
ጌታቸው ዲሪባ (ፒኤችዲ) “ግብርና እና የገጠር ልማት ትራንስፎርሜሽን በኢትዮጵያ ተግዳሮቶቹ፣ አበረታች ሁኔታዎች እና አስፈላጊ የማሻሻያ እርምጃዎች” (2020) በሚል ርዕስ ለውይይት መነሻ ይሆን ዘንድ ታስቦ ለቀረበ ጥናት በመጀመሪያ (መግቢያ) አንቀፅነት የተጠቀሙትን፣ የዩቫል ኖሃ ሀራሪ፣ ሆሞ ደስ (የነገ አጭር ታሪክ፣2007፥ 200) ጥቅስ እኛም የዚህ ጽሑፍ መግቢያ በማድረግ እንጀምር ዘንድ ወደድን። እንዲህ ይላል:-
“ትክክለኛውን መንገድ ካገኘነው ራዕያችንን ማሳከት እንችላለን:: ከዕውቀት ማነስ በስተቀር ወደፊት ለመጓዝ የሚያግደን መሰናክል በጭራሽ አይኖርም:: ድንገተኛ አደጋም ሆነ ድርቅ ተአምራዊ አይደሉም፤ በቁጥጥራችን ስር ሊውሉ የሚችሉ ናቸው:: ለወደፊት ብሩህ ተስፋ ያልታደልን ፍጡሮችም አይደለንም፤ ሠላም በእጃችን ነው:: ከሞት በኋላ ያለውን ገነት ብቻ ማለም አይኖርብንም፣ በቴክኖሎጂ ኋላ ቀርነትን አስወግደን ሀገራችንን ምድራዊ ገነት በማድረግ ኑሮን ማጣጣም ይቻለናል”::
ይህንን ዘመን አይሽሬና ተጠቃሽ ጥቅስ በልባችን ይዘን ወደ ተነሳንበት ርዕስ ጉዳይ እንዝለቅ።
ኢትዮጵያ በ3.28-11.48 ድግሪ ሰሜናዊ ላቲቲዩድ እና 33.00-47.52 ድግሪ ምሥራቃዊ ሎንግቲዩድ መካከል የምትገኝ፤ አጠቃላይ የቆዳ ስፋት 1,104,300 እስኩዌር ኪ.ሜትር ያላት፤ ትልቅ የመሬት ከፍታ ቦታዎች ልዩነት ያላትና ልዩነቱም ከ110 ሜትር ከባሕር ወለል በታች ከሚገኘውና የምድራችን ሞቃቱ ስፍራና አማካኝ ዓመታዊ የሙቀት መጠኑ 34.4 ሴንቲግሬድ፤ ያረፈበት ምድረ-ገጽ አርባ ኪ.ሜ በ10 ኪ.ሜ ስፋት ከሆነው፤ 96,707 ካሬ ኪ.ሜ. በሚሸፍነው አፋር ክልል የሚገኘው ደንከል ዝቅተኛ ሥፍራ እስከ 4,620 ሜትር ከባሕር ወለል በላይ የሚገኘው ራስ ዳሸን ተራራ ድረስ የሚዘልቅባት ልዩ ሀገር ነች።
እነዚህ ብቻ አይደሉም፤ ስለ ኢትዮጵያ ግብርና ሲታሰብ በ13 ወራት ውስጥ ያሉትን፣ የተለያዩ የአየር ጸባዮች ያሏቸውን አራት ወቅቶች (ክረምት፣ መፀው፣ በጋ እና በልግ)፤ እንዲሁም አጠቃላይ የዘመን ቀመሯን ማስላት ግድ ይሆናል።
የግብርና ሥራዋ በእነዚህ መልክአ ምድራዊ ማሕቀፎች፣ የአየር ንብረትና የዘመን ቀመር ውስጥ የሚገኘው፤ ነገር ግን፣ እስከ ዛሬ (በ1993 ዓ•ም የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው) 42 ያህል ትላልቅ ድርቅና ረሀብን ያስተናገደችው ኢትዮጵያ የሌላት ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ ሀብት እንደሌለ ሁሉ፣ የማትስማማው ወይም የማይስማማት የአዝርዕት (ብርዕ ሰብል፣ ጥራጥሬ፣ ፍራፍሬ፣ አትክልት፣ ሥራሥር ተክሎች (ካሳቫ፣ እንሰት፣ ስኳር ድንች፣ ጎደሬ እና ሌሎችም) አይነትም የለም። ይሁን እንጂ፣ የምግብ ዋስትና (በአሁኑ አገላለፅ “የምግብ ሉዓላዊነት”)ን ማሻሻል አቅቷት (ለውጦችና መሻሻሎች እንዳሉ ሆኖ) በርካታ ሕዝብ በምግብ እጥረት ሲጠቃ ይታያል።
የ1994 ዓ.ምቱን በተካው፣ ባለፈው ዓመት ፀድቆ ወደ ተግባር በገባው፤ በተለያዩ ጉዳዮች (የገጠር መሬት፣ ደንና ተፈጥሮ ሃብት አስተዳደርና አጠቃቀም፣ የቴክኖሎጂ፣ ግብዓት እና አገልግሎት አቅርቦት ሥርዓት፣ የውሃ አጠቃቀም እና አስተዳደር፣ የምርት ግብይት፣ የገጠር ኢኮኖሚ ልማት፣ መሠረተ-ልማት፣ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎን ማሳደግና ማጠናከር፣ የግብርናና ገጠር ልማት ፋይናንስ ሥርዓት፣ ተቋማዊ የአሠራር ሥርዓት እንዲሁም የግብርና አካታችነትና ዘላቂነት) ላይ ማሻሻያዎችን ያደረገው የግብርና ፖሊሲ ሰነድ የመጀመሪያው መግቢያ አንቀፅ፤ በመግቢያ አንቀፁ የመጀመሪያ መስመር ላይ ሰፍሮ እንደሚገኘው “የግብርና ዘርፍ ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት ውስጥ በ2015 በጀት ዓመት 32.1 በመቶ በላይ ድርሻ የሚሸፍንና የኢኮኖሚ መሠረት በመሆን ለማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸም ከፍተኛ አስተዋፅዖ የሚያበረክት የኢኮኖሚ ልማት ዘርፍ ነው።”
ከዓለም ኢኮኖሚ (ጂዲፒ) 4.1% (በ2024)፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሥራ እድል ከመፍጠር አኳያ 26.4% ድርሻን የያዘውን፤ በ2025 አጠቃላይ የምርት ዋጋው 4.82 ትሪሊዮን የአሜሪካን ዶላር ይደርሳል ተብሎ የተተነበየለትን፤ ለዓለም ሕዝብ የመኖር/አለመኖር (ሕልውና) ጉዳይ የሆነውንና የዓለም የምግብ ፍላጎት በየዓመቱ በ1.2% እየጨመረ ባለበት ሁኔታ ግብርናን የማዘመን መሰረታዊ ጉዳዮች ሲነሱ ከላይ የዘረዘርናቸው፤ በአብዛኛው ተፈጥሯዊ የሆኑ ጉዳዮች ብቻ አይደሉም መነሳት ያለባቸው። ተፈጥሮ እና የተፈጥሮ ሃብት፣ ምርጥ ዘር፣ የምግብ ሉዓላዊነት፣ ሥነሕዝብ፣ ድህነት ቅነሳ፣ የእንስሳት ሀብት፣ የሰው ሀብት፣ የአየር ንብረትና አፈፃፀሙ፣ ውኃና የውኃ ሀብት አቅም፣ መሬት እና ዘላቂ የመሬት አያያዝ፣ ኢኮኖሚ፣ ቴክኖሎጂ፣ እርሻ፣ ማዳበሪያ፣ የመስኖ ልማት፣ አርብቶ አደር፣ ከፊል አርብቶ አደር፣ ዝናብ፣ ቶፖግራፊ፣ የግብርና ሜካናይዜሽን፣ የአፈር አሲዳማነትና ምርታማነት፣ የገጠር ልማት፣ መስኖ ልማት እና የመሳሰሉትም ለግብርናው ዘርፍ መዘመን/አለመዘመን ወሳኝነታቸው ሊሰመርበት፤ ያሉበት ሁኔታም ሊፈተሽና መደረግ ያለበት ሁሉ ሊደረግ ይገባል።
ጉዳያችንን አፍሪካዊ መልክ እንስጠው ካልንም የችግሩ አሳሳቢነት ጎልቶ እንጂ አንሶ አናገኘውም።
Biotechnology Development in Africa (Abdulkabir Abdulmalik እና ሌሎች፣ 2023) በሚል ርዕስ ስር የቀረበ ጥናት እንደሚያሳየው ከ54 የአፍሪካ ሀገራት መካከል 48ቱ ለግብርና ልማት በአማካይ የበጀታቸውን 3.8 በመቶ (አንድ መቶኛም መኖሩን ጥናቱ ያሳያል) ብቻ ነው የሚመድቡት። ይህ ካልተለወጠና ከፍተኛ በጀት መድቦ መላ አፍሪካን የሚቀልቡትን 41 ሚሊዮን ባለ ትናንሽ ይዞታ አርሶ አደሮች ችግሮች መፍታት፤ እንዲሁም አጠቃላይ የግብርናውን ሴክተር ማዘመን ካልተቻለ አፍሪካ ከድህነት ትወጣለች ማለት ዘበት ነው።
እንደዚሁ ጥናት ከሆነ፣ በ2019 በመላው ዓለም 190 ሚሊዮን ሄክታር በባዮቴክ ሲለማ በአፍሪካ ግን 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ብቻ ነበር የለማው። ይህ የሚያሳየው የበጀት እጥረት መኖሩን ብቻ ሳይሆን የባዮቴክኖሎጂ ግንዛቤ ጭምር ገና ያልሰረፀ መሆኑንና ከፍተኛ የመልማት አቅም ያላት አፍሪካ እንደ አኅጉር ያላትን እምቅ አቅም እየተጠቀመችበት አለመሆኑንም ጉዳዩ ፋታ የሚሰጥ አይደለም።
የግብርናችን ልዩ ልዩነት
በጃፓኑ “JICA” ድጋፍ በተከናወነው፣ በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የግብርና ግብይት ሥርዓት መጠናከሪያ ጥናት (ሕዳር 2012 (እ.ኤ.አ) ላይ እንደሰፈረው፣ አብዛኛው የሀገሪቱ ክፍል የመኸር እና በልግ የዝናብ ወቅቶች ያሉት ሲሆን፣ በሰሜን የመኸር ወቅት ቀደም ብሎ በሰኔ ወር አጋማሽ አካባቢ የሚጀምር ሲሆን፤ በደቡብ እስከ ጥቅምት ወር ዘግይቶ ይጀምራል:: በሀገሪቱ ውስጥ በከፍተኛ አካባቢዎች ያለው የሰብል ልማት በአብዛኛው ከመኸር ዝናብ ጋር ተያያዥነት አለው::
በዚሁ ሰፋ ባለ ጥናት ላይ እንደሰፈረው፣ በአጠቃላይ ምዕራባዊ ከፍተኛ ቦታዎች ከፍተኛ ዝናብ የሚያገኙ ሲሆን አማካይ ዓመታዊ የዝናብ መጠንም ከ1200 ሚ.ሜትር በላይ ነው:: በተቃራኒው አብዛኛው አፋርና ሶማሌ አካባቢ የሚገኘው ዝቅተኛ ቦታ አነስተኛ ዝናብ የሚያገኝ ሲሆን፣ ዓመታዊ የዝናብ መጠኑም ከ400 ሚ.ሜትር በታች ነው::
ኢትዮጵያ የግብርና ሥነምሕዳር የሚወሰነው በመሬት ከፍታ ላይ ተመሥርቶ መሆኑን የሚገልፀው ይህ ጥናት ስድስት ዋና ዋና የሥነምሕዳር ቀጣናዎች እንዳሉም ይገልፃል:: ከስድስቱ ቀጣናዎች ሦስቱ ዋነኛ የእህል ሰብል አብቃይ ሲሆኑ፤ ቆላ፣ ወይናደጋ እና ደጋ መሆናቸውንም ያመለክታል:: እንደዚሁ ጥናት ማብራሪያ፣ በተለይም ወይናደጋ እና ደጋ ለእህል ምርት ምቹ ሲሆኑ አካባቢዎቹ ስንዴ፣ ጤፍ እና በቆሎ የሚመረትባቸው ናቸው::
አርሶ አደሩ እና ይዞታው
እንደምናውቀው፣ አብዛኛው ሕዝብ ኑሮው በግብርና ላይ የተመሠረተ ነው:: የሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገትም በከፍተኛ ደረጃ በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ላይ የቆመ ሲሆን፣ ግብርና 43% አጠቃላይ የሀገሪቱን ብሔራዊ ምርትና 60% የወጪ ምንዛሪ ግኝትን ይይዛል:: ይሁንና ባሕላዊ የሆነ የአነስተኛ አርሶ አደሮች እርሻ አሁንም ከፍተኛ ድርሻ አለው:: አብዛኛው አርሶ አደር ቅይጥ እርሻን የሚያዘወትር ሲሆን ለሰብል ልማትም ከፍተኛውን ትኩረት በመስጠት የከብት እርባታንም ያካሂዳል::በተለያዩ ጥናቶች ላይ እንደ ተመለከተው፣ 82% የሚሆነው አርሶ አደር ቤተሰቦች ከ2 ሄ/ር በታች መሬት ያላቸው ሲሆን ወደ 17% የሚሆኑት ከ2-5 ሄ/ር የሚሆን መሬት አላቸው።
ከላይ በጠቀስነው ደቡቡ የሀገራችንን ክፍል ማዕከል ያደረገ ጥናት ላይ እንደ ተመለከተው፣ በኢትዮጵያ አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች በአማካይ 1.03 ሄ/ር መሬት በቤተሰብ ደረጃ ሲሆን የሀገሪቱን 95% የሚሆነውን የሰብል ምርት የሚያመርቱት እነዚሁ አርሶ አደሮች ናቸው፡፡
እርግጥ ነው፣ ሃይንከን ኢትዮጵያ ከወርልድ ቪዥን ጋር በመሆን አነስተኛ የእርሻ መሬት ያላቸው 23ሺህ 387 አርሶ አደሮችን (በተዘዋዋሪ የ116,935 ማኅበረሰብ አባላትን) ምርት እና ገቢ በቀጥታ የሚያሳድግ ፕሮጀክት መጀመሩ፤ ፕሮጀክቱ እ.ኤ.አ ከጥር 2024 እስከ የካቲት 2027 ባለው ጊዜ ተግባራዊ እንደሚሆን መነገሩ ይታወሳል። ጥሩ ጅምር በመሆኑ ሊበረታታና ተጠናክሮም ሊቀጥል ይገባል።
ሰብሎቻችን እና ይዞታቸው
ሰብል ልማት የኢትዮጵያ ግብርና ልማት ዋንኛ አካል፤ በሀገሪቱ ሶሽዮ ኢኮኖሚ ያለው ሚና የጎላ ሲሆን የአብዛኛው ሕዝብ መተደዳሪያ፣ ዋንኛ የምግብ ምንጭ እንዲሁም፣ ለኢንዲስትሪው ዘርፍ በጥሬ እቃነት ከመዋሉም በላይ ለውጪ ምንዛሪ ግኝት አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ይገኛል::
በሚመለከተው አካል የግብርና ምርት ውጤቶች ተብለው የተለዩት በቆሎ፣ ቦሎቄ፣ ስንዴ፣ አተር እና ቡና ሲሆኑ፤ በአሁኑ ሰዓት ስንዴ ባገኘው ልዩ ትኩረት ምክንያት ምርቱ በከፍተኛ ደረጃ ጨምሮ በሚለከታቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት ሳይቀር ከፍተኛ እውቅናን እና አድናቆትን ሊያገኝ ችሏል። (ለተጨማሪ “ዘመን ኢኮኖሚ” መጽሔት (መጋቢት 2017 ዓ•ም)ን ይመልከቱ።)
ዝቅ ብለን የምንጠቅሰው መረጃ እንደሚያሳየው፣ በኢትዮጵያ የብርዕ ሰብሎች (በቆሎ፣ ማሽላ፣ ስንዴ፣ ገብስና ጤፍ) ከፍተኛ ድርሻ አላቸው:: ጥራጥሬ፣ ቅባት እህል፣ ሥራሥር፣ አትክልትና ቋሚ ሰብሎች (ቡና፣ ፍራፍሬ፣ ወ.ዘ.ተ.) በተለያየ ደረጃ የሚመረቱ ሲሆን በሕብረተሰቡ መተዳደሪያነት ከሚሰጡት ጥቅም አኳያ ጉልህ ሚና አላቸው::
ከማዕከላዊ እስታቲስቲክስ ባለሥልጣን (2008/09 (እ.ኤ.አ) ጥራዝ. VII (ቡልቲን 446)”) የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው በሀገሪቱ ምዕራባዊ በኩል ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ የኦሮሚያ ምዕራብ ክፍል፣ አማራ፣ ደቡብ እና ትግራይን የያዘ ክፍል ዋነኛ የሰብል ልማት የሚካሄድባቸው አካባቢዎች ሲሆኑ፤ ኦሮሚያ፣ አማራ እና ደቡብ የሀገሪቱን 91.2% ሰብል ምርት ያመርታሉ:: ለብርዕ ሰብል፣ ጥራጥሬ፣ አትክልትና ቋሚ ሰብሎች ልማት ያላቸው አስተዋጽኦ እንደየ ቅደምተከተላቸው 89.5%፣ 95.2%፣ 96.6% እና 98.8% ነው:: ደቡብ በአትክልትና ቋሚ ሰብሎች ልማት ጉልህ ቦታ ያለው ሲሆን፤ የሀገሪቱ 40% የሚሆነው የቡና ምርት የሚመረተውም በዚሁ ክልል ነው::
በቀድሞው በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የግብርና ግብይት ሥርዓት መጠናከሪያ ጥናት መሰረት በቆሎ በመጀመሪያ ደረጃ የሚገኝ የብርዕ ሰብል ሲሆን ሰፋ ባለ የአየር ፀባይ ባለበት፣ በዋነኝነት በወይናደጋ አካባቢ ይመረታል:: ጤፍ፣ ስንዴ ማሽላ እና ገብስም በተመሳሳይ አየር ፀባይ ባለበት ይበቅላሉ:: በአብዛኛው ስንዴ፣ ገብስ የቅባት እህልና ጥራጥሬ የአየር ፀባዩ /ከ2300-3200 ሜትር ከባሕር ወለል በላይ በሆኑ ደጋ አካባቢዎች ይበቅላሉ:: ማሽላ እና ዘንጋዳ ድርቅ የመቋቋም ችሎታ ያላቸው በመሆኑ በከፊል ደረቅና ዝቅተኛ አካባቢዎች የሚበቅሉ ሰብሎች ናቸው::
በኢትዮጵያ ዋነኛ የእህል ምርቶች የሚበቅሉት በዋነኛ የዝናብ ወቅት (መኸር) ነው:: በበልግ ዝናብ ወቅት የሚመረተው የእህል መጠን ከዓመታዊ የምርት መጠን ከ5-10% አይበልጥም:: ሆኖም በደቡብ ክልል እስከ 75% የበቆሎ ምርት የሚገኘው በበልግ ዝናብ ነው::
በ1958 ዓ.ም “የእርሻ ምርምር አንስቲትዩት” በሚል ከተመሠረተው ከዛሬው የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ጠቃሚ ከሆኑ ሰብሎች መካከል አንዱ የሆነውን በቆሎ በኩታገጠም በማምረት ምርታማነቱ ከፍ እንዲል በርካታ የጥናትና እየተሠሩ ይገኛሉ።
ከዚሁ ተቋም የተገኘ መረጃ (2024) እንደሚያሳየው በበቆሎ ምርት ላይ ከ48 በላይ የምርምር ሥራዎች የተሠሩ ሲሆን፤ በቆሎን በኩታገጠም በማምረት ምርታማነትን መጨመር ተችሏል (የበቆሎ ምርታማነት በሄክታር ከ20 ኩንታል ወደ 46 ኩንታል ከፍ ማለቱም ተገልፇል)። እንደዚሁ ተቋም ከሆነ፣ በቀጣይ የበቆሎ ምርታማነትን ይበልጥ ለማሳደግ በቴክኖሎጂ የታገዙ የምርምር ሥራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ ይሆናል።
ከፈተሽናቸው መረጃዎች መረዳት እንደተቻለው፣ በሀገሪቱ አብዛኛው የብርዕ ሰብል የሚመረተው ኦሮሚያና አማራ ክልል ሲሆን 82% የሚሆነው የብርዕ ምርት እና 79% የገበያ ሽያጭ መጠን ያለውም በ′ነዚሁ ክልሎች ነው:: በተለይ ኦሮሚያ ብቻውን ያለው ድርሻ የሀገሪቱ 50% ምርትና 49% የገበያ ሽያጭ መጠን ይሆናል::
የሰለጠነ የሰው ኃይል
ግብርናን ማዘመን ላይ በርትተው የሠሩ ሀገራት ዛሬ ቢጠሯቸው የሚሰሙ አይደሉም። በተለይ የግብርናውንና ሌሎች ዘርፎችን ካሉበት ችግር አስፈንጥሮ ያወጣል ተብሎ እየተሠራበት ያለው ባዮቴክኖሎጂን (Biotechnology ወይም Biotech) ከማልማትና በጥናት መስክነት አካዳሚያዊ መሰረት አስይዞ ባለሙያዎችን ከማፍራት አኳያ አሜሪካ፣ እንግሊዝ (ዩኬ)፣ ካናዳ፣ ጀርመን፣ አውስትራሊያ፣ ዴንማርክ፣ ሲንጋፖር፣ ስዊዘርላንድ፣ ስዊድን እና ጃፓን እንደየቅደም ተከተላቸው ቀዳሚ ተጠቃሾች (ቶፕ ቴን) ናቸው።
ወደ ራሳችን እንመለስ።
ከ1952 ወዲህ በአሜሪካ የልማት ድርጅት “ፖይንት 4” ተብሎ በሚጠራው ፕሮግራም አጋዥነት ግብርና ተኮር የሆኑ የሁለተኛ ደረጃና የኮሌጅ ት/ቤቶች መቋቋማቸውን፤ በመቀጠልም ተከታታይነት ያላቸው በመንግሥታትና ዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች የሚደገፉ የግብርና ልማት እንቅስቃሴዎች ተግባራዊ (ግብረ መጽሔት፣ 01/2020) መደረጋቸውን ተከትሎ የግብርናውን ዘርፍ የማዘመን ተግባር መጀመሩ ይታወቃል።
ከግብርና ምርምር ኢንስቲቲዩት አካባቢ ግብርናን እንደ ጥናት መስክ ለመከታተል ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋሟት የሚገቡ ተማሪዎች ቁጥር እየቀነሰ ነው የሚል ስጋት መኖሩ እንዳለ ሆኖ፤ የትምህርት ሚኒስቴር “ዓመታዊ የትምህርት አብስትራክት” (2000 ዓ/ም (2007/08 እ.ኤ.አ) እንዳሰፈረው፣ በሀገር ውስጥ ቢያንስ 19 ዩኒቨርሲቲዎች/ኮሌጆች በመጀመሪያ ዲግሪ ደረጃ የግብርና ትምህርት ፕሮግራሞች ያሏቸው ሲሆን ሰባት ዩኒቨርሲቲዎች የግብርና የድኀረ-ምረቃ ፕሮግራሞችን ያካሂዳሉ:: በተጨማሪም፣ በግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስቴር እና በእያንዳንዱ ክልል የግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ ሥር የሚተዳደሩ 25 የግብርና ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ማሰልጠኛዎች አሉ:: ይኑሩን እንጂ ከ230 በላይ አግሪቴክ ኩባንያዎች ካሏትን ናይጄሪያም ሆነ መሰል ሀገራት ጋር መድረስ አልቻልንም።
ከእርዳታና ድጋፍ አኳያም የግብርናው ዘርፍ የራሱ የሆነ ታሪክ ያለው ሲሆን “ፋድ ለተለያዩ ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ የሚሆን ከ1980 (እ/ኤ.አ) ጀምሮ [እስከ 2012 (እአአ) ድረስ] በድምሩ 190 ሚሊዮን ዶላር ወጪ አድርጓል:: የኢፋድ እስትራቴጂ በኢትዮጵያ ላይ የሚያተኩረው ዘላቂ የቤተሰብ ምግብ ዋስትና ለማረጋገጥና በድህነት ያሉ የገጠር ሕብረተሰብ፤ በተለይም አነስተኛ አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች እንዲሁም በተለያዩ ደረጃዎች ያሉ ሴቶች ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችን መደገፍ ላይ ነው::”፣ “የዓለም የምግብ ፕሮግራም ላለፉት በርካታ አስርት ዓመታት በኢትዮጵያ የምግብ እርዳታ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ሲያደርግ ቆይቷል::” የሚሉትን ጨምሮ ድጋፍ ያደረጉ አካላት ብዛታቸው ብዙ ነው። ይሁን እንጂ ምርትና ምርታማነት እንደ ናፈቀን፤ ረሀብና ድርቅ በዙር እንዳሹን እስካሁን አለን። ይህም ግብርናን እና እንደገና ማዘመን፣ ፕሮፌሰር ፍሬው መክብብ እንደሚሉት ሪብራንድ በማድረግ መሥራት ይገባል።
“በደ/ብ/ብ/ሕ/ክ/ ከ8 ዩኒያኖች በ2010 (እ.ኤ.አ) የዓለም የምግብ ፕሮግራም 2200 ቶን ቦሎቄና 3900ቶን በቆሎ ለመግዛት እቅድ ነበረው:: ሆኖም ከግዢ ሂደት መዘግየትና ከአምራቾች ዩኒየኖች የአቅም ማነስ የተነሳ ሊገዛ የቻለው 1789 ቶን ቦሎቄና 2650 ቶን በቆሎ ብቻ ነው::” የሚለው ሪፖርት የግብርናችን ወደ ፊት አለመራመድ አንዱ ማሳያ ሊሆን የሚችል ሲሆን፤ “ኢትዮጵያ ዋነኛው የምግብ ፍጆታ እህል የብርዕ ሰብል ቢሆንም የሚመረተው ምርት የሀገሪቱን ፍላጐት የማያሟላ በመሆኑ ከውጭ ማስገባት የማይታለፍ ጉዳይ ነው::” የሚለውም እንደዛው። በመሆኑም ዘርፉን ሪብራንድ በማድረግ መሥራትና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ይገባል።
የቴክኖሎጂ ሚና
በሞፈር፣ ማረሻና ገበሬ ትከሻ ከሶስት ሺህ በላይ ዓመታትን ያስቆጠረውን ግብርናችንን ለማዘመን ሲታሰብ ለአፍታ እንኳን ሊዘነጋ የማይገባው መሰረታዊ ጉዳይ ቢኖር ዘመናዊ ቴክኖሎጂና አጠቃቀሙ ሲሆን፣ በተለይም የግብርና ባዮቴክኖሎጂ ከራሱ ከግብርናው ተለይቶ ሊታይ የሚገባው ሆኖ አናገኘውም።
በሚመለከታቸው ሁሉ በተደጋጋሚ ሲነገር፣ ሲገለፅና ሲገሰፅ እንደሚታየው፤ በዚህ ፀሀፊ ሳይቀር ሊብራራ እንደ ተሞከረው ኢትዮጵያ፣ እንደ አጠቃላይም አፍሪካ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ አኅጉር አይደለችም። እንደውም፣ የተገላቢጦሽ ሆኖ “ባዮቴክኖሎጂ ጎጂ ነው” በሚል የሀሰት ፕሮፓጋንዳ በመሸወድ ከተጠቃሚነት ውጪ ስትሆን እየተመለከትን ነው። እንደ ባለሙያዎች ተዘውታሪ አስተያየት እውነቱ ግን ይህ ሊሆን ባልተገባው ነበር።
“ቴክኖሎጂው በግብርና እና በጤናው ዘርፍ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው እና በከፍተኛ የስነ ሕይወት ደህንነት ሕግ እና መመሪያ ተከትሎ የሚካሄድ ቢሆንም አንድ አንድ ግለሰቦች፣ ቡድኖች እና ማኅበራት እንዲሁም የአካባቢ ጥበቃ ተቆርቋሪ ነን ባዮች ነገሩን በማክረር ልውጠ ህያዋን (Genetically Modified Organisms (GMO)) እና ሳይንሱ (Genetic Engineering (GE)) በዓለም ሕዝቦች ሙሉ በሙሉ እንደትልቅ ወንጀልና ስጋት እንዲታይ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።” የሚለው የባለሙያዎችና የግብርና ባዮቴክኖሎጂ ሳይንስ አራማጆች ምሬትም፣ ከሀሰት ፕሮፓጋንዳ አሰራጮቹ በበለጠ ለተሳሳተውን መረጃ እጅ በመስጠት ከቴክኖሎጂው ተጠቃማነት ራሳቸውን የሚያርቁቱ ላይ እየሆነ መጥቷል።
በዚሁ ጽሑፍ የጠቀስናቸው ጌታቸው (ዶ/ር) እንደደረሱበት ከሆነ በአሁኑ ወቅት 4ኛው የኢንዱስትሪ አብዮት ያስገኛቸው ቴክኖሎጂ ውጤቶች በመሬት አጠቃቀማችን ላይ የተጋረጠውን አደጋ በመቀነስ የምግብ አቅርቦትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ትሩፋቶች መሆናቸው ይታወቃል:: ነገር ግን በዘርፉ የተሰማሩ የሀገራችን ተቋሞች ዘመናችን ያፈራቸውን የቴክኖሎጂ ውጤቶች ባለመጠቀማችን በመከሰት ላይ ያለውን አደጋ በማባባስ ላይ መሆናችንን የተገነዘቡት አይመስልም::
በአፍሪካ ደረጃ፣ በተለይ እአአ ከ2019 ወዲህ፣ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ማምረት (biotech crops) ከጀመረች ወዲህ ከፍተኛ ምርትና ምርታማነትን እያስመዘገበች ሲሆን፤ በዋና ዋና ባዮቴክ ምርቶች (በቆሎ፣ ጥጥ እና ባቄላ (soybean)) 2.93 ሚሊዮን ሄክታር መሸፈን ተችሏል።
ሁሌም “የባዮቴክኖሎጂ ምርምር ውጤቶች ተደራሽ እንዲሆኑ ሊሠራ” እንደሚገባ የሚገልፁት የባዮቴክኖሎጂ ምርምር ሥራዎችን ከሚሠሩት ተቋማት መካከል አንዱ በሆነው ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ስር የሚገኙትን ፕሮጀክቶች ከሚመሩት አንዱ የሆኑት ታደሰ በዳዳ(ዶ/ር) እንደሚሉት ከሆነ ሳንቲም አሳዳጆች ለግብርናው ዘርፍ መዘመንም ሆነ የገበሬውን ሕይወት ከመለውጥ አኳያ አንድም አስተዋፅኦ አድርገው የማያውቁ ናቸው ዛሬ ባዮቴክኖሎጂ ጎጂ ነው እያሉ የሚያደነቁሩን። የእነዚህ ሰዎች ትኩረት ገንዘብ ማግኘት ላይ እንጂ ሕዝብና ሀገርን ያማከለ አይደለም። በመሆኑም እነዚህን ወገኖች ማዳመጥ ከጉዳት በስተቀር ጥቅም የለውም።
“የውሃ ሀብት አጠቃቀም ከግብርናው ዘርፍ አኳያ” በሚል ርዕስ በግብርና ሚኒስቴር እና በአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን በጋራ በተዘጋጀ ጥናት ላይ እንደ ሰፈረው በግብርና ሥራችን በአጠቃላይና በተለይም ደግሞ የመስኖ ልማት ተግባራችን ዘመኑ ባፈራው ቴክኖሎጂ እየታገዘ ተገቢውን የእድገት እርከን እንዲያስጨብጠን ሙያችን፣ ቁሳዊ ሀብታችንና ትኩረታችን መቀናጀት ያለባቸው ጊዜ ቢኖር አሁን ነው።
የዲጅታል ቴክኖሎጂ ዕውቀትና ክህሎት ያላቸው ወጣቶች ሀሳባቸውን ወደ ተግባር መቀየር እንዲችሉ የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የሚገልፀው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መረጃ “በኢትዮጵያ ወጣቶች የዲጅታል ቴክኖሎጂ ዕውቀትና ክህሎት እንዲኖራቸው ማድረግ ብቻ ሳይሆን ያገኙትን ዕውቀት ወደ ተግባር የሚቀይሩበት ዕድል መፍጠር ይገባል” ሲልም ለጉዳዩ አፅንኦት ይሰጣል።
የዩኒቨርሲቲና ኢንዱስትሪ ትስስርን የሚያጠናክሩ ጥናትና ምርምሮችን ማጎልበት በሚቻልበት ሁኔታና በግብርናው ዘርፍ ያለውን የሰው ሰራሽ አስተውሎት አጠቃቀም አስመልክቶ በተካሄደ የ ውይይት መድረክ ላይ የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፈቶ ኢስሞ (ዶ/ር) እንደተናገሩት የግብርናውን ዘርፍ የሚያሳድጉ የሰው ሰራሽ አስተውሎት መተግበሪያዎች ጥቅም ላይ ማዋል አስፈላጊ ነው።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ንግግር የሰው ሰራሽ አስተውሎት (ሮቦት) በትራክተር ማረስ፣ የመሬት ዝግጅትና የመሬት ጥንካሬና ልስላሴን የሚለይ፣ አረም የሚያርም፣ ማዳበሪያ መጥኖ የሚጨምር እንዲሁም አጨዳና ለቀማ የሚሠራ መሆኑን አስረድተው ለዘርፉ ልማት መጠቀም ወሳኝ ነው። በመሆኑም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ኢንዱስትሪዎችን ጨምሮ የግብርናው ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ቴክኖሎጂዎቹ ጥቅም ላይ እንዲውሉ መሥራት አለባቸው።
ባለፈው ዓመት (ጥር) በተካሄደው በዚሁ መድረክ ላይ የባዮ እና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ካሳሁን ተስፋዬ (ዶ/ር) እንደ ተናገሩት በግብርናው ዘርፍ ያሉ የቴክኖሎጂ አማራጮች እየተበራከቱ በመምጣት ላይ ሲሆኑ፤ ቴክኖሎጂዎቹ በግብርና ምርቶች ላይ የሚያጋጥሙ በሽታዎችን የሚለዩና መፍትሔ የሚያመላክቱ ቴክኖሎጂዎች የሰውን ጊዜና ጉልበት መቆጠብ የሚያስችሉ ናቸው። በመሆኑም በግብርናው ዘርፍ ሰው ሰራሽ አስተውሎትን ይበልጥ ለመጠቀም የቅንጅት አሠራርን የሚጠይቅ በመሆኑ የሚመለከታቸው ሁሉ በጋራ ሊሠሩ ይገባል።
ምን ይደረግ
ጌታቸው (ዶ/ር) “የግብርና እና የገጠር ልማት ትራንስፎርሜሽን በኢትዮጵያ” ላይ ሰፋ አድርገው እንደዘረዘሩት፤
ኢትዮጵያ ከ10 ሺህ ዓመታት በፊት በኒዮሊቲክ አብዮት ዘመን ጀምሮ የበርካታ የአዝእርትና እንስሳት ሀብት መፍለቂያ ነች:: ከዚያን ዘመን ጀምሮ የሀገራችን ገበሬ በትግበራ ያካበተውንና በተፈጥሮ የተሰጠውን ችሎታ በመጠቀም በዘመናዊና ቴክኖሎጂ ወለድ በሆኑ መሳሪያዎች ሳይታገዝ፣ በአንድ በኩል በየጊዜው የአፈሩ ለምነት እየቀነሰ በሌላ በኩል ቁጥሩ እየናረ የሚሄደውን ሕብረተሰብ በመመገብ ላይ ይገኛል:: ይህንንም ግዴታ ለመወጣት አርሶ አደሮች በሚያደርጉት የእርሻ መሬት ማስፋፋት የተፈጥሮ ሀብትን መመናመንና የስነ-ምሕዳር መዛባትን በማያስከትሉ በዘላቂ ሕልውናቸው ላይ አደጋን ሊጋብዙ ችለዋል:: ለሀገራችን ግብርናና የገጠር ልማት ትራንስፎርሜሽን አለመሳካት ዐበይት ምክንያቶቹ የምናልመውን ትራንሰፎርሜሽን እውን ለማድረግ የሚያስችል ዘላቂና ትውልድ ተሻጋሪ ቁርጠኝነት አለመኖር፣ የሕገ-መንግሥትና የሕግ ማሕቀፍ ችግር መኖር፣ የመንግሥት ተሳትፎ የግሉን ዘርፍ ሚና መተካቱ፣ የግብርና ሜካናይዜሽን አለመስፋፋትና ዘመናዊ የግብርና ግብዓቶችን በበቂ ሁኔታ ማቅረብ አለመቻል፣ ውጤታማና ተጠያቂነት የሰፈነበት ተቋማዊ ድጋፍ ማነስ፣ የግብርናና ገጠር ልማት ተኮር የሆነ የፋናንስና ብድር አቅርቦት አለመኖር፣ እንዲሁም የአካባቢና ስነ ምሕዳር መሸርሸር ናቸው።
የግብርና ሚኒስቴርን ጨምሮ ቁልፍ የሆኑ የሚኒስቴር መ/ቤቶችን በማዋቀር የሀገራችንን ግብርና የማዘመን ተግባሩ የተጀመረው ዘግይቶ፣ በ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ቢሆንም፤ ምንም እንኳን፣ በሂደት ምቹ ሁኔታዎችና መሻሻሎች መኖራቸው ቢነገርም፤ ምርትና ምርታማነት መጨመሩ በተደጋጋሚ ሪፖርቶች ቢገለፅም • • • መንሸራተቶች መኖራቸው፣ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ላይ ክፍተቶች/ተግዳሮቶች እንዳሉ ይሰማል፤ ይታወቃልም።
ግብርናችን በአብዛኛው በዝናብ ላይ በመመርኮዙ፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችና ግብዓት አጠቃቀሙ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ምክንያት ምርታማነቱም አነስተኛ በምክንያትነት ሲገለፅ ቆይቷል። ይህም ከራሱ፣ ከአርሶ አደሩና ቤተሰቡ ገቢ ጀምሮ የሀገር ኢኮኖሚ ዝቅተኛ፤ የምግብ ዋስትና ችግርም ስር የሰደደ እንዲሆን አድርጓል::
በተለይም በዘርፉ (በተለይም በደጋማው የሀገሪቱ አካባቢዎች) ዋንኛ ችግር የሆነውን አፈር መሸርሸር በዘላቂነት መፍታት አጣዳፊ ሥራ ይሆን ዘንድ የችግሩ ስፋት ራሱ ያመላክታልና ፍጥነት የግድ ይሆናል።
በመጨረሻም፤
«ኢትዮጵያ በምግብ ራስዋን እንድትችል ግብርና ሪፎርም ወይም መንግሥት በግብርና ላይ ያለውን ፖሊሲ ትኩረት ሊያደርግበት ይገባል። ምሁራኑ ፖሊሲው አመቺ ስላልሆነላቸው ተግባራዊ ማድረግ አልቻሉም የሚል እምነት አለኝ።» የሚለውና ባለፈው ወር በግብርና ሙያ በጀርመን/ቦን ከተማ ከሚገኝ ዩኒቨርሲቲ በከፍተኛ ውጤት የዶክትሬት ማዕረጉን ያገኘው ደረጀ ታምሩ (ዶ/ር) ከዶቸቨሌ ጋር በነበረው ቆይታ እንደተናገረው “በ21ኛው ክፍለ ዘመን ገበሬው ማለዳ በሬዎቹን ይዞ፣ ሞፈርና ቀንበሩን ተሸክሞ ወደ ግብርና ሲሰማራ ማየት የሚያሳፍር ነው። ይህ ከግብርና ምሁራን፣ በተለይም ከውጭ ሀገር ምሁራን ጋር በጉዳዩ ላይ ማውራት የሚያሳፍር ነው።” በመሆኑም ግብርናውን ማዘመን የዘገየ ከመሆኑ በስተቀር ለነገ የሚባል አይደለም።
በየደረጃው ያሉ የሥራ ኃላፊዎችም ሆኑ በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚስማሙበት ከሆነ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን የመሬትና ውሃ አስተዳደር፣ እንስሳት እና የተፈጥሮ ሃብት ልማትን፣ የእርሻ ግብዓት አጠቃቀም፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን መጠቀም፤ እንዲሁም የገጠር ፋይናንስ አቅርቦትንና የመሳሰሉትን ቁልፍ ተግባራት ማዕከል ያደረጉ ሥራዎችን መሥራት የግድ ይሆናል። ሰሞኑን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የግብርና ስትራቴጂክ ትግበራ እቅድን አስመልክቶ የተደረገ ውይይት ላይ “የግብርናውን ዘርፍ ማዘመንና ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችል ስትራቴጂክ አሠራርን መከተል ይገባል” የሚለው የውይይቱ ማዕከላዊ ጭብጥ ሆኖ እንደ ነበረም ግንዛቤ መያዝ ያስፈልጋል። የኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኃይሉ ዳዲ (ዶ/ር) እንደሚሉት ከሆነ፣ የግብርና ባዮቴክኖሎጂን በመጠቀም የሰብልን ምርታማነት በከፍተኛ ደረጃ መጨመር ይቻላል፤ ይገባልም::
እንደ ጌታቸው ዲሪባ (ዶ/ር) ምክረ-ሀሳብ ከሆነ ደግሞ፣ የግብርናውን ዘርፍ አፈጻጸም ከአምስቱ መለኪያዎች አንጻር መገምገም ተገቢ ሲሆን፣ እነሱም የዜጎችን የምግብ ፍላጎት ማርካት፣ የሀገር ውስጥና የውጭ ማኅበራዊ ደህንነትን ማሳካት፣ በግብርናው ዘርፍ መዋዕለ ንዋይን ማፍሰስና ማሽነሪዎችን መተካት መቻል፣ ሊያጋጥም የሚችል ድንገተኛ አደጋን የመቋቋም ችሎታን መገንባት፣ እና ጥሬ ሀብትን ማፍራት ናቸው::
እኛም በዚህ መሰረት ከሠራን በአሁኑ ሰዓት አሜሪካንን በማስከተል በዘርፉ ቁጥር አንድ ከሆነችው፣ ከዓለም ታራሽ መሬት 7% (108 ሚሊዮን ሄክታር አካባቢ) የሆነውን ከምትሸፍነው፤ ከአጠቃላይ የዓለም ሕዝብ 22% የሆነውን ከምትቀልበው፤ በዓለም ካሉት ሀብታም ገበሬዎች ቁንጮውን ሊዩ (Liu Yonghao እና ሌሎችንም) ካፈራችው ቻይናም ሆነ በከፍተኛ ደረጃ ባዮቴክኖሎጂን በመጠቀሟ ምክንያት 178.7 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር (በ2023) የሚያወጡ የግብርና ምርቶችን ለውጭ ገበያ ካቀረበችው አሜሪካ እኩል የማንሆንበት፤ ከእነ ብራዚል፣ ሕንድ፣ ሩሲያ፣ ፈረንሳይ፣ ሜክሲኮ፣ ጃፓን፣ ጀርመን እና ቱርክ (ወንድወሰን እሸቴ፣ በ2024-በዓለም ላይ 10 ምርጥ የግብርና አምራች ሀገራት፣ 2025) ተርታ የማንሰለፍበት ምክንያት የለም፤ ለዚህ ደግሞ ከግብርናው መስክ ሳይንቲስቶቻችን የኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እና መሰል ተቋማት ሚና ወሳኝ መሆኑን፤ በ2030 ዓ.ም የግብርናውን መዋቅራዊ ሽግግር በማረጋገጥ በገጠር መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣትና ለሀገር ብልፅግና ጉልህ ሚና የሚጫወት ሆኖ የማየት ርዕይን የያዘውና ሚያዝያ 17/2016 ዓ.ም በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፀደቀው አዲሱ “የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ” የሴክተሩን ችግሮች ይፈቱታል ተብሎ የሚጠበቅ መሆኑን ከስሩ በማስመር ጽሑፋችንን እናጠናቅቃለን።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 5 ቀን 2017 ዓ.ም