
ተማሪዎች ከ12 የትምህርት ዓመታት በኋላ ልፋታቸው ፍሬ አፍርቶ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም እንዲገቡ፤ ከፈተና በፊት የሚያደርጉት ዝግጅቶች ለማለፍና ለመውደቃቸው ወሳኝ ሚና አለው። በእዚህ ዓመት ፈተናው በቴክኖሎጂ ታግዞ የሚሰጥ መሆኑ ደግሞ በራሱ ተጨማሪ ዝግጅት የሚጠይቅ ሆኗል ። በእዚህ ዙሪያ ተማሪዎች እና ትምህርት ቤቶች ምን አይነት ዝግጅት እያደረጉ እንደሆነ ቅኝት አድርገናል።
“የሀገር አቀፍ ፈተናው ሊጠይቀኝ ይችላል ብዬ ያሰብኩትን ያህል ዝግጅት እያደረኩ ነው።” የምትለው በኮተቤ ሳይንስ ሼር ካምፓስ የ12ኛ ክፍል ተማሪ ሄርሜላ ዓለምነህ፤ “ለፈተና በማነብበት ወቅት ሊረሱኝ ይችላሉ ያልኳቸውን ይዘቶች ማስታወሻ እይዛለሁ።” ትላለች።
ፈተና በሚደርስበት ወቅት ቀደም ብላ የያዘችውን ማስታወሻ በማንበብ፤ የተለያዩ የፈተና ጥያቄዎችን በመሥራት ልምምድ እንደምታደርግ በመግለጽ፤ ጥያቄዎቹን ለመሥራት “ኢትዮ ማትሪክስ” የሚባል መተግበሪያን እንደምትጠቀም ትናገራለች።
“ከመተግበሪያው በተጨማሪ መምህራኖቻችን ጥያቄዎችን እንድንሠራ ስለሚሰጡን፤ እሱን እሠራለሁ” የምትለው ሄርሜላ፤ ባለፈው ዓመት ከፍተኛ ውጤት ያመጣችው ተማሪ ሲፈን የምትለቃቸውን ትምህርታዊ ቪዲዮዎች እና ከውጭ ሀገራት የሚለቀቁ ቪዲዮዎችን በዩቱብ ትከታተላለች። ከእዚህም በተጨማሪ ፈተናውን የምትወስደው በበይነመረብ እንደመሆኑ ዝግጅት እያደረገች ነው።
ተማሪ ፋሲል ደረጀ ሌላኛው የኮተቤ ሼር ካምፓስ የ12ኛ ክፍል ተማሪ ነው፤ የመማሪያ መጻሕፍቱ ሰፊ እንደመሆናቸው ለሀገር አቀፍ ፈተናው ከስር ከስር እንደሚያነብ እና ከአነበበም በኋላ ጥያቄዎችን እንደሚሠራ ያስረዳል።
ዘመኑ የቴክኖሎጂ እንደመሆኑ ጥያቄዎችን ለመሥራት “ኢትዮ አካዳሚክስ” የሚባለውን መተግበሪያ ጨምሮ ሌሎች የተለያዩ መተግበሪያዎችን ይጠቀማል። በተጨማሪም አንዳንድ ያልተረዳቸው ነገሮች ሲኖሩ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ይጠቀማል።
በኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ ሼር ካምፓስ ምክትል ርዕሰ መምህር አቶ አብረሃም ድሪባ በበኩላቸው፤ ትምህርት ቤቱ ለሀገር አቀፍ ፈተናው ተማሪዎችን ከማብቃት ባለፈ፤ ተማሪዎቹ የሚፈተኑት በበይነመረብ እንደ መሆኑ የኮምፒውተር እና የበይነመረብ አቅርቦት ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን አስታውቀዋል።
የትምህርት ይዘት ከመሸፈን አኳያ 99 በመቶ መድረሳቸውን የሚገልጹት ምክትል ርዕሰ መምህሩ፤ በቀጣይ ጊዜያት የሚቀረው ነገር ለተማሪዎች የክለሳ ትምህርት መስጠት ነው ሲሉ ይጠቁማሉ።
ሌላው ትምህርት ቤቱ ከሌሎች ትምህርት ቤቶች በተለየ መልኩ የተለያዩ የልምምድ ፈተናዎች መስጠት የሚጀምረው ከመጀመሪያው ግማሽ ዓመት ጀምሮ ነው። ከ9ኛ ክፍል እስከ 12ኛ ክፍል ተመሳሳይ ይዘት ያላቸውን ትምህርቶች በመለየት ፈተና ይሰጣል። በእዚህም ተማሪዎች እስከ መጋቢት ወር ድረስ አራት የልምምድ ፈተናዎች መፈተናቸውን ይገልጻሉ።
እስካሁን የልምምድ ፈተናው ሲሰጥ የነበረው በአንድ ወር ከ15 ቀን ርዝመት መሆኑን በመግለጽ፤ ተማሪዎቹም የመማሪያ መጻሕፍትን ተምረው እያጠናቀቁ እንደመሆኑ፤ በቀጣይ ባሉት ቀሪ ግዜያት ፈተናው በ15 ቀናት ርዝመት እንደሚሰጥ አመልክተዋል።
አቶ አብረሃም እንደሚናገሩት፤ ቀደም ብሎ የልምምድ ፈተናዎች መሰጠት ተማሪዎቹ የፈተና አወጣጡን እንዲረዱ፤ ፈተናው ምን አይነት ይዘቶችን እንደሚያካትት ለማወቅ እንዲሁም ለጥያቄዎች መልስ በመፈለግ ሂደት በርካታ ነገሮችን መልሰው እንዲያነቡ ያስችላል።
ጥያቄ መሥራቱ በፈተና ሰዓት ፍርሀት እንዳይኖር ያስችላል የሚሉት ርዕሰ መምህሩ፤ በፈተና ሰዓት ከተማሪዎች ጋር መደናገጥ እና መፍራት እንዳይኖር ከእዚህ በፊትም እንደሚደረገው የሥነ ልቦና ባለሙያዎችን በማምጣት ለሦስት ቀናት ሥልጠና እንደሚሰጥ ይጠቁማሉ።
ትምህርት ቤቱ ከእዚህ በፊት ሙሉ ተማሪዎችን ያሳለፈ እንደመሆኑ፤ ከልምዳቸው በመነሳት እንደ ሀገር ላጋጠመው የተማሪዎች ፈተና መውደቅ መንስኤው የትምህርት ይዘት ሽፋንን በሙሉ አስተምሮ አለመጨረስ ነው። ከእዚህ አንጻር ትምህርት ቤቱ በእዚህ ላይ ትኩረት አድርጎ ከመሥራቱ ባለፈ፤ በትምህርት ቤቱ ደረጃ ስለሌለ ተማሪዎቹ በአዎንታዊ መልኩ እንደሚረዳዱ ያስረዳሉ።
አሁን ላይ አብዛኛው ተማሪ ትምህርት እየጨረሰ ስለ ሆነ፤ ሳይዘናጉ በቀሪ ግዜያት እንቅልፋቸውን መስዋዕት በማድረግ ግዜያቸውን ጥናት ላይ እንዲያሳልፉ ሲሉ መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ።
በዘንድሮ ዓመት 691 ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ለማስፈተን ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የሚገልጹት በዳግማዊ ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመማር ማስተማር ምክትል ርዕሰ መምህር አቶ አበባው አበበ ናቸው።
ከትምህርት ዝግጀት አንጻር በመጀመሪያ ጀረጃ መምህራን ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ እየተደረገ ያለው የትምህርት ይዘት ሽፋን ላይ ነው። ስለዚህ ለትምህርት ይዘት በትክክል ሽፋን እየተሰጠ ነው፤ ቀደም ብለው ያጠናቀቁ መምህራን ክለሳ እንዲያደርጉ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ይናገራሉ።
ከይዘት ሽፋን አንጻር ኬሚስትሪ፣ ባዮሎጂ እና ፊዚክስ ከ90 በመቶ በላይ የደረሱ ሲሆን፤ የእንግሊዘኛ ቋንቋ ትምህርት 10 ምዕራፎች ስላሉት ሁለት ምዕራፍ ሲቀረው፤ ቀሪዎቹ ትምህርቶች ከሁለት ምዕራፍ ያነሰ እንደቀራቸው ይናገራሉ።
ምክትል ርዕሰ መምህሩ እንደሚናገሩት፤ በእዚህ ዓመት የሂሳብና እንግሊዝኛ ትምህርቶች ትኩረት ተደርጎባቸው እየተሰጠ እንደመሆኑ፤ ሁለቱን ትምህርቶች ጨምሮ በሌሎች ፈተና በሚሰጥባቸው ትምህርቶች ላይ ከመደበኛው የትምህርት ክፍለ ጊዜ ውጪ የማጠናከሪያ ትምህርት እየተሰጠ ይገኛል።
በፈተና ወቅት የመረበሽ ነገር እንዳይኖር የሥነ ልቦና ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን በመግለጽ፤ ተማሪዎቹ ፈተናውን የሚወስዱት በበይነ መረብ እንደመሆኑ፤ ከትምህርት ሚኒስቴር የመለማመጃ ጥያቄ ስለተለቀቀ ወደ ልምምድ እየገቡ ይገኛል ሲሉ ያስረዳሉ።
ለፈተናው የቀረው ጊዜ ከሦስት ወር ያነሰ እንደመሆኑ፤ ተማሪዎች ጥያቄዎችን እያወጡ ልምምድ እንዲያደርጉ፤ በየትምህርቶቹ ላይ ትኩረት የሚደረግባቸው ይዘቶች ተለይተው ስለተሰጡ በእነሱ ላይ ትኩረት አድርገው እንዲያነቡ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የፈተናው ውጤት ተማሪዎች ከ12 ዓመት በኋላ የሚያገኙት ፍሬ ስለሆነ፤ መምህራን ትኩረት ሰጥተው ተማሪዎችን እንዲያግዙ፤ በተጨማሪም በትምህርት ዘርፉ የሚገኙ የመንግሥት አካላት በትምህርት ቤቱ የሚፈተኑ ተማሪዎች እና ያለው ኮምፒውተር ተመጣጣኝ ስላልሆነ ትምህርት ቤቱ ተጨማሪ ኮምፒውተር የሚያገኙበት እድል ካለ ድጋፍ እንዲደረግ ይጠይቃሉ።
በዳግማዊ ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ ቤቴልሄም ዮሐንስ በበኩሏ፤ የተለየ የማንበብ ልምድ አላት። የጥናት ፕሮግራሟ በየቀኑ ሳይሆን፤ በሦስት ቀን አንዴ አንድ የትምህርት አይነት እንደምታነብ እና በቀጣይ ጊዜ ደግሞ ሌላ የትምህርት አይነት እንደምታነብ ትናገራለች።
ከማንበብ በተጨማሪ መምህራኖቿ የሚሰጧትን ጥያቄ፤ ባለፉት ዓመታት የተሠሩ ጥያቄዎችን በተጨማሪም በራሷ ጥያቄ አዘጋጅታ ልምምድ ታደርጋለች። የሂሳብ ትምህርቶች የበለጠ መረዳት የሚቻለው በተግባር ሲታገዝ እንደመሆኑ፤ የዩቱብ ትምህርቶችን እንደምትከታተል ትገልጻለች።
ተማሪ አትመናቸው መልካሙ በዳግማዊ ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን፤ ለሀገር አቀፍ ፈተናው የተለያዩ አጋዥ መጻፍቶችን የሚያነብ ቢሆንም፤ የበለጠ የመማሪያ መጻሕፍት ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ይናገራል።
ፈተናው ብዙ ጊዜ መጻሕፍቱ ላይ ያሉትን የመማሪያ ዓላማዎች መሠረት አድርገው ስለሚወጡ መማሪያ መጻሕፍት ላይ ትኩረት አድርጎ ማንበቡ የበለጠ ተጠቃሚ እንደሚያደርገው የሚገልጸው ተማሪ አትመናቸው፤ ከአነበበ በኋላ የተለያዩ ጥያቄዎችን በመሥራት እንደሚለማመድም ይገልጻል።
ዓመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 14 ቀን 2017 ዓ.ም