እምነት እንደ ወታደር

ወታደር ምድራዊና ሥጋዊ የሰው ልጅ ፍጡር ነው። ሁላችንም በዓይናችን የምናየው፣ ምናልባትም የቤተሰባችን አባል የሆነ ነው። ይህ ወታደር ግን ለሰው ልጆች ሲል በመስቀል ላይ ከተሰቀለው ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ይመሳሰልብኛል። ወታደርን ምሳሌ ያደረኩት በሁለት ምክንያት ነው። አንድም ሃይማኖታዊ ላለማድረግ፣ ሁለትም በሰው ልጅ ደረጃ እንኳን እንዲህ አይነት ዋጋ ይከፈላል የሚለውን ልብ እንድንለው ነው።

ወታደር ሰው ነው፤ ሰው ሆኖ ሰዎችን ለማዳን ይሞታል። የወታደር ሞት ‹‹መስዋዕትነት›› የሚባለውም ለዚያ ነው። መሰዋት ማለት ለሌሎች መሞት፣ ለሌሎች ዋጋ መክፈል ማለት ነው። ሞቶ ማዳን ማለት ነው።

ሰሞኑን በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ሰሞነ ሕማማት ነበር። በሰሞነ ሕማማት የሚከለከሉ ብዙ ሃይማኖታዊ ነገሮች አሉ። ክፉ ነገር መናገር፣ ሰዎችን ማስቀየም፣ እንደ አልኮል ያሉ ነገሮችን መጠጣት… የመሳሰሉት በጥብቅ የተከለከሉ ናቸው። እርግጥ ነው እነዚህ ነገሮች በየትኛውም ጊዜ የተከለከሉ ናቸው፤ ዳሩ ግን በሰሞነ ሕማማት ደግሞ የበለጠ ይከለከላሉ፡፡

የሃይማኖት አባቶች ሁሌም የሚያስተምሩት ቢሆንም፤ የእምነቱ ተከታዮች ግን በሰሞነ ሕማማት ፆም፣ ጸሎትና ስግደት ላይ ስለሚሆኑ የሠሯቸውን ጥፋቶች ሁሉ ‹‹ይቅር በለን!›› የሚሉበት ነው። ሰሞነ ሕማማት የተጣላ ሁሉ ይቅር የሚባባልበት ነው። በሰሞነ ሕማማት የውስጥ ቂም ይዞ አይታለፍም። ከልብ ይቅር የሚባባሉበት የስግደት ሳምንት ነው።

ለመሆኑ የተከፈለውን ዋጋ ልብ ብለነው ይሆን? የእምነቱ ተከታዮች በእምነቱ አስተምሕሮ እና በተከፈለው ዋጋ ልክ ለሰው ልጆች መከባበር ተሠርቶበት ይሆን?

ከሰሞነ ሕማማት አንዱ ፀሎተ ሐሙስ ነው። በዚህ ዕለት የእግር እጥበት ሥነ ሥርዓት ይከናወናል። እግር የሚያጥቡት ትልልቅ አባቶች ናቸው። የሚያጥቡት ደግሞ የተራውን ምዕመን ነው። ይህ የሚያሳየን አገልጋይነትን ነው። በዓለማዊ ሕይወት እንኳን መርሕ ብናደርገው ክብር ነው። አገልጋይነት የትሑት ሰው መለያ ነው፤ የሥልጡን ሰው መገለጫ ነው።

አገልጋይነት በራስ መተማመን ነው። የውስጥ ሰላም ያላቸው ሰዎች የሚያደርጉት ነው። እኔ የበላይ ነኝ ብሎ የሚኮፈስ ግን በመንፈሳዊ አስተምሕሮ ብቻ ሳይሆን በዓለማዊ የሥነ ልቦና ባለሙያዎችም ተቀባይነት የለውም። እልህኛ፣ ቁጡ፣ እና በቀለኛ የሚሆኑ ሰዎች በራሳቸው የማይተማመኑ፣ የሆነ ነገር የጎደላቸው መስሎ የሚታያቸው ሰዎች ናቸው። አገልጋይ ሰዎች ግን ሌሎችን በማገልገላቸው ደስታ የሚሰማቸው ንፁሕ አማኞች ናቸው። ስለዚህ ከፀሎተ ሐሙስ አገልጋይነትን እንማራለን፡፡

የሰሞነ ሕማማት የመጨረሻው ሳምንት ስቅለት ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሲል የተሰቀለበት ማለት ነው። ራስን አሳልፎ የመስጠት ምሳሌ ይሆነናል። መግቢያ አካባቢ ወታደርን ምሳሌ አንስተናል። ወታደር ራሱን አሳልፎ የሚሰጠው የሰው ልጆችን ለማዳን ነው። ታዲያ እኛ ሰዎች ለምን ክፉዎች እንሆናለን? እስኪ ራስ ወዳድነታችንን ልብ እንበለው!

በንግድ ዓለም ውስጥ ብዙ አይነት ማጭበርበሮችን እናያለን። የሰው ልጅ ጤና ላይ ጉዳት የሚያደርስ ነገር ይደረጋል። ለምሳሌ፤ እንጀራ ውስጥ ባዕድ ነገር ቀላቅለው የሚሸጡ ብዙ አማኞች አሉ። የሚበላ ነገር ውስጥ ባዕድ ነገር መቀላቀል አደገኛ የሕሊና ወንጀል ነው። ታዲያ ምነው ከኢየሱስ ክርስቶስ እና ከወታደር መማር አቃተን?

ወታደር ሀገርና ሕዝብ የሚያድነው ሽንት እየጠጣ ነው። ቅጠል እየበላ ነው። ሌሎች ሰዎች ጣፋጭ ምግብ ይበሉ ዘንድ ቅጠል ሲበላ፣ ሌሎች በውስኪ ይራጩ ዘንድ ሽንት ሲጠጣ፣ ሌሎች የሚያነጥር ፍራሽ ላይ ይተኙ ዘንድ ድንጋይና እሾህ ላይ ሲተኛ፤ ታዲያ እኛ ምነው በተቃራኒው አደረግነው? እኛ ይመቸን ዘንድ ሌላውን መጉዳት፣ እኛ እናተርፍ ዘንድ የሌላውን ጤና ማቃወስ፣ እኛ ሀብታም እንሆን ዘንድ ሌላውን ድሃ ማድረግ፣ እኛ እንበላ ዘንድ ሌላውን ማስራብ ከየት ያመጣነው ጭካኔ ይሆን?

የሰሞነ ሕማማት የመጨረሻው ሳምንት በሆነው በዕለተ ስቅለት ከፍተኛ ስግደት ይሰገዳል። ምንም እንኳን ሳምንቱን ሙሉ የሚሰገድ ቢሆንም በዚህ ዕለት ግን አማኞች ለሠራነው ጥፋት ሁሉ በሚል በፆም ጸሎት ብዙ ይሰግዳሉ። በዚህ ዕለት ማንም ሰው በሆዱ ቂም እና በቀል እንዳይዝ አባቶች አጥብቀው ያስተምራሉ። ቅሬታ ያለው ወገን ሁሉ በዚህ ዕለት ይቅር ይባባላል። ያስቀየመው የመሰለውን ወገኑን ይቅር ይላል። ታዲያ ምነው ብዙዎቻችን ልባችን ለይቅርታ ድፍን ሆነ? ምነው እልኸኞችና እብሪተኞች ሆንን? ምነው ብሶተኞች ሆንን?

ይቅር ባይነት ልክ እንደ አገልጋይነት ሁሉ በራሳቸው የሚተማመኑ ሰዎች መገለጫ ነው። ውስጣቸው ንፁሕ የሆኑ ሰዎች መገለጫ ነው። ይህ ደግሞ መታደል ነው። ውስጥን ንፁሕ ማድረግ በመንፈሳዊ እምነት ብቻ ሳይሆን በዓለማዊ ሕይወት ራሱ ሰላም አለው፤ ጤና አለው። አካላዊና አዕምሯዊ ጤና ይሰጣል፡፡

ይቅር ባይ የሚሆኑት በጎ አሳቢ የሆኑ ሰዎች ናቸው። ወደፊት ተስፋ የሚታያቸው ሰዎች ናቸው። በጎ አመለካከትና ምኞት ያላቸው ሰዎች ናቸው። በተቃራኒው፤ ጨለማ ብቻ የሚታያቸው ሰዎች ውስጣቸው ለይቅርታ ሩቅ ይሆናል። ክፋትና ጭካኔ ያሸንፋቸዋል። ይቅር ባይነት መሸነፍ ይመስላቸዋል። ይቅር ባይነት ግን መሸነፍ ሳይሆን ማሸነፍ ነው። ይቅር ባይነት ፍቅር ነው፤ ፍቅር ደግሞ የትኛውንም ነገር ያሸንፋል። ጥላቻ እና በቀል ግን የተሸናፊነት ምልክት ነው። ይቅር ባይ ስንሆን የውስጥ ሕመማችንን ሁሉ እናሸንፋለን።

እሁድ ትንሣኤ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ ይነሳል። አገልጋይነት፣ ራስን ለሌሎች አሳልፎ መስጠት ይቅር ባይነት የመጨረሻ ዋጋው ልክ እንደ ትንሣኤው ነው። መጨረሻው ፋሲካ ይሆናል። በነገራችን ላይ ‹‹ትንሣኤ›› የሚባለው በሃይማኖታዊ አገላለጽ ነው። በማኅበራዊ አገላለጹ ‹‹ፋሲካ›› ይባላል። ፋሲካ ማለት ደስታ ማለት ነው፤ ሁሉ ነገር የተሟላበት፣ የተትረፈረፈበት፣ የሰው ልጆች የሚደሰቱበት ማለት ነው።

ይህ ፋሲካ የሚመጣው ታዲያ ከሁለት ወራት የሁዳዴ ፆም፣ ከሰሞነ ሕማማት በባዶ እግር መሄድና ስግደት፣ ከፀሎተ ሐሙስ ዝቅ ብሎ ማገልገል፣ ከዕለተ ስቅለት ፆምና ጸሎት፣ ከቀዳም ሱር (ቅዳሜ) አክፍለት በኋላ ነው። አክፍለት ማለት ዓርብ ማታ ምግብ የበሉ፤ ቅዳሜ ሌሊት ለእሁድ አጥቢያ ከ9፡00 በኋላ መብላት ማለት ነው።

ፋሲካ የሚገኘው ከዚህ ሁሉ በኋላ ነው። ይህን ሁሉ አሳልፎ ነው። ትንሣኤ የሚገኘው ራስን አሳልፎ ከመስጠት በኋላ ነው። መነሳት የሚኖረው መውደቅ ሲኖር ነው። በዓለማዊ ሕይወት እንኳን ብናየው ብዙ የሚመሰገነው፣ ብዙ የሚደነቀው ወድቆ የተነሳ ሰው ነው። ምክንያቱም ብርታቱ፣ ጽናቱ፣ እምነቱ ስለሚያስደንቅ ማለት ነው። ጫማ ከማፅዳት ሥራ ተነስቶ ቢሊየነር የሆነ ባለሀብት የበለጠ ተመስጋኝና ተደናቂ ይሆናል። ምክንያቱም ከፍተኛ ጽናት ነበረው ማለት ነው።

ያሰብነው ፋሲካ ላይ ለመድረስ ልክ እንደ አክፋይ አማኞች ጽኑ መሆን አለብን። አንድ አክፋይ ልክ ሌሊት 9፡ 00 ሲሆን ‹‹ተመስገን!›› ብሎ ፈጣሪውን ያመሰግናል። በጉጉት እና በምኞት የጠበቁት ነገር ያስደስታል። ያላከፈለ ሰው ግን ጠዋት ከአክፋዮች ጋር አብሮ ሲበላ ምግቡን ከምግብነት ያለፈ ዋጋ አይሰጠውም። አክፋዩ ግን ከምግብነት ያለፈ ዋጋ ይሰጠዋል። አመስጋኝ ይሆናል! ትንሣኤ ላይ ለመድረስ፣ ፋሲካ ላይ ለመድረስ፤ ይቅር ባይ መሆን አለብን፣ አገልጋይ መሆን አለብን፣ ታጋሽ መሆን አለብን! በዚህ ሁኔታ ትንሣኤ ላይ ስንደርስ አመስጋኝ እንሆናለን!

መልካም በዓል!

ሚሊዮን ሺበሺ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 14 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You