“ ፍቅር ተርበናል…ፍቅርን ታርዘናል…ፍቅርን ተራቁተናል”

“ሳለኝ”

“…ቀለም ቀለም፣

ያልነበረ በዓለም፣…”

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)

fenote1971@gmail.com

ታዋቂው አሜሪካዊ የሙዚቃ ሀያሲና ጸሐፊ ሮበርት ቶማስ ክሪስጋው፤”ጥሩ ሥነ ጥበብ ስለ አርቲስቱ ነፍስ ፍንጭ ይሰጠናል። ምርጥ ሙዚቃ ደግሞ ስለ ራሳችን ነፍስ ወይም ሕይወት ፍንጭ ይሰጠናል። ይለናል።/“Good art offers us a glimpse into the artist’s soul. Great music offers us a glimpse into our own.”/

የኩኩ ሰብስቤ የኩኩሻ አዲስ አልበም “ደጃዝማች”ም ስለ ሀገራችንና ሕዝባችን ሕይወትና ወቅታዊ ነፍስያ ፍንጭ ይሰጠናል። ፍንጭ በመስጠት ብቻ አይቆምም። መውጫ የማሪያም መንገድ ይመራል። ድልድይ ገንብቶ ያሻግራል። ከፍ ሲልም ፍቅርን በራሳችን ደጃዝማች አድርገን እንሹም ይለናል። ፍቅር ተርበናል። ፍቅርን ተርዘናል። ፍቅርን ተራቁተናል። ፍቅር እያለ በራሳችን ላይ ጥላቻን አሠልጥነናል። ጥላቻን ሹመናል። ጥላቻን ከመንበሩ አስለቅቀን፤ ፍቅር የበላይ አለቃ የበላይ መሪ፣ ደጃዝማች እናድርገው ትለናለች። በዚህ የኩኩሻ አልበም የቴዲ አፍሮ ቀለም ደምቆ ታይቷል።

የቴዲ አፍሮ ፍቅር አሸንፏል። የቴዲ አፍሮ የሕይወት መርህ፤ የቴዲ አፍሮ የሕይወት ፍልስፍና ግዘፍ ነስቶ ተከስቷል። ኩኩሻ የሙዚቃ ኃያልነት በራሷ አውድና መንገድ በ “ደጃዝማች” አሳይታናለች። የፍቅር ኃያልነት በሮሚዮና ጁሌት፣ በበዛብህና በሰብለ ወንጌል ተገልጦ ይሆናል። በ”ሳለኝ” ግን ነፍስ ዘርቶ በግርማ ሲመላለስ ታይቷል። ለዚህ መጣጥፌ ድፍረት ስለሆነኝ የሙዚቃ ልምምድ እና የእኔ ትውልድ ስለሆነው ሙዚቃ የማድመጥ ስቶሪ ልበለው ታሪክ ትንሽ ልበልና ወደ 8ኛው የኩኩ ሰብስቤ ኩኩሻ “ደጃዝማች” አልበም እመለሳለሁ።

ለእኔ ትውልድ ማለትም ለ70 ዎቹና 80 ዎቹ ሙዚቃ የሚደመጠው በካሴት ማጫወቻ ቴፕ ፣ በራዲዮና በቴሌቪዥን ሲተላለፍ ነበር። በተለይ በሬዲዮ የትምህርት ስርጭት እረፍት እረፍት ላይ የሚለቀቁ ሙዚቃዎች አይረሱንም። እድሜያችንና የትምህርት ደረጃችን እያደገ ሲመጣ ትምህርት በሬዲዮ የምንከፍተው የሙዚቃውን ሰዓት እየጠበቅን ነበር። በተለይ እኔ ያለ ሰዓት በልምድ አንድ የሬዲዮ ትምህርት አልቆ ቀጣዩ እስኪመጣ ያለውን የዕረፍት ሰዓት ስለማውቅ ሳልሳሳት ሙዚቃ ሙዚቃው ላይ በመክፈት በጓደኞቼ እታወቅ ነበር።

እንዲህ በማድረግ ባትሪ ድንጋይ እቆጥብ ነበር። አልፎ አልፎም ታዋቂ ሙዚቀኞች ከአዲስ አበባ ቴአትር ቤቶች ፣ ከፖሊስ ኦኬስትራ ወደ ፍኖተ ሰላም ከተማ እየመጡ በወቅቱ ዝነኛ በነበረው አዳራሽ የሙዚቃ ዝግጅት ያቀርቡ ነበር። ከዚያ በፊት በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ፎቅ ላይ በሚገኝ አዳራሽ መሰል የሙዚቃ ዝግጅት ይቀርብ ነበር።

የጎጃም ፖሊስ ባንድ ፣ የግሼዓባይና ሌሎች የሙዚቃ ቡድኖች በአደግንባት ፍኖተ ሰላም እየመጡ የሙዚቃ ዝግጅቶችን ያቀርቡ ነበር። ንዋይ ደበበን ለመጀመሪያ ጊዜ በአካል ያየነው በዚህ አጋጣሚ ነበር። የእኛ ታላላቆች እነ ጥላሁን ገሰሰም መጥተው እንደነበር አጫውተውናል። ከፍለን መግባት ስለማንችል ትኬት ቆርጠው የሚገቡ አዋቂዎች እንደ ልጃቸው ይዘውን ወደ አዳራሽ እንዲገቡ በር ላይ ቆመን ጋሼ ! እትየ ! ይዘኸኝ ግባ ! ይዘሽኝ ግቢ እያልን እንለምን ነበር። ይህ አልሳካ ካለ ደግሞ በአጥር ዘለን በመስኮት ለመግባት ከፖሊስና ጥበቃ ጓድ ጋር የምናደርገው መሯሯጥ ለእኔ ትውልድ ዛሬ የሆነ ያህል የሚታወስ ነው።

አዲስ ካሴት በወጣ ቁጥር በከተማችን በሚገኙ እንደ እማ ብርሃኔ፣ እማ አዲሴ፣ አባ ዮኑስና አባ ዳኘ ሻይ ቤቶች የ 10 ሳንቲም ሻይ እየጠጣን ሙዚቃችንን እንኮሞኩም ነበር። በነገራችን ላይ ሳንቲም ካለን ሙዚቃ ለማዳመጥ ስንል ሻይ እንደ ጠላ እስከ ሶስትና ከዚያ በላይ ልንደጋግም እንችላለን። ሳንቲም ከሌለን ደግሞ ከት/ቤት መልስ ወይም ቅዳሜና እሁድ ከሰፈራችን ወደ መሐል ከተማ ሄደን “ባንቴ ሙዚቃ” ቤት በስፒከር የሚለቀቀውን ሙዚቃ እናዳምጣለን። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ለምነን የምንፈልገውን ሙዚቀኛ ካሴት እናስደርጋለን። ለዓይን ያዝ ሲያደርግ ደግሞ ዳንሱን ጥግ ይዘን እናስነካዋለን። በተለይ ጎርመስ ማለት ስንጀምር ለፍቅር ደብዳቤ ማጀቢያ የሚሆን ግጥም ከሙዚቃው ለመምረጥ የእማ ብርሃኔ ሻይ ይደገማል። ይሰለሳል። ትንሽ የሥነ ጹሑፍ ነገር ስለነበረችኝ እና የእጅ ጹሑፌ ያምር ስለነበር በኋላ ዶሮ የጫረችው ሊመስል፤ የፍቅር ደብዳቤ ለጓደኞቼ ለመጻፍ የእማ ብርሃኔን ሻይ በአፍቃሪ ጓደኞቼ ደጋግሜ ተጋብዣለሁ። ለዛውም ተለምኜ ከአባ ንጋቴ ፉርኖ ዳቦ ጋር።

ያ የእኔ ትውልድ አዲስ የሙዚቃ ካሴት መውጣቱን የሚያውቅ በከተማችን አንድ ለእናቱ በሆነው የባንቴ ሙዚቃ ቤት የዘፋኙ ፖስተር ሲለጠፍ ወይም በሬዲዮ ሲለቀቅ ነው። ከአዲስ አበባ በሚመጣ ፍኖተ ሰላም አዳሪ ወይም አልፎ ሂያጅ አውቶብስ የአዲስ ካሴት ፖስተር ቀድሞ ለሙዚቃ ቤቱ ይላክና ፊት ለፊት ሕዝብ እንዲያየው ተለጥፎ ይሰነብታል። ካሴቱ ሲመጣ ደግሞ ሙዚቃ ቤቱ ድምጹን ከፍ አድርጎ በስፒከር ይለቀዋል። ይሄን የሰሙ ሆቴሎች፣ ቡና ቤቶች፣ ሻይ ቤቶች፣ ሎንችናዎች፣ ቺኳንታዎች፣ አንዳንድ ጠላ ቤቶች፣ ምግብ ቤቶች እና ካሴት ማጫወቻ ቴፕ ያላቸው አንዳንድ ግለሰቦች ካሴቱን ተሻምተው ይገዛሉ። እኔም የዘኒት ሙሀባ እና የኪሮስ አለማየሁ ካሴቶችን ከቤት ተልኬ መግዛቴን አስታውሳለሁ።

በነገራችን ላይ ለዓመት በዓል ለዓመት በዓል ብቻ ከሳጥን የሚወጣ አንድ ካሴት የሚያጫውት ናሽናል ፓናሶኒክ ቴፕ ነበረን። ሲወጣ ደግሞ አቧራ እንዳያርፍበት ዳንቴል ወይም ጥልፍ ጨርቅ ይሸፈናል። በዓል ሲያልፍ ተመልሶ ወደ ሳጥን ይገባል። ዓመቱን ሙሉ የማትገባው በጉልበቴ የግሌ ያደረግኋት የቤታችን ሬዲዮ ናት። አቤት ድንጋይ ወይም ባትሪዋ ሲያልቅ አስር ጊዜ ፀሀይ ላይ ማሰጣው አይረሳኝም። ከዚያ በስንት ልመናና ለቅሶ ከቀበሌ ህብረት ሱቅ ኤቨረዲ ባለ ድመቱ ወይም ምን ጊዜም ብርሃን ይገዛልኛል። ዛሬ እንዲህ በእጅ ስልካችን በቀላሉ ተደራሽ ሊሆን የካሴት ሙዚቃ ማድመጥ ብርቅና ድንቅ ነበር።

ዩኒቨርሲቲ ከገባን በኋላ ደግሞ ተማሪዎች ላውንጅና በየብሎኩ ባለ ቴሌቪዥን ህብረ ትርዒት ፣ 120 እና ታላቁን ፊልም እንከታተል ነበር። ይህ የልጅነትና የወጣትነት መነካት መሰለኝ ሙዚቃ አፍቃሪ ያደረገኝ። የተቃኘ የሰላ የሙዚቃ ጆሮ የሰጠኝ። አንድን አዲስ ሙዚቃ በጨረፍታ አድምጬ ወዲያው ዜማውን፣ የዘፈኑን ግጥም ሌሪኩንና የሙዚቃ ቅንብሩን አድምጬ ተወዳጅ እንደሚሆን ወይም እንደማይሆን መናገር እችላለሁ።

የሙዚቃ ሀያሲ ወይም ባለሙያ ባልሆንም አስተያየቴ ጠብ አይልም። ከአስቴር አወቀ “ጣፋጭ ብርቱካኔ”፣ “አወይ ሰው መሆኔ “እና “ካቡ”፤ ከኤፍሬም ታምሩ ደግሞ “እንደ ገብሱ ዛላ ጸጉሯ ተጎንጉኖ፣”፤ ከዳዊት ፅጌ “እትቱ በረደኝ፣”፤ ከሰሞነኛ አዳዲስ ሙዚቃዎች ደግሞ ከኩኩ ሰብስቤ/ኩኩሻ “ደጃዝማች”ከተሰኘው አዲስ አልበም “ሳለኝ” የሚለው ሙዚቃዋ ለእኔ ማስተርፒስ ወይም ድንቅ ሥራ ነው። ለነገሩ ራሱ የአልበሙ መጠሪያ “ደጃዝማች”ም ግሩም ድንቅ ሙዚቃ ነው።ኩኩሻ ኩኩ ናት እንኳ ቴዲ አፍሮ ግጥምና ዜማ ሰጥቷት ፊውቸሪንግ ገብቶላት።”Icing on the cake” እንዲሉት። በዛ ላይ ስምንት ግጥምና ዜማ ሰጥቷታል።

ለእኔ “ደጃዝማች” የዓመቱ አልቦሞች ደጃዝማች ነው። ለመሆኑ ደጃዝማች ማለት ምን ማለት ነው። ደጃዝማች፦ የጦር ሜዳ አዝማች ማለት ሲሆን በወታደራዊው መስክ የጦር ዘመቻዎች መሪ ሲሆን በሲቪል ማዕረግነቱ ደግሞ ከቢትዎደድ አንድ ደረጃ ዝቅ ያለ ነው። ፊታውራሪ ፦ ደግሞ ቀድሞ የሚዘምት ሠራዊት መሪ ሲሆን እንደ ወታደራዊ ማዕረግ የጦር ሠራዊቱ ዋና አዛዥ ማለት ሲሆን በደረጃው ከራስ ጋር ተመጣጣኝ ነው። በሲቪል ደግሞ ከደጅ አዝማች ዝቅ ብሎ የሚገኝ ማዕረግ ነው። ኩኩሻ ደጃዝማች የአልበሙ መጠሪያ የሆነው ፍቅር የሁሉም ነገር መሪ፤ አድራጊ ፈጣሪ ስለሆነ ነው ትለናለች። ኧረ ፍቅርስ ከደጃዝማች በላይ ንጉሥ ነው። አይደለም እንዴ…!?

እንደ አንድ ጥሩ ሙዚቃ አድማጭ “ደጃዝማች”እያደር እንደ ወይን በሚጣፍጠው ለዛ ባለው ተወዳጅ የኩኩ መረዋ ድምጽ፤ በሌሪኮቹ ወይም የዘፈን ግጥሞቹ፣ በሙዚቃ ቅንብሩ እና በዜማው ብንገመግመው ልቅም ጥንቅቅ ያለ ሥራ ሆኖ እናገኘዋለን። ከፍ ሲልም ኩኩሻ በዚህ የመጨረሻየ ነው ያለችውን 8ኛ አልበሟን ለማጠናቀቅ ሰባት ዓመት ደክማበታለች። ይህ ድንቅ ሥራ የድምጿ ሬንጅ ከዜማው ጋር የተንሰላሰለ ከመሆኑ ባሻገር የተዋሃደበት መንገድ ሚክስ ያደረገውንና ያቀናበረውን አቤል ጳውሎስ አቅም ይበልጥ ፍንትው አድርጎ አሳይቶናል። ምን አለፋችሁ ለ”ደጃዝማች” በኩኩሻ የተፈጠረው ቡድን ስብስብ በሀገራችን የሙዚቃ ኢንዱስትሪ አሉ የሚባሉ ሙዚቀኞችንና ደራሲዎችን ያካተተ መሆኑ ሥራውን ዘመን ተሻጋሪ ክላሲካል ከማድረጉ ባሻገር ከፍ ያለ እርካብ እንዲቆናጠጥ አድርጓል።

የድምፃዊት ኩኩ ሰብስቤ “ ደጃዝማች “ በተሰኘው አዲስ አልበም ላይ ስመጥር የሆኑ የሙዚቃ ባለሙያዎች የተሳተፉበት ሲሆን የሙዚቃ አቀናባሪው አቤል ጳውሎስ ዘጠኙን ሙዚቃዎች በማቀናበር እንዲሁም አስራ አንዱን ሙዚቃዎች ሚክስ በማድረግ እንደተሳተፈ ተነግሯል። ሁለቱን ሙዚቃዎች አሬንጅ ያደረገው ማሩ ዓለማየሁ ሲሆን ሙዚቀኛ ያሬድ ተፈራ፣ አክሊሉ ወ/ዮሐንስ (ጆኒ ሳክስ) እና ሙዚቀኛ ዘሪሁን በለጠ በሳክስፎን ፣ግሩም መዝሙር እና ሳሙኤል አሰፋ በጊታር ተሳትፈዋል። ፊውቸሪንግ – ቴዲ አፍሮ፤ ተቀባይ ቴዲ አፍሮ፣ ግርማ ተፈራ፣ ዲጄ ዊሽ መሆናቸው ለአልበሙ ሌላ ቀለም ሌላ ጥኡም ዜማ ከመደረብ አልፎ ከፍ አድርጎታል። ትዕዛዙ የእኔ 1ኛ የሆነውን “ሳለኝ”ሙዚቃ ደግሞ ታመነ መኮንን በክራር አጅቦታል።

ሌላው ይህ የኩኩሻ አልበም እንደ ቀደሙ ሥራዎቿ ለስሜትና ለነፍስያ የቀረበ መሆኑ የመወደዱ ሚስጥር ነው። የዘፈን ግጥሞቹ ወይም ሌሪኮቹ አልያም Lyrics እና ዜማቸው አብዛኛዎቹ በቴዲ አፍሮ መደረሳቸው ከሙዚቃ ከሚክሲንጉ፣ ከቅንብሩና ከማስተሪንጉ ስምም እንዲሆን አድርጎታል። ለእኔ በዚህ አልበም 1ኛ የቴዲ አፍሮ ግጥምና ዜማ የሆነውና ታመነ መኮነን በክራር ብቻ ያጀባት “ሳለኝ” የሚለው ሙዚቃ ነው። አዎ ይሄን ማስተርፒስ በስሜት አጋቢነት፣ በስሜት አድራሽነት፣ በስሜት ተላላኪነት፣ በስሜት ፖስተኛነት፣ በስሜት ጦፈኛነት ወይም በemotional deliveryነት መርጨዋለሁ። በነገራችን ላይ የዚህ ሙዚቃ ማስታወሻ ኩኩ በሞት ላጣቻት ሰዓሊ እህቷ መታሰቢያ እንዲሆን ቴዲ ያበረከተላት መሆኑን ኩኩሻ ትናገራለች። የሙዚቃው ታሪክ ስቶሪ በራሱ ስሜት ያጋባል። የተወሰኑ ስንኞችን እንመልከት፦

“ሳለኝ ሳለኝ በልብህ ብራና በፍቅር ቀለም፣

እንዳልጠፋ አድርገህ እስከ ዘላለም፤

ስየሃለሁ እኔማ ልቤ ላይ በእንባዬ ነክሬ፣

ባልነበረ ቀለም ባልታየ እስከዛሬ፤…”

ሥዕል ሲጀመር ስሜት መግለጫ መሆኑ ሳያንስ፤ ሥዕሉ የሚሳለው ደግሞ ልብን ብራና፣ ሸራ፣ ፍቅርን ቀለም አድርጎ ነው። ለዚያውም እንዳይጠፋ ዘላለማዊ eternal ተደርጎ።

እስኪ እነዚህን ስንኞች አፍታ ወስዳችሁ በምናባችሁ እዩአቸው።

“ሳለኝ ሳለኝ በልብህ ብራና በፍቅር ቀለም፣

እንዳልጠፋ አድርገህ እስከ ዘላለም፤…”

ከዚህ የሚጋባ የስሜት ባሕር ሳንወጣ፦

“ስየሃለሁ እኔማ ልቤ ላይ በእንባዬ ነክሬ፣

ባልነበረ ቀለም ባልታየ እስከዛሬ፤…”

የዚህ ሙዚቃ ገጸ ባህሪ “ሳለኝ”ብላ አታቆመም። “ስየሃለሁ” ትለዋለች። ለዛውም እንባዋን ቀለም አድርጋ በልቧ ላይ። ለዛውም እስከ ዛሬ ባልነበረና ባልታየ የእንባ ቀለም። ፍቅር ሰጥቶ መቀበል፣ ስሜት ሰጥቶ መቀበል እንደሆነ፤ ፍቅርም ሆነ ስሜት የሚጋባ ጸጋ መሆኑን ለመግለጽ ቴዲ የሄደበትን የምናብ ጥልቀት፣ የቃላት ምርጫ፣ ምጣኔ፣ ምት አለማድነቅ አይቻልም። ስንኙ መቺ በዚህ ሊያበቃ፤

ከአበቦች ገላ ላይ ቀለም ቢቀመም፣

የአንተን ውበት ስሎ የሚገልጽ የለም፤

እስኪ ከአሳሳቅህ ከውበትህ ቀባኝ፣

ያስጨነቀኝ ፍቅርህ ሚስጥሩ እንዲገባኝ፤

ቀለም ቀለም፣

ያልነበረ በዓለም፣

ውበት ውበት፣

ኤዶማዊ ገነት፤…

ይነዳል ወይ ዓይንም እንደ እሳት

እያየኸኝ ልቤን አትለኩሳት(×3)

እንደሰው አይቀልም አንተን ወዶ መርሳት፤…”

ብንወስድ የቴዲ አፍሮ የሌሪክ ድርሰት ምን ያህል ምናባዊ፣ ጥልቅ፣ በአንድ ሌሪክ አንድ ጉዳይ የሚያነሳ፣ አሰስ ገሰሱን የማያግበሰብስ፤ ቅጥልጥል ቅርንጫፍ የሌላቸው ወጥና እዚህና እዚያ የማይረግጡ፤ ሊመዛቸው ለፈለገ የሚመዘዙ ናቸው። ቃላቱ ለዜማ ለምት የሚስማሙ፣ ተጠይቃዊ መሆን ባይጠበቅባችሁም ሌሪኮቹ ተጠየቃዊ መሆናቸው ልዩ ያደርጋቸዋል። የቴዲ ሌሪካዊ ሀብቱ ድልብና ተዝቆ የማያላቅ ጭምር ነው። ቴዲ የሌሪኮቹም የዜማዎችም ደራሲ መሆኑ ዜማውን በግጥሞቹ፣ ግጥሞቹን በዜማው በቀላሉ እንዲገለጡ አድርጓቸዋል። ዜማውን ሲደርስ ሌሪኩን፣ ሌሪኩን ሲደርስ ዜማውን እያሰበ ስለሆነ የተዋጣላቸው ሊሆኑ ችለዋል።

የቴዲ አፍሮ ሌሪኮች ይዘት ዘመንና ትውልድ ተሻጋሪ ከመሆናቸው ባሻገር ስለ ፍቅር፣ ስለ ትዝታ፣ ስለ ታሪክ፣ ስለ ሀገር፣ ስለ አንድነት ፣ ስለነጻነት፣ ስለ አርበኝነት፣ ስለ ባህል እና ማህበራዊ ሕይወት በሙላት የሚሰብኩ የሚለፍፉና የሚሔሱ መሆናቸውን በሁሉም ሥራዎቹ አስመስክሯል። በኩኩሻ ዘፈኖቹም ይሄን ነው ያረጋገጠልን። ቅንብሩና ሚክሲንጉ ትውልዶችን ብቻ ሳይሆን ራሳቸውን ሙዚቃዎችን ድልድይ ሆኖ ያገናኘ ነው። በዚህ አልበም የሮሃ ባንድ ቀለም፤ ከባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያችን ክራር ደምቆ ታይቷል። ኩኩሻ በዚህ አልበም የፍቅርን ኃያልነት ሰብካናለች። የአልበሙ ስቶሪም ይኸው የፍቅር አሸናፊነት ነው።

አልበሙ በእራሷ በኩኩ ሰብስቤ የዩቲዩብ ቻናል እና በሁሉም የዲጂታል መተግበሪያዎች ባለፈው ሚያዚያ 24 ቀን አመሻሽ ለአድማጭ በደረሰ በ11ኛ ቀኑ ብቻ ሚሊየኖች አይተውታል። ወይም አድምጠውታል። የአልበሙ መጠሪያ “ደጃዝማች”እስከ ማክሰኞ 1 ሰዓት ድረስ ከ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ የሙዚቃ አፍቃሪዎችን እይታ ያገኘ ሲሆን፤ በአጠቃላይ አልበሙ በሚሊየኖች የሚቆጠር እይታ አግኝቷል።

ድምፃዊት ኩኩ ሰብስቤ ለሰባት ዓመታት በደከመችበት “ደጃዝማች “ በተሰኘው አዲስ የሙዚቃ አልበም 13 ዘፈኖችን የያዘ ሲሆን ከእነዚህ ዘፈኖች ውስጥ የስምንቱ ግጥምና ዜማ የድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ሲሆኑ ሌሎቹን ሙዚቃዎች ደግሞ በግጥም ገጣሚ ይልማ ገብረአብ፣ መሰለ ጌታሁን፣ መሰለ አስማማው፣ ናትናኤል ግርማቸው የሠሩ ሲሆኑ ሞገስ ተካ እና ምስክር አወልም እንዲሁ በግጥምና ዜማ ተሳትፈዋል።

ከተቀሩት ሥራዎች ውስጥ “ወለላዬ” የተሰኘው ሙዚቃ ደግሞ የኩኩ የድሮ ሥራ ሲሆን ቴዲ ማክ እንደገና ሪአሬንጅ (Re Arrange) አድርጎ የሠራው ሙዚቃ ነው። ይህን ማስተርፒስ “ደጃዝማች” በእኔ ላይ የፈጠረው ስሜት እስኪፈጠርባችሁ እስኪጋባባችሁ ደጋግማችሁ አድምጡት። ከዚያ እውነትም ማስተርፒስ፣ እውነትም ድንቅ ሥራ ትላላችሁ። ስለ ኩኩሻ ይትባረክ ዋለልኝ የተባሉ ጸሐፊ ካስነበቡን ይሄን ላጋራችሁና ልሰናበት።

አንጋፋው የሙዚቃ ባለሙያ ተስፋዬ ለማ የኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ በሚለው መጽሐፋቸው ስለ ድምጻዊት ኩኩ ሰብስቤ እንዲህ ይላሉ፤” እንደ አጥቢያ ኮከብ ብቅ ያለችው ኩኩ ሰብስቤ የአዘፋፈን ስልቷ ማራኪና የብዙውን አድማጭ ስሜት የሳበ ስለነበር በአጭር ጊዜ ወደ ታዋቂነቱ ዓለም እንድትገባ ረድተዋታል፡፡ ኩኩ በተለይ ትዝታን ስትጫወት ልዩ ሕይወት ትሰጠዋለች። ኩኩ ሳቂታ ቀልድ አዋቂና አሉ ከሚባሉ ሴት ድምጻውያን አንዷ ናት።” ይላሉ፡፡

እውነት ነው፡፡ ድምጻዊት ኩኩ ሰብስቤ ተጫዋች ቀልድ አዋቂና ቁምነገረኛም ናት። እድሜዋን ሙሉ በምትወደው የሙዚቃ ሙያ ውስጥ በየጊዜው (professional knowledge) እራስዋን አበልጽጋ በሙያው ሥነምግባር ታንጻ በምትወደው ሙያ ውስጥ ያሳለፈች ድንቅ የሙዚቃ ባለሙያ ናት። ኩኩ ሰብስቤ በዘመናዊቷ የኢትዬጵያ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ፍላጎት፣ ተሰጥኦ፣ ልምድን በማዋሃድ ለረጅም ዓመታት የሠራቻቸው ሙዚቃዎች በሕዝብ ዘንድ ብቻ ሳይሆን በሙዚቃ ባለሙያው ዘንድም ዛሬ ድረስ እጅግ ተወዳጅና ተደማጭ ናቸው።

ኩኩ ዛሬ ድረስ ሥራዎችዋን በእውቀት በልምድና በሙያ ዲሲፕሊን እራስዋን አስገዝታ የምትሠራ ድምጻዊት ናት፡፡ ይህ የሙያ ዲሲፕሊን ደግሞ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ በሙዚቃ ሥራዎቻቸው ስማቸው ግዘፍ ሆኖ ከሚጠቀሱ ድምፃውያን መካከል አንዷ እንድትሆን አድርጓታል። ድምጻዊት ኩኩ ሰብስቤ ለረጅም ዓመታት ሙያዋን በእውቀት፣ በፍቅራና በዲሲፕሊን በመታገዝ ስለምትሠራቸው እነዚህ ሥራዎች እንደወይን እያደር እየጣፈጡ በሕዝብ ዘንድ እጅግ ተወዳጅ ሆነው ዘመን የሚሻገሩ ሆነው ዛሬ ድረስ ዘልቀዋል።

ሻሎም !

አሜን።

በቁምላቸው አበበ ይማም(ሞሼ ዳያን)

fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You