ደረጃውን የጠበቀ የአትሌቲክስ ቻምፒዮና ይገባናል!

በአህጉራዊም ሆነ በዓለም አቀፍ የስፖርት ውድድር መድረኮች ተሳትፎ የኢትዮጵያ ዋነኛው ብሔራዊ የኩራት ምንጭ የአትሌቲክስ ስፖርት ነው። በወንዶች የአበበ ቢቂላን ፈለግ እንዲሁም በሴቶች የደራርቱ ቱሉን ፈለግ የተከተሉ በርካታ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች አትሌቶች በትላልቅ የውድድር መድረኮች ላይ አስደናቂ ስኬቶችን በማስመዝገብ የሀገራቸውን ስም እና ሰንደቅ ደጋግመው ከፍ ማድረግ ችለዋል። ዛሬም ቢሆን ኢትዮጵያ መሰል የአትሌቲክስ ጀግኖችን አላጣችም።

እነዚህ እልፍ ጀግና አትሌቶች መነሻቸው ከየትም አይደለም፣ ከሀገር ውስጥ ውድድሮች እንጂ። የሀገር ውስጥ ውድድሮችን ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ማካሄድ ግን ዛሬም ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ትልቁ ፈተና ሆኖ ቀጥሏል። ከሚያዝያ 28 እስከ ግንቦት 03 ቀን 2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የተካሄደውን ዕድሜ ጠገቡ 54ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ደረጃውን የጠበቀ ትራክ(መም) አለመኖሩን ተከትሎ የሀገሪቱን ትልቁ ቻምፒዮናን የስፖርት ቤተሰቡ ብዙ ጥያቄ እንዲያነሳበት አድርጓል።

ቻምፒዮናው ገና ሳይጀመር ከቀናት በፊት ይካሄድ ወይስ ይቅር በሚል የፌዴሬሽኑን ሥራ አስፈፃሚዎች ጭምር ለሁለት ከፍሎ ሲያነጋግር ነበር። ለዚህም ዋነኛው ፈተና ቻምፒዮናው እጅግ በተጎዳው የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ መም ተለጣጥፎና ተጠጋግኖ መካሄዱ ሲሆን፣ መሙ በተለይም የመጀመሪያው የአትሌቶች መሮጫ መስመር ከጥቅም ውጭ መሆኑ ጥያቄ አስነስቷል። ይህም አትሌቶችን ለጉዳት ከማጋለጥ በተጨማሪ ቻምፒዮናው ደረጃውን የጠበቀ እንዳይሆን ያደርገዋል በሚል አስተያየት ከስፖርቱ ቤተሰብ ቅሬታ ሲቀርብ ቆይቷል። በዚህም ቻምፒዮናው ቢሰረዝ ወይም የተሻለ መም ያለባቸው ከተሞች ላይ ይካሄድ የሚ ሉ ድምፆች ተሰምተዋል።

ኢትዮጵያን በሚያክል በአትሌቲክስ ታላቅ ታሪክ፣ ዓለምን ያስደመሙ ጀግኖች አትሌቶችን ያፈራች ሀገር በዚህን መሠሉ ደረጃውን ያልጠበቀና የዓለም አትሌቲክስን መስፈርት በማያሟላ ትራክ እንቁ አትሌቶቿን ማወዳደር አሳፋሪ ነው። ይሄ አትሌቲክሱ ወዳልሆነ መንገድ እየተጓዘ እንደሚገኝ አንዱ ማሳያ ነው። በትራክ ውድድር የዓለም መሪ የሆነች ሀገር እንዴት ነው ደረጃውን የጠበቀ ትራክ ችግር ሊሆንባት ይችላል?። የሀገሪቱ ትልቁ ቻምፒዮና በፍፁም በአዲስ አበባ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ በተጠጋገነ ትራክ በታጠፈ መም መካሄድ አልነበረበትም፤ ከዚህ ይልቅ የተሻለ ትራክ ወዳላቸው ድሬዳዋና ባሕርዳር መካሄድ ነበረበት።

በየትኛውም መስፈርት ይሄ በርካታ ታላላቅ አትሌቶች ያለፉበት ትልቅ ቻምፒዮና በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ትራክ ላይ መካሄድ አልነበረበትም። ፌዴሬሽኑ ቻምፒዮናውን በሌሎች ከተሞች ለማካሄድ ምክንያት ያደረገው የበጀት ጉዳይ ነው። ሌሎች ትንንሽ ውድድሮችን ከአዲስ አበባ ውጭ የሚያካሂድ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሀገሪቱን ትልቁን ውድድር በክልል ከተሞች ለማካሄድ በጀት የለውም ማለት ስላቅ ነው። እሺ ፌዴሬሽኑ ገንዘብ ከሌለው እንኳን በመንግሥት ሊደገፍ ይገባ ነበር። ይሄም ካልሆነ ደግሞ ውድድሩ መተላለፍ ወይም መቅረት ነው የነበረበት። ምክንያቱም ይሄ የሀገሪቱ ትልቁ ውድድር ነውና።

በዓለም ላይ ስማችንን የሚያስጠራውን አትሌቲክስ ይቅርና ለእግር ኳስ ብሔራዊ ቡድናችን ለሴካፋ ወይ ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በሚል ብዙ ዶላሮች ይፈስ የለም እንዴ? ሞሮኮ ድረስ ሄደው በብዙ ሺህ ዶላሮች እየፈሰሱ ሆቴል ተቀምጠው ውድድሮች እንዲካሄዱ መንግሥት ያግዝ የለም እንዴ? ታዲያ በትራክ ችግር አትሌቱ እየተሰቃየ ለምን ዝምታ ተመረጠ? ለምንስ መፍትሔ የሚሰጥ አካል ጠፋ? የስፖርት ቤተሰቡ ጥያቄ ነው።

ቻምፒዮናው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቻምፒዮና እንጂ የአዲስ አበባ አለመሆኑ ይሰመርበት። ከአዲስ አበባ ውጭ ቢካሄድ ያለውን ጥቅምም መለስ ብሎ መፈተሹ ተገቢ ነው። ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ እድሜ ያስቆጠረው አንጋፋው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቻምፒዮና በረጅም ዓመታት ጉዞው አዲስ አበባ ከተማ ላይ ብቻ ተወስኖ ሲካሄድ ቆይቷል። በሁለት አጋጣሚ ብቻ ከአዲስ አበባ ወጥቶ 2005 ዓ.ም ላይ በአሰላ አረንጓዴው ስቴዲየም መም ላይ ተካሂዷል። በዚያ ቻምፒዮናም በአንድ የኢትዮጵያ ክብረወሰን ብቻ ነበር የተሻሻለው። በተረፈ በተለያዩ ውድድሮች የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ክብረወሰኖች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የተመዘገቡት አዲስ አበባ ላይ ነበር።

ለሁለተኛ ጊዜ ከአዲስ አበባ ውጭ የተካሄደው 51 ቻምፒዮና ሲሆን በሀዋሳ ነበር የተከናወነው። የአዲስ አበባ አንጋፋው ስቴዲየም በእድሳት ላይ መገኘቱ ከተማዋ ትልልቅ ውድድሮችን እንዳታስተናግድ እንቅፋት የመሆኑን ያህል ከአትሌቲክስ አንጻር ይዞት የመጣው መልካም አጋጣሚም ይህ ነበር። ይህም በቻምፒዮናው በአትሌቲክስ ፈጣን ሰዓት ለማስመዝገብ በሚረዳ የአየር ጸባይ እንዲካሄድና ለረጅም ዓመታት ሳይደፈሩ የቆዩ ክብረወሰኖች በብዛት እንዲሰበሩ ማድረጉ ይታወቃል።

በዚያ ቻምፒዮና ከባሕር ጠለል ከ2ሺ ሜትር በላይ በምትገኘው ቀዝቃዛዋ አዲስ አበባ ወጥቶ ከባሕር ጠለል ከ1500 ሜትር በላይ በምትገኘውን ሞቃት የአየር ንብረት ባላት ሀዋሳ በመካሄዱ ለረጅም ዓመታት ያልተደፈሩ በርካታ ክብረወሰኖች ሊሻሻሉ ችለዋል። በዚህ ቻምፒዮና ለ18 ዓመታት ያልተሰበረው አሁን ላይ ፌዴሬሽኑን በፕሬዚዳንትነት የሚመራው የስለሺ ስህን የወንዶች 10ሺ ሜትር ክብረወሰንን ጨምሮ ለ16 ዓመታት ያልተደፈረው የሴቶች መቶ ሜትር ክብረወሰኖች ተሻሽለዋል። በ10ሺ ሜትር በሁለቱም ጾታ፣ በዲስከስ ውርወራ በሁለቱም ጾታ፣ በ20 ኪሎ ሜትር ርምጃ ውድድር በሁለቱም ጾታ አዳዲስ ክብረወሰኖች ተሻሽለዋል። የወንዶች ስሉስ ዝላይ፣ የሴቶች መቶ ሜትር፣ የወንዶች 3ሺ ሜትር መሰናክል ውድድሮችም አዲስ ክብረወሰን ያገኙ ነበሩ።

ባለፉት በርካታ ዓመታት በተለያዩ እርከኖች በሚካሄዱ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቻምፒዮናዎች በርካታ ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ የበላይነት የነበራቸው መከላከያና ኦሮሚያ ክልል ብቻ አልነበሩም በዚያ ቻምፒዮና ብርቱ ፉክክር ሲያደርጉ የነበሩት። በተለያዩ ውድድሮች ሁለቱ የቻምፒዮናው አውራዎች ያስመዘግቡ የነበረው ድል ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነው በቀረቡት እንደ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክና ደቡብ ፖሊስ በመሳሰሉ ክለቦች ሲነጠቁ ታይቷል። ታላላቅ ዓለም አቀፍ ክብር የተሰጣቸው የዓለም ቻምፒዮኖች ጭምር በዚህ ቻምፒዮና በአዳዲስ ቻምፒዮኖች ሲሸነፉ ታይተዋል።

ከክብረወሰኖቹ ባሻገር በተለያዩ ውድድሮች በርካታ አትሌቶች ያስመዘገቧቸው ሰዓቶች በዓለም አቀፍ ውድድሮች ለመሳተፍ የሚያስችላቸው እንደሆነ መታዘብ ይቻላል። ይህም ኢትዮጵያ ኦሊምፒክን ጨምሮ ለታላላቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮች አትሌቶችን ለሰዓት ማሟያ(ሚኒማ) ወደ ኔዘርላንድስ ሄንግሎና ሌሎች ከተሞች በመውሰድ የማጣሪያ ውድድሮችን እንዲያከናውኑ የሚደረገው የተለመደ አሠራር ጥናቶች ተደርገው በሀገር ውስጥ ሊሆን እንደሚችል እንደ ሀዋሳ ያሉ የአየር ንብረቶች ፍንጭ የሰጡበት ነው።

የኢትዮጵያን አትሌክስ ውድድሮች ለብዙ ዓመታት የተከታተሉ የስፖርት ቤተሰቦች የፌዴሬሽኑ የሀገር ውስጥ የመም፣ የሀገር አቋራጭ እና የጎዳና ላይ ውድድሮች ዓለም አቀፉን ደረጃ በጠበቀ ጥራት ሲካሄዱ ለማየት አልታደለም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ዓለም አቀፉን ደረጃ በጠበቀ ጥራት የተካሄዱ የስታዲየም ውድድሮችን ማየት የተቻለው ሁለት ጊዜ ብቻ ነው፡፡ እነሱም እ.አ.አ. በ2008 ዓ.ም. እና በ2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ስታዲየም የተስተናገዱት የአፍሪካ አትሌቲክስ ቻምፒዮና እና የአፍሪካ ታዳጊዎች አትሌቲክስ ቻምፒዮና ናቸው፡፡

አትሌቲክስ አፍቃሪዎች በእነዚያ ውድድሮች ላይ የነበረው የውድድር አፈፃፀም እና የጥራት ደረጃ በኢትዮጵያ ቻምፒዮና ላይም በተመሳሳይ ጥራት እና ደረጃ ሲከናወን የማየት ጉጉት የነበራቸው ቢሆንም ምኞታቸው እውን ሳይሆን ዓመታት አልፈዋል። በአጫጭር ርቀቶች እና በሜዳ ላይ የሀገር ውስጥ ውድድሮች የሚሳተፉ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ደረጃውን የጠበቀ የውድድር ተሞክሮ የሚያገኙበት ዕድል ሳይፈጠርላቸው ይሄን ያህል ጊዜ ማለፉ በጣም አሳዛኝ ነው፡፡

ኬንያውያን ከእኛ በኋላ እ.አ.አ. በ2010 ዓ.ም. የተካሄደውን 17ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ሲያስተናግዱ እኛ በነበርንበት ተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ነበሩ፡፡ አሁን ግን በዚህ ረገድ እጅግ የተሻለ ሥራ መሥራት መቻላቸውን በተግባር እያሳዩን ይገኛሉ፡፡ ስለዚህ ፌዴሬሽኑ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ውድድሮች ማካሄድ እንዴት እንደሚቻል ለማወቅ ሩቅ ሳይኬድ ጎረቤት ኬንያውያን ልምዳቸውን እንዲያካፍሉት መጠየቅ ይችላል፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ስፖርትን ወደኋላ እየጎተቱት ከሚገኙ ነገሮች መካከል በዋናነት ትኩረት ተሰጥቶበት ሊሠራበት የሚያስፈልግ ነገር የሀገር ውስጥ ውድድሮችን በዓለም አትሌቲክስ ደረጃ ማካሄድ ነው፡፡ በሀገር ውስጥ የሚካሄዱ ውድድሮች በዓለም አትሌቲክስ ደረጃ አለመካሄድ የኢትዮጵያውያን አትሌቶችን በሙሉ በተለይም የአጭር ርቀት እና የሜዳ ላይ ተግባራት ተወዳዳሪዎች ልፋት ተገቢውን እውቅና እንዳያገኝ እያደረገ የሚገኝ ችግር ነው፡፡ ይህ ችግር ወደ ረጅም ርቀቶችም መምጣቱን የዘንድሮው ቻምፒዮና አሳይቶናል።

በ10ሺ ሜትር በወንዶች 82 በሴቶች ደግሞ ከ70 በላይ አትሌቶች መሳተፋቸው ብዙዎችን ያስገረመ ነው። በ10ሺ ሜትር ከ80 በላይ አትሌቶችን መም 1 በማይሠራበት ትራክ ላይ ማስሮጥ የትም ታይቶ አያውቅም። ያውም ደረጃውን ባልጠበቀ ትራክ ላይ ይሄ ቀልድ ነው። በዓለም አቀፉ ሕግ በ10ሺ ከ25 እና ከ30 አትሌቶች በላይ ማስሮጥ አይቻልም። 80 እና 70 አትሌቶችን በአንዴ የሚወዳደሩት የጎዳና ላይ ውድድር፣ ሀገር አቋራጭና ማራቶን ነው። ይሄ አሠራራችን ባሕላዊ እየሆነ ወደኋላ እየተመለስን እንደሆነ ማሳያ ነው። በዚህ ውስጥ አልፈን እንዴት ነው በዓለም አቀፍ መድረክ ውጤት የምንጠብቀው?።

ሌላው መረሳት የሌለበት ጉዳይ ቢያንስ በዓለም ደረጃ (በወርልድ ራንኪንግ) ነጥብ ለማስመዝገብ የሚረዱ ዋና ዋናዎቹን የሀገር ውስጥ ውድድሮች ውጤት በኤሌክትሮኒክስ የሰዓት መቆጣጠሪያ የሚደገፍ ለማድረግ መሥራት እጅግ አስፈላጊ መሆኑ ነው፡፡ የውድድሮችን ውጤቶች በዘመናዊ እና ዓለም አቀፉን መለኪያ በሚያሟላ መልኩ አለመያዝ በአህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮች ላይ ለተሳትፎ የሚያበቁ ውጤቶችን (የዓለም ደረጃዎች ነጥብ) በማስመዝገቡ ረገድ የሚኖረው አሉታዊ ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው፡፡

የዓለም አትሌቲክስ እ.አ.አ. በዲሴምበር 2022 ዓ.ም. ለብሔራዊ ፌዴሬሽኖች በላከው መልእክት የትኛውም ዓይነት ውድድሮች በዓለም አትሌቲክስ የውድድር ካላንደር ላይ እንዲመዘገቡ እስካልተደረጉ እና ውጤታቸው በአወዳዳሪው አካል እስካልተላከለት ድረስ ውጤቶቹ በድረ ገፁ ላይ እንደማይሰፍሩ እና ለማንኛውም የስታትስቲክስ ዓላማው (የመግቢያ ደረጃዎች፣ የዓለም ደረጃዎች፣ ከፍተኛ ዝርዝሮች፣ ሪኮርዶች፣ ወዘተ) እንደማይጠቀማቸው አሳውቋል። መልዕክቱ ከተላከ በኋላ ባለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በኩል ለዓለም አትሌቲክስ የተላከ ብቸኛ የውድድር ውጤት እ.አ.አ. ከጁላይ 02 እስከ 06 /2024 የተካሄደው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ቻምፒዮና ውጤት ነው፡፡ ስለዚህ ፌዴሬሽኑ በዓመቱ ውስጥ የሚያደርጋቸውን ውድድሮች በወርልድ አትሌቲክስ የውድድር ካላንደር ላይ እንዲመዘገብ በማድረግ እና ውጤቶችን በሰዓቱ በመላክ የአትሌቶቹ ልፋት ዓለም አቀፍ ዕውቅናን እንዲያገኝ የመሥራት ኃላፊነትም እንዳለበት መዘንጋት የለበትም፡፡

ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው። በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።

ልዑል ከካምቦሎጆ

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You