የዘጠኝ ወራት የውጤት አብነቶች እና ቀጣይ ትኩረቶች

እንደ ሀገር ላለፉት ስድስት ዓመታት ከተጓዝንበት መንገድ ትይዩ የሚነገሩም፣ የሚገለጡም አያሌ የለውጥ ተግባራት፤ ተግባራቱን ተከትለው የመጡ ውጤቶች፤ ውጤቶቹን ተከትለው የተገኙ አስቻይ ሁኔታዎች፤ እንዲሁም በአስቻይ ሁኔታዎች አጋዥነት በቀጣይ ሊከወኑ የሚገባቸው የቤት ሥራዎች አሉ። እነዚህ በአንድ ሀገር እና መንግሥት ቁርኝት ኑባሬ ውስጥ የነበሩ፤ አሁንም ያሉና ወደፊትም የሚኖሩ የአንድ ሳንቲም መንታ ገጽታዎች ናቸው፡፡

ከዚህ አኳያ ከሰሞኑ የመንግሥት የዘጠኝ ወራት አጠቃላይ የልማት እና የኢኮኖሚ እድገት ላይ የታዩ አፈጻጸሞች፤ የተገኙ ውጤቶች እና ቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በፕላን ሚንስትሯ ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ቀርቦ ተገምግሟል። ሚንስትሯ የበጀት ዓመቱ የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ሲያቀርቡ በዋናነት ስድስት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ሲሆን፤ እኔም ለዛሬው ነፃ ምልከታዬ እነዚህኑ ነጥቦች ማዕከል ማድረግን መርጫለሁ፡፡

ዓለም አቀፍ አዝማሚያ

ዛሬ ላይ ያለውን ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ አዝማሚያ መገንዘብ ለሀገራችን የእድገትና ልማት ጉዞው እጅጉን ወሳኝ ነው። የቅርብ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት ደግሞ፤ የዚህ ዓመት ጥቅል የዓለም የኢኮኖሚ እድገት ሦስት ነጥብ ሦስት በመቶ እንደሚሆን ይጠበቃል። ተናጥላዊና አህጉዳዊ የኢኮኖሚ እድገት ትንበያዎችም በዚሁ አግባብ የተጠቆሙ ሲሆን፤ በዚህ መሠረትም ያደጉት ሀገራት የአንድ ነጥብ ዘጠኝ በመቶ፤ አሜሪካ ሁለት ነጥብ ሰባት በመቶ፣ አውሮፓ የአንድ በመቶ፣ ቻይና የአራት ነጥብ ስድስት በመቶ እድገት እንደሚያስመዘግቡ ተመላክቷል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ፣ ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት የአራት ነጥብ ሁለት በመቶ ጥቅል የኢኮኖሚ እድገት እንደሚያስመዘግቡ የተተነበየ ሲሆን፤ ይሄም አምና ከተመዘገበው የሦስት ነጥብ ስድስት በመቶ እድገት አንጻር የተሻለ እድገት እንደሆነም መገንዘብ ይቻላል። ኢትዮጵያም ብትሆን የስምንት ነጥብ አራት በመቶ የኢኮኖሚ እድገት እንደሚኖራት ነው ትንበያው ያሳየው፡፡

እነዚህ የእድገት ትንበያ አሃዞች ደግሞ ዝም ብለው የሚቀመጡ አይደለም። ይልቁንም እንደ ዓለምም እንደ አህጉርም፣ እንደ ሀገርም ያሉ የልማት እንቅስቃሴዎችና የእድገት አመላካቾች አንጻር የተቀመጡ ናቸው። የኢትዮጵያ የእድገት አመላካቾችም በዚሁ አግባብ የተቃኙ ናቸው። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገቷን ከማሳካት አኳያ ዓለም አቀፍ፣ አህጉር አቀፍና ሀገራዊ አዝማሚያዎችን በልኩ መዝና የምትጠቀም ሲሆን፤ ይሄም ፈተናዎችን ወደ እድል፣ እድሎችንም ወደ ውጤት በመቀየር ውስጥ የሚገለጥ ይሆናል፡፡

ከዚህ አኳያ አንዱ ሊታሰብ የሚገባው ጉዳይ ዛሬ ላይ የዓለም ሀገራት በተለይ የልማት ትብብራቸውን እየቀነሱ እና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ማስፈጸሚያ አድርገው እየተጠቀሙበት መሆናቸው ነው። ይሄን ለመገንዘብ ደግሞ የተለያዩ ሀገራት (ዛሬ ላይ በአሜሪካ እንደሚታየውም) አደረጃጀታቸውን ጭምር መልሰው እየፈተሹ ያሉበትን እውነት ማጤን ይገባል፡፡

ይሄ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት የሚኖረው አሉታዊ ገጽ እንዳለ ሆኖ፤ ከዚህ በተቃራኒው ግን አዝማሚያውን ተገንዝቦ በራስ አቅም የራስን ጥያቄ መመለስ የሚያስችሉ ሥራዎችን ወደመከወን መግባትን የግድ ይላል። ኢትዮጵያም በዚህ በኩል ፈተናዎችን ወደ እድል ለመቀየር ቀድማ የጀመረቻቸው፤ በኮቪድ እና ሌሎችም የፈተና ጊዜዎችን ማለፍ የቻለችባቸውን ስኬቶችን አስመዝግባለች፡፡

ምክንያቱም፣ የዓለም አቀፉ የትብብር መቀዛቀዝ የሚፈጥረውን ጫና ቀድማ የተገነዘበችው ኢትዮጵያ በግብርናውም፣ በኢንዱስትሪውም በሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራውም፣… ዘርፎች አዲስ የመቻል ምዕራፍ እንድትከፍት አድርጓታል። ፈተናዎችን ለመሻገር ተገድዳ የገባችበት መንገድም ዛሬ ላይ በዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ስም ከሚፈጠሩ የውጭ ፖሊሲ ማስፈጸሚያ አጀንዳዎች ተቀባይነት ራሷን እንድታላቅቅ እድል ሰጥቷታል፡፡

በራስ አቅም ልማትን ከማሳካት አኳያ የዓለም አቀፍ የንግድ እንቅስቃሴም፣ እንደ ዓለም አቀፉ የልማት ትብብር ሁሉ ኢትዮጵያ በልኩ ተገንዝባ ልትጠቀምበት የሚገባ ሌላው አዝማሚያ ሲሆን፤ አሁን ላይ ካለው የንግድና የታክስ ታሪፍን የማናር ጦርነት አኳያ የዓለም አቀፍ የንግድ እድገት በአማካይ የሦስት በመቶ፤ የዓለም አቀፍ ኤክስፖርት እድገት ደግሞ የአራት ነጥብ ስድስት በመቶ እድገት ብቻ እንደሚኖረው ተተንብዮአል፡፡

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ልትጠቀምባቸው የሚገባት አጋጣሚዎች መኖራቸው እሙን ነው። ምክንያቱም፣ የታሪፍና ንግድ ጦርነቱ በኃያላኑ መካከል ያለ ሽኩቻ እንደመሆኑ፤ የኢትዮጵያን ተወዳዳሪነት የሚያሳድግ እንጂ የሚጎዳ አይደለም። ይሁን እንጂ በዓለም አቀፉ የንግድ ሥርዓት ላይ የሚፈጥረው መናጋት እንደመኖሩ በጥንቃቄ ሊታይ የሚገባው ነው። በመሆኑም እድሉንም ለመጠቀም፤ ሥጋቱንም ለመሻገር የሚያስችል ስልት ነድፎ በጥንቃቄ መሥራት ይገባል። ይሄን ማድረግ ከተቻለም ዓለም አቀፉን አዝማሚያ እንደ አመጣጡ ማለፍ እና የተተነበየውን እድገት ማሳካት ይቻላል፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸሞች

እንደ ሀገር በአስር ዓመቱ የተቀመጡ ግቦችን ከማሳካት አኳያ፣ ተከታታይ የሪፎርም ሥራዎች ሲተገበሩ ቆይተዋል። እነዚህ የሪፎርም ተግባራትም የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን ከማረጋገጥ፤ የንግድ እና የኢንቨስትመንት ከባቢን ከማሻሻል፤ የዘርፎችን የማምረት አቅም፣ ምርታማነትና ተወዳዳሪነትን ከማሳደግ፤ እንዲሁም የመንግሥትን የመፈጸም አቅም ከማጎልበት አኳያ የተቃኙ ናቸው። በእነዚህ መነሻነት በየሴክተሩ የተከናወኑ የሪፎርም ተግባራትም በርካታ ውጤቶች አስገኝተዋል፡፡

ለአብነት፣ በተያዘው ዓመት በዘርፎች መካከል ያለው የእድገት እና የተወዳዳሪነት የወል ምጣኔን ብንመለከት ግብርና የስድስት ነጥብ አንድ በመቶ እድገት እንደሚኖረው የሚጠበቅ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ የሰብል ልማት ዘርፉ የስድስት ነጥብ ስድስት በመቶ እና የእንስሳት ሀብት ልማት ዘርፉ የአምስት ነጥብ አራት በመቶ እድገት ይኖራቸዋል። ኢንዱስትሪውም ቢሆን የ12 ነጥብ ስምንት በመቶ እድገት የሚኖረው ሲሆን፤ አምራች ኢንዱስትሪው ደግሞ የ12 በመቶ እድገት ይኖረዋል የሚል ትንበያ ተይዟል።

በተመሳሳይ፣ ኮንስትራክሽን የ12 ነጥብ ሦስት በመቶ፣ አገልግሎት የሰባት ነጥብ አንድ በመቶ፣ የትራንስፖርትና አገልግሎት ዘርፉም የስምንት ነጥብ አምስት በመቶ፣ እንዲሁም የጅምላና ችርቻሮ ንግዱ የስድስት ነጥብ ዘጠኝ በመቶ እድገት እንደሚኖራቸው ተተንብዮአል። የእነዚህ ድምር ውጤት ነው አጠቃላይ ሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገቱ በዓመቱ መጨረሻ ላይ የስምንት ነጥብ አራት በመቶ እንደሚሆን ቅድመ ትንበያ የተቀመጠለት፡፡

ከዚህ በተጓዳኝ በተወሰዱ የሪፎርም ተግባራት ምክንያት፣ ቁጠባ እና ኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ በሀገራዊ እድገቱ ላይ ያደገ ድርሻ እንደሚኖራቸው ተመላክቷል። በዚህም ኢንቨስትመንት የ23ነጥብ ሁለት፣ ቁጠባ ደግሞ የ19ነጥብ አራት በመቶ በአጠቃላይ ሀገር ውስጥ የኢኮኖሚ እድገት ውስጥ ድርሻ እንደሚኖራቸው ይጠበቃል፡፡

ከገቢ አኳያም ከሪፎርም ባሻገር በፖሊሲም፣ በታክስ አስተዳደር ሥርዓትና ሌሎች አሠራሮች በመታገዝ በተሠራ ሥራ የክልሎችም ገቢ ተሻሽሏል፤ የጋራ ገቢም አድጓል። በዚህ መልኩ የመንግሥት ገቢ ማደጉ ደግሞ፣ መንግሥት ለዜጎች የኑሮ ሁኔታ መሻሻል የሚያግዙ አሠራሮችን ዘርግቶ እንዲተገበር፤ የውጭ ምንዛሬ አስተዳደሩም ውጤታማ እንዲሆን አስችሏል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የድጎማ ሥርዓቶችን እውን እንዲያደርግ አቅም ፈጥሮለታል።

ከዚህ አኳያ፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ ለሴፍቲኔት 41 ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር፤ ለማዳበሪያ 62 ቢሊዮን ብር፤ ለመድኃኒት ሦስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር፣ ለደመወዝ 38 ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር፣ ለዘይት ስድስት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር፣ እንዲሁም ለነዳጅ 100 ቢሊዮን (በትሬዠሪ በኩል 60 ቢሊዮን እና በነዳጅ ድርጅት በኩል 40 ቢሊዮን ብር)፣ በድምሩ ከ211 ቢሊዮን ብር በላይ ዜጎችን በተለይም ዝቅተኛ አቅም ያላቸውን የሕብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ማድረግን ታላሚ ያደረገ ድጎማ ተደርጓል።

ይሄ የድጎማ ሥርዓት የበጀት ዓመቱ እስኪጠናቀቅ ወደ 400 ቢሊዮን ብር ገደማ እንደሚደርስ የተመላከተ ሲሆን፤ ሂደቱም ከመንግሥት ገቢ አኳያ እድገት፤ ከወጪ አኳያም ከፍተኛ ሰው ተኮር የድጎማ ሥርዓት የመኖሩ አዝማሚያን አመላካች ነው፡፡

የዚህ አዝማሚያ ተደማሪ አብነት የሚሆነውም በመንግሥት በኩል በበጀት ዓመቱ አንድም የንግድ ብድር ያለመውሰዱ፤ ይልቁንም የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙን ከሚደግፉ አጋር አካላት ጋር በመተባበር የእዳ ሽግሽግ ተጠቃሚ መሆን ተችሏል። በዚህም የእዳ ጫናን መቀነስ እና ያለውን ሀብትም ለሀገራዊ የልማት ሥራዎች ማዋል እንዲቻል እድል ሰጥቷል፡፡

ምክንያቱም ሪፎርሙ የሦስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር የእዳ ሽግሽግ እድል ይዞ መጥቷል። ይሄ የእዳ ሽግሽግ በመገኘቱም በዘንድሮው በጀት ዓመት ለእዳ ይከፈል ከነበረ ሁለት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ዶላር ውስጥ ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚሆን ገንዘብ ለልማት እንዲውል ማድረግ ተችሏል፡፡

በመሆኑም የተሠራው የሪፎርም ሥራ በአንድ በኩል የውጭ እዳችን ከሀገራዊ ጥቅል ምርት አኳያ ያለውን ድርሻ ሪፎርሙ ሲጀመር ከነበረበት የ30 በመቶ፣ እስከ 2016 በጀት ዓመት ባለው ጊዜ ወደ 13 በመቶ ማውረድ ያስቻለ ነው። በሌላ በኩል አጠቃላይ ለሀገራዊ እድገቱ ፋይዳ ያላቸው፤ የዜጎችን የመልማት ጥያቄ መመለስ በሚያስችሉ ማህበራዊም፣ ኢኮኖሚያዊም ፋይዳ ባላቸው ዘርፎች ላይ የፋይናንስ አቅምን የፈጠረ ነው።

መሠረተ ልማት እና ፕሮጀክቶች

የተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች በመሠረተ ልማት እና ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ላይም ከፍ ያለ መሻሻልን አምጥተዋል። ለምሳሌ፣ የትምህርት ዘርፉን መሠረተ ልማት ብንመለከት፤ በመንግሥትም በሕዝብም ተሳትፎ የነባር ትምህርት ቤቶች እድሳትና ደረጃ ማሻሻልን እንዲሁም አዳዲስ ትምህርት ቤቶች መገንባትን ጨምሮ የተከናወኑ በርካታ ተግባራት አሉ፡፡

በዚህም በትምህርት ለትውልድ ኢኒሼቲቭ በሁለት ዓመት ብቻ ወደ 82 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ አምስት ሺህ 904 የቅድመ መደበኛ፣ 832 አንደኛ እና መካከለኛ፣ 712 የሁለተኛ ደረጃ፤ በአጠቃላይ ስድስት ሺህ 815 ትምህርት ቤቶች ተሠርተዋል። ከስድስት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችም በቀን ሁለት ጊዜ በትምህርት ቤቶች ምገባ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡

ሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው መሠረተ ልማቶችም በስፋት የተከናወኑ ሲሆን፤ ከእነዚህ መካከል በተለያዩ ደረጃ እና በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ያሉ ወደ 123 የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች አሉ። በዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ385 ኪሎ ሜትር በላይ የመንገዶች ሥራ ተከናውኗል። የድንጋይ ከሰል፣ የሲሚንቶ እና የብረት ፋብሪካና ፕሮጀክቶችም ተግባራዊ ተደርገዋል፡፡

ከፕሮጀክቶች አኳያም የቀደሙትን ለውጤት ከማብቃትም ሆነ አዳዲስ የተጀመሩትን በተቀመጠላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ የማድረግ ተግባራት ተከናውነዋል። መስከረም ላይ ሪቫን እንደሚቆረጥለት የሚጠበቀው የዓባይ ግድብ አሁናዊ አፈጻጸሙ ከ98 ነጥብ ስድስት በመቶ መሻገሩ አንዱ የዚህ አብነት ሲሆን፤ እስካሁንም ስድስት ዩኒቶች ሥራ የጀመሩበት ነው፡፡

በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ተጠናቅቆ ወደ ሥራ እንደሚገባ የሚጠበቀውና አሁን ላይ አፈጻጸሙ ወደ 71 በመቶ የደረሰው የኮይሻ ኃይል ማመንጫ ግድብም ከዓባይ ፕሮጀክት ቀጥሎ እንደ ሀገር በኃይል ልማትና ተደራሽነት ብሎም ቀጣናዊ ትስስር ረገድ የሚኖረው ሚና ከፍ ያለ ነው። የአይሻ እና የአሰላ የነፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችም ተደማሪ አቅሞች ናቸው። አዲሱ የኤርፖርት ከተማ ግንባታ ፕሮጀክትም በፕሮጀክት ትግበራ ረገድ ሊጠቀስ የሚገባው ታላቅ ጅምር ነው፡፡

የዲጂታል መሠረተ ልማቶች እድገት፤ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ መሠረተ ልማቶች፤ የመንግሥት አገልግሎትና ሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ አሠራር የመሠረተ ልማት አውታሮች፤ የኢንዱስትሪ ልማት እና የአገልግሎት ዘርፍ የመሠረተ ልማትና ፕሮጀክቶች ክንውን፤ የቤት ልማት ግንባታዎች፤ የከተሞች መልሶ ልማትና የኮሪደር ልማቶች፤ የሌማት ቱሩፋት እና ሌሎች ሰው ተኮር ተግባራት፤ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች እና ሌሎችም በዚሁ ረገድ ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው፡፡

አስቻይ ሁኔታዎችና የቀጣይ ትኩረቶች

ይሄን መሰሉ የመሠረተ ልማት እና የፕሮጀክቶች አፈጻጸም ደግሞ፣ እንደ ሀገር የተያዘውን ዘላቂ ልማት ከማሳካት እና አይበገሬ ኢኮኖሚን ከመገንባት አኳያ የበኩሉን እያበረከተ ይገኛል። ምክንያቱም በተሠሩ ሥራዎች የኃይል አቅርቦት አድጓል፤ የቱሪዝም ሥፍራዎች እንዲሰፉ በመደረጋቸው የቱሪስት ፍሰቱ ጨምሯል፤ የኮንፍረንስ ቱሪዝም እና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሁነቶች እንዲበራከቱ እድል ተፈጥሯል። እንደ ሀገር ሁነት የማስተናገድ አቅምንም አሳድጓል፡፡

በጥቅሉ ተግባራቱ በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርና፣ በኢንቨስትመንት፣ በአገልግሎትና በሌሎችም መስኮች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እንዲሳለጡ አቅም ሆነዋል። የዲጂታል ኢትዮጵያን ጉዞ ከማፋጠን አኳያም የማይተካ ሚናን ተወጥተዋል።

የእነዚህ ድምር ውጤትም በአምስቱ የኢኮኖሚው እድገት አመላካች ዘርፎች ላይ ውጤት እንዲመዘገብ፤ በቀጣይም ሊመዘገብ እንደሚችል ተገማችነትን አስፍኗል። ለምሳሌ፣ በግብርናው ዘርፍ በመኸር ብቻ ከተሸፈነው 20 ነጥብ 57 ሚሊዮን ሄክታር 610 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ተገኝቷል። ከዚህ ውስጥ 152 ሚሊዮን ኩንታሉ ስንዴ ነው። የቡናን ምርትና ምርታማነት ከማሳደግ አኳያም ከፍ ያለ ውጤት ተመዝግቧል።

በኢንዱስትሪው ዘርፍም ቢሆን ከፍ ያለ እድገት የመጣ ሲሆን፤ ይሄ ደግሞ ከግብዓት፣ ከጉምሩክና ሎጀስቲክስ፣ ከፋይናንስና ታክስ፣ ከመሠረተ ልማትም ሆነ ከኃይል አቅርቦት አኳያ፣ እንዲሁም ከአቅም አንጻር ያሉባቸው ችግሮች እንዲቃለሉ በመደረጉ የመጣ ለውጥ ነው፡፡

ለዚህ አብነት የሚሆነውም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ኢንዱስትሪዎች የተጠቀሙን የኃይል መጠን (የኤሌክትሪክ ፍጆታ) ሲሆን፤ ከአምና ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ29 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። ይሄም ኢንዱስትሪዎች አምና ካመረቱት በላይ የማምረታቸው አንዱ ማሳያ ነው፡፡

ከዚህ ባሻገር የፖለቲካ ድርድሮች እያመጡ ያለው ሰላም፤ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተግባራት ያለበት ደረጃ፤ የትግራይ ክልል የጊዜያዊ አስተዳደር ለሁለተኛ ዙር ሥራ መጀመሩ፤ ቀጣናዊ ቅቡልነት (በሰላምም፣ በልማትና ትብብር ረገድ)ን የመሳሰሉ ዘርፈ ብዙ ውጤቶችም ለኢኮኖሚያዊ እድገት ሂደቱ አስቻይ ሁኔታዎች ናቸው፡፡

እነዚህ እና መሰል ውጤታማ አፈጻጸሞች የተገኙበት ያለፉት ዘጠኝ ወራት ጉዞ ታዲያ፤ ከእስካሁኑ ስኬቱ ባሻገር አስቻይ ሁኔታዎችን ተጠቅሞ በቀጣይ ከዚህ ለላቀ ስኬት መነሳሳትንና መትጋትን ይጠይቃል። ለዚህ ደግሞ ሀገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ አዝማሚያዎችን እያነበቡ መሥራት፤ የፖለቲካና ዲፕሎማሲ ስኬቶችን ማስቀጠል፤ የገቢ አቅምን ማሳደግ፤ የተጀመሩ ዘርፈ ብዙ ውጤቶችን ከፍ አድርጎ ማስጓዝ ይገባል፡፡

በተለይም የዜጎችን የኑሮ ሁኔታና ደረጃ የማሳደግ፤ የማኅበራዊ አካታችነትን የማስቀጠል፤ የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበትን የመቆጣጠር፤ የሰላም እና ፀጥታ አጀንዳን የሁሉም ጉዳይ አድርጎ ዘላቂ እልባት እንዲያገኝ ማስቻል፤ ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም የመሸፈን ጅምርን ወደተሟላ ትግበራ ማስገባትን የመሳሰሉ ሥራዎችም ትኩረት ሊሰጣቸው ከሚገቡ ጉዳዮች መካከል ናቸው። ለዛሬው አበቃሁ፤ ሰላም!

በየኔነው ስሻው

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 14 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You