የሴቶች “ስኒከር” ጫማ አብዮት

በአውሮፓውያኑ 2014 የዓለማችን ታዋቂ ሞዴሎችና ዲዛይነሮች የተሰበሰቡበት አንድ ትልቅ ፋሽን ትርኢት ተካሂዶ ነበር። በወቅቱ በፋሽን ትርኢቱ የተመልካቾችን ቀልብ ገዝቶ የነበረው ሞዴሎቹ የለበሱት ልብስ አልነበረም። ያደረጉት ጫማ እንጂ።

በፋሽን ትርኢቱ ላይ የታዩት ሁሉም ሞዴሎች ያደረጓቸው ጫማዎች በወቅቱ ከ95 ሺህ ብር በላይ የወጣባቸው ሲሆን፣ ጫማዎቹን ለመስራትም ከ30 ሰዓታት በላይ መፍጀቱ ሌላው አስገራሚ ጉዳይ ነበር።

በሚያስገርም ሁኔታ እነዚህ ጫማዎች ሞዴሎች የሚያደርጓቸው የተለመዱት አይነት “ሂል” ጫማዎች አልነበሩም። በስፋት ለስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ጥቅም ላይ የሚውሉ ‘ስኒከሮች’ን ነበር ሞዴሎቹ ተጫምተው የታዩት።

ይህ ከሆነ ከአስር ዓመታት በላይ የተቆጠሩ ሲሆን የ’ስኒከር’ ተወዳጅነት እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አልመጣም። እንዲያውም ያ አጋጣሚ ሴቶች ከሂል ጫማ ወደ ስኒከር እንዲሳቡ ያደረገ አብዮት ተደርጎ ተቆጥሯል። ከዚያም ወዲህ የሆሊውድ ተዋናዮችና ታዋቂ ሴት ዘፋኞች ሳይቀሩ በትልልቅ ዝግጅቶች ላይ ‘ስኒከር’ አድርገው በብዛት ማየት እየተለመደ መጥቷል።

ታዋቂዋ አሜሪካዊት የቴኒስ ስፖርት ተወዳዳሪ ሴሬና ዊሊያምስ የእንግሊዙ ልዑል ሃሪና ሜጋን ሜርክል ሠርግ ላይ ስኒከር ጫማ አድርጋ ብዙዎችን አስደምማ የነበረ ሲሆን፣ እንደውም ይግረማችሁ ብላ በእራሷ ሠርግ ላይም ስኒከር አድርጋ ተሞሽራለች። ይህም የሴቶች ‘ሂል’ ጫማዎች ፋሽንነት እያበቃላቸው ይሆን? የሚል ጥያቄ በብዙዎች ዘንድ መፍጠሩ አልቀረም።

ከአስርና አስራ አምስት ዓመታት በፊት ትልልቅ ዝግጅቶች ላይ በተለይም ለሴቶች ‘ስኒከር’ ጫማዎችን ማድረግ የማይታሰብ ነበረ። አሁን አሁን ግን ሴቶች ስኒከር ጫማዎች ተጫምተው ትልልቅ መድረኮች ላይ ሳይቀር መታየታቸው ከመለመድም አልፎ እየተዘወተረ ይገኛል።

የአለባበስ ሥርዓትም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተቀየረ መጥቷል። ቀለል ያሉና ለእንቅስቃሴ የሚመቹ ጫማዎች ተመራጭ እየሆኑ መጥተዋል። ወጣቶች ብቻ ሳይሆን ከአርባዎቹ እስከ ስልሳዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሰዎችም ጭምር በእነዚህ ስኒከሮች እየተሳቡ ይገኛሉ።

“ሴቶች ዘነጡ የሚባለው ቆንጆ ቀሚስና ረጅም ሂል ጫማ ሲያደርጉ አልያም ትክክለኛው የሥራ አካባቢ አለባበስ ከሂል ጫማዎች ጋር የተያያዘ ብቻ እንደሆነ ማሰብ እየቀረ መጥቷል” ትላለች የፋሽን ዘጋቢዋ ሞርጋን ለኬይር።

እንደውም ለውጡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተበራከቱ ከመጡት የሴቶች እንቅስቃሴዎች ጋር የተያያዘ ነው ትላለች።

ሂል ጫማዎችን ሆን ተብሎ ሴቶች ቀስ ብለው እንዲንቀሳቀሱ ለማድረግና ለመቆጣጠር ሆን ተብሎ በወንዳዊ ሥርዓት የተቀረጸ ነው ብለው የሚያምኑ ሴቶች ብዙ ናቸው። የ’ስኒከሮች’ እንደዚህ ተወዳጅ መሆን ደግሞ ከዚህ አመለካከት ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል እሙን ነው የሚሉም ጥቂት አይደሉም።

ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ መጽሃፍ ያሳተመችው ሰመር ብሬናን እንደምትለው ‘ሂል’ ጫማዎችና ኃይል ተያያዥ ጉዳዮች ናቸው። ”ሂል ጫማዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ሲተዋወቁ የሚያደርጓቸው ወንዶች ብቻ ነበሩ።” ትላለች።

ጫማዎቹ ለመጀመሪያ ጥቅም ላይ የዋሉት በ16ኛው ክፍለ ዘመን አውሮፓ ውስጥ ሲሆን፣ ፈረስ የሚጋልቡ ወንዶች ብቻ ነበሩ የሚያደርጓቸው።

ፈረንሳይን ከአውሮፓውያኑ 1643 እስከ 1715 ድረስ የመራው ሉዊስ አስራ አራተኛ በየትኛውም ቦታ ሂል ጫማ ነበር የሚያደርገው። ምክንያቱም ጫማው ለምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ስለማይመች ሥራ እንደማይሠራ ማሳያ ተደርጎ ይቆጠርለት ስለነበር ነው።

ነገር ግን አሁንም ድረስ ረጅም ሂል ጫማዎችን አድርጎ በሥራ ገበታ ላይ መገኘት ለሴቶች ተቀባይነት ያለው አለባበስ እንደሆነ የሚያስቡ ብዙዎች ናቸው። በፈረንጆቹ 2016 ትልቅ ድርጅት ውስጥ በእንግዳ ተቀባይነት የምትሠራ አንዲት እንግሊዛዊት ለምን ሂል ጫማ አላደረግሽም በሚል ከሥራዋ ተባርራ ነበር።

ታዋቂው የጣልያን ዲዛይነር ፍራንሴስኮ ሩሶ በ2018 ለሁለቱም ጾታዎች የሚሆን አዲስ የጫማ ዓይነት አስተዋውቋል። ምክንያቱ ደግሞ ሰዎች ስለ ጫማ ሲያስቡ የወንድ የሴት ብሎ ማሰብ ማቆም አለባቸው ብዬ ስለማምን ነው ብሏል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 14 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You