ቀን 2025 ዓ.ም ለሚከናወነው 25ኛ ዓመት የሩጫ መርሐ ግብር ‹‹ሀገርን በ10 ኪሎ ሜትር›› የሚል ሃሳብ ተሰጥቶታል። ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ 55 ሺ ሰዎች በሚሳተፉበት በዚህ ሩጫ ምዝገባ የተጀመረ ሲሆን፤ የመሮጫ ቲሸርት ሽያጩም ሙሉ ለሙሉ በዲጂታል የሚከናወን መሆኑን ይፋ በተደረገበት ወቅት ተጠቁሟል።የሩጫውን 25ኛ ዓመት ተከትሎም እያንዳንዱ 25ኛ ተመዝጋቢ ነፃ የመሮጫ ቲሸርት የሚያስገኝ ዕድል ይሰጠዋል፤ በዚህም 700 ሰዎች የዕድሉ ተጠቃሚ ይሆናሉ።
የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ 10 ኪሎ ሜትር ሩጫ በአዲስ አበባ ከተማ ከሚከናወነው ውድድር ባለፈ በ25 የዓለም ከተሞች ውስጥ በርቀት (በቨርችዋል) የሚሳተፉበትም ይሆናል። ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ 10 ኪሎ ሜትር ሩጫ ከውድድርና መዝናኛነቱ ባለፈ በርካታ ጠቃሚ መልዕክቶች የሚተላለፉበትና የበጎ አድራጎት ሥራዎች የሚከናወንበት መሆኑ ይታወቃል። ከሩጫው የተገኘውን ገቢ በየዓመቱ ከኢፌዴሪ ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በመሆን ለተመረጡ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች በሚሊዮን የሚቆጠር የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል።ይህንን ተከትሎም ሚኒስትሯ ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) የሀገር ኩራት መሆን ለቻለው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ 25ኛ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የአንድነት፣ የጽናትና የቀጣይነት ተምሳሌት የሆነው ሩጫው የይቻላል ምልክትም ነው። ከስፖርቱ ባሻገር ሀገራዊ ጽንሰ ሃሳቦችን በማስተላለፍ፣ ከሀገር አልፎ በጎረቤት ሀገራት አትሌቶችን የሚያሳትፍ፣ የቱሪዝም መስኅብ የሆነ፣ ሰፋፊ ማኅበራዊ ችግሮችን የሚቀርፍ እንዲሁም ማኅበራዊ ኃላፊነቱን የሚወጣ ተቋም ነው።ለዚህም ምስጋና ይገባዋል ሲሉም ገልጸዋል።
በ‹‹ልወቅሽ ኢትዮጵያ›› መርሕ አራት ከተሞች ላይ የሚካሄደው የሩጫ ውድድር አዘጋጅ የሆነው የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሚኒስትር የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አጋር ነው። ስፖርት ቱሪዝም ላይ ትኩረት የሚያደርገው ሚኒስትሩም በመድረኩ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክቱን አስተላልፏል። የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ እንደገና አበበ (ዶ/ር)፤ ከትንሽ ጀምሮ 55ሺ ሯጮችን የሚያሳትፈው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ፤ ሀገሪቷ ዓለም አቀፍ ሁነቶችን የማስተናገድ አቅሟን የሚያሳይ ነው። ስፖርት በተለይም አትሌቲክስ ለኢትዮጵያ ቱሪዝም ትልቅ ዕድል ሲሆን፤ ባላት የአየር ሁኔታና የቦታ አቀማመጥ ታላላቅ የሌላ ሀገራት አትሌቶችንም ሊጋብዝ የሚያስችል ነው። ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ገጽታን ከመገንባት ባለፈ ዓይነተኛ የቱሪዝም መስኅብ በመሆኑ የሚመሰገን ነው።
ለመጀመሪያ ጊዜ ኅዳር 16 ቀን 1994 ዓ.ም በተካሄደው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የጎዳና ላይ ሩጫ አዘጋጁ ጀግናው አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ ተሳታፊ በመሆን በወንዶች አሸናፊ ሊሆን ችሏል።በሴቶች በኩል ደግሞ አንጋፋዋ ምርጥ አትሌት ብርሃኔ አደሬ አሸናፊ ነበረች።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን እሁድ ሐምሌ 13 ቀን 2017 ዓ.ም