በሀገር እድገት ላይ የራሳቸውን ጠጠር የጣሉ የፈጠራ ሥራዎች

በአሁኑ ጊዜ በሁሉም ዘርፍ አኗኗርና አሠራርን ያቀልላሉ የተባሉ ቴክኖሎጂዎችን የማስተዋወቁ እና ወደ ሥራ የማስገባቱ ጉዳይ ከዕለት ወደ ዕለት እያደገ መጥቷል። ልዩ ተሰጥዖ ያላቸው የፈጠራ ሰዎች በተለይም ወጣቶች መንግሥት ያመቻቸውን ጥሩ ሁኔታ በመጠቀም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እያስተዋወቁ ይገኛል።

ከሰሞኑ 145 ወጣቶችን ያሳተፈ 3ኛው የብሩህ አዲስ ወጣቶች የንግድ ሃሳብ ፈጠራ ውድድር በመዲናዋ ሲካሄድ ሰንብቷል። በውድድሩ ላይ ከቀረቡት የንግድ ሃሳብ ፈጠራዎች መካከል ለከተማዋ እና ለማኅበረሰቡ ጉልህ ጠቀሜታ አላቸው የተባሉ የፈጠራ ሥራዎችን ይዘው እየቀረቡ ወጣቶች ለሽልማት በቅተዋል።

ማዕረግ ዘውዱ በዳንዲቦሩ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ ነው። ታካሚዎች መድኃኒት ለመግዛት የሚያጠፉትን ጊዜ እና እንግልት በማስተዋል ችግሩን የሚፈታ የቴክኖሎጂ መተግበሪያ መፍጠሩን ይናገራል። ለዚህ መነሻ የሆነውን ጉዳይ ሲያስረዳ ‹‹መድኃኒት ቤቶች በተለያየ ርቀት ሆነው የተለያየ መድኃኒት ይሸጣሉ፤ ሆኖም ግን ታካሚዎች የሚፈልጉትን መድኃኒት በሚፈልጉት አቅራቢያ ቦታ አያገኙትም፤ የፈጠራ ሥራው

ሰዎች የሚፈልጉት መድኃኒት ያለምንም ውጣውረድ የት እንዲያገኝ ማወቅ የሚያስችል ነው። ከ50 በመቶ በላይ ሰዎች የስማርት ፎን ተጠቃሚ በመሆናቸው በቀላሉ መተግበሪያውን በመጠቀም የመድኃኒት መገኛውን በመለየት ግብይት ይፈጽማሉ። ታካሚዎች መድኃኒት ፍለጋ ብዙ ርቀት እንዳይሄዱ እና ወጪ እንዳያወጡ እንዲሁም በወረፋ ምክንያት ጊዜያቸውን እና ጉልበታቸውን እንዳያባክኑ ይረዳል።

ይህ ብቻ ሳይሆን መድኃኒቶች ለረጅም ጊዜ ከመቆየታቸው የተነሳ ለብክነት ይዳረጋሉ፤ መተግበሪያው ይህን ለመቆጣጠርም ያስችላል ይላል።››

የኦንላይን የመድኃኒት መሸጫ መተግበሪያው ከመድኃኒት ቁጥጥር እና ከሌሎች አጋሮች ጋር በመሆን ወደ ሥራ እንደሚገባ ይናገራል። መድኃኒቶች በተፈጥሯቸው የመበላሸት ዕድላቸው ሰፊ በመሆኑ በዚህ ዙሪያ ከሚሠሩ አካላት ጋር በመሆን በአንድ ጣሪያ ሥር መሥራት እንደሚፈልግ እና ለዚህም የመሥሪያ ቦታ እንደሚያስፈልግ ይናገራል፤ በመሆኑም ይህን ፈጠራ በዓለም አቀፍ ደረጃም ቢሆን ለመተግበር ፍላጎት ካላቸው ድርጅቶች ጋር በትብብር የመሥራት ዕቅድ እንዳለው ወጣቱ ያስረዳል።

በተመሳሳይ በንግድ ፈጠራ ሃሳብ የኮዳ ላስቲኮችን በመቆራረጥ እና በማቅለጥ ወደ ገመድ (ፊላሚን) እየቀየረ ወደ ገበያ ተደራሽ የማድረግ ሥራን ያስተዋወቀው ወጣት ያዕቆብ ዓባይነህ ነው፤ ‹‹በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ›› እንዲሉ፤ ወጣቱ በዋናነት የፕላስቲክ ኮዳ የሚፈጥረውን የአካባቢ ብክለት ለመቆጣጠር እንዲሁም ከውጭ ይገባ የነበረውን የፕላስቲክ ገመድ (ፊላሚን) በሀገር ውስጥ በመተካት በቅናሽ ዋጋ የማቅረብ ዓላማ አንግቦ ወደ ሥራ የገባ ነው።

ይህን ፈጠራ ተግባራዊ ለማድረግ የራሱን ማሽን አምርቶ በመጠቀም እና ሌሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሽያጭ አቅርቦት መጀመሩንም ያስረዳል፤ ወጣቱ በቀን አንድ ኪሎ ግራም የፕላስቲክ ኮዳ በመቆራረጥ የሚያመርት መሆኑን ያስረዳል። ምርቱን ከሚጣል እና በቅርበት ከሚገኝ የፕላስቲክ ኮዳ የሚያመርት መሆኑና የገበያ ተፈላጊነት ያለው በመሆኑ ቀጣይነት ያለው ገቢ የሚያስገኝ ሥራ ነው ይላል።

ሌላኛው የፈጠራ ሃሳብ አቅራቢ ፀጋይ ተስፋዬ ይባላል፤ የሰው ልጅ ፀጉር ተረፈ ምርት ወደ ፕሮቲን እና ማዕድን በመቀየር በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኝ የንግድ ሃሳብ አቅርቧል፤ የሰው ልጅ ፀጉር በዓመት 140 ሺህ ሜትሪክ ቶን ከፀጉር ቤቶች ይወገዳል፤ ይህ በቆሻሻ መልክ ሲጣል ለረጅም ጊዜ መሬት ውስጥ በመቆየት ከፍተኛ ብክለት ይፈጥራል ይላል።

ታዲያ ይህ የሚጣል ፀጉር በውስጡ በርካታ ጠቃሚ ንጥረ ነገሮች እንዳሉት በምርምር ማረጋገጡን ያስረዳል፤ እነዚህን ጠቃሚ ንጥረ ነገሮች ጥቅም ላይ ለማዋል መጀመሪያ የፀጉር ተረፈ ምርትን በከፍተኛ ሙቀት በመቀቀልና ተከታታይ ሂደቶችን እንዲያልፍ በማድረግ ለሰው ልጅ በምግብነት፣ በመዋቢያ ቀለምነት እንዲሁም ለኅትመት ሥራዎች ሊውል እንደሚቻል ያስረዳል።

ይህ ተረፈ ምርት ለእንስሳት መኖ፣ ለመሬት ማዳበሪያ እንደሚያገለግል ይጠቅሳል። ተመራማሪው ሥራውን ከግብ ለማድረስ ከጤና ሚኒስቴር እና ከሌሎች ተቋማት ጋር በመሆን የምርምር እንዲሁም በዚህ የሃሳብ ፈጠራ ከሚሠሩት ጥቂት ሀገራት ጋር አብሮ የመሥራት ፍላጎት እንዳለው ገልጾ፤ ይሁንና ከፍተኛ የገንዘብ አቅርቦት እንደሚያስፈልገው ያስረዳል።

ሁሉም የንግድ ሃሳብ ፈጠራዎች ለሀገርና ለማኅበረሰብ እጅግ ጠቃሚ ናቸው፤ በተለይ የፈጠራ ሃሳባቸውን በተግባር ማሳየታቸው ይበልጥ ተዓማኒ ያደርጋቸዋል፤ በመሆኑም እነዚህ ጅምር ሥራዎች የበለጠ አብበውና ፈክተው ለፍሬ እንዲበቁ በተለይም በመሥሪያ ቦታ አቅርቦትና በፋይናንስ በኩል አይዟችሁ ሊባሉ ይገባል።

ሔርሞን ፍቃዱ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You